Friday, March 1, 2024

የተቃውሞ ሠልፎቹ ዘርፈ ብዙ ሥጋቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሐምሌ 30 እና ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በአገሪቱ ሁለት ትልልቅ ክልሎች ማለትም በኦሮሚያና በአማራ ብሔራዊ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የተቃውሞ ሠልፎች ተደርገዋል ወይም ለማድረግ ሙከራ ተደርጓል፡፡ በሒደቱ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ የተወሰኑት ጉዳት ደርሶባቸዋል ወይም ተጎሳቁለዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ በተሳትፏቸው ሳቢያ ለእስር ተዳርገዋል፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችም በማኅበራዊ ሚዲያ የተደረገውን የሠልፍ ጥሪ በመቀበል በአዲስ አበባ ባልተለመደ ሁኔታ ለሠልፍ ወጥተው ነበር፡፡ የፖለቲካ ነፃነትን ጨምሮ የተለያዩ ጥያቄዎችን እያቀረቡ የነበሩት ሠልፈኞች ከመስቀል አደባባይ በፖሊስ ተበትነዋል፡፡ የተለያዩ ሪፖርቶች እንዳመለከቱትና የዓይን እማኞች ለሪፖርተር እንደገለጹት ፖሊስ በተሳታፊዎቹ ላይ ድብደባ ፈጽሟል፡፡ ይሁንና ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይና በአቅራቢያው ሊደረግ በተሞከረው ሠልፍ ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ የሰው ሕይወት አልጠፋም፡፡

ከአዲስ አበባ በተቃራኒ በኦሮሚያና በአማራ ግን የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በበርካታ ሰዎች ላይ በመተኮስ ሞት አስከትለዋል፡፡ ሪፖርቶች እንዳመለከቱትና የዓይን እማኞች ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት ሠልፎቹ በፀጥታ ኃይሎች የኃይል ዕርምጃዎች ተቋርጠዋል፡፡ ነሐሴ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በሁለቱ ቀናተ 97 ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች እጅ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ አምነስቲ ታማኝ ምንጮቼ አረጋገጡልኝ እንዳለው በኦሮሚያ ብቻ 67 ሰዎች ሲገደሉ በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ ብቻ በአንድ ቀን (ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም.) 30 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ አምነስቲ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውንም አመልክቷል፡፡

ሌሎች ሪፖርቶች በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል በአሥር ከተሞች ሰላማዊ ሠልፎች ተደርገው ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ጠቁመዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አምቦ፣ ደምቢ ዶሎና ነቀምት ተጠቃሽ ሲሆኑ በነቀምት ብቻ 15 ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ ዘገባዎች በባህር ዳር የሞቱትን ቁጥር 60 ቢያደርሱትም የአማራ ክልል ግን ሰባት ሰዎች ብቻ ሕይወታቸውን እንዳጡ አስታውቋል፡፡ አምነስቲ ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ በተካሄደው ሠልፍ ሰባት ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ በሪፖርቱ አካቷል፡፡ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ለተለያዩ ሚዲያዎች እንደገለጹት ፓርቲያቸው በኦሮሚያ የተገደሉ 33 ሰዎችን ዝርዝር አጠናቅሯል፡፡

አምነስቲ ሪፖርት እንዳደረገው በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የታሰሩት በይፋ በማይታወቁ ማቆያ ቦታዎችና ወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፖች ውስጥ ነው፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ክልላዊ የፖሊስ ኃይሎች በመከላከያ ሠራዊት እንደተተኩም አክሏል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ባለፉት አሥር ወራት እየተካሄዱ የነበረ ቢሆንም፣ በአማራ ክልል ከጥቂት ወራት ጀምሮ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ መጀመሩ አገሪቱ በደኅንነት ሥጋት ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፡፡ እነዚህ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ለምን ደም አፋሳሽ እንደሆኑና አሁን እንደተነሱ ግን የበርካቶች ጥያቄዎች ናቸው፡፡

የማን ሠልፎችና ተቃውሞዎች ናቸው?

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችና በተለያየ የዕድሜ ክልል ላይ ያሉ ዜጎች በመሳተፋቸው የሕዝብ ተቃውሞና ቅሬታዎች ማሳያ ናቸው ተብለው ቢገለጹም፣ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ግን የሕዝብ ሳይሆኑ የሕዝብን ሰላም ማደፍረስ የሚፈልጉ የአገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች (ለምሳሌም ሻዕቢያና ኦነግ) ጋር በመጣመር የፈጠሯቸው የግርግር መድረኮች ናቸው በማለት ይገልጻቸዋል፡፡

በዚህም የተነሳ በውጭ የሚገኙ ኃይሎችና የኢንተርኔት አክቲቪስቶች ለሠልፉ ጥሪ በማድረግ ብጥብጥ እንዲፈጠር አድርገዋል ያለው መንግሥት ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ አድርጎ ነበር፡፡ በርካታ ሪፖርቶች እንደገለጹት የተቃውሞ ሠልፎቹ የተካሄዱት በማኅበራዊ ሚዲያ በተደረጉ ጥሪዎች አማካይነት ነው፡፡

ስለሚካሄዱት ሠልፎች ግንዛቤው የነበረው መንግሥት ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ባስተላለፈው መልዕክት ሕዝቡ በ‹‹ሕገወጥ›› ሠልፎቹ ላይ እንዳይገኝ አስጠንቅቆ ነበር፡፡ መንግሥት ሠልፎቹ ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ እያስጠነቀቀም ቢሆን በሁለቱ ቀናት የተቃውሞ ሠልፎችን ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡

የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሕጋዊ መሥፈርቶችን ሳያሟሉ በ‹‹ፀረ ሰላም ኃይሎች›› የተካሄዱ ሠልፎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ቢዘግቡም፣ በዕርምጃው የደረሰውን የጉዳት መጠን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ቀድሞ ማሳወቅ ይጠይቃል፡፡ ይህ ማሳወቂያ የሠልፉን አዘጋጅ፣ ዓላማ፣ ቦታ፣ ሰዓት፣ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ሰው ቁጥርና የመሳሰሉትን መረጃ መያዝ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ እነዚህ መረጃዎች የሚፈለጉት መንግሥት ለሚያደርገው ጥበቃ ቅድሚያ ዝግጅት እንዲያደርግ እንጂ በሠልፎቹ ላይ ቅድመ ምርመራ እንዲያደርግ አይደለም፡፡

ከዚህ በተቃራኒ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ለተቃውሞ ሠልፎች ያለው አመለካከት እጅግ በጎ ያልሆነ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ የተካሄዱት ሠልፎች ቁጥር በጣት የሚቆጠርና በርካታ ጉዳት ያደረሰ መሆኑ ለዚህ ምስክር እንደሆነም ይጠቀሳል፡፡ በዚህም ሒደት መንግሥት ማሳወቅን በተግባር ወደማስፈቀድ ቀይሮታል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር እስከነጭራሹ የሰላማዊ ሠልፍ ፈቃድ ክፍል እስከማቋቋም ደርሷል፡፡ ስብሰባና ሠልፍ ለማሳወቅ የሚቀርቡ ማመልከቻዎችን አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች ባለመቀበል ክልከላን የተለመደ አሠራር በማድረጉም ይተቻል፡፡

‹‹ባለፉት ጊዜያት ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ስንሞክር የተለያዩ ሰበባ ሰበቦች እየተፈጠረ እንዳናደርግ ስንከለከል ነበር፤›› ያሉት የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መሥራችና የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው ናቸው፡፡ አንጋፋው ፖለቲከኛና የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) ፓርቲ ሊቀመንበር እያሉ የተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፎችን ለማድረግ በሕግ የተቀመጡ መሥፈርቶችን በማሟላት ለማሳወቅ ጥረት ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ለማስታወቅ ወደሚመለከተው አካል ስንሄድ ወይ አሉታዊ መልስ ይሰጠናል፣ አልያም ደግሞ ትክክለኛ የሆነ አቀባበል አይደረግልንም፡፡ በዚህም የተነሳ ሠልፍ ማድረግ አስቸጋሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የመንግሥት ምላሽ

ለሰላማዊ ሠልፍ የመንግሥት ምላሽ አልበዛም ወይ? ሲሉ የጠየቁ በርካቶች ናቸው፡፡ የመንግሥት አስተያየት ግን የተለየ ነው፡፡ ሠልፎቹ በሰላም ተቃውሞ ለማሰማት ብቻ ያለሙ አልነበሩም ሲል ይከራከራል፡፡

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ሊቀመንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንንና የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ምክትል ሊቀመንበርና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ አስቴር ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት በሰላማዊ ሠልፍ ሽፋን የተሞከረው የአመፅ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ዋና ተልዕኮውም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ማፍረስ ነው፡፡ ከእንቅስቃሴው ጀርባም የሻዕቢያና የኦነግ እጅ እንዳለበት ተጠቅሷል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ነሐሴ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የመንግሥትና የግለሰብ ንብረት ሲያወድሙ፣ መንገድ ሲዘጉና በንፁኃን ዜጎችና በፀጥታ ኃይሎች ላይ የሞት አደጋ ሲያደርጉ በመገኘታቸው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች አሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የሕገ መንግሥት ኤክስፐርትና ተመራማሪው ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሁለቱ ቀናት አደጋ ላይ የወደቀው በሕይወት የመኖር መብት እንጂ የመቃወም መብት ብቻ አይደለም፡፡ ‹‹በሕይወት ከመኖር የላቀ መብት የለም፡፡ ሰላማዊ ሠልፍ እንዳታደርግ ከተከለከልክ ወይም በተሳትፎህ ከታሰርክ ዛሬ ባላገኘውም መብቴን ነገ ላገኘው እችላለሁ ብለህ ልታስብ ትችላለህ፡፡ የተወሰደብህ ዕርምጃ ሕይወትህን እንድታጣ ካደረገህ ግን ሁሉም ነገር ያበቃል፤›› ብለዋል፡፡

ለዶ/ር ጌድዮን አሁን ጥያቄው የሰብዓዊነት ጥያቄ ነው፡፡ በመቶዎች የሚቆጠር ዜጋ ሕይወት በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እጅ የጠፋ ቢሆንም እስካሁን አንድም ኃላፊ ተጠያቂ አልሆነም፡፡ ‹‹የእያንዳንዱ ሰው አሟሟት መመርመር አለበት፡፡ አገሪቱ ተዓማኒነት ያለው የምርመራ ሥርዓት ያስፈልጋታል፡፡ በቅርቡ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተከናወነውን ምርመራ ጨምሮ የተደረጉ ምርመራዎች ትኩረት ፖለቲካዊ ምክንያትን ለመለየት የተገደበ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሥርዓቱ ትልቅ አደጋ ላይ ነው፤›› በማለት አክለዋል፡፡

የአምነስቲ ኢንተርናሽናሏ ሚቼል ካጋሪ መንግሥት የወሰደው ከመጠን ያለፈ ምላሽ መንግሥት ካለው ሪከርድ አኳያ የሚገርም አይደለም ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሰላምና ደኅንነት ተንታኝ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት ከሚያራምደው ዴሞክራሲያዊ ያልሆነና ለሰብዓዊ መብት ግዴለሽ ከሆነው የአመራር ዘይቤው አንፃር ምላሹ ያልተጠበቀ ነው የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡ ‹‹ራሱን በሕገ መንግሥቱ ላይ ተመሥርቼ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አከብራለሁ የሚል መንግሥት ተጠያቂ ሊሆን ይገባል፤›› ያሉት ኤክስፐርቱ፣ መንግሥት ያለምንም ተጠያቂነት ሁሌም የምወስዳቸው ዕርምጃዎች ተመጣጣኝ ናቸው እያለ ሊቀጥል አይችልም ብለዋል፡፡ ‹‹ይኼ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መለያ አይደለም፡፡ ዜጎች ለተቃውሞና ለሠልፍ ሲወጡ መንግሥት በኃላፊነት ጥበቃ ያደርግልናል ብለው ነው፡፡ ድንጋይ ወርውረሃል ብሎ መንግሥት በጥይት የሚገድል ከሆነ ይኼ ፀረ ሕገ መንግሥታዊ፣ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነና ፖለቲካዊ ዋጋውም ከባድ የሆነ ድርጊት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞ መነሻ ማስተር ፕላኑ እንደነበር ያስታወሱት ኤክስፐርቱ፣ መንግሥት ማስተር ፕላኑን የሰረዘው ቢሆንም ተቃውሞው የቀጠለበት አንዱ ምክንያት የፖሊስ ዕርምጃዎች የፈጠሩት ቅሬታ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡ ‹‹መንግሥት በሚወስዳቸው ዕርምጃዎች የሚፈጸሙ ስህተቶችና ግድያዎች ኅብረተሰቡ ላይ ሌላ ተጨማሪ ቁስል ይፈጥራሉ፡፡ ሌላ ምንም ዓይነት ጥያቄ የሌለው ሰው በግድያዎቹና በድብደባዎቹ ምክንያት ብቻ ለተቃውሞ ሊሠለፍ ይችላል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

የተቃውሞው መነሻዎች

በተቃውሞ ሠልፎቹ መንግሥት ላይ ጠንካራ ትችቶች ቀርበዋል፡፡ ተቃውሞው በቅርብ ጊዜና ለረጅም ጊዜ እየተንከባለሉ በመጡ ምክንያቶች እንደተነሳ አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡ በመንግሥት ላይ የሰላ ትችት የሚያቀርቡ ተንታኞች የተቃውሞዎቹ መነሻዎች መንግሥት እየሄደበት ካለው የአመራር ዘይቤ ጋር እንደሚገናኙ ይገልጻሉ፡፡

ለአንዳንዶች በመንግሥት አመራሮችና በሕዝቡ መካከል ውጥረት እየነገሠ ስለመምጣቱ ተቃውሞዎቹ ማሳያ ናቸው፡፡ በተለይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መገለል እየተፈጠረ መሆኑን ሠልፈኞቹ በግልጽ አመልክተዋል፡፡ የፖለቲካ ነፃነት፣ የፍትሕ ዕጦትና የሕግ የበላይነት መከበርም እንደ አጀንዳ ቀርበዋል፡፡

አቶ ልደቱ ለተቃውሞው መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ ያሏቸውን አራት ዋና ዋና ምክንያቶች ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህም የፖለቲካ ሥርዓቱ ልዩነት ላይ ያተኮረ መሆኑ፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያሉ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተግባር አለመዋላቸው፣ ዜጎች ሐሳባቸውንና ተቃውሟቸውን የሚገልጹበት ዴሞክራሲያዊ መድረክ አለመኖሩና ከፍተኛ የሆነ ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዘ በደል ዜጎች ላይ የሚፈጸም መሆኑ ናቸው፡፡

ሥርዓቱ ለልዩነት የተለየ ትኩረት መስጠቱን በተመለከተም አቶ ልደቱ ሲናገሩ፣ ‹‹ልዩነት መከበር አለበት፡፡ ነገር ግን አንድ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የጋራ የሆኑ ጉዳዮች ተጠናክረው መውጣት አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ በአጠቃላይ ሥርዓቱ ከፍተኛ ጉድለት አለበት፡፡ በልዩነት ላይ በጣም ማተኮር በሕዝብ ዘንድ መቃቃር እየፈጠረ፣ አንድነት እየላላ ግጭት የሚያጭር እንደሆነ በተደጋጋሚ ስንገልጽ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ልደቱ ከዚህ በተቃራኒ መንግሥት ማንነት ላይ መሠረት ያደረገው የፌዴራል ሥርዓት የበለጠ አንድነት የሚያመጣ ነው፣ ሕዝቡም ተቀብሎታል፣ ችግሮችንም እየፈታ ነው በማለት እንደሚሞግት አስታውሰዋል፡፡ ‹‹በእነዚህ የተቃውሞ ሠልፎች ይህ እውነት እንዳልሆነ የታየ ይመስለኛል፤›› ብለዋል፡፡ መሰል ችግሮች ከዚህ በፊትም የታዩ ቢሆንም አሁን ብዙ አካባቢዎችን ማካለሉ ለየት እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡

ሐሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት መድረክ እየጠበበ ስለመሆኑ ሲያስረዱም፣ ‹‹ሰዎች ቅሬታቸውን የሚገልጹበት ዴሞክራሲያዊ መንገድ ካጡ ወደ አመፅና ግጭት መሄዳቸው የማይቀር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ሐሳባቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ እያጡ ነው፡፡ በዚህም ፅንፈኛ የሆኑ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ይጠናከራሉ፤›› ብለዋል፡፡

መልካም አስተዳደርን በተመለከተም፣ ‹‹ካድሬዎች ጉልበተኛ ሆነዋል፣ ኅብረተሰቡ ደግሞ አቀመ ቢስ ሆኗል፡፡ የፈለገውን አድርጎ ተጠያቂነት የለበትም፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የሰላምና ደኅንነት ተንተኙ ለተቃውሞ መነሻ ሦስት ምክንያቶችን ያቀርባሉ፡፡ የመጀመሪያው እንደ አቶ ልደቱ ሁሉ ከፌዴራሊዝም ንድፈ ሐሳብና አተገባበር ጋር ይያያዛል፡፡ ሁለተኛው በሙስናና በመልካም አስተዳደር ዕጦት የሚገለጽ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ከውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ አንፃር የታየ ነው፡፡

‹‹የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት የተዋቀረበት መንገድ ምን ያህል ርቀት ተጉዟል? ቅቡልነቱ ምን ያህል ተጠናክሯል? የፌዴራል ሥርዓቱ ሊኖረው የሚችለውን ተግዳሮት የሚመልስ ባህላዊና ተቋማዊ አቅም ተገንብቷል ወይ? ተቋማቱ ከፓርቲ አደረጃጀት በዘለለ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ወይ? የክልሎች የሥልጣን ባለቤትነትና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተረጋግጧል ወይ? በክልሎች መካከል ያሉ ድንበሮች ተከልለዋል ወይ? የድንበር ግጭቶች የሚፈቱበት ሥርዓት አለ ወይ? የፌዴራል መንግሥት ክልሎች ላይ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት እየፈጸመ ነው ወይ? ሕወሓት ሌሎች የኢሕአዴግ አባላትንና አጋር ፓርቲዎችን ያላግባብ እየተጫነ ነው ወይ? የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ላይ በግልጽ ልንወያይ ይገባል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ላይ ግልጽ ውይይት ቢደረግ ኖሮ ተቃውሞው እንደዚህ ደም አፋሳሽ ባልሆነ ነበር፤›› በማለትም አብራርተዋል፡፡

ሙስናና የመልካም አስተዳደር ክፍተትን በተመለከተ ሲገልጹም ችግሩ መኖሩን መንግሥት በተደጋጋሚ እንዳመነ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹በጉዳዩ ላይ ሕዝቡ ከፍተኛ ቅሬታ አለው፡፡ በጣም ብዙ የተማረና ሥራ የሌለው ወጣት አለ፡፡ የአገሪቱ ሲቪል አስተዳደር የፖለቲካ ታማኝነት ላይ በመመሥረቱና በመገንባቱ አቅምን መሠረት ያደረገ አስተዳደር ጠፍቷል፡፡ ከፖለቲካው በመጠጋት ብዙ ሀብት በማፍራት ተራው ሕዝብ ሊያገኝ የሚገባውን አገልግሎት የሚያሳጡ በዝተዋል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ የሙስና ኢኮኖሚው የራሱን ውድድር መፍጠሩን ያመለከቱት ኤክስፐርቱ፣ በዘር በተያያዘ ኔትወርክ በመጠቀም ሌሎች የመገለል ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ አሠራር መንሰራፋቱንም ጠቁመዋል፡፡

ለኤክስፐርቱ የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ በፍፁም ሊገርም አይገባም፡፡ ‹‹የፖለቲካ ስምምነት መፍጠር ለዚህ አገር ቁልፍ አጀንዳ ነው፡፡ በተለይ በውጭ አገር የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር የሚገናኙበት ድልድይ አለመኖር ችግሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ እነዚህ ኃይሎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከመንግሥት ጋር እንዲደራደሩ ማድረግ እስካልቻልን ድረስ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ሲያገኙ መጠቀማቸው አይገርምም፤›› ብለዋል፡፡ እነዚህ ውጭ አገር ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች መልዕክታቸውን የሚያስተላልፉበት የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ቁጥጥር የሚደረግበት አለመሆኑ አስቀድመው የተያዙ የተዛቡ አመለካከቶች ነገሮችን እንዲያቀጣጥሉ ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

የሕገ መንግሥት ኤክስፐርትና ‹‹አንቀጽ 39›› በሚል ርዕስ ራስን በራስ ማስተዳደርን የተመለከተ መጽሐፍ ያሳተሙት አቶ ውብሸት ሙላት እንደገለጹት፣ የተቃውሞ ሠልፎቹ ሕዝቡ በግልጽ ሕወሓት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለውን ከመጠን ያለፈ እጅ እንዲሰበሰብ መልዕክት ያስተላለፈባቸው መድረኮች ናቸው፡፡ ‹‹በተለይ በመከላከያ ሠራዊቱ፣ በፀጥታና ደኅንነት ተቋማቱ የበላይነት እንደያዘ ሕዝቡ ያምናል፡፡ የሕወሓት ባህርያት በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተገሩ መሆናቸውን በነፃነት የሚከታተሉ ተቋማት የሉንም፤›› ብለዋል፡፡        

ዶ/ር ነጋሶም ሠልፎቹ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እርካታ እንደሌለው ያሳየባቸው ናቸው ብለዋል፡፡ ‹‹በሠልፉ ሰፊ ሕዝብ ነው የወጣው፡፡ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ ሽማግሌዎች በስፋት ወጥተዋል፡፡ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ችግሮች ምክንያት በመንግሥት ላይ እርካታ የላቸውም፡፡ ጠቅላላ ምርጫ ከተደረገ ገና አንድ ዓመቱ በቅርቡ ቢያልፍም ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ መቃወሙ የሚያሳየው ነገር ሕዝቡ በኢሕአዴግ አለመርካቱን ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ለዶ/ር ነጋሶ ሌላኛው ምክንያት አካባቢያዊ መሠረት ላላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ አለመሰጠቱ ነው፡፡

የማንነት ጥያቄ እንደ ልዩ ምክንያት

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከተነሱት ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች መካከል የማንነት ጥያቄ ተጠቃሽ ነው፡፡ የኦሮሞ ማንነት ሙሉ በሙሉ አልተመለሰም በሚል የችግሩ መገለጫ የሆኑ ከመሬት፣ ከቋንቋና ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች መነሳት ከጀመሩ ሰንብተዋል፡፡ ይሁንና በአማራ ክልል የወልቃይት የማንነት ጥያቄ እንዲሁ ለግጭት እየዳረገ ይገኛል፡፡

በባህር ዳርና በጎንደር የተደረጉትና የሰው ሕይወት የቀጠፉት ሠልፎች አሁን በትግራይ ክልል የምትገኘው ወልቃይት ቀድሞ ወደነበረችበት አማራ ክልል መልሳ ትቀላቀል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ወልቃይት በታሪክ በአማራ ክልል ውስጥ ነበረች፣ በትግራይ ክልል ነበረች፣ ራሷን የቻለች ነበረች የሚለው ሁሉንም አካል የሚያስማማ ባይሆንም ቢያንስ ሠልፈኞቹ ወልቃይት በሕገወጥና አግባብ ባልሆነ መንገድ በኢሕአዴግ/ሕወሓት አማካይነት ወደ ትግራይ ክልል ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ተቀላቅላለች ብለው ያምናሉ፡፡ የወልቃይት የማንነት ጥያቄን ለመከታተል የተቋቋመው ኮሚቴ አባል የሆኑት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ለመያዝ ሲሞክሩ በጎንደር ከተማ የተፈጠረው ግጭት በአማራ ክልል ተቃውሞ ለመጀመር የቅርብ ምክንያት ሆኗል፡፡

አቶ ውብሸት የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ከተለመደው የማንነት ጥያቄ ወጣ ያለ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የወልቃይት ጥያቄ የተፈጠረው በአማራ ክልል አይደለም፡፡ የወልቃይት ሕዝቦች የአማራ የማንነት ጥያቄ የተነሳው በትግራይ ክልል ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ጥያቄው ሊፈታ የሚችለው በትግራይ ክልልና በፌዴራል መንግሥቱ ነው፡፡ ሆኖም ችግሩ ሕዝቡን እያንገላታ ያለው በአማራ ክልል በመሆኑ ሁለቱ ክልሎች ከፌዴሬሽን ምክር ቤትና ከፌዴራልና የአርብቶ አደሮች ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ፖለቲካዊ መፍትሔ ቢሰጡት የተመረጠ ነው፤›› በማለት ሐሳባቸውን አካፍለዋል፡፡ የወልቃይት ጥያቄ የግዛትና የአዲስ ማንነት ይገባኛል ድርብ ጥያቄ መያዙ የተወሳሰበ እንዳደረገውም ሌሎች ምሁራን ይጠቅሳሉ፡፡

የተቃውሞ ባህል

ብዙዎች በአገሪቱ የዴሞክራሲ ባህል ባለመዳበሩ የተቃውሞ ባህል አብሮት በመክሰሙ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ተቃውሞ ማሰማት በአገሪቱ ብርቅ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ይህ አመለካከት በኢሕአዴግ በኩልም የመቀየር አዝማሚያ አለማሳየቱን ይተቻሉ፡፡

የደኅንነት ተንታኙ ለዚህ ችግር ዋናው መፍትሔ ሊሆን የሚችል መሀል ያለ ነገሮችን የሚያረግብ ተቋም ወይም አስታራቂ መጥፋቱ አሳሳቢ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በቂ ነፃ ሚዲያ አለመኖሩ፣ ሲቪል ማኅበራት አለመኖራቸው፣ የአደባባይ ምሁራንና አመለካከቶችን የሚቀርፁ ሰዎች ተገፍተው እንዳይኖሩ መደረጋቸው በፖለቲካ መድረካችን አስታራቂ እንዲጠፋ አድርጓል፡፡ በዚህም መድረኩ በመንግሥትና በተቃዋሚዎቹ ንትርክ እንዲሞላ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡ እንደ መፍትሔ ምሁራን፣ የቀድሞ የፖለቲካ መሪዎችና የሃይማኖት ተቋማት ይህን ክፍተት እንዲሞሉ ጥሪ አድርገዋል፡፡

አቶ ልደቱም፣ ‹‹አሁን በአገሪቱ እየታዩ ያሉት ነገሮች በጣም አደገኛ በመሆናቸው መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች መፍትሔ መሻት አለባቸው፡፡ ሁላችንም የችግሩ አካል ነን፡፡ መፍትሔውም የሚገኘው ከሁላችንም ነው፡፡ አንዱ አካል ችግር ፈጣሪ ሌላው አካል ደግሞ መፍትሔ ፈላጊ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ችግሩ ከዚህ ከቀጠለ የአገር ህልውናም ሊናጋ ይችላል ያሉት አቶ ልደቱ፣ ‹‹እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ ችግሩ የመንግሥት ለውጥ ብቻ አምጥቶ ሊያበቃ ይችላል፡፡ በዚህም መንግሥት የለሽ ሊያደርገን ይችላል፡፡ ወደማያቋርጥና አደገኛ ወደሆነ ጦርነት ሊያስገባን ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በኋላ ብጥብጥና ጦርነት ማስተናገድ የምንችልበት ሁኔታ ላይ አይደለንም፤›› ብለዋል፡፡ ይህንንም ለመቀልበስ ሁሉም በጋራ ለመሥራት ሊረባረብ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ በተመሳሳይ ዶ/ር ነጋሶ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ የሚሰጥ አገር አቀፍ ኮንፈረንስ ተዘጋጅቶ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

የሰላምና የደኅንነት ተንታኙን ጨምሮ መንግሥት ችግሮቹን ለራሱ በሚጠቅም ብቻ መተርጎሙ ዘላቂ መፍትሔ ለመሻት የማይጠቅም በመሆኑ፣ በግልጽ ችግሮቹን ተቀብሎ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መጀመር እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ ተንታኙ፣ ‹‹አሁን እውነታውን ተቀብሎ የሚመለከታቸውን አካላት ለማዳመጥ ፈቃደኛ መሆን ያለበት ጊዜ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ምናልባትም ብዙዎች በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡  

 

         

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -