በከበደ ካሳ
እስኪ አንድ የሚገርመኝን ነገር ላንሳ፣ ተሳስቼ ከሆነም አርሙኝ፣ የምወቅሳችሁ ወገኖች ተሳስታችሁም ከሆነ ለመታረም አትፈሩ።
አሁን ላነሳ የፈለግሁት ስለ ሁለት ሰንደቅ ዓላማዎች ነው። ርዕሴን ‘የሁለት ሰንደቅ ዓላማዎች ወግ’ ልለው ፈልጌ ነበር። ቢሆንም ቅሉ እነዚህ ሰንደቅ ዓላማዎች አብረው ሊያወጉ የሚችሉበት ተፈጥሮ የላቸውምና ርዕሴን ቀይሬዋለሁ።
አንደኛው ሰንደቅ ዓላማ በጎንደርና በባህር ዳር ሠልፈኞች ይዘውት ያየነው ነው። አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሆኖ መሀሉ ላይ ምንም ዓርማ የሌለበትን ማለቴ ነው። ይህ ሰንደቅ ዓላማ ጎንደር ከተማ አደባባይ ላይ የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማን በማውረድ እንዲውለበለብ ተደርጓል። ሌላው በተመሳሳይ ወቅት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ከተሞች (አዲስ አበባን ጨምሮ) በተደረጉ ሠልፎች ላይ ሠልፈኞች ይዘውት የነበረው የኦነግ ባንዲራ ነው።
የኦነግ ባንዲራ በቃ የኦነግ ነው። ስሙም፣ ግብሩም፣ ዓላማውም ጥንቅቅ ተደርጎ የታወቀ የለየለት ባለቤት አለው። እኔን የሚገርመኝ ግን የዚያኛው ባንዲራ ባለቤት ማንነት ነው። በእርግጥ ‘የእኛ ባንዲራ ዓርማ የሌለው ነው’ የሚሉ ወገኖች በአገር ውስጥም በውጭም እንዳሉ አውቃለሁ። ጥያቄዬ ግን ‹‹እኛ›› የምትሉት እናንተ ማን ናችሁ? የሚል ነው።
እንደሚታወቀው ሰንደቅ ዓላማ ከጀርባው ትልቅ መልዕክትን ያዘለና አንድን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የሚወክል ነው። የየትኛውም አገር ወይም የኅብረተሰብ ክፍል ባንዲራ ከዚያ አገር ሕዝብ ማንነትና ከሚከተለው የፖለቲካ ሥርዓት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ትርጓሜና ውክልና ይሰጠዋል። ሌላው ቀርቶ የኦነግ ባንዲራም ራሱን የቻለ መልዕክትና ዓላማ ያዘለ ነው።
እኔ አሁን ጥያቄ የማነሳው የዚህ ልሙጥ ባንዲራ ትርጓሜና መልዕክት ምንድን ነው? በማለት ነው። ትርጓሜው ይህ ነው፣ የሚወክለውም ይህንን ነው የሚለኝ ካለ በቅንነት ለመቀበልና የማላውቀውን ለመማር ዝግጁ ነኝ። እስከዚያው ግን እኔ የሚረዳኝን ላካፍላችሁ።
ይህ ባንዲራ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ካለው የኢፌዴሪ ባንዲራ የሚለየው መሀሉ ላይ ዓርማ ስለሌለው ብቻ ነው እንጂ በቀለም ተመሳሳይ ናቸው፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ። በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 አንቀጽ 7 ላይ የቀለማቱን ትርጉም አስመልክቶ እንደተቀመጠው አረንጓዴው የሥራ፣ የልምላሜና የዕድገት ምልክት ሲሆን ቢጫው የተስፋ፣ የፍትሕና የእኩልነት ምልክት ነው። ቀዩ ደግሞ ለነፃነትና ለእኩልነት መስፈን የሚደረግ የመስዋትነትና የጀግንነት ምልክት ነው፡፡ በዚህ ላይ ልዩነት ያለ አይመስለኝም።
የልዩነት ነጥብ ሆኖ የሚታየው ዓርማው ነው። እዚህም ላይ ቢሆን ውይይት ሊያስነሳ የሚችለው ጉዳይ ዓርማው የያዘው መልዕክት እንጂ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ዓርማ ማስቀመጥ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን፣ በብዙዎቹ የዓለም አገሮችም የሚደረግ በመሆኑ አከራካሪ ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡ እንግዲህ በባንዲራችን ላይ ያለው ዓርማ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 3 ሥር የተሰጠው ትርጓሜ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ የሚል ነው። ይህ መቼም በእኩልነትና በአንድነት ለማያምን ካልሆነ በስተቀር ለማንም የሚያስከፋ ሊሆን አይችልም። እናም ዓርማው ያረፈበትን መደብ ተቀብሎ ዓርማውን መቃወም ማለት ዓርማው ያዘለውን የእኩልነትና አንድነት ተስፋ መቃወም ነው ብዬ አስባለሁ። አይደለም እንዴ?
ከዚህ አንፃር የኦነግን ባንዲራ እንመልከት። የኦነግ ባንዲራን ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባንዲራም ሆነ ከፌዴራል መንግሥቱ ባንዲራ ጋር ብናነፃፅረው ልዩነቱ በዓርማ ብቻ ሳይወሰን የቀለምም ሆኖ እናገኘዋለን። ልዩነት እንዲህ ሲሆን ለክርክርም ይመቻል፣ ግልጽ ልዩነት። በታሪክ አጋጣሚ የተዛቡ ግንኙነቶች እንዳሉ ተቀብሎ እነዚህን ስህተቶች በማረም፣ የጋራ እሴቶቻችንን በማጎልበትና የጋራ ጥቅሞቻችንን በማሳደግ በአንድነት የመኖር ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትና ያለፈውን ቁስል ሁል ጊዜ እንዲያመረቅዝ እያደረገ ተገንጥሎ መኖርን በሚሻ ጠባብነት መካከል ያለ ግልጽ ልዩነት። እናም ኦነግ አንድነትን ሳይሆን መገንጠልን የሚሻ አካል በመሆኑ የአገሪቱን ባንዲራም ሆነ የክልሉን ዓርማ ያለመጠቀሙ፣ ብሎም የራሱን ባንዲራ መቅረፁ የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከባንዲራ አጠቃቀም መርህ አንፃርም ተገቢ ነው።
በከፊል ከላይ ካነሳሁት ጉዳይ ጋር የሚያያዘው ሁለተኛው ጥያቄዬ ልሙጡን ባንዲራ ‘የእኛ ነው’ የሚሉ ወገኖች ይህን ባንዲራ ከየትኛው ሥርዓት ጋር እያስተሳሰሩት እንደሆነ እንዲነግሩኝ ነው። አንዳንድ ጸሐፊዎች እንደሚያስቀምጡት ኢትዮጵያ ከአሁኑ በፊት በተለያዩ የመንግሥት ሥርዓቶች ሰባት ጊዜ ያህል ብሔራዊ ባንዲራዋን ቀያይራለች። ይኼ ልሙጡ ባንዲራ ግን በየትኛውም ሥርዓተ መንግሥት ወቅት አገልግሎት ላይ አልዋለም። በየሥርዓቱ የነበሩ ሰንደቅ ዓላማዎች የጋራ የሆኑ ባህሪዎች ነበሯቸው፡፡ በመጀመሪያ ከጥንት እስከ አሁን በሁሉም ሰንደቅ ዓላማዎቻችን የነበሩት ቀለሞች አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ናቸው፡፡ በተጨማሪ ከ1890 በፊት ከነበረውና ከደርግ ውድቀት በኋላ በሽግግሩ ወቅት ለአጭር ጊዜ ከነበረው ሰንደቅ ዓላማ ውጪ በሁሉም ላይ ዓርማዎች ነበሩ፡፡
በአፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት በሰንደቅ ዓላማው ላይ ዘውድ የጫነ አንበሳ መስቀል ይዞ ይታይ ነበር፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም ይሄው አንበሳ ‹‹ሞዓ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ›› የሚል ጽሑፍና ኮከቦች ተጨምረውለት እስከ ወታደራዊው የደርግ ሥርዓት ድረስ ቀጥሏል፡፡ ደርግ ሥልጣኑን እንደያዘ አንበሳው ላይ የነበረውን ዘውድ ያነሳ ሲሆን፣ በመስቀሉም ቦታ የጦር ጫፍ ምልክት አስቀምጧል፡፡ በ1979 ዓ.ም. ደርግ አንበሳውን ሙሉ በሙሉ በማውጣት በምትኩ ጦር፣ ጋሻ፣ ማረሻ፣ የስንዴ ዘለላና ሌሎች ምልክቶችን ያካተተ ዓርማ አስቀምጧል፡፡ ከኢሠፓ ምሥረታ በኋላም ሌላ ለውጥ በማድረግ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ›› የሚል ጽሑፍና የኢሠፓ መገለጫ የሆነ አነስተኛ ዓርማ በውስጡ ያካተተ ዓርማ በሰንደቅ ዓላማው ላይ እንዲሰፍር አድርጓል፡፡
እንግዲህ ሰሞኑን የምናየው ባንዲራ ሙሉ በሙሉ የሚመሳሰለው ደርግ ከተገረሰሰ በኋላ በነበረው የሽግግር መንግሥት ወቅት ከነበረው ባንዲራ ጋር ብቻ ነው፡፡ በደርግ ውድቀት ማግሥት (በሽግግሩ ወቅት ማለቴ ነው) አገራችን ትመራበት የነበረው ገዢ አስተሳሰብ በመሠረታዊነት ከአሁኑ የፌዴራላዊ ሥርዓት የተለየ አልነበረም። በየጊዜው በማጥራት ውስጥ እያለፈ የጠራ መስመር ሆኖ የወጣው በኢሕአዴግ ውስጥ ከተካሄደው ተሃድሶ በኋላ ቢሆንም የመንግሥት አስተዳደር፣ አወቃቀርና ገዢው ፓርቲ የሚከተለው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ደርግን ለማስወገድ በተደረገው ትግል ወቅት ተመልሶ ያደረ ነው። ስለዚህ አሁን አገሪቱ ከምትመራበት የፖለቲካ ሥርዓት ጋር ልዩነት ያላቸው አካላት ቢያደርጉ የሚያምርባቸውና የሚገባቸው ከቀደሙት ሥርዓቶች ዓርማዎች ውስጥ አንዱን መመለስ ወይም ደግሞ የራሳቸውን ዓርማ መሥራት ነው እንጂ፣ አሁን የሚያውለበልቡት ባንዲራ እነሱ ለያዙት ዓላማም የሚመጥን አይደለም።
ለነገሩ ይህ መፍትሔ ለእነሱም ከብዷቸው እንጂ ጠፍቷቸው አይደለም። የቀደሙት ሥርዓቶች ዓርማዎች ሲታዩ በግልጽ የገዥዎችን የበላይነትና እነርሱ ነን ብለው የሚያስቡትን ሥዩመ እግዚአብሔርነት የሚሰብኩ፣ ኋላ ላይ የመጡት ዓርማዎች ደግሞ በነፃ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የሕዝቦች አንድነትን ሳይሆን በኃይል የሚመጣን የግዛት አንድነት የሚናፍቁ ናቸው፡፡ እናም እነዚህን በልባቸው ያሉ ዓርማዎች አንግቦ አደባባይ መውጣት የዓርማዎቹን ባለቤቶች ታግሎ ከጣለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በቀጥታ የሚያላትማቸው መሆኑን ይረዱታል። ስለሆነም እንዲሁ በደምሳሳው ማጣፊያ የሚያጥራቸውን አጀንዳዎች በመቅረፅ የቻሉትን ያህል ኃይል ለማደናገርና ከጎናቸው ለማሠለፍ ይተጋሉ። ከሰሞኑ የታየውም ይኼው ነው።
ለዚህ ጽሑፍ የተነሳሳሁት ሠልፎቻችን ሕጋዊ ጥያቄዎችና ሕጋዊ ያልሆኑ ጥያቄዎች ተቀላቅለው ከሚተላለፉባቸው ወይም ደግሞ ሕጋዊ ጥያቄዎች በሕገወጥ አካሄድ ከሚቀርቡባቸው መገለጫዎች አንዱ ይኼው የባንዲራ ጉዳይ ስለሆነ እንጂ ከተሰለፍን አይቀር የምንጠይቃቸው፣ መንግሥትም ሊፈታቸው የሚገቡ ብዙ ችግሮች እንዳሉን ጠፍቶኝ አይደለም። በአካል ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብም የተሠለፍንበት ጎራ ከተደበላለቀ ግን ትርፉ ኪሳራ፣ መጨረሻውም የኋሊት ጉዞ ነው የሚሆነው።
ባነሳኋቸው ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ያለው ሰው በኢሜይል አድራሻዬ ቢነግረኝ ወረታውን በምሥጋና እከፍላለሁ።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡