- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አሁን የምሰጥህን ዶክመንት በጥንቃቄ እንድትይዘው፡፡
- ምን ዓይነት ዶክመንት ነው?
- ይህ ዶክመንት በአሁኑ ወቅት ወሳኝ የሚባል ዶክመንት ነው፡፡
- ይኼ በእጅዎ የያዙት ዶክመንት ነው?
- አዎን፡፡
- በጣም ብዙ ገጽ ነው፣ ሁለተኛው ዙር ሊጀመር ነው እንዴ?
- የምን ሁለተኛ ዙር ነው?
- የሙስና ዘመቻው ሁለተኛ ዙር ነዋ፡፡
- ምንድነው የምትቀባጥረው?
- የስም ዝርዝሩን ነው እንዴ የያዙት?
- ሰውዬ በሰላም ነው አድረህ የተነሳኸው?
- እኔማ ሁለተኛው ክፍል ተጀመረ ብዬ ነው?
- ምን ይላል ይኼ?
- ያው በመንግሥትና በሕዝብ ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር ጉዳት ያደረሱት ተያዙ ብዬ ነዋ፡፡
- እነሱማ ያኔ ተያዙ አይደል እንዴ?
- ዋናዎቹ መቼ ተያዙ?
- እ. . .
- ጭፍራዎቹ በቢሊዮን ከዘረፉ ዋናዎቹ እኮ ስንት ነው የዘረፉት እየተባለ ነው የሚወራው፡፡
- ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
- እኔ እርስዎን ማለቴ አይደለም፡፡
- እሱም አምሮህ ነበር?
- ያው መቼም ራስዎ ያሉበትን ሊስት ራስዎ አይዙትም ብዬ ነው፡፡
- መልዕክት ልታስተላልፍልኝ ፈልገህ ነው?
- ኧረ በፍፁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለማንኛውም ዶክመንቱን ተቀበለኝ፡፡
- ምንድንው ግን ዶክመንቱ?
- መግለጫው ነዋ፡፡
- የምን መግለጫ?
- ሰሞኑን ከ15 ቀናት በላይ በራችንን ዘግተን የተገማገምንበትን፡፡
- ምን ላድርገው ክቡር ሚኒስትር?
- መግለጫ ምንድነው የሚደረገው?
- በቲቪና በሬዲዮ ላሠራጨው?
- አንተ ግን 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ መሆናችንን ረሳኸው?
- ምን እያሉኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- በዚህ ወቅት ቲቪና ሬዲዮ የሚከታተል አለ?
- እ. . .
- አንተ አሁን ለምሳሌ በቲቪ ዜና ታያለህ?
- ሲኤንኤንና አልጄዚራ ላይ አያለሁ፡፡
- ስለእነሱ ማን ጠየቀህ?
- ታዲያ ስለማን ነው የጠየቁኝ?
- ስለአገራችን ሚዲያዎች ነው የጠየቅኩህ?
- እነሱንማ አይቻቸውም አላውቅ፡፡
- ታዲያ አንተ የማታያቸውን ሕዝቡ እንዲያያቸው ትጠብቃለህ?
- እሱስ እውነትዎን ነው፡፡
- ስለዚህ አሁን በአስቸኳይ ይለቀቅ፡፡
- ምን ላይ ነው የሚለቀቀው?
- ፌስኦፍ ላይ ነዋ፡፡
- ምን ላይ?
- በኢንተርኔት ልቀቀው፡፡
- ፌስቡክ ለማለት ነው?
- አዎን እሱ ላይ፡፡
- እሱማ ተዘግቷል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማን አባቱ ነው የዘጋው?
- መንግሥት ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን ተብሎ?
- ለአገሪቷ ሰላምና ደኅንነት ሲባል ተዘግቷል፡፡
- እሱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜ አልነበር እንዴ የተዘጋው?
- አሁንም ግን ተዘግቷል፡፡
- እንዴት ግን ሊዘጋ ቻለ?
- ምናልባት በይፋ ያልታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ ላይ እንሆናለና?
- ለነገሩ ፌስቡክ ሲዘጋ የሚታይበት መንገድ አለ አይደል?
- ቪፒኤን ማለትዎ ነው?
- ነው መሰለኝ፡፡
- ታዲያ በቪፒኤን ተጠቅሜ ፌስቡክ ላይ ልልቀቀው?
- እህሳ፡፡
- ይህ ግን ትዝብት ውስጥ አይከተንም?
- የምን ትዝብት?
- መንግሥት ራሱ ፌስቡክን ዘግቶት፣ መግለጫውን በፌስቡክ ሲለቅ ነዋ?
- ምንም ችግር የለውም ዝም ብለህ የታዘብከውን አድርግ፡፡
- አሁን ግን ዶክተሩን አስታወሱኝ፡፡
- የትኛውን ዶክተር?
- ሲጋራ አታጭሱ እያለ የሚመክረውን ነዋ፡፡
- ቢመክር ምን ችግር አለው?
- ራሱ ስለሚያጨስ!
[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ሚኒስትር ቢሯቸው ይመጣሉ]
- እንዲያው አንዳንድ ነገሮች ላይ እንድንመካከር ብዬ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ዓይነት ነገሮች ላይ?
- ሕዝቡ እኮ በጉጉት ሲጠብቀን ነበር፡፡
- ለምንድነው በጉጉት የሚጠብቀን?
- ያው 17 ቀን ዘግተን ተሰብስበን ከእኛ ትልቅ ነገር ነበር የሚጠብቀው፡፡
- ታዲያ ከእኛ የሚጠብቀውን ነገር ሰጠን አይደል እንዴ?
- ምን ሰጠን ክቡር ሚኒስትር?
- መግለጫ ሰጠን አይደል እንዴ?
- ችግሩ መግለጫው አይደል እንዴ?
- ምን ሆነ መግለጫው?
- ሕዝቡ በመግለጫው መላጫ እያደረገን ነው፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- መግለጫው በመጽሐፍ መልክ ቢታተም ይሻል ነበር መሰለኝ?
- ለምን?
- መብዛቱ ሳያንስ ውስጡ አደናጋሪ ነው፡፡
- አንተ ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ውለሃል ማለት ነው፡፡
- ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ መግለጫውን በሚገባ የተረዳው አልመሰለኝም፡፡
- ስማ ፓርቲያችን እኮ ሚስጥራዊ ፓርቲ መሆኑን አትርሳ፡፡
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሁሉን ነገር ለሕዝብ ግልጽ የማድረግ ባህል የለውማ፡፡
- በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ግልጽ መሆን አለበት እንላለን፡፡
- መንግሥት ሌላ ፓርቲ ሌላ፡፡
- በመግለጫው አመራሩ ጥፋተኛ ከሆነ ተጠያቂም መሆን አለበት እያለ ነው ሕዝቡ፡፡
- አንተ በፓርቲው ማንም ተጠያቂ ሊሆን እንደማይችል አታውቅም እንዴ?
- መንግሥት ግን ተጠያቂ መሆን አለበት እኮ?
- ሰውዬ መንግሥት ሌላ፣ ፓርቲ ሌላ አልኩህ እኮ?
- አሁን ግን እኔንም እያደናገሩኝ ነው፡፡
- ለምን ተደናገርክ?
- በመንግሥት ደረጃ ግልጽና ተጠያቂ መሆን አለብን እያልን በፓርቲ ደግሞ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባህላችን አይደለም እንላለን፡፡
- ታዲያ ምን ችግር አለው?
- ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ በመግለጫው ላይ ተመሥርቶ መላምት እያቀረበ ነው፡፡
- ሕዝቡ የተለያዩ መላምቶችን ካቀረበ እኛም ግባችንን መተናል ማለት ነው፡፡
- የእኛ ግብ ምንድነው?
- ማደናገር!
[ለክቡር ሚኒስትሩ ኢንቨስተር ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል]
- ክቡር ሚኒስትር ያወጣችሁትን መግለጫ አየሁት፡፡
- እንዴት አገኘኸው?
- ክቡር ሚኒስትር የእናንተ ነገር እኮ እንቆቅልሽ እየሆነብኝ ነው፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- እስኪ መጀመርያ አንድ ጥያቄ ይመልሱልኝ?
- ምንድነው ጥያቄህ?
- አሁን አገሪቱ ለገባችበት ቀውስ አመራሩ ጥፋተኛ ነው አላችሁ፡፡
- ትክክል ነው፡፡
- ታዲያ አመራሩ የታለ የተቀጣው?
- አንተ ኢትዮጵያዊ አይደለህ እንዴ?
- ነኝ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ እኛ በባህላችን ይቅር ባይና ሩህሩህ አይደለንም እንዴ?
- ይኼ ነው እኮ ችግሩ?
- እንዴት?
- ሕዝቡን በልታችሁ ከጨረሳችሁት በኋላ ይቅር ይበለን ስትሉ አታፍሩም?
- ስማ አንተ ከዳያስፖራዎቹ ጋር ግንኙነት ስላለህ ጨካኝ ሆነሃል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አሁን የሚሉት ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ባህል እየተወሰደ ነው፡፡
- አልገባኝም?
- ስንቱን ያማረረ ሰው ሞቶ ታሪኩ ሲነበብ ደግ፣ ሩሩህና ቸር ነበሩ ነው የሚባለው፡፡
- ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
- እናንተም ሕዝቡን አሰቃይታችሁ ስታበቁ ደግ፣ ሩሩህና ቸር ነበራችሁ እንዲባልላችሁ ትፈልጋላችሁ?
- አንተ ለማንኛውም የለየልህ ተቃዋሚ እየሆንክ ነው፡፡
- ሌላው ደግሞ መግለጫውን ለምንድነው እንደዚህ አደናጋሪ ያደረጋችሁት?
- ምኑ ነው ያደናገረህ?
- አሁን መርህ አልባ ግንኙነት ማለት ምን ማለት ነው?
- እንደገባህ ነዋ የምትፈታው፡፡
- ምን ማለት ነው እንደገባህ ፍታው ሲሉ?
- እንደተጻፈው መርህ አልባ ግንኙነት ማለት ነዋ፡፡
- ቡድናዊ ትስስርስ ማለት ምንድነው?
- እሱም የቡድን ትስስር ማለት ነዋ፡፡
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር በዚህ ሕዝብ ላይ አትቀልዱበት?
- ሰውዬ እንዲያውም ይኼ እስከ ዛሬ ካወጣናቸው መግለጫዎች ግልጽ መግለጫ ነው፡፡
- እኔ ግን ክቡር ሚኒስትር አንድ ነገር አልደብቅዎትም፡፡
- ምን?
- መግለጫውን ለመረዳት አምስት ጊዜ አንብቤዋለሁ፡፡
- እሺ?
- ከማንበብ ባለፈ ሦስት ጊዜም አዳምጨዋለሁ፡፡
- ታዲያ እንዴት አገኘኸው?
- ምንም አልገባኝም፡፡
- እ. . .
- ሌሎችም ብጠይቅ እነሱም አልገባቸውም፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- አሁን የቀረኝ አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡
- ምንድነው የቀረህ?
- መግለጫውን ማስፈታት፡፡
- የት?
- ጠንቋይ ቤት!