በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሥር በሚገኙ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤቶች በኃላፊነት ይሠሩ የነበሩትን ጨምሮ 63 ሠራተኞች በሕግ ሊጠየቁ መሆኑ ታወቀ፡፡
ትራንስፖርት ቢሮው ኃላፊዎቹን ጨምሮ እስከ ታች ሠራተኞች ድረስ ባደረገው የ2008 በጀት ዓመት ግምገማና የማጣራት ሥራ ከፍተኛ ጥፋት መፈጸማቸው በማስረጃ የተረጋገጠባቸውን 63 ሠራተኞች፣ ሕግ ፊት አቁሞ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ አስፈላጊ ማጣራቶችን አድርጐ ለሚመለከተው አካል ማስተላለፉን፣ የቢሮው ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ቀደም ባለው አደረጃጀት ቢሮው በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች አንድ አንድ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እንደነበሩ የጠቆሙት የቢሮ ኃላፊው፣ አብዛኛዎቹ የተሽከርካሪ አሽከርካሪ አገልግሎቶች የሚሰጡባቸው ከመሆናቸው አንፃር፣ ከፍተኛ የሚባሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንደነበሩ በተደረገው ማጣራት ማረጋገጥ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ አገልግሎት ለመስጠት መሟላት የሚገባቸው መሥፈርቶች በቢሮ ደረጃ የተቀመጡ ቢሆንም፣ ኃላፊዎቹና ሠራተኞቹ ግን አሠራሩን በመጣስ ሕገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ እንደነበር በማስረጃ ሊረጋገጥ መቻሉን አቶ ያብባል ተናግረዋል፡፡ አሠራሩን በመጣስ የተቀመጡ መሥፈርቶች ሳይሟሉ ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ፣ የተለያዩ በትራንስፖርት ሴክተሩ ሊከበሩና ሊተገበሩ የሚገባቸውን አሠራሮች በመጣስ፣ በመንግሥት ገቢም ላይ ይሁን በተገልጋዩ ኅብረተሰብ ላይ ጥፋት ሲፈጽሙ እንደነበር በመረጋገጡ እንዲጠየቁ ድምዳሜ ላይ መደረሱን አክለዋል፡፡
ኃላፊዎቹና ሠራተኞቹ የተሰማሩበትን ኃላፊነት ወደ ጐን በመተውና ሕገወጥ አሠራርን በመከተል ኪራይ ሰብሳቢነት ውስጥ ገብተው መገኘታቸው፣ ከሙሉ ማስረጃ ጋር የቀረበለት የሚመለከተው አካል ሕግ ፊት ያቆማቸዋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
በትራንስፖርት ጽሕፈት ቤቶቹ ለሚመጡ አገልግሎት ፈላጊዎች ሕጉንና መመርያውን ተከትለው ማስተናገድ ሲገባቸው፣ ያልሆነ ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩት እጅግ ብዙ ሠራተኞች እንደነበሩ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ሁሉንም በማሰርና በማስቀጣት ብቻ ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት ስለሌለው፣ በማስተማርና በመምከር እንዲስተካከሉ ያደረጋቸውም እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡ ጥፋት የፈጸመ ሁሉ በሕግ ይጠየቅ ቢባል ሁሉም ሠራተኛ ከተጠያቂነት ሊያመልጥ እንደማይችል የጠቆሙት ኃላፊው፣ በሴክተሩ ያለው ችግር ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል፡፡