Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ23 ሚሊዮን ብር የተገዙ ዘመናዊ ታክሲዎች አገር ውስጥ ገቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ታክሲዎቹን ጨምሮ ለ500 አውቶቡሶች 60 ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል

የአዲስ አበባ ከተማን የቱሪስት ታክሲዎች በዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ለመተካት እንዲያስችል መንግሥት 1,163 ታክሲዎች ከታክስ ነፃ እንዲገቡ በመፍቀዱ ምክንያት፣ የመጀመሪያዎቹን 50 ዘመናዊ ታክሲዎች አዲስ ሜትር ታክሲ የተባለ ማኅበር በ23 ሚሊዮን ብር ወጪ በማስመጣት ሥራ ለማስጀመር መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

አዲስ ሜትር ታክሲ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ውስጥ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ከሚንቀሳቀሱ ማኅበራት መካከል አንዱ ነው፡፡ የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ብርሃነ ወደ አገር ውስጥ መግባት ከጀመሩት 50 ታክሲዎች መካከል 15 ተሽከርካሪዎች ከአስመጪው ወኪል ኩባንያ መረከቡን በማስመልከት ነሐሴ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ወቅት እንዳሉት፣ በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ታክሲዎች ስላረጁና በአዳዲስ እንዲተኩ ለማድረግ የታክሲ ማኅበራት የቀረጥ ነፃ ፈቃድ እንዲሰጣቸው በጠየቁት መሠረት አዲስ ሜትር ፈር ቀዳጅ ሆኗል፡፡

የአዲስ ሜትር ታክሲ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ መኮንን በበኩላቸው፣ እ.ኤ.አ. የ2016 ሥሪት የሆኑ አቫንዛ ሞዴል ቶዮታ መኪኖችን ኦክሎክ ጠቅላላ የንግድ ሥራ ድርጅት በተባለው አስመጪ አማካይነት እየገቡ ካሉት ውስጥ 15 ተረክቦ ቀሪዎቹን 35 መኪኖች እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ እንደ አቶ ደረጀ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሚገቡትን ጨምሮ ሃምሳዎቹን ተሽከርካሪዎች የኩባንያው ባለድርሻዎች ባላቸው የአክሲዮን ድርሻ መጠን በባለቤትነት ይረከባሉ፡፡ ድርጅቱ ተሽከርካሪዎቹን ከቀረጥ ነፃ ለማስገበት ሕግ በሚፈቅደው አግባብ የአክሲዮን ድርሻ ባላቸው 35 አባላት አማካይት ለመመሥረት መገደዱን፣ ይህንንም ለማሳካትና ከታክሲ ማኅበርነት ወደ ኩባንያነት ተለውጦ ለመሥራት ከአንድ ዓመት በላይ እንደወሰደበት አቶ ዮናስ ገልጸዋል፡፡

ከአዲስ ሜትር ታክሲ ውክልና በመቀበል ተሽከርካሪዎቹን ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት ሁሉንም ሒደቶች የተወጣው ኦክሎክ ጠቅላላ ንግድ ሥራ ባለቤት አቶ አህመዲን መሐመድ እንዳብራሩት፣ መኪኖቹ እያንዳንዳቸው 460 ሺሕ ብር ወጥቶባቸው ወደ አገር ቤት ገብተዋል፡፡ ቀረጥ ቢከፈልባቸው ኖሮ እያንዳንዳቸው ከ1.1 ሚሊዮን ብር በላይ ይከፈልባቸው እንደነበር አቶ አህመዲን ተናግረዋል፡፡

አስመጪው ድርጅት ለተለያዩ የመንግሥት አካላት የቀረጥ ነፃ ፈቃድ እንዲሰጠው በማመልከት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ጉዳዩን እንዳደረሰው አቶ አህመዲን ጠቁመው፣  ኩባንያቸው እስከ 400 ለሚደርሱ ተሽከርካሪዎች የቀረጥ ነፃ ዕድል እንዲሰጥ ቢጠይቅም መንግሥት 1,163 ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ ፈቃድ ሊሰጥ ችሏል ብለዋል፡፡ በዚህ መሠረት የኤርፖርት ታክሲዎች በተጨማሪ ሌሎች የከተማ ትራንስፖርት የሚሰጡ 500 ያህል ተሽከርካሪዎች እንደሚገቡም አብራርተዋል፡፡ መንግሥት ለእነዚህ ተሽከርካሪዎች በጠቅላላው 60 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መፍቀዱንም አቶ አህመዲን ገልጸዋል፡፡

አዲሶቹ ታክሲዎች 1,500 ሲሲ የፈረስ ጉልበት ያላቸው፣ የመቆጣጠሪያ ካሜራ፣ የኪሎ ሜትር መለኪያና መቁጠሪያ፣ የአቅጣጫ መጠቆሚያና ማመላከቻ (ጂፒኤስ) እንዲሁም ከኋላ ወንበር ለሚቀመጡ ተሳፋሪዎች የቴሌቪዥን መስኮቶች የተገጠሙለት፣ የተሟላ አገለግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ መመረቱ ተገልጿል፡፡ ከዚህም ባሻገር እስከ ሰባት ሰዎች በአንድ ጊዜ የማሳፈር አቅም እንዲኖረው ታስቦ የተሠራ መሆኑን አቶ አህመዲን አብራርተዋል፡፡ ሻንጣ ለመጫን ሲፈለግም ከኋላ የሚገኙ ወንበሮች ይታጠፋሉ፡፡  ከመስከረም ወር ጀምሮ ሥራ እንደሚጀምሩ የተነገረላቸው አዳዲሶቹን ታክሲዎች በስልክና በኢንተርኔት አማካይነት ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አገልግሎት ማግኘት እንደሚቻል አቶ ደረጀ አስረድተዋል፡፡

ከአዲስ አበባ እስከ ቢሾፍቱ/ደብረዘይት፣ ከዚያም አዳማ/ናዝሬት ሌሎች ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻ ከተሞች ድረስ የሚመላለሱ የሜትር ታክሲ አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን ለማሰማራት አዲስ ሜትር ታክሲ ኩባንያ ከኳታርና ከማሌዥያ ኢንቨስተሮች ጋር መነጋገር እንደጀመረ አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡ ከኤርፖርት ወደ ቱሪስቶች መዳረሻ ድረስ እንዲሁም የመኪና ኪራይ ጨምሮ ያሉትን አገልግሎቶች እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

አቶ ዮናስ በሰጡት ማብራሪያ መሠረት የከተማም ሆነ የኤርፖርት ታክሲ አገልግሎት በጣሊያን ወረራ ወቅት እንደተጀመረ ጣሊያናውያን አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች አገልግሎቱን ይሰጡ ነበር፡፡ እንዲህ የተጀመረው የግል ታክሲ አገልግሎት በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ በኢትዮጵያውያን አማካይነት በማኅበር ሲሠራበት ቆይቶ በደርግ ጊዜ ግን ፈቃዳቸው ተሰርዟል፡፡ ከደርግ በኋላም ቀድመው የነበሩት ማኅበራት ሕጋዊ ሰውነታቸው እንዲመለስላቸው በመጠየቅ ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ በኤርፖርት የቱሪስት ታክሲ አገልግሎት መስጠት እንደጀመሩ ተብራርቷል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትን ታክሲዎች በአዲስ ለመተካት በኤርፖርት ውስጥ የቱሪስት ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ማኅበራት በአክሲዮን ማኅበራትና በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ እየተዋቀሩ አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን በማስገባት ላይ ይገኛሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች