Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትተቃውሞ የሚፈራ - ሞት የማይመዘግብ - ገዳይ የማይቀጣ ዴሞክራሲ?

ተቃውሞ የሚፈራ – ሞት የማይመዘግብ – ገዳይ የማይቀጣ ዴሞክራሲ?

ቀን:

በበሪሁን ተሻለ

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ በ2008 ዓ.ም. ሐምሌ መጨረሻ ሳምንት ላይ በሪፖርተር ጋዜጣ (ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ቁጥር 1696) በነገሩን አፍላና ትኩስ ስታትስቲክስ መሠረት፣ በሕግ ብቸኛው የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ድርጅት 80 ሚሊዮን ደንበና የሚሸከም ኔትወርክ አለው፡፡ በዚህ ማዕቀፍም ውስጥ ቴሌ 64 ሚሊዮን ሞባይሎችን ያለ ጭንቅና ጥብ ማስተናገድ እንደሚችል፣ እስካሁን 46.9 ሚሊዮን ሲም ካርዶች የገዙ ደንበኞች እንዳሉት፣ ከእነዚህ ውስጥ እስከ 35 ሚሊዮን የሚደርሱ ትጉና ንቁ ተጠቃሚዎች ያሉት መሆኑን ሰምተናል፡፡ ይህንን ያህል ሕዝብ እጅግ አነሰ ቢባል ደግሞ ከ20 ሚሊዮን የማያንስ ሰው ከቴሌኮም አገልግሎት ሰጪው የንግድ ማስታወቂያ በተጨማሪ፣ ‹‹የሕዝብ አገልግሎት ማስታወቂያ›› የተባለው የአጭር የጽሑፍ መልዕክት ወደደም ጠላም ይደርሰዋል፡፡

ሐምሌና ነሐሴ ወስጥ የሚገርም አጋጣሚ ድንገት አገጣጥሟቸው የኢትዮ ቴሌኮም ጥፋትም ክፋትም ሥልጣንም ባልሆነ ምክንያት (አቶ አንዱዓለም በሪፖርተር ቃለ መጠይቅ በኩል እንደነገሩን) የኢትዮጵያ የሴሉላር ሞባይል ኔትወርክ የሚሰጠው አገልግሎት መንገራገጭ በደረሰበት ወቅትና አካባቢ፣ የኢትዮጵያ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ሐምሌ 30 ቀን የሚጀምረውን ልደትን፣ ጋብቻንና ሞትን የማስመዝገብ ግዴታ ‹‹የሕዝብ አገልግሎት ማስታወቂያ ሆኖ›› በስልክ አገልግሎት ጭምር ተሠራጨ፡፡

ኢትዮጵያ ልደት፣ ሞትና ጋብቻ ይፋ ሆነው የሚታወቁበትንና የሚረጋገጡበትን ሥርዓት መዘርጋት የዘመናዊ ሥልጣኔና የጥሩ አስተዳደር ቁልፍ ነው ብላ የመሠረት ድንጋዩን የጣለችው ከመስከረም 1 ቀን 1953 ዓ.ም. ጀምሮ በፀናው የ1952 ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ የክብር መዝገብን ስትደነባ ነበር፡፡ ከ55 ዓመታት በላይና አሁንም ሥራ ላይ ያለው የፍትሐ ብሔር ሕግ ግን የክብር መዝገብ ሥርዓት የሚዘረጉትን የሕጉን ድንጋጌዎች በሥራ ላይ የሚውሉበት ቀን ተወስኖ በነጋሪት ጋዜጣ ታውጆ ካልወጣ በቀር በሥራ ላይ አይውልም፣ ተፈጻሚ አይሆንም ሲል ደነገገ፡፡ ከዚያ በኋላም እነዚህን ድንጋጌዎች አንቀሳቅሶ ተፈጻሚነታቸው ላይ ነፍስ የሚዘራ ሕግ ሳይወጣ የቤተሰብ ሕግ እስኪወጣ እስከ 1992 ዓ.ም. መጨረሻ፣ እንደገናም የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አዋጁ እስኪታወጅ እስከ 2004 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ በቀጠሮ ቆየን፡፡ እንደገናም በሌላ ማሻሻያ አዋጅ ቀጠሮው እስከ ሐምሌ 2008 ዓ.ም. ተራዘመ፡፡ በስንት መከራና በርካታ የ‹‹ፉርሽ ባትሉን›› ሕጎች በኋላ ልደት፣ ጋብቻንና ሞትን መመዝገብ ሥርዓት ሆኖ በኢትዮጵያ ተቋቋመ፡፡ በዚህም መሠረት ከሌሎች መካካል ልደትን፣ ጋብቻንና ሞትን ማስመዝገብ የዜጎችና አግባብ ያላቸው ሌሎች አካላት ግዴታ ሆነ፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም በኩል በሚደርሰን የኤስኤምኤስ መልዕክት ጭምር በግድ፣ ወደድንም ጠላንም፣ የሚደርሰን የፌዴራል ወሳኝ ኩነት የምዝገባ ኤጀንሲ የሕዝብ ማስታወቂያ የሚነግረንም ልደት፣ ጋብቻና ሞት የሚመዘገብ ኩነት መሆኑን፣ እነዚህን መመዝገብና ማስመዝገብ ግዴታ መሆኑን ነው፡፡ በዚህ መሠረት የሞት ምዝገባ የሟችን ማንነት በዝርዝር፣ የሞቱን ቀን ቦታና ምክንያት ጭምር ማካተት እንዳለበት ደንግጓል፡፡ ሞትን የማስመዝገብ ግዴታ ከሟች ጋር አብሮ ይኖር የነበረ ሰው፣ እሱ የሌለ እንደሆነ የሟች የሥጋ ወይም የጋብቻ ዘመዶች፣ እነዚህ ከሌሉ የቅርብ ጎረቤት ወይም ስለሟቹ መሞት የሚያውቅ ማንኛውም ሰው፣ ወዘተ. መሆኑን በሕግ ተወስኗል፡፡ ሕጉ ከዚህ በተጨማሪም በግዳጅ ላይ ስላለ የመከላከያ ሠራዊ አባል ሞት፣ በጋራ መኖሪያ ሥፍራ፣ በማረሚያ ቤት ወይም በጤና ተቋም የተከሰተ ሞት፣ በአደጋ ጊዜው ስለሞቱ ብዙ ሰዎችና ስለሟቹ የምዝገባ ቦታ በዝርዝር ይደነግጋል፡፡

ሕጉ እንደሚለው ተደራሽ፣ ሁሉን አቀፍና አስገዳጅ የሆነ የወሳኝ ኩነቶች የሞትም ጭምር የምዝገባ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ የሆነባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማቀድ ነው፡፡ በሕይወት የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብት ያለሕግና ያላግባብ እንዳይረገጥም ጭምር ነው፡፡

ሞትን የማስመዝገብ ግዴታ ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ መሆኑና ይህን ግዴታ አለመወጣት በዚህ ሒደት ውስጥ ሴራና ደባ መፈጸም በሕግ እንደሚያስጠይቅና እንደሚያስቀጣ ብሥራቱ በነጋሪት ብቻ ሳይሆን፣ 80 ሚሊዮን ደንበኞች በሚያስተናግደው በኢትዮ ቴሌኮም የሴሉላር ሞባይል ኔትወርክ ሥርዓት ውስጥ ጭምር በተነዛበት አገር ግን በርካታ ሞቶችን እንኳንስ ስም ቁጥር እንኳን የሚነፍጋቸው አሠራር ዓይተናል፡፡

በ2008 ዓ.ም. ከኅዳር ወር ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ተቃውሞዎች፣ ሐምሌ 2008 ዓ.ም. ውስጥ በጎንደር ከተማና በአካባቢው ላይ፣ ከዚያም በኋላም በበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ጭምር የታየው ተቃውሞ ሠልፍ ለስንት ሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት እንደሆነ መናገር ይፋዊ ወይም ኦፊሴል ኢትዮጵያ ውስጥ ዕርም ነው፡፡ ነውር ነው፡፡ ድብስብስ ያለ ነገር ነው፡፡ ተቃውሞው ከተነሳበት አወዛጋቢ ጉዳይ የበለጠ አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖ የተወሰደው ሌላው አወዛጋቢ ነገር፣ በፀጥታ አስከባሪዎች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ራሱ ሆኗል፡፡ የሚያወዛግበው ግን በቃሉ ትክክለኛ አግባብና ትርጉም እውነታም አጨቃቃቂ፣ አነታራኪ፣ አነጋጋሪና አንዳችም ነገር ስላለበት አይደለም፡፡ እከሌ የሚባል ሰው ስለመፈጠሩ፣ ስለመወለዱ አለዚያም በተቃውሞው ሠልፍ ውስጥ ስለመገኘቱ፣ በጥይት ስለመመታቱ፣ ከዚያም ስለመሞቱ፣ የሞተውም በተተኮሰበት ጥይት ምክንያት ወይም በእሱ ጠንቅ ስለመሆኑ የሚያከራክር ነገር ቢኖር በዚህ ዙሪያ የተነሳ እሰጥ አገባ ቢኖር አወዛጋቢ ይባላል፡፡

እንዲህ ያለ ጭብጥና ክርክር ግን ቀድሞ ነገር ወግ አይደለም፡፡ በዚያ መንገድና መስመር የሚያስኬድ ወግም ከነጭራሹ የለም፡፡ ከሕይወትና ከአካል ደኅንነትና ከነፃነት መብት አንፃር ይህን ያህል ሰው ሞተብኝ፣ በዚህን ያህል ሰው ላይ የአካል  ጉዳት ደረሰ፣ ይህን ያህል ሰው ደግሞ ተጎዳ ማለት ቀድሞ ነገር ‹‹ሪፖርት›› የሚያደርጉትና የሚጠየቁበት ጉዳይ መሆኑ ቀርቷል፡፡ ከቀርቷል ይልቅ ምን ጊዜም ያልነበረ እንዳመቸ የሚነሳ፣ የሚጣልና የሚጠራ ‹‹ቁጥር›› ሆኗል፡፡

ከዚህም የተነሳ እንኳንስ የሌላው ተቃራኒ፣ ተከራካሪ ወይም ባላንጣ ወገን ‹‹ጥሪ›› (ቁጥር) የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሚዲያ የሚያነሱትና የሚሰጡት ቁጥር ከመንግሥት ቁጥር ወይም እምነት ጋር በጭራሽ አይገናኝም፡፡ መንግሥት ቁጥር አይወድም፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ጥይት የቆጠሩባቸውን ሰዎች መቁጠር አይፈልግም፡፡ እንዲህ ዓይነት ‹‹ኃጢያት መቁጠር›› ማለትም መያያዝ፣ መጠያየቅ ሲመጣ፣ አንድ ሰው ራሱ ብዙ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ቁጥሩ አይደለም ማለት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ሳይጠየቁ መቅረትን መመረቂያ ዘዴ ሆኗል፡፡

ለተቃውሞ መነሻ የሆነውን ዋነኛ ብሶት፣ ቅሬታና ፖለቲካዊ ጥያቄ እንዲድበሰበስ የሚያደርገው እኛንም ወደዚያ እንድንገባ የከለከለንና የምንነጋገርበት ጉዳይ፣ ማለትም የተቃውሞ መብት የዛሬን አያድርገውና እንዲህ እንደ ዛሬው ሳይሆን ከሐምሌ 15 ቀን 1983 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው የሽግግሩ ወቅት ቻርተር የመጀመርያው መብትና ነፃነት ሆኖ የተነደገገ መብት ነበር፡፡ ቻርተሩ በመጀመርያ ክፍሉ በመጀመርያው አንቀጹ በ‹‹የዴሞክራሲ መብቶች›› ሥር መብቶቹን ሲደረድር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 10 ቀን 1948 ዓ.ም. የፀደቀውንና የታወጀውን ቁጥር 217 A(III) ውሳኔ መሠረት በማድረግ የግለሰብ ሰብዓዊ መብቶች ያላንዳች ገደብ ሙሉ በሙሉ ተከብረዋል፡፡ በተለይም እያንዳንዱ ግለሰብ፣

ሀ) የእምነት ሐሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ በሰላም የመሰብሰብና የመቃወም ነፃነት አለው፣

ለ) የሌሎችን ሕጋዊ መብቶች እስካልተጋፋ ድረስ በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላንዳች ገደብ የመሳተፍና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የማደራጀት መብት አለው በማለት ‹‹ሀ›› ብሎ ይጀምራል፡፡

የሽግግር መንግሥቱን ቻርተር የቀደመውም ሆነ እሱን የተከተለው ተቃውሞን የማስተናገድና አገሪቱ የምትገነባው ሥርዓት ፍጥርጥር አካል የማድረግ ጉዳይ፣ እንኳንስ ትምህርቱና ይዘቱ ማስመሰሉም እንኳን አልቻልህ አለን፡፡ ኢሕአዴግ ከተቃውሞ አያያዝ ጋር መፈታተን የጀመረው ዴሞክራሲያዊ ትግሉን በወሳኝ መክረር ጊዜ ላይ የማርገብና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ዝንባሌዎችን የማጋሸብ ጥፋቱ እየደጋገመው ሲመጣ ነው፡፡ በተለይ ወደ መጨረሻው አካባቢ ወደ መሀል አገር ባካሄዳቸው ወታደራዊ ግስጋሴዎች ሒደት ውስጥ የሐሜትና የተቃውሞ ፍትጊያዎች የታየባቸው ነበሩ፡፡ ችግሩ ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ አዘዞና ጎንደር ሲገቡ የተቀበሉትና ያወገዙት ሠልፎች ከርቀትም በአዲስ አበባ፣ በጅማ፣ በሐሮማያና በናዝሬት የኮሌጆችና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ያለሙት ቅዋሜ መፈተኛውና ያስመዘገበውን ውጤት ያሳዩ ነበሩ፡፡

ኢሕአዴግ ደንገጥ ብሎ ገመናውን ከማየት ይልቅ የደርግ ኢሠፓ ርዝራዦች፣ ሴተኛ አዳሪ፣ ቦዘኔና ሕፃናት አሠልፈው ‹‹ከመንግሥቱ ጋር ወደፊት! ኢሠፓ ይለምልም! ወያኔ ሌባ! ወንበዴ፣ ወዘተ.›› የሚል መፈክር ማሰማታቸውን ምራቅ በመትፋት፣ ድንጋይ በመወርወርና ንብረት በማጥፋት መተናኮላቸውን እየገለጸ፣ የዚህን ሁሉ መፈጸምና የተዋጊዎቹን ቻይነት ለድርጅቱ ዴሞክራሲያዊነትና በደርግ ጊዜ ታይቶ የማይታወቅ ዴሞክራሲያዊ መብት ለመታየቱ ማረጋገጫ አድርጎ ይተረጉም ነበር፡፡ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የታየውን የተማሪዎች ተቃውሞ፣ በኢሠፓ ካድሬዎች የተከናወነ የጥቂቶች ሥራ አድርጎ እያቃለለ ራሱን በራሱ አታለለ፡፡

ተቃዋሚዎቹ ሁሉ የፈለጋቸውን ያህል ፀረ ዴሞክራሲ ቢሆኑ በፀረ ዴሞክራሲ ዝንባሌዎች የተልኮሰኮሱ ቢሆንም፣ ለኢትዮጵያ ገዥነት ለመታመን ባልቻለው የወያኔ/ኢሕአዴግ ጥበትና መልቲነት ላይ ያነጣጠሩ ነበር፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ወደ ‹‹እንዝመት›› ጠምዝዞት የነበረውም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞም ቢሆን ዋነኛ የውስጥ ትርታው ኢሕአዴግን ያላመነ፣ ወታደራዊ አምባገነንትን የጠላ፣ የአገር ወዳዶች ጭንቀት ነበረ፡፡

ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ሲገባም የተቃውሞ ሠልፉ አልቀረለትም፡፡ እሱም አልማረም ገደለ፡፡ በዚያው በሽግግሩ ወቅት ኢሕአዴግ ሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት የሚደነግግ አዋጅ ቢያወጣም፣ በፖለቲካው በኩል ኢሕአዴግ ራሱ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት መለወጥ አልቻለም፡፡ ይህ የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር መያዝ በጭራሽ አልታየውም፡፡ ከለመደው የጦርነት ሥልት መውጣት ባለመቻሉ በተማረው ኃይልና በሌሎች አስተሳሰቦች ላይ ንቃትና ጥላቻ ተጠመደ፡፡ እኔ ብቻ ልክ ዳፍንት ውስጥ ገባ፡፡ በሐሳብ መለየትን ሞት አደረገ፡፡

እዲያም ሆኖ ግን ገና የፕሬስ ሕጉ ሳይወጣ ጀምሮ መጽሔቶችና ጋዜጦች በአንፃራዊነት እንደ አሸን ፈሉ፡፡ ከአብዮት/መስቀል አደባባይ ተነስቶ አራት ኪሎ ድረስ በሠልፍ ሄዶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተወካይ አቤቱታን/ጥያቄን ማቅረብ ፋሽን ሆነ፡፡

ከ1997 ዓ.ም. በኋላ ግን የሐሳብ ነፃነት ማስመሰያ የነበረው የግል ጋዜጦች ጫጫታና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ጩኸት ፀጥ እረጭ አለ፡፡ የሠልፉና የአደባባይ ስብሰባ ግርግር የሌለበት አጠቃላይ ርጭት እንደገና ተመልሶ ተደፋ፡፡ ተናግቶ የነበረው አንገት መድፋት መልሶ በሕዝብ ላይ ወደቀ፡፡ ከእንግዲህ የሐሳብ ነፃነት ያለ አስመስላለሁ በማለት በተቃውሞ ትችት መለብለብ መታገስ ዕርም ሆነ፡፡ መሣሪያ ያልያዘን ተቃውሞ በጥይት እየቀነደቡት ሳይጠየቁ መቅረት፣ የፀጥታ አስከባሪዎች የገደሉበትን ሰላማዊ ሠልፍ ቁጥር ሳይቀር ማጣጣልና መካድ ባህል ሆኖ የቆየበት እስከ 1967 ዓ.ም. የነበረው ሁኔታ ደግሞ ላይመለስ ከስምንት ዓመት በላይ ሞት አካል እንቅልፍ ወስዶት ያን ያህል ዘመን ባጀ፡፡ ከረመ፡፡

ሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ለማድረግ ‹‹የማሳወቅ ግዴታ››ን የመወጣት (በተግባር ግን ፈቃድ የመጠየቅ) ማመልከቻ የማስገባት ወሬ ራሱ አደባባይ ማየት የጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በሰላማዊና በተቃውሞ ሠልፍ የመገልገል የማንኛውም ሰው መብት ዛሬም የብጥብጥና የአመፅ ድርጊት እንዳይባል ፈርቶ፣ ሕገ መንግሥቱን የጣሰና የፌዴራል ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ የተደረገ ሙከራ ተብሎ እንዳይከሰስ ሰግቶ ጭራሽ እንዳይላወስ ሆኖ ተመትቷል፡፡

ሰላማዊ ሠልፍ ፍላጎትን፣ ብሶትን እንዲሁም ተቃውሞን መግለጫና ተፅዕኖ ማሳያ መንገድ ነው፡፡ በተቋማዊ መንገዶች አቤቱታን ከማቅረብ ባሻገር በሠልፍና በተቃውሞ ጥያቄን ማሰማት የትም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ያለ መብት ነው፡፡ ሠልፍ የማድረግና የመቃወም መብት፣ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ተቃዋሚ አደባባይ ወጥቶ ዝናዬን ይቀንሰዋል፣ ግዙፍ ሠልፍ ሊመጣ ነው ብሎ በፈራ ቁጥር የሚከለክልና የሚታገድ አይደለም፡፡ የገዥው ቡድን መራመድና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በኃይል የመለወጥ አደጋ በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡

አገራችን ውስጥ በተለይም እንደ ግንቦት 1997 እና በ2008 ዓ.ም. ደግሞ በጎንደርና በባህር ዳር እንዲሁም በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረው ዓይነት ተቃውሞ በመጣ ቁጥር ለአመፅና ለሁከት የሚሰጠው ትርጉም የማንኛውም ሰው በተለይም የዜጎችን የሠልፍና የስብሰባ እንዲሁም የተቃውሞ መብት የሚደፍቅ ነው፡፡

ከአሥር ዓመት በላይ የሆነውን፣ ተብሎ ተብሎ ያለቀለትን መርማሪ ኮሚሽን ያጣራውን ታሪክም መዝግቦ የለየለትን የ1997 ዓ.ም. እና ተከታይ ወራት ተቃውሞ ለምሳሌ እንውሰድ፡፡ ተቃውሞው ጎማ ከማቃጠልና ድንጋይ ከመወርወር ያላለፈና በመሠረቱ ሰላማዊነቱን ያለቀቀ ቅዋሜ ነበር፡፡ ብጥብጥና አመፅ አልነበረም፡፡ ብጥብጥ ከቁጥጥር የወጣ ድብልቅልቅ ሁከት ነው፡፡ የአመፅም ትርጉም መሣሪያ ላንሳ እምቢታ ያደላ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ፕሮፓጋንዳ በሚዲያው በ‹‹ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሕዝብ አስተያየት›› በተቀጥላ ምሁራን ስብከትና ትንተና እነዚህን የብጥብጥና የአመፅ ቃላት ያጠበቀው ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ መሆን፣ ቅሬታን አስመልክቶ ውሳኔ መጠበቅና የተሰጠን ውሳኔ በፀጋ መቀበል ነው፡፡ ከዚህ አልፎ ተቃውሞን በዴሞክራሲያዊ መብቶች ማለትም በስብሰባ፣ በሠልፍና በሥራ ማቆም መግለጽ አመፅ ነው፡፡ ሰላምን ማናጋትና ሁካት መፍጠር ነው የሚል ‹‹እምነት›› በኅብረተሰቡ አዕምሮ ላይ መጋገር ስለፈለገ ነው፡፡ የተሳካለትም ይመስላል፡፡

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ለመሆኑ ደመነውጠኛ ማነው? የቅዳሜውን የአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የቢቢሲና የአልጄዚራ ‹ፉቴጅ› ያየ ሰው የፖሊስ ዱላና የፖሊስ ጫማ አጠቃቀም ሕግ የለውም እንዴ አይልም? ፖሊሶቻችን የተማሩበትና የሠለጠኑበት ሥነ ምግባርና ዕውቀት ይህን የሚመርቅ ነው ወይ? በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከኢትዮጵያ የሚሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል ማስተዋወቂያስ እንዲህ ያለ በተጠቀሰው ዜና ያየነው ዓይነት ምግባር ነው ወይ?

ባልታጠቀ ሰላማዊ ተቃውሞ ላይ ጥይት እንዲተኮስ አዛዥና አስገዳይ ሆኖ ወይም ይህን ያደረገውን ከለላ ሰጥቶ ለግድያው ተጠያቂዎች ሠልፉን ያናሳሱት ናቸው ማለትስ በዚህ ሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የሚኮሩበት ማብራሪያ ነው ወይ? ሌላ ሁከት ከእንግዲህ ቢሞከር እሳት አቀጣጣዩን የሚያቃጥል ስለመሆኑ እንዲህ ያለ ጉዳይ ባጋጠመ ቁጥር ማስጠንቀቅም በግድያው ከተላለፈው መልዕክት የተለየ አይደለም፡፡ ሠልፍ የተደረገው እንደ 1997 ዓ.ም. ሠልፍ በታገደበት ጊዜ ወይም እንደ 2008 ዓ.ም. እና የአሜሪካ ኤምባሲ ያለብልኃት ብቻ ሳይሆን በድንቁርና እንዳለው ‹‹ባልተፈቀደ›› ሠልፍ መሆኑም የግድያ ድርጊቱን ተገቢ አያደርገውም፡፡

በመጨረሻም ከሁሉም በላይ ዋነኛውን ጉዳይ በአጭሩ ሳላነሳ ማለፍ አልፈልግም፡፡ መንግሥት ለሰላማዊ ተቃውሞ የሰጠው ምላሽ አለ፡፡ ከእሱ በፊት ተቃውሞ አለ፡፡ ከዚያ በፊት ለተቃውሞው መነሻ የሆነው ጉዳይ ነው፡፡

ስለሕዝቦች ሉዓላዊነት/ልዕልናና ስለዴሞክራሲ ድል መምታት 25 ዓመታት አውርተናል፡፡ አሁንም የፀረ ዴሞክራሲ አፈና ዘይቤዎች እንደ ደላቸው፣ እንደተንቀባረሩ ናቸው፡፡ አሁንም የሕዝብ ቅሬታዎች መጠራቀማቸውና አጋጣሚ እየጠበቁ መፈንዳታቸው አልተቋረጠም፡፡ ስለጠባብነት፣ ስለትምክህት አደገኛነት ለዓመታት ስናወራ ኖረናል፡፡ አሁንም ግን መስፋፋተቸውን ማዳከምና አደጋቸውን ማምከን አልተሳካልንም፡፡

ጠባብና አጫጭር ጥቅሞች ሕዝቦችን ጭምር የከፋፈሉበት፣ የጥላቻ ንፋስም ሕዝብ ውስጥ ገብቶ ዕይታን ያሳሳተበት ሁኔታ ሳይታከም ባለበት የሚፈነዳ ቁጣ ሥጋት የሚሆነው ለአገዛዙ ብቻ ሳይሆን፣ ለራሱ ለሕዝቡም ሰላምና ደኅንነት ጭምር ነው፡፡

በዚህ ዓመት በኦሮሚያና በጎንደር በተደጋጋሚ በተከሰቱ የብሶት ቁጣዎች ውስጥ ብልጭ ያሉት ጥያቄዎች የእርስ በርስ ፍጅት አገሩ ሩቅ እንዳልሆነ የጠቆሙ ማስጠንቀቂያዎች ናቸው፡፡ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መስተናገጃ መድረክ እስከቸገራቸው ወይም እስከተነፈጉ ድረስ አዘንግተው ወደ ቁጣዎች መቀየራቸውና ጥፋት ማድረሳቸው አይቀርም፡፡ በቅሬታዎች ውስጥ የሕዝቦችን ግንኙነት ያቆሳሰለ ነገር ካለ ደግሞ መንገድ ስቶ ሊደርስ የሚችለው ጥፋት ‹‹ያውጣን›› የሚያሰኝ ነው፡፡ እንዲያ ያሰኝ እንጂ ‹‹ያውጣን!›› ማለትም፣ ደግ ስብከትም ከአደጋ አያድንም፡፡ መፍትሔው ጠንቆችን ከነመርዛቸው መንቀል ነው፡፡ ዴሞክራሲን ማስፋት ነው፡፡ ተቃውሞን በዴሞክራሲያዊ ልቦናና ማዕቀፍ ውስጥ ማስተናገድ ነው፡፡ ከቡድን ቁጥጥር የተላቀቁ ተቋማትን ማልማት አለብን፡፡

ዴሞክራሲ የህልውና ጥያቄ ነው ካልን ውለን አድረናል፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓተ መንግሥት የራሱ ህልውና ደግሞ የየትኛውም ፓርቲ ይዞታ ያልሆነ አምደ መንግሥት (State) ማደራጀት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ አድሮ ጥጃ ያደረገው የዚህ ዕጦትና ችግር ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...