‹‹መቅደላ አፋፍ ላይ ያስካካል ፈረሱ፤
የዘጠኝ ንጉሥ ልጅ ዐሥረኛው እሱ፡፡
እንኳን ሴቶችና ወንዶች ቢነግሡ፤
አልጋውን አይለቅም አባ ጤና ኢያሱ፡፡
ላሟ ጥጃ ወልዳ በቀንዷ አስቸገረች፤
ጤና መች ይገኛል ያቺ ላም ካልሞተች፡፡››
ከዳግማዊ ምኒልክ (1836‑1906) ኅልፈት በኋላ መንበረ ሥልጣኑን ለተረከቡት የልጃቸው ልጅ፣ ልጅ ኢያሱ ሚካኤል (1887‑1928) በፈረስ ስማቸው አባ ጤና የተገጠመላቸው ይህ አንጓ የተገኘው፣ በጎበዜ ጣፈጠ በተዘጋጀው ‹‹አባ ጤና ኢያሱ›› መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ በ1980ዎቹ መጨረሻ ታትሞ የነበረው ይህ መጽሐፍ መሰንበቻውን ዳግም ለኅትመት በቅቷል፡፡ ዋጋው 65 ብር ነው፡፡
በሌላ በኩል ከሃያ ሰባት ዓመት በፊት በአሜሪካዋ መዲና ዋሺንግተን ዲሲ በፍሪ ኢትዮጵያ ፕሬስ አማካይነት የታተመው የባቢሌ ቶላ “To Kill a Generation – The Red Terror in Ethiopia” መጽሐፍ ከ23 ዓመት በፊት አውግቸው ተረፈ ‹‹የትውልድ እልቂት! (ቀይ ሽብር በኢትዮጵያ)›› በሚል ርእስ ተርጉሞ መታተሙ ይታወሳል፡፡ መሰንበቻውን ይህ መጽሐፍ ዳግም የኅትመት ብርሃን አይቷል፡፡ ዋጋው 69 ብር ነው፡፡