Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ600 በላይ የሚሆኑ የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሠራተኞች ያለምንም ማስጠንቀቂያ ተባረርን አሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹አደረጃጀትን ከመቀየር በስተቀር አንድም የተባረረ ሠራተኛ የለም›› የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተመድበው ይሠሩ ከነበሩት ከ900 በላይ ሠራተኞች፣ ከ600 በላይ የሚሆኑት ያለምንም ማስጠንቀቂያ ከሥራ መባረራቸውን ገለጹ፡፡ አደረጃጀቱን ከመቀየር በስተቀር አንድም ሠራተኛ እንዳላባረረ ቢሮው እየገለጸ ነው፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሠራተኞች እንደገለጹት እየተሠራ የነበረው አደረጃጀት ለሠራተኛው ጥቅም የሚያስገኝ፣ ደመወዛቸውን የሚያሳድግ አሠራርን ቀልጣፋና ፈጣን የሚያደርግ ይሆናል ብለው ጠብቀው ነበር፡፡ የሠራተኛ ቅነሳ፣ ምደባና መባረር ግን ምንም የተባለ ነገር እንዳልነበር አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን በሐምሌ ወር ማጠናቀቂያ ላይ በመሥሪያ ቤቱ ከሚገኙት ከ900 በላይ ሠራተኞች፣ የተወሰኑት ብቻ መመደባቸውን በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ማየታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ሠራተኞቹ ከሚሉት በተቃራኒ ምላሽ የሰጡት የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ፣ ‹‹ቀድሞ የነበረንን አሠራር በመሰረዝ በአዲስ አደረጃጀት ከመተካት በስተቀር አንድም ሠራተኛ አላባረርንም፤›› ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት ሴክተሩንና አገልግሎቱን ለማሻሻል አደረጃጀቱ መቀየሩን የገለጹት ኃላፊው፣ ቀደም ብሎ በቢሮው ሥር ሆነው በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች የነበሩ የትራንስፖርት ጽሕፈት ቤቶች በትራፊክ ኤጀንሲ፣ በትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ በአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ቁጥጥር ባለሥልጣን መተካታቸውን አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም በአሮጌው አደረጃጀት ውስጥ የነበሩ ሠራተኞች ወደ አዲሱ አደረጃጀት ሲቀየሩ፣ ሠራተኞች በሁለት መንገድ ሊመደቡ መቻላቸውን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ቀደም ብሎ በነበረው አደረጃጀት የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ሳይኖራቸው የተመደቡና ከሠርተፊኬት እስከ ዲግሪ ድረስ የተማሩ የነበሩበት እንደነበር ያስረዱት ኃላፊው፣ በአዲሱ አደረጃጀት አገልግሎቱን በብቃት ለመወጣትና የተቀላጠፈ አሠራር ከመዘርጋት አንፃር፣ ሁሉንም በትምህርት ዝግጅታቸውና ልምዳቸው መመደባቸውን ተናግረዋል፡፡ አዲሱ አደረጃጀት መደቡ ከፍ ያለ ከመሆኑ አንፃር፣ በመጀመሪያው ዙር ከሠርተፊኬት በላይ ያላቸው ሠራተኞች ተመድበው ከዚያ በታች የሆኑት ሳይመደቡ የቀሩ ቢሆንም፣ በሁለተኛው ዙር ግን ሁሉንም እንደየችሎታው መመደቡን አክለዋል፡፡

መንግሥት አንድም ሠራተኛ መፈናቀል እንደሌለበት በሰጠው አቅጣጫ መሠረት፣ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ተጠሪ በሆኑ ሴክተሮችና በከተማ አስተዳደሩ ሥር ባሉ የሥራ ዘርፎች እንደየትምህርት ችሎታቸውና የሥራ ልምዳቸው፣ ሁሉም ሠራተኞች እንዲመደቡ መደረጉን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ በመጀመሪያው ዙር 330 እና በሁለተኛው ዙር 270 ሠራተኞች መመደባቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፣ ሌሎቹ የከተማ አስተዳደሩ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ከየቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቹ ጋር በመነጋገር እንደሚመድባቸው አስታውቀዋል፡፡   

እንዳልተመደቡ የሚናገሩትና ‹‹ተባረናል›› የሚሉት ሠራተኞች እንደሚናገሩት፣ ቢሮው ምደባ ያደረገው በትምህርት ዝግጅት ሳይሆን የፖለቲካ አመለካከትን በመመዘን መሆኑንና በዝምድና ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ነው፡፡ አቶ ያብባል ግን አባባሉን አልተቀበሉትም፡፡ ሠራተኞቹ በፈለጉበትና በለመዱበት ቦታ ላይ ባለመመደባቸው የሚናገሩት እንጂ፣ እነሱ እንደሚሉት የተመደበ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች