ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ወደ አፋር ጉዞ የጀመርነው አረፋፍደን ወደ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ነበር፡፡ ዝናብ እየጣለ ነበርና ሁሉም ልብስ ደራርቧል፡፡ በምቾትና በፍጥነት ለመጓዝ አዲሱ የፍጥነት መንገድን መረጥን፡፡ ወደ ፍጥነት መንገዱ እስክንገባ የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ለማምለጥ አቋራጭ መንገዶችን ለመጠቀም ተገደድን፡፡
በአዲሱ የፍጥነት መንገድ ጥቂት ተጓዝን፡፡ እንደ ፍየል፣ በግና አህያ ያሉ የቤት እንስሳት በመንገዱ ዳርና ዳር ሆነው ሳር ሲግጡ ያጋጥሙን ጀመር፡፡ አልፎ አልፎ የመንገዱ አካፋይ ብረቶች ባጋጠማቸው ግጭት ተጣመው ይታያሉ፡፡ ከብረቶቹ በላይ ከተደረደሩት አረንጓዴ ቆርቆሮ መሳዮች አብዛኞቹ ተሰብረዋል፡፡ ስለሁኔታው እየተወያየን የፍጥነት መንገዱን ጨርሰን አዳማን አልፈን መተሀራ ከተማ ደረስን፡፡
በየመንገዱ የሚቆሙ ነጋዴዎች በፌስታል የያዟቸውን ፍራፍሬዎች ከፍ አድርገው ወደ ተሽከርካሪዎቹ ይጠጋሉ፡፡ አራት ኪሎ ብርቱካን በ80 ብር የሚሸጡ ሲሆን የመተሀራን ጣፋጭ ብርቱካን የቀመሱ አያልፋቸውም፡፡ ተሻምተው ይገዟቸዋል፡፡ በከተማው በስፋት ከሚከናወነው የፍራፍሬ ንግድ ባሻገር የከረዩ ባህል አለባበስ የለበሱ፣ ፀጉራቸውን ያጐፈሩና ጥርሳቸውን እየፋቁ ግመል የሚነዱ የከረዩ ኮበሌዎች ሌላው የመተሀራ ገጽታዎች ናቸው፡፡
መተሀራን አልፈን አዋሽ የሚወስደው መንገድ ላይ ወጣን፡፡ ጅግራና ዝንጀሮ ወደ መንገዱ ወጥተው ጥሬ ይለቃቅማሉ፡፡ ዝንጀሮዎቹ ከነመንጋቸው መኪና ባለፈ ቁጥር ዳሩን ይዘው ሮጥ ሮጥ እያሉ ይከተላሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉት በአካባቢው የሚያልፉ መንገደኞች የተለያዩ ምግቦችን እየወረወሩ ስላስለመዷቸው መሆኑን ሾፌራችን ገለጹልን፡፡ ምግብ ለማግኘት በሚያደርጉት ሩጫ ብዙዎቹ በመኪና ተገጭተው ሕይወታቸው እንደሚያልፍ ተገጭቶ መንገዱ ላይ የወደቀ የዝንጀሮን በድን ሳይ ተረዳሁ፡፡ ከዝንጀሮዎች ሌላ ጅብና የተለያዩ የአዕዋፍ ዝርያዎችም በየመንገዱ በመኪና ተገጭተው ሞተው ይታያሉ፡፡
አፋር እስክንደርስ በርካታ የመንገድ ጥገናዎች ስለነበሩ ተለዋጭ መንገዶችን ለመጠቀም ተገደናል፡፡ አንዳንዶቹ መንገዶች ፒስታ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ አባጣ ጐርባጣ የበዛባቸው አስቸጋሪ ናቸው፡፡ መንገዶች በጥገና ላይ መሆናቸውንና ተለዋጭ መንገድ እንዲጠቀሙ እንዲያመለክቱ የተዘጋጁት አንፀባራቂዎች በተገቢው መጠን አያንፀባርቁም፡፡ ከርቀት ለማየትም አስቸጋሪ ናቸው፡፡
መንገዱ ኮንቴይነር በያዙ የጭነት ተሽከርካሪዎችና የነዳጅ ቦቴዎች የተሞላ ነው፡፡ አደጋም ይበዛበታል፡፡ ባጋጠማቸው አደጋ ከጥቅም ውጪ ሆነው በየመንገዱ ጥግና ጥግ የቆሙ ተሽከርካሪዎች ጥቂት አይባሉም፡፡ የመኪና መስተዋቶችና የቢራ ጠርሙሶች ስብርባሪም ይበዛል፡፡ አደጋው ማቆሚያ ያለው አይመስልም፡፡ በሚያጋጥሙ አዳዲስ የመኪና ግጭቶች መንገዶች ይዘጋሉ፡፡ አደጋ የደረሰባቸውን የጭነት ተሽከርካሪዎች ጭነው የሚያልፉ ግዙፍ ተሽከርካሪዎችና ክሬኖች እዚህም እዚያም ይታያሉ፡፡ ሌላ ያልተገባ ድርጊት የሚፈጽሙ ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎችም አጋጥመውናል፡፡ ወደ አዲስ አበባ እየመጡ ከነበሩት ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች መካከል አንደኛው ፍጥነቱን እያቀዘቀዘ ወደ ዳር ወጣ፡፡ አሽከርካሪው እረፍት ለማድረግ እንደፈለገ ገመትኩኝ፡፡ ጉዳዩ ግን ሌላ ነበር ቦቴው ጥጉን ይዞ እንደቆመ አንዳንድ የአካባቢው ሰዎች በፍጥነት ቢጫ ጀሪካንና ቱቦ በመያዝ ወደ ቦቴው ተጠግተው ነዳጅ ይቀዱ ጀመር፡፡
ጉዞው አድካሚ ስለነበር አዋሽ ሰባት ላይ አልጋ ይዘን ማደር ነበረብን፡፡ በከተማው በሚገኝ ሜሪዲያን በተባለ ሆቴል አልጋ ያዝን፡፡ የሆቴሉ ባለቤት ከፍተኛ የሆነ የውኃ ችግር እንዳለ አጫወቱን፡፡ ‹‹የቧንቧ ውኃ የሚመጣው አልፎ አልፎ ነው፡፡ ለሆቴሉ የሚያስፈልገውን ውኃ የማስመጣው ራቅ ካለ አካባቢ በመኪና በማስጫን ነው፡፡ ለውኃ ብቻ በወር 35,000 ብር አወጣለሁ፤›› ሲሉ አንገብጋቢ የሆነባቸውን የውኃ ችግር ገለጹልን፡፡ ወደ ሆቴሉ የሄደ ደንበኛ ውኃ ጠፋ ተብሎ ሻወር ሳይወስድ አያድርም፡፡ ያለውን የውኃ ችግር በራሳቸው ጥረት ለመቅረፍ የቻሉ ይመስላል፡፡ እኛም ሻወር ወስደን ነፍስ ዘርተን ማልደን ጉዞ ጀመርን፡፡
ከአዋሽ በተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኘው ገዳማይቱ ከተሰኘችው ከተማም ደረስን፡፡ በገዳማይቱ የተለያዩ ኤሌክትሮኒክሶች፣ ሰልባጅ ልብሶች፣ ዘይት በኮንትሮባንድ ይገባሉ፡፡ አካባቢውን የሚያዘወትሩ ሾፌሮችና መንገደኞች በኮንትሮባንድ ንግድ ለተሰማሩ የገዳማይቱ ነጋዴዎች ዋነኛ ደንበኞች ናቸው፡፡ ዲኮደሮች ከ400 ብር ጀምሮ ይሸጣሉ፡፡ ስልኮችም ርካሽ ናቸው፡፡ አምስት ሊትር የሱፍ ዘይትም በ180 ብር ይገኛል፡፡ እንደተገለጸልን ዘይቱን የሚያስገቡት በጂቡቲ መስመር የሚሠሩ ሾፌሮች ሲሆኑ ከአንድ ዘይት መጠነኛ ትርፍ አትርፈው ገደማይቱ ለሚገኙ የሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴዎች ያስረክቧቸዋል፡፡ ነጋዴዎቹም በከተማው ለሚያልፉ መንገደኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች በ180 ብር ይሸጡታል፡፡ በየመንገዱ የሚሸጡት የሰልባጅ ልብሶችም በርካታ ደንበኞች አሏቸው፡፡
የተለያዩ ልብሶች ከ20 ብር እስከ 100 ብር ድረስ ይሸጣሉ፡፡ ከነጋዴዎቹ መካከል አንደኛው እንደነገረኝ ሥራው በድፍረት የሚሠራ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ብዙ ማትረፍ ይቻላል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ኪሳራም ያጋጥማል፡፡ ‹‹አንድ ቦንዳ ምን ዓይነት ዕቃዎች እንዳሉት አላውቅም፡፡ በደፈናው ነው የምንገዛው፡፡ ቦንዳው ሲፈታ በጥሩ ዋጋ የሚሸጡ ሰልባጆች ይኖሩታል፡፡ ላይኖሩትም ይችላል፤›› ይላል፡፡ ከደረጃ በታች የሆኑ በእሱ አገላለጽ ‹‹የለፉ›› አልባሳት ሲያጋጥሙ ከሚደርስባቸው ኪሳራ ሌላ የሚነጠቁበት ሁኔታ እንዳለ፣ በዚህም ሥራቸው አስተማማኝ ትርፍ የማይገኝበት፣ በድፍረት የሚሠራ መሆኑን ይናገራል፡፡
በኮንትሮባንድ ንግድ ከደመቀችው ገዳማይቱ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው አካባቢ በማጠቃ 02 ቀበሌ የሚገኙ ከ20 በላይ የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶች በጐርፍ ተጥለቅልቀው ነበር፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ቤቶች ከበረንዳቸው ጀምሮ እስከ ዋናው መንገድ ድረስ በጐርፍ ተሞልተዋል፡፡ ሁኔታው ለቀናት የቆየ ሲሆን ነዋሪዎቹ ለመንቀሳቀስ ከመግቢያቸው ጀምሮ እስከ ዋናው መንገድ ድረስ አሸዋ የተሞሉ ማዳበሪያዎችን በመደርደር ለመረማመድ ተገደዋል፡፡ ለቀናት የቆየው ጐርፉ አካባቢው ሙቀታማ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በቀላሉ የትንኝ መራቢያ እንደሚሆን፣ ይህም ነዋሪዎቹን የወባ በሽታ ተጋላጭነት እንደሚጨምር አያጠራጥርም፡፡ ነዋሪዎቹም እርዳታ እንደሚሹ ገልጸዋል፡፡
ወደ ሰመራ መግቢያ አካባቢ የምትገኘው አዳይቱ የተሰኘችው ከተማ ብዙዎች ምሳ ለመብላት ይመርጧታል፡፡ በከተማው የሚገኙ ምግብ ቤቶች የሚያዘጋጁት ጥብስ እጅ ያስቆረጥማል፡፡ የሚያዘጋጁት የፍየልና የበግ ጥብስ ለስላሳ ነው፡፡ ብዙዎች የሥጋውን ልስላሴ ሲገልጹ ‹‹ሽንኩርት ነው›› ይላሉ፡፡ በተለይም ‹‹በከል›› የተባለው የግልገል ፍየሎች ጥብስ ተወዳጅ ነው፡፡ ትሪ ሙሉ የሚቀርበው አንድ ጥብስ ለሦስት ሰዎች ይበቃል፡፡ ብዙዎቹ ለአንድ ጥብስ 100 ብር ያስከፍላሉ፡፡
አርብ ዕለት ሰመራ ስንደርስ የከተማዋ ሙቀት መጠን 43 ዲግሪ ደርሶ ነበር፡፡ ከባድ ነበር፡፡ ሁላችንም ላብ አጥምቆናል፡፡ ቀዝቃዛ ነገር ፍለጋ ወደ አንዱ ምግብ ቤት አመራን፡፡ ምንም እንኳን በአዳራሹ ኮርኒስ ላይ ቬንትሌተሮች መደዳውን የተሰቀሉ ቢሆንም ሙቀቱን ለማቀዝቀዝ አልተቻለም፡፡ በአዳራሹ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ወንዶች ጃፖኒ ለብሰዋል፡፡ ከወገባቸው በላይ ራቁታቸውን የሆኑም አሉ፡፡ ሴቶቹ ሰፋፊ ድርያ ለብሰዋል፡፡ ሽፍን ጫማ መጫማት አይታሰብም፡፡ ሁሉም ሸበጥና ነጠላ ጫማ ነው የተጫሙት፡፡ አስተናጋጁ ያቀረበልን በረዶ የያዘ ውኃ በደቂቃዎች ውስጥ ሞቀ፡፡ ደጋግመን ሚሪንዳና ኮካ ጠጣን፡፡ በመጠኑም ቢሆን ፋታ አገኘን፡፡
የአፋር ክልል ዋና ከተማ በሆነው ሰመራ አልፎ አልፎ ከሚታዩ ፔንሲዮኖችና ሆቴሎች ውጪ ነዋሪዎችን ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ማደሪያዎች ውድ ናቸው፡፡ የዋጋቸው ልዩነትም በየክፍሉ በሚገጠሙ የማቀዝቀዣ መሣሪያዎች የሚወሰን ነው፡፡ ኤሲ የተባለው ማቀዝቀዣ መሣሪያ የተገጠመለት ክፍል ውድ ሲሆን ቬንትሌተር ብቻ ያለው ደግሞ መጠነኛ ቅናሽ አለው፡፡ ክፍሉ ምንም ዓይነት ደረጃ ቢኖረው ኤሲ ከተገጠመለት ከ460 እስከ 700 ድረስ ያስከፍላል፡፡ ባለቬንትሌተሩ ደግሞ ከ200 ብር በላይ ነው፡፡ በከተማው የሚገኙ ሆቴሎች በጣት የሚቆጠሩ በመሆናቸው የተሻለ ማደሪያ ለማግኘት ከባድ ነው፡፡ በቆላ የአየር ንብረት ክፍል በሚመደበው በአፋር ክልል ቴምር ይመረታል፡፡ በክልሉ የሚመረተው ቴምር ከሌላው በተለየ ደረቅ ይላል፡፡ ጣዕሙም ደስ ይላል፡፡ የመልስ ጉዟችን እሑድ ነበር፡፡ ጉዞው አድካሚ ቢሆንም በቆይታዬ በጥቂትም ቢሆን ስለክልሉ ለማወቅ ችያለሁ፡፡