Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ከሳምንት ወዲህ ያለም ዓይንና ጆሮ ወደ ላቲን አሜሪካዋ ብራዚል መዲና አድርጓል፡፡ ጉዳዩ በየአራት ዓመቱ የሚመጣው ኦሊምፒክን ያመት ተራው ሪዮ ላይ አድርሶታል፡፡ ከእንቅልፋችን ጋር እየተናነቅን እየተከታተልነው ነው፡፡ እኔና ኦሊምፒክ ከተዋወቅንና ነፍስ ማወቅ ከጀመርኩ 44 ዓመት ደፍኜያለሁ፡፡ የማሞ ወልዴና የምሩፅ ይፍጠር በማራቶንና በ10,000 ሜትር ያስመዘገቡት የነሐስ ሜዳሊያ ድል ትውስ ይለኛል፡፡ ከሠፈር ባልንጀሮቼ ጋር እየተጫወትኩ ‹‹ቆዩ የማራቶንን ውጤት ሰምቼ ልንገራችሁ›› ብዬ የብስራት ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ የማሞን ሦስተኛነት ሲነግረን እየሮጥሁ መናገሬ ይታወሰኛል፡፡

ዘንድሮ ቴክኖሎጂው ዘምኖ መረጃ መጠየቂያም በያይነቱ በሞላበት የአሁኑ ሪዮ ኦሊምፒክ የመጀመሪያው ሰሞን የብዙዎችን ቀልብ የሳበው፣ የሚዲያዎችን ትኩረት የገዛው በዓለም ከገነኑት አትሌቶች መካከል የሆነ አይደለም፡፡ ዓለሙን በሳቅ ጎርፍ የወሰደው ለታዳጊ አገሮች በተሰጠው ኮታ የዋና ውድድር ተሳታፊ የሆነው የኢትዮጵያ ‹‹ተወካይ›› ሮቤል ኪሮስ እንጂ፡፡

 በሞንትሪያልና በሞስኮ ኦሊምፒኮች መካከል በነበሩት አራት ዓመታት በዓለም አትሌቲክስ ዋንጫና በአህጉራዊ በ10,000 እና በ5,000 ሜትር ውድድሮች ድርብ ድል በተደጋጋሚ የተቀዳጀውና በአሯሯጥ ስልቱ ‹‹ማርሽ ለዋጩ›› የተባለው ምሩፅ ይፍጠር ዓለም የተቀባበለው ‹‹ይፍጠር ዘ ሺፍተር›› (Yifter the Shifter) በማለት ነበር፡፡ ይኸው ስሙ እስካሁን እንዳስከበረው አለ፡፡ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ከለንደን በኋላ ዋናተኞች የላከችው ኢትዮጵያችን ስሟ እንደምሩፅ ሳይሆን በአሉታ መልኩ ያስጠራት ዋናተኛ ተክለ ሰውነቱና ዝግጁነቱ በአገሪቱ ዋናተኞች የለም ወይ አሰኝቷል፡፡ እንዴት ተመረጠ? ሚኒማውንስ እንዴት አሟላ? በማለት ብዙዎች ተቀባብለውታል፡፡ ሮቤል ኪሮስን “Robel the whale” ሮቤል አሳነባሪው ብለውታል፡፡ ‹‹ወደላ እና ቀርፋፋ›› ሲሉም ተሳልቀውበታል፡፡

እንደኔ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውና ብሔራዊ ዋና ፌዴሬሽን ግብረ አበርና ስም አበር (በኦሊምፒክ) ሆነው አዋርደውናል፡፡ እንደሰማሁትና መረጃዎችን በቅርበት እንደተከታተልሁት፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አባቱ በመሆናቸው ተጠቃሚ የሆነበትም አድልዎ መፈጸሙ እየተወሳ ነው፡፡ በኮምቦልቻና በድሬዳዋ በተደረጉት ውድድሮች ውጤት የነበራቸውን አትሌቶች ትቶ አምና በሩሲያ ባገኘው ውጤት መለኪያነት እንዲገባ ያደረጉት የፌዴሬሽኑም ሆነ የኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች መጠየቅ አለባቸው፡፡ የዋና ቡድኑ ያለአሠልጣኝ እንዲሄድ መደረጉስ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ለምን ብሎ አልጠየቀም፡፡ ነው ወይስ የቡድን መሪውና የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት የተወዳዳሪው አባት ‹‹ለአንድ ደቂቃ ውድድር አሠልጣኝ ምን ያደርጋል›› ያሉትን ተቀብለውታል ማለት ነው፡፡ ለዘጠኝ ሰከንድ ሩጫ የ100 ሜትር ሯጮች እኮ አሠልጣኝ አላቸው፡፡ የሮቤል ገመና የአገራችንን የስፖርትና የኦሊምፒክ አመራሮች ጉድን የሚያሳየን ነው፡፡ በ‹‹ጅረት›› ተጠራርተው የተቀመጡ ከሚመሩት ስፖርት ጋር እንደማይተዋወቁ ያሳየን አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ሁሌ በአመራሮቻችን እንደተሳቀቅን እንደሳቅን ነው፡፡ የሮቤልን ጉድ በየፌስቡኩ፣ በየሚዲያው የተከታተለው አንድ ወዳጄ ሳቁን መቆጣጠር አልቻለም፡፡ ውሎውን ሁሉ ሳቁ የንዴት፣ የቁጭት እንደሆነበት የነገረኝ የገሞራውን ቅኔ በማንበብ ነበር፡፡ ‹‹ከጥንት ጀምሮ ስናይ እንደኖርነው

ሲነድ ሲቃጠል የሚስቅ እሳት ነው፡፡››

አዎ እየነደድን እንስቃለን፡፡ ፈውስ ግን እንፈልጋለን፡፡ የኢትዮጵያ ዋና ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን ከይቅርታ ጋር መግለጽ አለባቸው፡፡

(ኃይለሚካኤል አድማሱ፣ ከመናገሻ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...