Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ 447 ጉዳዮች የመመርያ ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል አለ

የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ 447 ጉዳዮች የመመርያ ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል አለ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አገልግሎት ከሰጣቸው 7,108 ፕሮጀክቶች ውስጥ፣ 447 የሚሆኑት የመመርያ ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል አለ፡፡

የከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አገልግሎት የሰጣቸውን እነዚህ ፕሮጀክቶች በምን መንገድ እንደተስተናገዱ ለማወቅ ባካሄደው የኦዲት ምርመራ፣ በርካታ አገልግሎቶች መመርያ ተጥሶ መስተናገዳቸውን አመልክቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አገልግሎት ከተሰጣቸው ፕሮጀክቶች ውስጥም 2,559 የሚሆኑት የአሠራር ችግር ያለባቸው መሆናቸውን፣ የአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መኮንን አምባዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተካሄደው የኦዲት ምርመራ የአሠራር ክፍተት መፍጠራቸው የተረጋገጠባቸው አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡

‹‹በተወሰደው ዕርምጃ ጥፋተኛ መሆናቸው በመረጃ የተረጋገጠባቸው 32 አመራሮችና 119 ፈጻሚዎች በሕግ እንዲጠየቁ ተደርጓል፡፡ የዲሲፕሊን ዕርምጃ የተወሰደባቸው አመራሮችና ሠራተኞች ደግሞ 30 ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ከመሬት ተቋማት ውጪ የተደረጉ አመራሮችና ሠራተኞች ደግሞ 406 መሆናቸውን አቶ መኮንን ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ 406 አመራሮችና ሠራተኞች ላይ በቂ መረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ በሕግ ተጠያቂ ማድረግ አለመቻሉን አቶ መኮንን ገልጸው፣ በአጠቃላይ ዕርምጃ በተወሰደባቸው አመራሮችና ሠራተኞች ምትክ የሰው ኃይል እንዲሟላ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

የሙስና መፈልፈያ ከተባሉት መካከል አንዱና ግንባር ቀደም በሆነው መሬት ዘርፍ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት የሞከሩ ከተባሉት መካከል ቅሬታ አቅራቢዎችም እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፡፡

መረጃዎች እንደጠቆሙት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 8,359 ቅሬታዎች ለመሬትና ማኔጅመንት ቢሮ ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህ ቅሬታዎች ውስጥ 7,974 ለሚሆኑት ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ ነገር ግን ምላሽ ከተሰጣቸው ውስጥ 5,592 የሚሆኑት ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሆን ተብሎ አስተዳደሩን ለማሳሳት የቀረቡ መሆናቸውን አቶ መኮንን አስረድተዋል፡፡  

የመመርያ ጥሰት ተፈጽሞ አገልግሎት እንዲያገኙ በተደረጉ ፕሮጀክቶች ላይ የሚወሰደውን ዕርምጃ ቢሮው ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ