Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከሆርቲካልቸር ኤክስፖርት 275 ሚሊዮን ዶላር ተገኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የኢኳደር ኩባንያዎች በዘርፉ ፍላጐት አሳይተዋል

 ከሆርቲካልቸር ኤክስፖርት ልማት ዘርፍ 275 ነጥብ 45 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን፣ የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ መኰንን ኃይሉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አገሪቱ የውጭ ምንዛሪውን ያገኘችው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለዓለም ገበያ ባቀረበችው የአበባ፣ የአትክልት፣ የፍራፍሬና የዕፀ ጣዕም ምርቶች ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ ከተገኘው አጠቃላይ ገቢ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የአበባ ኤክስፖርት ሲሆን፣ ከዘርፉ የተገኘው ከ225 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቀሪው 50 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ደግሞ ከአትክልት፣ ከፍራፍሬና ከዕፀ ጣዕም ምርቶች የተገኘ ነው ብለዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪው የተገኘው አገሪቱ በተጠቀሰው ወቅት ለዓለም ገበያ ባቀረበችው ከ49 ሺሕ ቶን በላይ ጽጌረዳና የበጋ አበባ፣ እንዲሁም 714.5 ሚሊዮን ዘንግ ቅንጥብ አበባና 166 ሺሕ ቶን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች አማካይነት ነው፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከሆርቲካልቸር ኤክስፖርት ልማት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ10.7 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አቶ መኮንን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘርፉ በምትሰጠው ድጋፍና ልዩ ማበረታቻ ምክንያት በሆርቲካልቸር ኤክስፖርት ልማት ዘርፍ በውጭ ባለሀብቶች ተመራጭ እየሆነች ትገኛለች ብለዋል፡፡ ወደ አገሪቱ የሚመጡ የውጭ ኩባንያዎች ቁጥር በማደግ ላይ ሲሆን፣ አሁንም ሌሎች ኩባንያዎች በዘርፉ ከፍተኛ ልማድ ካላቸው ከኢኳዶርና ከመሰል አገሮች በኢትዮጵያ ለመሥራት ፍላጐት እያሳዩ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

አገሪቱ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑትን የሆርቲካልቸር ምርቶች የላከችው ለአውሮፓ ገበያ ነው፡፡ ሰሜን አሜሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ሩቅ ምሥራቅና የአፍሪካና ሌሎች አገሮች የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ምርቶች የተላኩባቸው አገሮች ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በሆርቲካልቸር ኤክስፖርት ልማት ዘርፍ 130 የሚሆኑ ኩባንያዎች የተሰማሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም አብዛኞቹ የውጭ ኩባንያዎች መሆናቸውን ከኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች