Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርመልካም ለሠራ ምስጋና ይገባዋል

መልካም ለሠራ ምስጋና ይገባዋል

ቀን:

በ2008 ዓ.ም. አሥራ አንደኛው ወር፣ ስድስተኛው ቀን ላይ ከደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍል መናገሻዋ ሐዋሳ ከተማ፣ በአንደኛውም ሆነ በሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ የተካተተና ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ለሚደረገው ጉዞ ተስፋ የሚደረግበት አስደሳች ነገር ሰምተናል፤ አይተናልም፡፡

ብዙዎች የአገሪቱ ዕቅዶች ከውጤታማ አተገባበር ይልቅ በየጊዜው ‹‹የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ፤›› በሚባለው ምሳሌ አነጋገር ዓይነት እየተጓተቱ፣ የምክንያት ድርደራና ሰበብ እየተደረደረላቸው ይገኛሉ፡፡ ታዛቢዎች ትራንስፎርሜሽኑ ሩጫ ይፈልጋል፣ እይሄደ ያለው ግን በሶምሶማ ነው ይላሉ፡፡

እንደ ማሳያም የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታው፣ የስኳር ፋብሪካዎች፣ የኤሌክትሪክ ግድብ ሥራዎች፣ የኤለሌክትሪክ ኃይል፣ የመንገድ ወዘተ. ሥራዎች በተግባር ከሚታይ አፈጻጸማቸው ይልቅ ምክንያታቸው እየበዛ ተጨባጭ ነገር ሲታጣባቸው በአብዛኛው በዕቅዳቸው መሠረት አለመሄዳቸው በኅብረተሰቡ ዘንድ እየታወቀ በመምጣቱ ተስፋ አስቆራጭ ድባቦች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ለዚህ ነው የአገሪቱ የሐዋሳው ኢንዱስትሪ ፓርክ ስኬታማነት ሁሉንም ወገን በአንድ ላይ ያስደሰተው፤ ያስጨበጨበው፡፡

ለሌሎችም ፕሮጀክት አስተማሪ ሊሆን የሚገባው ሥራ ነው፡፡ የዚህ ውጤት ፊት አውራሪ የሆኑት ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ በኢንቨስተሮቹ ብቻ ሳይሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም እንዲሞካሹ ያበቃቸው፡፡ ከመንግሥታቸውና ከድርጅታቸው ባህል አፈንግጠው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶ/ር አርከበን እንዲያመሰግኑ የተሠራው ሥራ  አስገድዷቸዋል፡፡ የሚያዩት የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታው ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ ውጤት ግለሰብን ያለማመስገን አጉል ባህል ጥለው በሥፍራው በተገኙ እንግዶች ፊት፣ በቴሌቪዥን መስኮት በሚከታተለው ሕዝብ ፊት ዶ/ር አርከበን ሳያቅማሙ አመስግነዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ መንግሥታቸው በውጤታማ ሥራ ከሕዝባቸው ጋር መደሰት ከቻሉ፣ በየጊዜው የምንሰማው የፕሮጀክት መጓተቶች ሕዝብን እንደሚያስከፋው ማስረጃ ነው፤ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑንም ሊረዱት ይገባል ማለት ነው፡፡

ከዚህ የምንረዳው በታቀደላቸው ጊዜ የማይተገበሩ፣ የሚጓተቱና የማያሳኩ ፕሮጀክቶች ላይ መንግሥት ዓይኑንና ቀልቡን ሊያነሳ እንደማይገባው፡፡ ጊዜን ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚያዊ፣ የማኅበራዊና የፖለቲካዊ ኪሳራቸው ቀላል ባለመሆኑ ጥንቃቄ ቢደረግበት መልካም ነው፡፡

አገራችን የተሻለች ሆና ለመገኘት ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ነድፋ እየተንቀሳቀሰች ቢሆንም፣ አብዛኞቹ በተያዘላቸው ዕቅድ እየሄዱ አይደለም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ ከታቀደላቸው በላይ እስከ አምስት ዓመት፣ በገንዘብም እስከ አምስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ የጠየቁ ፕሮጀክቶች እንዳሉ እሙን ነው፡፡ እነዚህን ፕሮጀክቶች በማስተባበርና በማስፈጸም በወጉ ያልተገበሩትን አካላት የአፈጻጸም ችግር መገምገም ይገባል፡፡

እነሱ ያቀበሉትን ለሕዝብ ከማቀበል፣ ድክመታቸውን ከመሸፈን፣ ከሆዳምነትና ከአቅም ማነስ በስተጀርባ የአገር ክህደት እየፈጸሙ ስላለመሆናቸው ማረጋገጥ ያስፈልጋል እንጂ የፖለቲካ ሹመኛ አልያም የመንግሥት ባለሥልጣን ናቸው በሚል ሽፋን ድክመታቸውን አሜን ብሎ መቀበል የዕድገት ሽግግሩን በእሾህ እንደማጠር ይሆናል፡፡

የዶ/ር አርከበ ውጤት ደካማ አፈጻጸም የሚያሳዩ ሹማምንትን ያጋለጠና በትጋት ከተሠራም የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ሊተገበር እንደሚችል ማስረጃ ነው፡፡ የተጠናና የተቀናጀ እንዲሁም በቅርብ ክትትል የሚደረግበት ሥራ ውጤቱ ልክ እንደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ አስደሳች ይሆናል፡፡

መንግሥት ካረጀና ካፈጀ አሠራሩ ወጥቶ ጎበዞችን ማመስገን፣ ደካሞች ለማበርታት፣ ለጠንካሮቹም ፅናት ሲሆን፣ በሚሠሩት ሰዎች የተሸፈኑ ደካማና አጥፊዎችን ለይቶ የማወቂያ መነፅርም ይሆነዋል፡፡ ለዚህ መለኪያው ግን ውጤትና ውጤት ብቻ እንጂ ከላይ እስከ ታች የተዘረጋ ኔትወርክ መሆን የለበትም፡፡ ይህ የመመላለሻ መድረክ እንዳይሆንና የእውነት መስዋዕትነት ተከፍሎ የተገኘውን ዕድል በዋሾች መጫወቻ እንዳይደረግ በመጠንቀቅ ጥሩ የሠራውን ማመስገን ቢለመድ ጥሩ ነው፡፡ በትጥቅ ትግሉ ጊዜ ግለሰብን አለማመስገን በገዢው ፓርቲ፣ የዚያን ጊዜ አመለካከት ትክክል ነበር፤ ውጤትም አስገኝቷል ሊባል ይችላል፡፡ አሁን ግን ከነባራዊው ሁኔታ ጋር አይሄድም፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበር ጥሬ ሀቅ አስገድዷቸው ይህን እንደጣሱት በዚሁ ሊቀጥሉ ይገባል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያምን፣ ኢንቨስተሮችንና በርካቶችን ያስደሰተውን አመርቂ ሥራ ግን በተደጋጋሚ ማየት አልቻልንም፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ ብናይማ ኑሮ አይደንቀንም ነበር፡፡ እንኳንና የራሳችን ሚዲያዎች የውጭዎችንም ያስደነቃቸው የኢንዱስትሪ ፓርኩ መገንባቱ አይደለም፡፡ እንደዚያማ ቢሆን ኑሮ ናይጄሪያ ቀድማ ትልልቅ ፓርኮችን ገንብታለች፡፡ ባለሀብት ስላልገባባቸው ግን ተራ ሼድ ሆነው ቀርተዋል፡፡ የኢትዮጵያን ለየት የሚያደርገው ፓርኩ ሳያልቅ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው የዓለማችን ትላልቅ ኩባንያዎች ኢንቨስት ለማድረግ መምጣታቸውና ተሳታፊ መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ በፓርኩ ውስጥ የቪዛ፣ የጉምሩክ ሌሎችም መሰል አስፈላጊ አገልግሎቶች  ተሟልተው መዘጋጀታቸው ከውጣ ውረድ የሚያድንና አላስፈላጊ መጉላላትን የሚስቀር ነው፡፡

ፓርኩ በሁሉ ዘርፍ የተዋጣለት ሥራ ተሠርቶበታል፡፡ በአገሪቱ የዕድገት ማነቆ የሆነውና ሕዝቡንም እያማረረ የሚገኘው የመልካም አስተዳደር ችግርና የኪራይ ሰብሳብነት ጥያቄ መንግሥት ብሎም ገዥው ፓርቲ ጭምር የሚያውቀው ነው፡፡ በተለይ በመቐለ ከተማ በተካሄደው የኢሕአዴግ 10ኛ ጉባኤ ላይ ድርጅቱ ችግሩ ጫፍ እንደነካ አምኖ በመልካም አስተዳደርና በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ በሰማዕታት አዳራሽ ቃል ተብቶ ነበር፡፡

ቃል ገብተው ቢመጡም መሬትና መሬት ነክ ላይ ነው ዋናው ኪራይ ሰብሳቢነት የሚታየውና አጠናሁት ባለው እንጂ ችግሮቹ አሁንም ድረስ እንዳሉ አሉ፡፡ በእርግጥም መሬት አካባቢ ያለውን ችግር ለማፅዳት ዘመቻ የተጀመረ ቢመስልም፣ በሌሎች ዘርፎች ላይ ግን አሁንም ሕዝብ እያማረረ ነው፡፡ በጉባዔው የታየው ቁርጠኝነት ተስፋ ቢሰጥም፣ ውሎ ሲያድር ግን ፉከራ ብቻ ሆኖ የቀረ ይመስላል፡፡ በተለይ እንደ አዲስ አበባ በክፍለ ከተማም ሆነ በወረዳ ደረጃ እከክልኝ ልከክልህ ደርቶ እንኳንና ኅብረተሰቡን ያህያ ጆሮ የሚያህል ደመወዝ እያበላ ያለዕውቀታቸው ያስቀመጣቸውን ሕዝብና መንግሥት ንቀዋል፡፡ የሆነ ነገር በአንድ ወቅት ይጀመርና ወዲያው ይቆማል፡፡ ይኼ ደግሞ ለንቀታቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ ጠንካራና የዓላማ አባላት ቢኖሩም ግንባር ቀደምትነቱን በኪራይ ሰብሳቢዎች እየተነጠቁ ስለመሆኑ የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች ሙስና ሳይቀር በግልጽ የሚጠየቅባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ የመንግሥት ሌቦች ተገልጋዩን በማማረር በተለይ ኢንቨስተሮች ከውጭ በስንት ልመና እንዲመጡ ሲደረግ በተገኘው አጋጣሚ ለመመዝበር የሰላ ቢሮክራሲና ሰፊ ኪሳቸውን አስፍተው፣ የመጣው ኢንቨስተር ተማሮ በመጣበት እግሩ እየተመለሰ ነው፡፡ ያጋጠመውን ውጣ ውረድ ተቋቁሞ ሲያልፍና መሬት ሲያገኝ፣ ለዲዛይን፣ ለሕንፃ ግንባታ፣ ለፈቃድ፣ ለባንክ ብድር፣ ለውኃ፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል ወዘተ. እየተባለ እስከ አራትና አምስት ዓመት ውጤታማ ሥራ ሳይሠራ ጊዜውን ይፈጃል፡፡

ይህን ሁሉ ችግር የተረዱት ዶ/ር አርከበ የመጡት እንዳይሄዱ፣ የሄዱትም እንዲመጡ ሊያደርግ በሚችል አኳኋን የተቀናጀና የተቀላጠፈ ሥራ፣ ለዚያም አገሪቱ ከነደፈችው ከአየር ብክለት የነፃና ከአረንጓዴ ልማት ጋር የሚጣጣም ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ያለው፣ ውኃንና ሌላውንም ፍሳሽ መልሶ መጠቀም የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተሟላለት ፓርክ በቅልጥፍናና በአጭር ጊዜ እንዲገነባ ታግለዋል፡፡  የኪራይ ሰብሳቢዎችን እጅ እንዲሰበሰብ ያደረጉ የአመራር ሰው ናቸው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ‹‹ዕድገቱ ያመጣውን ችግር ዕድገት ይፈታዋል፤›› ይሉት የነበረው ነገር በቁርጠኝነት ከተሠራ ትክክል መሆኑን ይህ ፓርክ አሳይቶናል፡፡

ህዳሴው የሚፈልገው ይህን ስለሆነ ዶ/ሩ የሠሩትን ሥራ መንግሥት እንደማንቂያ ደወል ቢጠቀምበት የተሻለ ነው፡፡ ይህን ህዳሴውን ያደሰውን ሥራ ያተባበሩት ዶ/ር አርከበ ዕቁባይን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከድርጅታቸውና ከመንግሥታቸው ባህል ወጣ ብለው፣ ለዚህ ሥራ በሰጡት ትኩረትና ኃላፊነት እንቀልፍ ነስቷቸው ለዚህ ትልቅ ስኬት እንዲደርስ አድርገውናል ሲሉ አክብረዋቸዋል፡፡

ዶ/ር አርከበ እንቅልፍ አጥተውና አሳጥተው በሐዋሳው ፓርክ ብቻ በሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ከአፍሪካ አንደኛ ሊያደርገን የሚያስችለንን ስኬት አስጨብጠዋል፡፡ ከዚህም ተሞክሮ ተነስተን ሌሎች ፓርኮች በተሳካ ሁኔታ እንደሚጠናቀቁ ተስፋ ለቆረጠው ሁሉ ተስፋ ሰጥተዋል፡፡

ብዙዎቻችን ዶ/ር አርከበን ያወቅናቸው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሆነው በ1995 ዓ.ም. ሲሾሙ ነው፡፡ በከንቲባነት ጊዜያቸው የቀለበት መንገድ፣ የኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቶ ስለመሥራት፣ የአርከበ ሱቅ ተብላ በስማቸው የተሰየመችውን ትንሿን የኮንቴነር ሱቅና መሰል ነገሮች ያየነውና የሰማነው በሳቸው ጊዜ ነው፡፡ ኤችአይቪ/ኤድስ የሚገኝባቸው ሰዎች እንዳይገለሉና ሁሉም ሰው ተመርምሮ ራሱን እንዲያውቅ ግንዛቤ መስጫ እንዲሆን የሳቸውን ምስል የሚያሳይ ትልቅ ባነር በአዲስ አበባ ተሰቅሎ አይተናል፡፡

በዚህም ከባለሥልኖች የመጀመሪያው ሆነዋል፡፡ የቦብ ማርሌ 60ኛ ልደት ዓመት ሲከበርም፣ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረጉ የቦብ ማርሌ ቤተሰቦችና አዘጋጆች ሲያመሰግኗቸው ሰምተናል፡፡ በመስቀል አደባባይ ማታ ማታ ውበት የሚሰጡ መብራቶች በእሳቸው ጊዜ ነበር የተተከሉት፡፡ ስለሰውየው ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ሁለት ነገሮችን ጠቅሼ ጽሑፌን ላብቃ፡፡ በ1997 ምርጫ ወቅት ኢሕአዴግን የጠሉ ሰዎች ‹‹አርከበን እንወደዋለን፡፡ እሱን መምረጥ ግን ኢሕአዴግን መምረጥ ስለሆነ እየወደድነው አንመርጠውም፤›› ብለው ያልመረጡት ነበሩ፡፡ ዞሮ ዞሮ ኢሕአዴግ 23 ለ 0 በሆነ ውጤት በአዲስ አበባ ሲሸነፍ፣ ከከንቲባነታቸው ተነስተው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው የሠሩ ሲሆን፣ ከዚያም በኋላ በሕውሓት ማዕከላዊ ኮሚቴና ሥራ አስፈጻሚነት ሳሉ በመተካካት ሰበብ ሲነሱ የትግራይ ሕዝብ ‹‹ይሄ በመተካካት ስም መገፋፋት ነው፡፡ አርከበ ገና ብዙ የሚጠበቅበት ሰው ነው፤›› በማለት ያላቸውን ያደረባቸውን ቅሬታና ለእሳቸው ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል፡፡ ወደ እንግሊዝ አቅንተው የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሠርተው ሲመጡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ በመሆንና በሌሎችም ተቋማት ውስጥ በቦርድ ሰብሳቢነት ጥሩ ሥራ መሥራታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ዶ/ር አርከበ እንደ አገር ወዳድ ዜጋ በሠሩት ሥራ ተደስተናል፡፡ በሌሎቹም ላይ ይህ ተግባርዎት ይቀጥል እንላለን፡፡

(ታደሰ በርሔ፣ ከአዲስ አበባ)

******************

ስለአገሪቱ ለውጥ የሚሰብክ ተቋም ቀድሞ ራሱን ያርቅ

አንድ ለእናቱ የሆነው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አንዳንዴ ምን ዓይነት ሰዎች እንዲመሩት እንደሚሾሙበት ሳስብ ግራ ይገባኛል። ሌላ ሌላውን ትተን በቀላሉ ብሔራዊ ባንክ አካባቢ የሚገኘው የተቋሙ ሕንፃ ላይ ተሰቅሎ ያለውን ሰዓት ቆጣሪ ተመልክታችሁታል? እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የአገራችን የሰዓት አቆጣጠር ጠዋት አንድ ብሎ ጀምሮ ምሽት አሥራ ሁለት ብሎ እንደሚጠናቀቅ ነው።

ስለአገሪቷ ህዳሴ እሰብካለሁ የሚለው ኢቢሲ ምነው ሰዓቱን በአውሮፓውያን አቆጣጠር አደረገውሳ? በቀደም ጠዋት ሰዓት ለመመልከት ቀና ብል ከጠዋቱ ስምንት ሰዓት ይላል። ሁለት ሰዓት ለማለት መሆኑ ቢገባኝም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አገልጋይ ነኝ ከሚል ተቋም እንዲህ ዓይነት ግድፈት ተቀባይነት እንደሌለው አምናለሁ።

ተቋሙ ሥር ነቀል ለውጥ ማድረግ ካለበት ከዚህ ይጀምር።

 

(ሀብትሽ፣ ከአዲስ አበባ)

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...