Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየሕዝብ ድጋፍ አንግበው ወደ ሩሲያ ያቀኑት የቱርክ ፕሬዚዳንት

የሕዝብ ድጋፍ አንግበው ወደ ሩሲያ ያቀኑት የቱርክ ፕሬዚዳንት

ቀን:

የቱርክ ፕሬዚዳንት ጣይብ ሬሲፕ ኤርዶጋንን በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ለማስወገድ በሐምሌ 2008 ዓ.ም. በወታደራዊ ክፍሉ የተደረገው ሙከራ ከከሸፈ በኋላ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች መፈንቅለ መንግሥቱን አውግዘው ሰላማዊ ሠልፍ የወጡት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነው፡፡ በፕሬዚዳንት ኤርዶጋን የተጠራውና በአገሪቱ ከሚገኙት ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሁለቱ ማለትም በሪፐብሊካንስ ፒፕልስ ፓርቲና በናሽናል ሙቭመንት ፓርቲ ድጋፍ ያገኘው ሠልፍ፣ የተጠናከረች ቱርክንና የሕዝቡን ለኢዴሞክራሲያዊ አካሄድ አልገዛ ባይነት ያሳየ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

መስዕዋት የሆኑትን ከ200 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ለመዘከርና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማጠናከር በኤርዶጋን በተጠራው ሠልፍ በደቡብ ኢስታንቡል በሚገኘው የባህር ዳርቻ ሲካሄድ፣ ሠልፈኞች የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው፣ ‹‹ኤርዶጋን ከእግዚአብሔር የተሰጠን ስጦታ ነው፡፡ ለመስዋዕትነት እዘዘን፣ የምታዘንን ሁሉ እናደርጋለን፤›› ሲሉ መሰማታቸውን ዘገባው ያስረዳል፡፡

በኢስታንቡል በተካሄደው ሠልፍ አምስት ሚሊዮን ያህል ሲታደሙ በ81 ከተሞችም ሠልፉ ተካሂዷል፡፡ መፈንቅለ መንግሥቱን አቀነባብሯል በማለት ቱርክ የምትኮንናቸውና በአሜሪካ የሚገኙት ፌቱላህ ጉለንን አሜሪካ አሳልፋ ለመስጠት ግዴለሽ መሆኗን፣ አውሮፓውያንም ፕሬዚዳንቱን ከመውቀስ አለመቆጠባቸው ላስቆጣቸው ቱርካውያን ንግግር ያደረጉት ኤርዶጋን፣ ‹‹ከአሁን በኋላ በውስጣችን ያለው ማን እንደሆነ በጥንቃቄ እንመረምራለን፡፡ በወታደሩም ሆነ በሕግ አውጪውና አስፈጻሚው ያለውን እንፈትሻለን፡፡ ያጠፉትን ከበር ውጪ እንወረውራለን፤›› ብለዋል፡፡ ፓርላማው ካፀደቀ የሞት ፍርድ በአገሪቱ እንዲፀና እንደሚተጉም ተናግረዋል፡፡ በቱርክ የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ከተደረገ አንድ ወር የሞላው ሲሆን፣ በእነዚህ ጊዜያት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ሠራተኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ወታደሮች፣ ፖሊሶችና በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየካሄደባቸው ነው፡፡

ከከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ጋር ተያይዞ በአውሮፓውያኑ ወቀሳ የተሰነዘረባቸው ኤርዶጋን፣ ሴራውን የጠነሰሱትና መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት  ጉለን አባላት በደኅንነት አካላት፣ በሕግ አውጪው፣ በመንግሥት ሠራተኞች ውስጥ በመሰግሰግ አገሪቷን ወዳልተፈለገ ብጥብጥ ውስጥ ሊከቷት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ሆኖም 240 ሰዎች መስዋዕት ሆነውና ከ1,400 በላይ ቆስለው መፈንቅለ መንግሥቱን አክሽፈዋል፡፡

በሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጀት (ኔቶ) ከፍተኛ የወታደር ቁጥር ካላቸው አገሮች በሁለተኛ ደረጃ የምትገኘውና የአውሮፓ ኅብረት አባልነትን ለመቀላቀል የምትሻው ቱርክ፣ በምዕራባውያኑ ትችት እየተሰነዘረባት ነው፡፡ ኤርዶጋን የአገሪቱ ፓርላማ ከተቀበለ የአገር ክህደት በሚፈጽሙት ላይ የሞት ፍርድን ለማፅናት ቃል መግባታቸውም ወደ አውሮፓ ኅብረት ለመቀላቀል የሚያደርጉትን ጉዞ ውኃ ይቸልስበታል ተብሏል፡፡ በጀርመን የሊበራል ፍሪ ዴሞክራትስ ፓርቲ መሪ ኤርዶጋንን ከሒትለር ጋር አነፃፅረው መናገራቸውም፣ ምዕራባውያን ኤርዶጋንን በአሉታዊ መነፅር የሚያዩዋቸው መሆኑን የሚያሳይ ነው እየተባለ ነው፡፡

እንደ ሮይተርስ ዘገባ፣ ምዕራባውያን በኤርዶጋን ላይ የሚሰነዝሩት የሰላ ትችት መፈንቅለ መንግሥቱን ተቃውመው በወጡት የሴኪዩላር (የዓለማዊ) ሆነ የናሽናሊስት አመለካከት አራማጆች ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ ምዕራባውያን መፈንቅለ መንግሥቱን ከመቃወም ይልቅ የበለጠ ትኩረት የሰጡት መፈንቅለ መንግሥቱን በሞከሩትና በእስር ላይ በሚገኙት የመብት አጠባበቅ ላይ መሆኑ ያልተገባ ነው ሲሉም፣ የቱርክ ባለሥልጣናት ምዕራባውያንን ኮንነዋል፡፡ መፈንቅለ መንግሥቱ ባይከሽፍ ኖሮ ቱርክ ከማትወጣበት ቀውስ ውስጥ ልትገባ ትችል ነበር ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ በአሜሪካ የሚኖሩ ቱርካውያንም በዋይት ሐውስ ፊት ለፊት በመሰብሰብና የአገራቸውን ባንዲራ በማውለብለብ፣ በኤርዶጋን ላይ የተቃጣውን መፈንቅለ መንግሥት አውግዘዋል፡፡ መፈንቅለ መንግሥቱን አቀነባብረዋል የተባሉት ጉለንም አሜሪካ ለቱርክ አሳልፋ እንድትሰጥ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ኤርዶጋን ስህተቶችን ሠርቷል፡፡ ሆኖም አምባገነን አይደለም፤›› ሲልም በአሜሪካ በመማር ላይ የሚገኝ ቱርካዊ ተናግሯል፡፡

ኤርዶጋን የተቃጣባቸውን በጦር ጄትና በታንክ የታጀበ መፈንቅለ መንግሥት ለማክሸፍ ሲሉ ሕይወታቸውን የሰውትን ለመዘከር፣ በአገሪቱ የዴሞክራሲ አስፈላጊነትን ለማረጋገጥና የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ለማውገዝ በጠሩት ሰላማዊ ሠልፍ ሕዝቡና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከጎናቸው ቆመዋል፡፡ ሠልፉን በጠሩ ማግሥትም ከአሥር ወራት በፊት ጀምሮ የሻከረውን የሩሲያና የቱርክ ግንኙነት መልሶ ለማጠናከር ወደ ሴንት ፒተርስበርግ አቅንተዋል፡፡

ከምዕራባውያን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማቀዝቀዝና ቱርክ ለሶሪያ መንግሥት ወታደራዊ ድጋፍ ሲያደርግ የነበረውን የሩሲያ የጦር ጄት በመምታቷ ምክንያት በሩሲያና በቱርክ መካከል ሰፍኖ የነበረውን ውጥረት ለማርገብ ወደ ሩሲያ ያቀኑት ኤርዶጋን፣ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የሚያደርጉት ውይይት በሁለቱ አገሮች መካከል አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት እንደሚሆን ተገምቷል፡፡ ኤርዶጋን እንደሚሉት ሁለቱ አገሮች አብረው ሊሠሩ የሚችሏቸው ብዙ ሥራዎች አሉ፡፡

የኤርዶጋንና የፑቲን በሴንት ፒተርስበርግ መወያየት ሁለቱ አገሮች ከምዕራባውያን የሚሰነዘርባቸውን ወቀሳ ለመመከት ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ ለረዥም ዓመታት ዘልቆ የቆየው የሁለቱ አገሮች መልካም ግንኙነት ከአሥር ወራት በፊት የሻከረ ቢሆንም፣ መልሰው ለመገንባት ዕድሉን አግኝተዋል፡፡ በተለይ በኤርዶጋን ላይ ተቃጥቶ የነበረው መፈንቅለ መንግሥትና የምዕራባውያኑ ቸልተኝነት ኤርዶጋንን አስቆጥቷል፡፡ በሶሪያ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ከምዕራባውያን በመወገን፣ የሶሪያውን ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ ለመገርሰስና አይኤስን ለማጥፋት ሲሠሩ የከረሙት ኤርጋንዶን፣ በችግሯ ጊዜ የደረሱላቸው ምዕራባውያን ሳይሆኑ በሶሪያ ጉዳይ ሲያወዛግቧቸው የነበሩት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ፑቲን ናቸው፡፡

ኤርዶጋን ከመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ለጥቂት ባመለጡበት ቅፅበት ፑቲን ከጎናቸው በመቆም አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ለኤርዶጋን ቤተሰቦች፣ ሕይወታቸውን ላጡ ወታደሮችና ሲቪሎች በግላቸው ጭምር የሐዘን ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ ለቱርክ መንግሥትም በቅድመ ሁኔታ ያልታጀበ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ይኼም ቱርክ በምዕራባውያን ላይ ፊቷን እንድታዞርና ከሩሲያ ጋር እንድትወግን መንገድ ከፍቷል፡፡

ቱርክ የሩሲያን ጄት መትታ ከጣለች በኋላ የሩሲያ ቱሪስቶች ቱርክ እንዳይገቡ ገደብ ጥላ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ከሩሲያ ጋር ከሚለያያት ጉዳይ ይልቅ አንድ የሚያደርጋት ጉዳይ የሚያይል መሆኑን ተገንዝባለች፡፡ ኤርዶጋንም ጣታቸውን ከሩሲያ ላይ አንስተው በምዕራባውያኑ ላይ ቀስረዋል፡፡

የቱርክ መፈንቅለ መንግሥትን አቀነባብረዋል ብላ ቱርክ የምትወነጅላቸውን ጉለን፣ አሜሪካ አሳልፋ አልሰጥም በማለቷም ኤርዶጋን ተቆጥተዋል፡፡ ‹‹የቱርክን ጠላቶች የሚደግፉትን ቱርክ ወዳጆቼ ብላ አትጠራቸውም፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የመፈንቅለ መንግሥቱን ሙከራ ተከትሎ ኤርዶጋን 60 ሺሕ የመንግሥት ሠራተኞችንና የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮችን ከሥራ አግደዋል፡፡ መፈንቅለ መንግሥቱን አቀነባብረዋል የተባሉ 15 ሺሕ ያህል ደግሞ ዘብጥያ ወርደዋል ሲል ሒዩማን ራይትስ ዎች ማሳወቁን ተከትሎ፣ ምዕራባውያን ቅሬታቸውን ሲገልጹ ሩሲያ በቀጥታ የቆመችው ከኤርዶጋን ጎን ነው፡፡ ኤርዶጋን ወደ ሩሲያ ለማቅናት በሚዘጋጁበት ወቅት መግለጫ የሰጡት የቱርክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማህመት ሲምሴክ፣ ‹‹ሩሲያ በቅርባችን የምትገኝ አስፈላጊ ጎረቤት ብቻ ሳትሆን ስትራቴጂካዊ አጋርም ናት፤›› ብለው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...