Tuesday, March 28, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ይድረስ ለአቶ ሞገስ ሀብተ ማርያም

እውነታውን ለምን ፈሩት?

በመድኃንዬ ላፍቶ

በኢሕዲሪ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተና ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ ‹‹አብዮቱና ትዝታዬ›› በሚል መጽሐፋቸው ላይ ተመርኩዘው በሪፖርተር ሐምሌ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ዕትም የጻፉትን ሐተታና ስሞታ በጥሞና አንብቤዋለሁ፡፡

በመጀመሪያ የተጠቀሰው መጽሐፍ ሀቅን ያቀፈ፣ እውነትን የተላበሰ ብቻ ሳይሆን በመሥሪያ ቤትዎ የተፈጸመውን ጥፋትና ግፍን ጨምሮ በአብዮቱ ውስጥ በማወቅም ሆነ በስህተት ስለተፈጸመው ሁሉ የይቅርታን መልዕክት የያዘ ነው፡፡ በመሆኑም መጽሐፉ ከፍተኛ ተቀባይነትና ተወዳጅነት ያገኘ መሆኑን ልገልጽልዎት እወዳለሁ፡፡ በመሠረቱ ረጅሙ ሐተታዎን ካነበብኩ በኋላ ሌተና ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ የእርስዎን ሳይሆን የራሳቸውን ትዝታ መጻፋቸውን አለመረዳትዎን ተገንዝቤያለሁ፡፡ ለማንኛውም ስለትችቱ የመጽሐፉ ባለቤት ተገቢ መልስ ይሰጡበታል ወይም ንቀው ይተውት ይሆናል፡፡ ይህንን ለሳቸው መተው ይሻላል፡፡

በበኩሌ ግን በጽሑፍዎ መግቢያ አካባቢ በእኛ የሰደድና የኢሠፓአኮ አባላት የነበርን የትግራይ ተወላጆች በሐሰት ተወንጅለን በማዕከላዊና በቤርሙዳ የደረሰብንን ግርፋት፣ ሰቆቃና ግድያ ሌተና ኮሎኔል ፍሰሐ በዝርዝር በመጻፋቸው ስህተት እንደሆነና ራሳቸውን ለመከላከል ያቀረቡት አስመስለው የሰነዘሩት ትችት አሳዝኖኛል፡፡ አለቃዎና ሌሎች የዚህ ወንጀል ተባባሪ የነበሩት በሕይወት ቢኖሩ የወሰዱት ዕርምጃ ትክክል መሆኑን ያስረዱን ነበር የሚል መልዕክትም ለማስተላለፍ ሞክረዋል፡፡ ሌተና ኮሎኔል ፍሰሐ በአብዮቱ ውስጥ የገጠማቸውን ሁኔታ ዘርዘር ባለ መልኩ በማቅረባቸውም ቅሬታዎን ገልጸዋል፡፡ እውነታውን ነው የፈሩት? ወይስ ለወረቀቱ ነው የተጨነቁት? በአብዮቱ ወቅት መሥሪያ ቤትዎ በንጹኃን ዜጎች ላይ የፈጸመውን ድርጊት ሕዝቡ እንዲያውቅ ለምን ተደረገ የሚሉ ይመስለኛል፡፡ የአብዮቱ ታሪክ አካል ነውና ዛሬም ነገም መጻፉ የማይቀር ነው፡፡

ይህንን ካልኩ በኋላ እኔ በአካል ባላውቅዎትም በደኅንነቱ መሥሪያ ቤቱ ሁለተኛ ሰው ስለነበሩ የመረጃ ዕውቀት ይኖርዎታል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በመሆኑም በሌተና ኮሎኔል ፍሰሐ የቀረበውን ጽሑፍ እውነተኛነቱን ለማረጋገጥ ከፈለጉ ጥቂት ግን የማያወላዳ ማስረጃ ላቅርብልዎት፡፡ በመጀመሪያ ‹‹ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በአቶ ገብሩ አሥራት በተጻፈው መጽሐፍ ከገጽ 159 እስከ 161 ያለውን ያንብቡ፡፡ በአጭሩ ‹‹ሕወሓት የውሸት የከተማ መዋቅር ሠርቶ የደርግ ታማኞችና ሕወሓትን ያውካሉ የተባሉትን የሕወሓት አባላት አስመስሎ የስም ዝርዝር ላከ፡፡ በዚህም መሠረት የደርግ የደኅንነት መሥሪያ ቤት የኢሠፓአኮና የደርግ ታማኞች የነበሩትን በራሱ እጅ አጠፋቸው፤›› በማለት በግልጽ አስቀመጥውታል፡፡ እዚህ ላይ መቐለ የነበሩ እሥረኞች በሕወሓት ነፃ የወጡት ከዚህ በኋላ መሆኑን ልብ ይበሉ፡፡

ሁለተኛ እርስዎ የተቃወሙት የሌተና ኮሎኔል ፍሰሐ ጥቂት ገጾችን ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ የማዕከላዊ ምርመራ ሰነዶችን አገላብጦ፣ ግለሰቦችን ጠይቆ አቶ ግርማይ አብርሃ ‹‹ያመነም ያላመነም›› በሚል ርዕስ ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ጽፏልና ያንብቡት፡፡ ሦስተኛ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኮሎኔል ተስፋዬ ፍሰሐን የወያኔ አባል ነው እያለ ይጠረጥረዋል፣ ማስረጃ ግን ለማቅረብ አልቻለም ሲሉ ለገነት አየለ በሰጧት ቃለ መጠይቅ አረጋግጠዋል፡፡ በመጨረሻ ግን ታደሰ ገብረ እግዚአብሔር በግርፋት ማቆ በገመድ ታንቆ ከመገደሉ በፊት፣ ለአለቃዎና ለማዕከላዊ ምርመራ የጻፈውን 190 ገጽ ሰነድ ይመልከቱት፡፡ እነዚህን ካነበቡ በኋላ ብዕሬን ለምን አነሳሁ ብለው ይቆጭዎታል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በተለይ የታደሰን ጽሑፍ ካነበቡ በኋላ እንደ አለቃዎ ‹‹የአዞ እንባ›› ሳይሆን ርህሩህ ከሆኑ እውነተኛ እንባ ያነባሉ፡፡

ኮሎኔል ተስፋዬ ማዕከላዊ እሥር ቤት ሊያነጋግሩን መጥተው ነበር፡፡ እኛም ‹‹በአንድ በኩል ሕወሓት ዓላማችንን ይቃወማሉ በማለት ሊገድለን ያሳድደናል፡፡ እኛ ለደርግና ለኢሠፓአኮ ታማኝ ስንሆን ደርግ ካልተገለበጠ በስተቀር እንዴት ለመታሰር በቃን? መንግሥት ያልደረሰበት ሴራና አሻጥር እየተሠራ ነውና ያጣሩልን፤›› ብለን ጠየቅናቸው፡፡ ‹‹አጣርቼ መልስ እሰጣችኋለሁ፤›› ብለውን ሄዱ፡፡ አውቆ የተኛ እንደሚሉት እስሩ ያነሰን ይመስል የተወሰን ሰዎች ፀሐይ ሳይሆን ብርሃን ተነፍገን በጨለማ ቤት ለሰባት ወራት ተዘጋብን፡፡ በኤሠፓአኮ መዋቅር አንድም የትግራይ ተወላጅ እንዳይኖር የሚል ፖሊሲ የነበረ ይመስል ቤርሙዳና ማዕከላዊ በእስረኞች ተጨናነቁ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ታደሰ ገብረ እግዚአብሔርን ጨምሮ አምስት ሰዎች ተገደሉ፡፡ ዶ/ር መንገሻም ከግርፋቱ ብዛት እግራቸው ተቆራርጦ እሳቸውም አብረው ተገደሉ፡፡

ከግድያ የተረፍነው ደግሞ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ጠባቂዎቻችን ጥለውን ሲሄዱ ከወህኒ ወጣን፡፡ ብዙም ሳንቆይ ፀረ ሕወሓት ነበራችሁ ተብለን በኢሕአዴግ በቁጥጥር ሥር ዋልን፡፡ ከተለያየ እስር ጀምሮ ዕድሜ ልክ ተፈረደብን፡፡ የሁለት መንግሥት ሰለባ ሆንን፡፡ ይህ ራሱ ንጹኃን ሰዎች እንደፈለጋችሁ አስራችሁ እንዳሰቃያችሁ በቂ ማስርጃ ሊሆንዎት በተገባ ነበር፡፡ ዳሩ ያልተያዘ ግልግል ያውቃል ሆነና በኢሕአዴግ ዘመን በእስር ያሳለፍናቸውን ረዥም ዓመታት እርስዎ ሜዳሊያና ኒሻን፣ ሹመትና ሽልማት አድርገው ወስደውታል፡፡ በቁስላችን ለመሳቅና ለመሳለቅ በመፈለግዎ አምላክ ይቅር ይበልዎት፡፡

‹ጥርስና ከንፈር አብሮ ይደማል› እንደሚባለው ለአለቃ መከላከል ተገቢ ነው፡፡ አገር ያወቀውን ፀሐይ የሞቀውን ነገር ለመከላከል መሞከር ግን ትርፉ ትዝብት ነው፡፡ ‹‹ሙት ወቃሽ አያድርግኝ›› ይላሉ አበው ሲተርቱ ተናግሮ አናጋሪ እያለ ግን ሙት መወቀሱና መቀስቀሱ አይቀርም፡፡ ከአለቃዎ ጋር አብሬ ታስሬ ነበር፡፡ የመሥሪያ ቤታችሁ ባልደረቦች ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ስቀርቡ ኮሎኔል ተስፋዬ ሳይጠየቁ፣ ‹‹በእኔ መሥሪያ ቤት እኔ ሳላውቅና ሳላዝ አንድም ነገር አልተፈጸመም፣ ኃላፊነቱን በሙሉ እኔ እወስዳለሁ፤›› ብለው ተናገሩ፡፡ ዳኛውም ወቅቱ ሲደርስ ይህንን ይገልጻሉ ሲሉ መለሱላቸው፡፡

ወቅቱም ደርሶ የመሥሪያ ቤታችሁ ባልደረቦች የነበሩ መለዮ ለባሾች ለምስክርነት ሲጠሩዋቸው ግን በዓቃቤ ሕግ እንደሚለቀቁ ቃል ተገብቶላቸው ነው መሰለኝ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው አላውቃቸውም ሲሉ ካዱ፡፡ በዚህ ብቻ አላበቁም፡፡ ወታደሮች መሆናቸውን እያወቁም፣ ወታደሮች አልነበሩም ስሉ መሰከሩ፡፡ እነዚህ ታዛዦች በእሳቸው ምስክርነት ዕድሜ ልክና ሞት ተፈረደባቸው፡፡ ሞት የተፈረደባቸው ኢሕአዴግ ይቅርታ አድርጎላቸው አሁንም በሕይወት አሉና ይጠይቁዋቸው፡፡ አለቃዎ ግን እነሱን ጭዳ አድርገው ሊወጡ ቋምጠው ነበር፡፡ ሌላም ሌላም አለ፡፡ ሆድ ይፍጀው!

በመጨረሻ እርስዎ በመሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ  ባለሥልጣን ከነበሩ በማዕከላዊና በቤርሙዳ ይፈጸም የነበረውን ግፍ አያውቂም ነበር? በመሆኑም በመሥሪያ ቤትዎ የነበሩ ከአለቃ እስክ ምንዝር በኢሕአዴግ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ሲውሉ እርስዎ የውጭ ዜጋ አይደሉ እንዴት ተረፉ? በትብብር ወይስ በድርድር? ‹‹መጫር ያበዛች ዶሮ የመታረጃዋን ቢላዋ ታወጣለች›› አሉ ቸር ይግጠመን!!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles