Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በር መስበር ወይስ ቁልፍ መፈለግ?

ሰላም! ሰላም! ፖለቲካ አናይም አንሰማም ብለን ወደ ኦሊምፒክ መንደር ብንሰደድ እሱም ፖለቲካ ሆኖ አረፈው። እንግዲህ ዘንድሮ ስንት መቶ ሺሕ ሰው ነው በጎርፍ ይበላል የተባለው? ከአሁን አሁን ተበላን እያልን ስንጠባበቅ 100 ሚሊዮናችንም ሪዮ ተበልተን አረፍነው። አጀብ! ባሻዬ መቼም ወልደዋልና በሪዮ ኦሊምፒክ የውኃ ዋና ውድድር የወከለንን ሰውዬ (አትሌት እንዳንለው ዓሳ ነባሪ ብለውታል) ሁኔታ ሲያዩ የወላጆቹ ነገር በጣም ያሳስባቸው ጀመር። እና ምን ቢሉኝ ጥሩ ነው? ‹‹እንዲያው አደራህን በአገራችን በምድራችን በክብደት የማይሞከረውን የዋና ውድድር ምን ሲደረግ አሰበው?›› ብለው ጠየቁኝ። ባሻዬ ደግሞ አንዳንዴ ዕውቀታቸውና ንግግራቸው አልገናኝ ይላል። እንደ እሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያነብ በሰለሞን ጽሑፎች የሚመሰጥ ሃይማኖተኛ አላየሁም። ታዲያ ሰለሞን ምን ብሏል? ‹ሩጫ ለፈጣኖች፣ ጥበብ ለአዋቂዎች፣› የውኃ ዋና ደግሞ ለዋናተኞች (ይህቺን የጨመርኳት እኔ ነኝ) አይደለም? ነገር  ግን ጊዜና ዕድል ሁሉን ያገናኛቸዋል አላለም። ይኼን የነገሩኝ እኮ ራሳቸው ባሻዬ ናቸው።

እኔማ ተፍ ተፍ ስል እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ላነብ ስልኬ ላይ የሚንጣጣውን የደንበኞቼን የጽሑፍ መልዕክትስ መቼ በቅጡ አነባለሁ? ለነገሩ ይኼን አሁን ያነሳነውን ጉዳይ ሰለሞን አስቀድሞ እንዳለው ብናውቅ ባናውቅ ችግር ያለው አይመስለኝም። ምክንያቱማ ጊዜና ዕድል የሚያገናኛቸውን ገድለኞች በዕለት ተዕለት ኑሯችን እያየናቸው ስለሆነ ነው። አሁን ጭራሽ ከእኛ አልፎ ዓለምም ብቻችሁን አታዩም ብሎ ተጋራን። ዕድሜ ‹ለዓሳ ነባሪያችን።› ታዲያ አንድ ወዳጄ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹አንተ ለካ ፈረንጅም ይኮምካል፤›› አለኝ። ‹‹ምን አሉ?›› እለዋለሁ ‹የአገሪቷ የኢኮኖሚ ዕድገት ዜጎችን በቀን ሦስቴ ከመመገብ አልፎ እንዴት እያዝረጠረጣቸው እንደሆነ ለማሳያ የተላከ ልዑክ እንጂ፣ አትሌት አይደለም› ብላ አንድ ፈረንጅ የጻፈችውን ሲያስነብበኝ እንዳላለቅስ አፈርኩ እንዳልስቅ ፈራሁ። ካላመናችሁ ዴይሊ ሜልን አንብቡ!

እናማ እላችኋለሁ በዚህ ጭጋግና ነገር ባፈነን ጊዜ እንዲህ ፈታ የሚያደርግ ዜና መገኘቱ በበኩሌ ተመችቶኛል። ማንጠግቦሽማ የዓሳ ነባሪያችንን ድፍረትና ወኔ ካየች በኋላ፣ ‹‹በል በሚቀጥለው ኦሊምፒክ የምትወዳደርበትን የውድድር መስክ ምረጥ . . .›› እያለች ትነዘንዘኝ ጀምራለች። ‹‹ዝም ተብሎ ስፖርተኛ ይኮናል እንዴ? ሚኒማ አለ ብርታት፣ ጥንካሬ፣ ትንፋሽ፣ ወጥ አቋም፣ ወዘተ. የሚባል ነገር እኮ አለ፤›› ብዬ ሳልጨርስ፣  ‹‹ግዴለም ለእሱ አታስብ። ሁሉን እንደሚሆን ታደርገዋለህ። ዋናው ዘመድ ነው፤›› አትለኝ መሰላችሁ? ምን ማለትሽ ነው? ብዬ ልቆጣት ስል ከጋብቻ ትስስር በስተቀር ዘንድሮ ሁሉም ነገር በትውውቅና በዝምድና መሆኑ ትዝ ብሎኝ ዝም አልኩ። ትዝታዬ ትዝታ ሲቆሰቁስ ደግሞ ልጆች እያለን በአቅራቢያችን ያለ ወንዝ እየሄድን የምንዋኘው ትዝ አለኝ። የምንዋኘው ስል መቼም ይገባችኋል። የዛሬን አያድርገውና መዋኘት እንዲህ ቀላል ነገር አልነበረም። ሲጀመር ከቤት የሚያስወጣ ሰው ሲኖር ነው።

የዛሬን ባላውቅም የእኛ ወላጆች ልጆቻቸውን ከውኃ ዋናና ከሰው ዓይን ሰውረው በማሳደግ የሚያምኑ ነበሩ። ያውስ ልዋኝ ነው ተብሎ ቀርቶ እዚህ በራፉ ላይ ልጫወት ብንል የሚለቀን ነበር እንዴ? አንዳንዴ ሳስበው እየተፈራረቀ የምናየው ጭቆናና አፈና ምንጩ እዚያ ይመስለኛል፡፡ ቤታችን! አይመስላችሁም? ታዲያ እንደምንም ተሽሎክሉከን አንዴ ከቤት ልንወጣ አይደል? ምናልባት ካደግን በኋላ የሚታይብን ተሽሎክልኮ ከአገር የመውጣት አባዜም ጥንስሱ እዚያ (ዕድገታችን ሠፈር) ይሆናል። እንደ ልጅነታችን ራቁታችንን ወንዝ ለወንዝ ስንቦጫረቅ ውለን ስንመለስ ቀጥታ ወደ ፓስቲ ቤት ነው። ከውኃ የወጣ ሰው የረሃብ ስሜት ስለሚሰማው አይምሰላችሁ ፓስቲ ቤት የምንሮጠው። ለዘይቱ ነው እንጂ። ጠርሰቅ አድርገን በልተን ስብ ለማቃጠል እንደምዋኝማ ዕድሜ ለዓሳ ነባሪያችን ይኼው ዛሬ ዓለም አወቀለን። ምናልባት ሰው ተጠራጥሮ ደረታችንን ሲያሻሸው አመዳችን ቡን ካለ ወንዝ እንደወረድን ይታወቅብናንና ዋጋችን ይሰጠናል። ስለዚህ መፍትሔው የፓስቲ ዘይት መለቅለቅ ነበር። እንጂ እንደ ዛሬው ከዋና በኋላ ያውም ከ59 ተወዳዳሪዎች 59ኛ ተወጥቶ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት? እኮ በምን ዕድላችን?

መቼም ውይይትን የመሰለ የበሳል ሕዝብ መገለጫ ነገር የለም። የእኛ ነገር አልመቸን እያለ ከልማታዊ ዳንሱ፣ ጭፈራውና ሆታው፣ ፖለቲካዊ አቋም ፍተሻው ፋታ ወስዶ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገር እያቃተን፣ ይኼው እንደምታዩት ብዙ ያልተዘጉ የውይይት ፋይሎች አሉን። ከሰሞኑን ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ልምድ የተማሩት ይመስላል ከወጣቶች ጋር ውይይት ሊያደርጉ ማሰባቸውን ባሻዬ ሰሙ። ወዲያው የመንደሩን ወጣቶች ሰበሰቡ። ኋላ ለምን ቅድመ ስብሰባ እንዳሰቡ ስጠይቃቸው፣ ‹‹ኋላ ደግሞ የማይሆን የማይሆን ነገር ጠይቀው ጀርባቸው ሲጠና መድረሻ ልጣ?›› ነበር ያሉኝ።

እናም ወጣቶቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚጠይቋቸውን ምን ምን እንደሆነ ሊገመግሙ ቁጭ አሉ። ጥያቄዎች መቅረብ ባሻዬ ደግሞ መከርከምና ማረም ጀመሩ። አንዱ ተነስቶ፣ ‹‹እኔ የማነሳው ስለጤናማ የተስተካከለ አቋም ያለው ብቁ ተወዳዳሪ ዜጋ ስለመፍጠር ነው። እንደሚታወቀው አገራችን በምታስመዘግበው ፈጣን ዕድገት ሳቢያ ወጣቱ ወገቡ አልታጠፍ ክንዱ አልዘረጋ እስከሚል በምቾት ሸምግሏል። ቦርጭ መጫወቻ አድርጎናል። ጫት፣ ሲጋራና አልኮል በስትሮክ ሊጨርሰን ነው። ኳስ ማንከባለል ሲያምረን የምንገኘው ዲኤስ ቲቪ ቤት ነው። ሌላው ቀርቶ በየአካባቢው የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ሳይዘጋጅ አገራችን በዓለም አቀፍ ስፖርታዊ የውድድር መድረኮች ለማግኘት ያሰበቻቸውን ሜዳሊያዎች እንዴት ታገኛለች? ለምን? እስከ መቼ?›› ሲል አዳራሹ በጭብጨባ ደመቀ። ራሳችን ለራሳችን እናጨብጭብ እንጂ ሌላውማ እየሳቀብን ነው!

እናላችሁ ከመሸ የተቀላቀልኩት ፌስቡክ የሚባል ዘመናዊ ብራና ሥራዬን እያስረሳኝ ተቸግሬያለሁ። አንዳንድ ወዳጆቼ ሁኔታዬን እያዩ የማይዳሰሰው ብራናቸው ላይ ሲያሙኝ ተደብቄ አያለሁ።  ‹‹አንበርብር እንዲህ 24 ሰዓት ኢንተርኔት ላይ ተሰጥቶ መዋል የጀመረው ከገዥው ፓርቲ የለየ ቅናሽ የኢንተርኔት መስመር ስለተቀጠለለት ነው፤›› ይሉኛል። እኔ ደግሞ ከታማሁ አይቀር እልና ‹‹ሕገ መንግሥታችን ባጎናፀፈን የእኩልነት የመናገርና የመጻፍ መብት ዛሬ እንኳን ገበሬው  ፌስቡከሩ ሳይቀር ምርትና ግርዱ በነፃነት እያጨደ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፤›› እላለሁ። እንዲህ ስጃጃል ለካ በላዬ ላይ ስንት ቤት ተሸጠ፣ ስንቱ ተከራየ አትጠይቁኝ። እየተደናበርኩ ተነስቼ አንድ እጄ ላይ የነበረ ካሚዮን ላሻሽጥ ከቤቴ ወጣሁ። ተፍ ተፍ ብዬ አስማምቼ ለፍፃሜ በነጋታው ቀጠሮ ይዤ ስመለስ፣ አንዲት በቆሎ ሻጭ ጠብሳ ልትሸጥ ከሰል እፍ ስትል ዓይኔ ገባ።

ዓለም በሥጋትና በተስፋ በሚያያት ውዲቷ አገሬ በቆሎ በዘመናዊ መንገድ ተጠብሶ የሚሸጥበትን ቀን በሴትዮዋ በኩል አልሜ ሳልጨርስ፣ ከጀርበዋ ተቀምጦ የነበር የሚድህ ሕፃን ቅቅል በቆሎ የያዘውን ድስት ከነበለው። ፍል ውኃው እግሩ ላይ ፈሰሰ። ሰው ተደናግጦ ሳያበቃ፣ ‹‹ይድፋህ ያባቴ አምላክ፤›› ብላ በጥፊ መታችው። ይኼኔ አንዱ ምን ቢል ጥሩ ነው? ‹‹አሁን ይኼ ልጅ ነው አድጎ የፍትሕና ዴሞክራሲ ጠበቃ የሚሆነው?›› ሲል አጠገቡ ቆመው ትዕይንቱን ሲመለከቱ የነበሩ የባሻዬ እኩያ፣ ‹‹እስኪ መጀመርያ ይደግ ተወው . . .›› እያሉ አለፉ። አላስተውለው እያልን እንጂ እኮ ፀረ ሰላምም ሆነ ሰላማዊ የሚባለው ሠልፋችን ለካ የሚጀምረው ገና ስንድህ ነው!

በሉ እንሰነባበት። ነገር ስለበዛ ብቻ አያነጋግርም። አዕምሮ ያለው ሁሉ ያስባል ማለት አይደለም። አፍ ያለው ሁሉ የሚናገረው ትክክል ነው ማለት አልነበረም። ግን እንደምታዩት ዘመኑ ሁሉን ሸጋ፣ ሁሉን ትክክል፣ ሁሉን አዋቂ አድርጎታል። ነገር ሁሉ ሲያታክታችሁ እናንተ የምታደርጉትን ራሳችሁ ታውቃላችሁ። በበኩሌ እኔ የባሻዬን ልጅ እጠራና ወደ ግሮሰሪያችን እጎትተዋለሁ። እሱ ደግሞ እንደምታውቁት በተሳለ ምላሱ በምሁራዊ አንደበቱ፣ በዕውቀት በተገራ የማሰብ ሕግጋትን በተከተለ ጤናማ አገላለጹ የፈረሰብኝን ሲገነባልኝ፣ የተዛባብኝ ሲያስተካክልኝ ያመሻል። አንዳንዴ ይኼን መልካም ወዳጅነቱን እያየሁ ምነው ሰው ስለፀጉር አስተካካዩ ብቻ ይጨነቃል። ለምን አስተሳሰቡን የሚከረክምለት፣ የሚያስተምረውና የሚያንፀው ሰው አያሳስበውም? እላለሁ፡፡ ታዲያ እንዲህ ስንባባልና ወቅታዊ ጉዳዮችን እያነሳን ስንጫወት ቆየንና አንድ ጥያቄ ጠየቅኩት።

‹‹አንተ ፌስቡክ እንዲህ የቀለጠ ሕዝባዊ መንደር ነው እንዴ?›› ስለው፣ ‹‹ነበር ባይሰበር። ግን መጣ መጣና እኛ ጋ ሲደርስ ሳተ፤›› አለኝ። ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹በአጠቃላይ ይኼ ቴክኖሎጂ አመጣሽ የመናገሪያ፣ የማዳመጫ፣ የመጻፊያ መሣሪያ?›› እኛ ዘንድ ከሽፏል አንበርብር። ነጥብ በነጥብ አንነጋገርበትም። ሐሳብ ለሐሳብ አንወያይበትም። ሰው ትናንት የኖረው ኑሮ ዛሬውን ሲሞርደውና ሲመክረው ታያለህ። እንዴት ትናንት የጻፍከው፣ የዘለፍከው፣ የሳትከው ስህተት ዛሬ አይቆነጥጥህም? የሆነ አዙሪት ውስጥማ ገብተናል። ታዲያልህ ምን ይሻላል? ሲባል አዋቂ ተብየዎቹ ይብሳሉ። እንቁላሉን ሰብረን መውጣት አለብን ይሉናል። የሰው ልጅ ከአጥቢ እንስሳት የሚመደብ ነው። ተምጦ ተወልዶ አምጦ ነው የሚወልደው። ያ ማለት ኑሮው በጥረት፣ በትጋት፣ በመከራና ከአሳለፈው በመማር የሚመራ ፍጡር ነው ማለት ነው እንጂ፣ የስሜትና የጉልበት ፍጡር አይደለም ነው ነገሩ። ታዲያ ለምድነው ቁልፉን ፈልገን እናግኘው አናግኘው ገና ሳይታወቅ በር ስለመስበር የሚወራው? ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜታዊነት ለምን ይቀድማል?›› ሲለኝ ደንዝዤ አዳምጠው ነበር። ለዚህች አገር ችግር መፍትሔ የሚባለው በር መስበር ሳይሆን አሁንም ነገም ከነገ ወዲያም ቁልፉን ማግኘት ላይ ነው ብሏል አንበርብር ምንተስኖት ብላችሁ አደራ ፌስቡካችሁ ላይ ሼር አድርጉልኝ። ሰላም ተመኘሁ። መልካም ሰንበት!       

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት