‹‹ባለቤቱ የማይታወቅና የጦር መሣሪያ ጭምር በመታጠቅ ሰልፍ ለማድረግ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሕገወጥ ተግባር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ደርጊት ሲያጋጥም ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭና የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የሚጎዳ በመሆኑ መንግሥት ዕርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል፡፡››
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በወቅታዊ የአገሪቱ ጉዳዮች ዓርብ ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ቅዳሜና እሑድ ትዕይንተ ሕዝብ እንደሚካሄድ መገለጹን ተከትሎ በዋዜማው ማሳሰቢያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፣ በአገሪቱ ባለፉት 15 ዓመታት በተደረገው የተሐድሶ እንቅስቃሴ የተገኙ ውጤቶችንና የገጠሙ ችግሮችን ለመገምገም ዝግጅት መደረጉን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡