Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከቡና ኤክስፖርት 750 ሚሊዮን ዶላር ቢገኝም በገቢና በመጠን ቅናሽ አሳይቷል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተጠናቀቀው የ2008 በጀት ዓመት ከቡና የወጪ ንግድ 750 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ፡፡ ከሚጠበቀው ገቢና ይላካል ከተባለው መጠን ያነሰ ሆኗል፡፡ 

በዚህ ዓመት ከቡና የወጪ ንግድ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ገቢ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት አንድ ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ባስቀመጠው የተከለሰ ዕቅድም ይገኛል ተብሎ የነበረው ገቢ 879 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ይታወቃል፡፡

ወደ ውጭ የተላከው የቡና መጠን 180 ሺሕ ቶን ሲሆን ይላካል የተባለው ግን 206 ሺሕ ቶን ቡና እንደነበር፣ ከቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ባለፈው ዓመት 190 ሺሕ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ ቀርቦ እንደነበር መረጃዎች ቢጠቁሙም፣ አቶ ሳኒ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ ግን ዘንድሮ ከዓምናው ይልቅ የ20 በመቶ የመጠን ጭማሪ ቢታይም በዓለም ገበያ ከግማሽ ዓመት ጀምሮ እስካለፈው ግንቦር ወር እየቀነሰ የመጣው የቡና የዓለም ዋጋ የታሰበውን ገቢ ለማስገኘት አላስቻለም፡፡

ሆኖም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሠረት 780 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የነበረው ዓምና ነበር፡፡ የዘንድሮ ዕቅድ አንድ ቢሊዮን ዶላር የማግኘት ሲሆን፣ በ2009 በጀት ዓመት 1.33 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2010 ዓ.ም. 1.62 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2011 ዓ.ም. 1.87 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ ደግሞ 2.17 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከቡና እንደሚጠበቅ ዕቅዱ አስፍሯል፡፡ በመጨረሻው ዓመት ለውጭ የሚቀርበው የቡና መጠንም ከአንድ ሚሊዮን ቶን በላይ እንደሚሆን ዕቅዱ ይጠቁማል፡፡ ይሁንና አቶ ሳኒ በገለጹት መሠረት የቡና ኤክፖርት ሻይና ቅመማ ቅመምን ጨምሮ 240 ሺሕ ቶን ገደማ እንደሚሆን የሚጠቁም ነው፡፡

ምንም እንኳ ከቡና ዘርፍ የታቀደውን ገቢ ማግኘት ባይቻልም በቡና ምርት፣ በኤክስፖርት መጠንና በውጭ ምንዛሪ ገቢ ረገድ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ብራዚልን በመከተል በዓለም ሁለተኛ ትልቅ የቡና አምራች አገር እንደምትሆን አቶ ሳኒ ገልጸዋል፡፡ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮም፣ ‹‹አሁን ካለው ነባራዊ እውነታ በመነሳት አገሪቱ ከዓለም ሁለተኛ ቡና አምራችና ላኪ አገር ትሆናለች፤›› በማለት ሐሳቡን አጠናክረዋል፡፡

በሌላ በኩል ለ15ኛ ጊዜ የሚካሄደው የአፍሪካ ምርጥ ቡናዎች ኮንፈረንስና ዓውደ ርዕይ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ይፋ ተደርጓል፡፡ ሐሙስ ነሐሴ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ይፋ እንደተደረገው ከየካቲት 8 እስከ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ፣ አዘጋጁ የአፍሪካ ምርጥ ቡናዎች ማኅበር አስታውቋል፡፡

የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ አብደላ ባገርሽ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በጉባዔው 2,000 ያህል ተሳታፊዎች ሲጠበቁ ትልልቅ ቡና ገዥዎችም ይታደማሉ፡፡ የዓለም ዋና ዋና ቡና ገዥዎች ከሆኑት መካከል ቦል ኮፊ፣ ኢኮም ትሬዲንግ፣ ኑማን ግሩፕ፣ ዶልቼ ካፌ እንደሚመጡ ከሚጠበቁት ትልልቅ ቡና ገዥዎች መካከል መሆናቸውን አቶ አብደላ ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ ገዥዎችም ትልልቅ ቡና ቆይ ለሆኑት እንደ ስታርባክስና ኔስሌ ላሉት የሚያቀርቡ ናቸው፡፡   

በጉባዔው ከሚጠበቁት 2,000 ተሳታፊዎች በተጨማሪ 100 ያህል የዓውደ ርዕይ ተሳታፊዎች እንደሚታደሙ ሲታወቅ፣ ከጉባዔው ጎን ለጎንም የአፍሪካ ባሬስታዎች ሻምፒዮና፣ የቡናና የሌሎች ምርቶች ቅምሻ የመሳሰሉት ፕሮግራሞች ተካተዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች