Sunday, December 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበኢቢሲ ላይ የቀረበው ትረካ የማይታመን ነው

በኢቢሲ ላይ የቀረበው ትረካ የማይታመን ነው

ቀን:

በዕውቀቱ ሲንጅ

ደራሲ ከበደ ሚካኤል ባሳተሙት ታሪክና ምሳሌ መጽሐፍ ‹‹በዓለም ላይ ትልቅ ሥራ ለመሥራት የሚቻለው ሠሪው ሰውና ለመሥራት የተመቸበት ጊዜ እነዚህ ሁለቱ ሲገናኙ ነው፡፡ ትልቁን ሥራ ለመሥራት የሚቻለው ሰው ባልተመቸ ጊዜ ሲፈጠር ሊሠራው የሚችለውን ሥራ ሳይሠራው መቅረት ግድ ይሆንበታል፡፡ ልሥራም ቢል ጊዜው አይደለምና አይሆንለትም፡፡ ትልቁ ሥራ ለመሥራት የተመቸ በሆነበት ጊዜ ደግሞ ሊሠራው የሚችል ሰው ባለመፈጠሩ መልካሙ ጊዜ በከንቱ ያልፋል፡፡ እነዚህ ሁለቱ ተፈላላጊ ነገሮች የሚገናኙት በብዙ ዘመን ጥቂት ጊዜ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አንባቢያን ሐምሌ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በሪፖርተር ጋዜጣ ልናገር በሚለው ዓምድ ሥር ‹‹የኢቢሲ ግዞተኞች›› የሚል መጣጥፍ እንዳነበባችሁ ታሳቢ በማድረግ፣ ከመነሻው እስከ መድረሻ በጽሑፉ ይዘትና በጸሐፊው ’አብዮት’ በቀረቡ ትችቶችና ትዝታዎች ያየነውን ብዥታ ከንፈር ከመምጠጥ ባሻገር በተቻለ ለማጥራት በማለም፣ የሚከተለውን አጭር አስተያየት ለማቅረብ በማሰብ እንዲህ ተዘጋጀ፡፡

ጸሐፊው በኢቢሲ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በሦስት ዘመናት በመከፋፈል ትዝታቸውን ሲያካፍሉን፣ በመጀመሪያው ዘመን በአመራሩ የተደረገው እንቅስቃሴ ሥር ነቀል ለውጥ ነበር ወይ? ለሚለው አይደለም ያሉ ወገኖች ለለውጡ እንደ አደናቃፊ ታይተው በአመራሩ የታዩበትን አግባብ፣ በአመራሩ መካከል የድርጅቱ አካሄድ ትክክል አይደለም ባሉ የሐሳብ መከፋፈል በመፈጠሩና ወደ ሠራተኛው በመውረዱ ቡድንተኝነት መፈጠሩን፣ አምባገነናዊነት መንገሡንና የመሳሰለውን ጠቅሰዋል፡፡ አመራሩ የሚዲያ ዕውቀት እንደሚያንሰው፣ አንዳንዶቹን የቀድሞ አመራር ተልዕኮ የተሰጣቸው ናቸው በአግባቡ አልረዱኝም በሚል በአመራሩ ጀማሪነት የፖለቲካ ሽኩቻ መፈጠሩን፣ በሥልጣን ላይ ያለው የራሱን ቡድን በመመሥረት ሌላውን ማዳከም መሆኑን፣ በአመራሩ መሀል የሐሳብ ልዩነት መስፋት የተሰናባቹ አመራር መብዛት፣ የስፖርት ዶክመንተሪ ሥራ ኃላፊዎች መልቀቃቸውን አትርሱ ብለውናል፡፡ አንዳንዶቹ አመራሮች የሐሳብ ልዩነቱን ይበልጥ በማስፋት አስተያየት በመስጠታቸው የፈሩት ላይቀር ከኃላፊነት ቦታ መነሳታቸውን፣ ኢቢሲ 50ኛ ዓመት በዓሉን የራሱን አመራር ዘመን ብቻ ማወደሱ ተወቅሶ፣ ሕዝቡን ከጊዜያዊ ስቱዲዮ እያለ ከጅማና ከድሬዳዋ የሚያስተላልፈው በዲኤስኤንጂ መሣሪያ በመጠቀም እንጂ ከጊዜያዊ ስቱዲዮ ስላይደለ ኢቢሲ ሕዝብ ማታለሉን፣ የሬዲዮ ጋዜጠኞች በግዞት ወደ ዘነበወርቅ መላካቸው ትኩረት አለመሰጠቱን በጠቅላላው የመልካም አስተዳደር ልሳን ነኝ እያለ የመልካም አስተዳደር ችግር ያለበት፣ ዴሞክራሲ የሌለበት ሚዲያ ሆኖ በመዝለቁ መንግሥት ውሳኔ ይስጥበት ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ለዴሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ ድርሻ ካላቸው ተቋማት የመንግሥት ሚዲያ አንዱ ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተግባራዊ የሚሆነውም በሚዲያ መድረኮች ነው፡፡ ሚዲያው ነፃነቱን ጠብቆ እንዲስፋፋና እንዲዳብር ማድረግ ዋነኛ የመንግሥት አቅጣጫ ሲሆን፣ ይህንኑ ተቋም ለማጠናከርና በነፃነትና በጤናማ አኳኋን እንዲያድግ ለመደገፍ ከፍተኛ ርብርብ መደረጉና መንግሥት ለዋና ዋና ሥራዎች ከሚሰጠው ትኩረት የማይተናነስ ትኩረት በመስጠቱ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ሚዲያው ለኪራይ መሰብሰብ ዓላማ እንዳይውልና የኪራይ ሰብሳቢዎች መፈንጫ እንዳይሆን የሚያስፈልጉ ኢኮኖሚያዊ ዕርምጃዎችን መንግሥት የወሰደው ዘግይቶ በቅርቡ ነው፡፡ ጤነኛ የመንግሥት ሚዲያ ተቋማትን በተለየ ሁኔታ በመደገፍ የሕግ የበላይነትን በጥብቅ እንዲያከብሩ ዋነኛ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተደርገው መወሰዳቸው ሌላው በጎ ጎን ነው፡፡

አንባቢያን እንደሚያውቁት የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ ፀረ ዴሞክራሲያዊ የጠባብነትና የትምክህተኝነት አመለካከቶች አንዱ ሲሆን፣ የመንግሥትን ሥልጣን ተቆጣጥሮ ይህንኑ እንደማትነጥፍ ጥገት እያለቡ መክበር ነው፡፡ ጠባቦችና ትምክህተኞች የሚያነሷቸው ጉዳዮች በሙሉ የመንግሥትን ሥልጣን ተጠቅሞ ኪራይ መሰብሰብ የሚመለከቱ ናቸው፡፡ አንዱ ትልቁ መፈክራቸው የመንግሥት ቦታዎች ለእኛ ብሔር ተወላጆች አልተሰጡም ስለሆነም ተጠቃሚ አልሆንም ነው፡፡ የየብሔሩ ጥገኛ በመንግሥታዊ የኃላፊነት ቦታዎች የሚደለደል ቢሆን ካበረከተው አስተዋጽኦ በላይና ከዚሁ ደመወዝ ውጪ እየተከፈለው የሚጠቀም ሲሆን፣ በዚሁ ላይ የሕዝብ ንብረት መዝረፍ፣ በአካባቢው ያለውን ተቆጣጥሮ ሌላ ብሔር ሳይጋራው ብቻውን መዝረፍ ላይ ከገባ የሚያገኘው የኪራይ ሰብሳቢነት ጥቅም ቀላል እንደማይሆን ይገመታል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ሊናድ የሚችለው በሰዎች ነው፡፡ ሰዎች ደግሞ ሥራቸውን የሚሠሩት እንዲሁ በደመ ነፍስ ሳይሆን አንዳች አመለካከት ይዘው በአመለካከቱ በመመራት ነው፡፡ የሕግ ልዕልና በጥብቅ እንዲከበር በማድረግ ኪራይ ሰብሳቢነትን መናድ ይቻላል፡፡

የሕግ የበላይነት መሠረታዊ የሕግ መርሆ ነው፡፡ ሕዝብ በተስማማባቸው ሕጎች አጥር ውስጥ ታጥሮ መሥራት ጉልበተኛውም ደከም ያለውም መብትና ጥቅሙን የማስጠበቅ አኩል ዕድል እንዲያገኝ የሚያደርግ መሣሪያ ነው፡፡ ሕግ የማያከብረው ጥቂትና አልፎ አልፎ የሚከሰት ነገር እንዲሆን፣ ሲከሰትም የሚያስቀጣና የሚታረም ነገር እንዲሆን ማድረግ የመልካም አስተዳደር አንዱ መርሆ ነው፡፡

ጸሐፊው ‹‹አብዮት›› በጽሑፋቸው እንዳስቀመጡት በአመራር ደረጃ የነበሩ ከሥራቸው የመልቀቅ ሚስጥር ከፍ ሲል እንደገለጽኩት ግለሰቦቹ ካበረከቱት አስተዋጽኦ በላይ አካባቢያቸውን ተቆጣጥረው ሌላው ሳይጋራቸው ለመዝረፍ የሚያስችለው ቀዳዳ ስለተደፈነባቸው ነው የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ ‘ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ እንደማይወጣ’ እያወቁ በኢቢሲ በሥልጣን እርካብ ላይ ያሉቱ ያለ ፈቃድ ደግሞ ተመሳሳይ የግላቸውን ሥራ ሲያከናውኑ ሲደረስባቸው ‘ግመል ሰርቆ አጎንብሶ’ እንደሚባለው ሆነው ከሁለት አንዱን እንዲመርጡ ተጠይቀው በፈቃዳቸው በመልቀቃቸው ነው፡፡ ሁሉንም አንጋፋ ጋዜጠኞች እናከብራለን ሲለዩንም እናዝናለን፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በአዲሱ አመራር ድጋፍና ትብበር ሲጠየቁ ኩራት ስለተሰማቸው በያዙት ቱባ ደመወዝ የሚመጥናቸው ቦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሌሎቹም ቢሆን ኢቢሲን ሳይሆን አገር ከድተው ኮብልለው ወደ አውሮፓ መሄዳቸው ድብቅ አይደለም፡፡ በኢቢሲ መንደር የፈጠረው ጸሐፊው እንደሚሉት ድንጋጤ ሳይሆን አግራሞት ነው፡፡ አመራሩ ሰውን ከተግባሩና ከአመለካከቱ እንጂ እንደ ጨው ቀምሶ የሚለይበት መሣሪያ የለውም፡፡

ስለሆነም እንደ ቀድሞው አሠራር እንደ ልብ መገላበጥ ያልቻሉቱ ጥቂቶቹ በራሳቸው ፈቃድ ለቀዋል፡፡ የዶክመንተሪ ሥራ ክፍልና ስፖርት ክፍል ጋዜጠኞች በተመሳሳይ የሚታይ ነው፡፡ የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ መለያቸው ‘ከአምስት እስከ ስድስት’ የሚል ቅጽል በሠራተኛው የተሰጣቸው አመራር ሥራ የሚገቡና የሚወጡበት ሰዓት ለማመልከት ሲሆን፣ በእርግጥም ተረጋግጧል፡፡ እኝሁ ሴት ከነበሩበት የተነሱት ቀደም ሲል በተለያየ ጊዜ በስብሰባ በሰጡት አስተያየት መነሻ ሳይሆን፣ ከያዙት ሥራ መደብ  ይልቅ ሙሉ ጊዜያቸውን ለኢቢሲ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ በሚችሉበት በሙያቸው በሌላ ሥራ ለመመደብ በማስፈለጉ ነው፡፡

አሁን አሁን በወቅቱ ያልታዩ በርካታ የቀድሞ አመራር የአሠራር ግድፈቶች ዘግይተውም ቢሆን እየሰማን ሲሆን፣ ከአሁኑ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ የባለሙያ ፍልሰት የሚስተዋልበት ጊዜ ነበር፡፡ በሚዲያ እንደተነገረው ኢሬቴድ በፕሮጀክት ሥራዎች የማስፋፋት ሥራው ከፍተኛ ብክነት የተስዋለበት ዘመን ሲሆን፣ ድርጅቱ የሚያሠራጫቸው ፕሮግራሞችም በሕዝቡ ዘንድ በአግባቡ በጥራት ባለመድረሱ ዛሬም ድረስ የዘለቀው የሕዝቡ እሮሮ ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ኢሬቴድ ተጠሪ በሆነበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ በብሮድካስት ባለሥልጣንና በፍርድ ቤት ሳይቀር የተቋሙን ገጽታ የሚያጠቁሩ የግምገማ ውጤቶችና ክሶች የአንባቢያን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ናቸው፡፡ በዋናነት ባዕድና የቤት ልጅ በሚል ሠራተኛውን የሚከፋፍል ሥርዓት ስለነበር አብዛኛው ሠራተኛ ለብዙ ጊዜ የተካበተ ችግር፣ ብሶትና ሰቆቃ እንደ ብል የበላው በእጅጉ የተማረረ ስብስብ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በመጨረሻ የቀድሞው ኤሬቴድ (ኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት) የኪራይ ሰብሳቢነት መፈንጫ ለመሆኑ እንደ ጋንግሪን በሽታ በታዩበት የጎሉ ምልክቶች በሚመለከታቸው ሐኪሞች በመረጋገጡ፣ መፍትሔው ሥር ነቀል ለውጥ በመሆኑ አመራሩን በሌላ መተካቱ አስፈላጊ ነበር፡፡

እነዚህን አሉታዊ ዕዳዎች መረከቡን ታሳቢ ያደረገው አዲሱ አመራር ገና ከመነሻው ሚዲያው ከቀድሞው በተሻለ ነፃነት ለማከናወን የሚያስችል ምኅዳር ለመፍጠር ባዕድና ቤተኛ የሌሉበት፣ ለሁሉም ሠራተኛ እኩል የመሳተፍ ዕድል የሚሰጥና እንደየድርሻቸው እንዲያበረክቱ ዕድል የሚሰጥ፣ ሁሉም ባበረከተው አስተዋጽኦ ልክ ከጥቅሙ ተጋሪ የሚሆንበት ስትራቴጂካዊ መካከለኛና የአጭር ጊዜ ዕቅድ በመንደፍ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

በዕቅድ በክንውንና በአፈጻጸምና በግምገማ በየደረጃው ሠራተኛው የተሳተፈበት ሪፖርት በየጊዜው ቦርድ በተገኘበት ለጠቅላላው ሠራተኛው እየቀረበና እየተገመገመ፣ ስኬቱ እየተሞገሰ በድክመቱ ደግሞ እየተተቸ በአብላጫ ስኬታማ ሥራዎች ማስመዝገብ ችሏል ባይ ነኝ፡፡ ይህ ልምድ ባለፉት የቀድሞ አመራሮች ያላየነውና የሠራተኛውን ተስፋ ያለመለመ መልካም ጅምር ሆኖ ታይቷል፡፡ ሌላው ቢቀር ይህ ተግባር ብቻ በራሱ ሥር ነቀል ለውጥ ነበር ለማለት እደፍራለሁ፡፡ በዓለም ከታወቁ ዝነኛ የሚዲያ ተቋማት ልምድ በመቀመር በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደረገ ጨረታ ተወዳድረው ባሸነፉ የእንግሊዝ ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዕገዛ መዋቅርና የሥራ መደብ ተዘጋጅቶ በማስፀደቅ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

ስለሆነም ያ የቀድሞው ኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የነበሩበት ብርቱ ችግሮች በቅጡ ተጠንተው ያ ባዕድና ቤተኛ የሚባሉ ሠራተኞች የነበሩት ተቋም ፈርሶ ወደ ኮርፖሬሽን ተሸጋግሯል፡፡ ለዚህ አዲስና ከፍተኛ ኃላፊነት የመሸከም ተቋም የሚመጥን ሙያዊና ትምህርት ብቻ ሳይሆን የተስተካከለ አመለካከት ለውጥ ይፈለግ ነበርና ተገቢው ተደርጓል፡፡ በዚህ ፈጣን ለውጥ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን በሚል አንዳንዱ ፍርፋሪ ተቋዳሽ ሠራተኛና ኪራይ ሰብሳቢው ሁሉ በለውጡ ምክንያት ቀድሞ የለመደውን እንዳያጣ መፍራቱ አይደበቅም፡፡ ይህን ለውጥ ሥር-ነቀል አይደለም ብለው እነዚህ ሰዎች በመከራከር የሐሳባቸውን የበላይነት በማሳየት ሌላውን ለማሸማቀቅ ሞክረዋል፡፡ በሰው ልጆች መካከል ሊኖር የሚገባውን የሐሳብና የአመለካከት ልዩነት ከግምት በማግባት እነዚህ ተከራካሪዎችን ወይ በሒደት እንዲረዱትና ለውጡ ለሚፈልገው ሁሉ ተባባሪ እንዲሆኑ፣ ያልተመቸው ደግሞ አማራጩ ከድርጅቱ በራሳቸው ፈቃድ ማግለል እንደሚችሉ በአመራሩ አስተያየት መሰጠቱ ምን ክፋት አለው? ጸሐፊው ‹‹አብነት›› ግን ተሳልቀዋል፡፡ በዋናነት ሊመልሱት የሚገባው እነዚህን እንቅልፍ የነሷቸው ጉዳዮች በጊዜው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ሌሎች መፍትሔ እንዲፈለግ እንደ ጋዜጠኛ ምን ዕርምጃ ወስደዋል?

በጸሐፊ አብዮት የቀረቡትም ሐሳቦች ስለአዲሱ አመራር አሉታዊ ብቻ በመሰሉ ጉዳዮች በማተኮር ጊዜ ማጥፋታቸው በሥነ ልቦነ ባለሙያዎች አስተያየት ለከፋ ድብርት የመጋለጥ ምልክት ሊሆን ስለሚችል ጥላቻውን የሚለውጡበትን መንገድ እንዲያስቡ ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ያነሷቸው ሐሳቦች በንፅፅር ያለመቅረቡና ከስታንዳርድ ምን ያህል ወደፊት ወይ ወደኋላ እንደራቀ ስለማያሳይ ለማወዳደር የሚቸግር ነው፡፡ የሆነውስ ሆነና ጽሑፉን ሲዘጉ ማሳረጊያው አንባቢያንን የዘለፉበት መንገድ አነጋጋሪ ጉዳይ መስሎ ይታየኛል፡፡ ጸሐፊው ’አብዮት ’ጽሑፍዎትን በሪፖርተር ጋዜጣ የሚያነብ ‘ደደብ ነው’ ብለው መደምደሚያ የመስጠትዎ ቅኔው አልገባኝም፡፡

ይልቁንስ አሁን ያለው አመራር መገለጫ በመወያየት ሁሉም በአሸናፊነት ሊወጣ የሚችልበትን ሥልት ነው የተከተለው ብዬ የማስበው፡፡ ችግሮችን ለመፍታት ሰዎችን እንደ አጋር እንጂ እንደ ተቀናቃኝ አልተመለከተም፡፡ ሐሳብ መካፈል፣ አማራጭ ማየት፣ ጥቅምና ጉዳቱን መመዘን እንጂ አቋም ይዞ መከላከልና ተቀናቃኝ ለማጥቃት ጊዜ የነበረው አይመስለኝም፡፡ ሌላውን የሚያዳምጠው ያላያቸውን ሐሳቦች የማየት ዕድል ለማግኘት ነበር፡፡ በአንፃሩ የሠራውን ለማፍረስ ብርቱ ጥረት ተደርጓል፡፡ የስትራቴጂካዊ ዕቅድ ለማውጣት ጨረታ ሲወጣ በሐሰተኛ ክስ ጨረታው በስድስት ወራት እንዲዘገይ በማስድረግ ለጊዜውም ቢሆን ተሳክቶላቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አመራር መወቀስ ካለበት ሊወቀስ የሚገባው ከነስ£ሩ በመረጃ የያዛቸውን የቀድሞ አመራሮች በዝምታ ማለፉ ትልቅ ውለታ ውሎ ይሆን? ለነገሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኪራይ ሰብሳቢነታቸው በኦዲት የተረጋጡትንና ጥፋት ላይ ያገኛቸውን የቀድሞ አመራሮች ለቀድሞ ለበረሃ ትግል ውለታቸው በማሰብ በዝምታ አልፎ የለምን?

ወደ ጉዳያችን ስንመጣ በየትኛውም መሥፈርት ብናየው ከሥራ የለቀቁትም ሆኑ ሌሎቹ ለአዳዲስ ሐሳቦች ዓይናቸውን የዘጉ፣ በክርክር የራሳቸውን የበላይነትና የሌላውን ደካማነት በመፈለግ የሚደክሙ ነበሩ፡፡ ሌላውን የሚያዳምጡት ደካማ ጎኑን በመፈለግ ለማጥቃት ነበር፡፡ በሐሳብ መለየትን የማይደግፉት የተለየውን ሐሳብ ባለማክበር ጭምር ነበር፡፡ ሙያችን ጥበብ ነው በሚል ብሂል ሥራችንን በቼክ ሊስት ለምን አቅዱ ትሉናላችሁ? ለምንስ የምንወጣና የምንገባበትን ጊዜ ቁጥጥር ይደረግብናል? ሰዓት ፊርማ አሻራ አንሰጥም በቼክ ሊስት አናቅድም ማለት ሄዶ ሄዶ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባሮች ናቸው፡፡ ይልቁንስ እንደ መጨረሻ መጨረሻ የለውጥ እንቅስቃሴውን በማያደናቅፍ መንገድ ኪራያቸውን የሚሰበስቡበትን ዘዴ ቢያስቡ ለሌላው ሥራ እንዳይበላሽ በመጠንቀቅ መቻቻል ማለት ይኼ ነው፡፡

እርግጥ ነው የቡድንተኝነት፣ ጠባብነት፣ አምባገነንት፣ የሐሳብ ልዩነቶች ዛሬም ድረስ በጉልህ መዝለቃቸው የሚስተዋሉ ክስተቶች ሲሆን፣ ወደፊት ትግል የሚጠይቁ አጀንዳዎች ናቸው፡፡ ቀደም ሲል እንዳልነው መልካም አስተዳደር የሕግ የበላይነት ምሰሶው ነው ስንል ሕግ የማያከብረው ጥቂትና አልፎ አልፎ የሚከሰት ነገር እንዲሆን፣ ሲከሰትም የሚያስቀጣና የሚታረም ነገር ማድረግ አሁን ያለው አመራር ዓብይ ጉዳይ እንደሚያደርግ ተስፋ ይደረጋል፡፡ ሌላው የኢቢሲ 50ኛ ዓመት የተሳካ ሲሆን፣ ከቀድሞ አመራሮችና ሠራተኞች ፈቃደኛ የሆኑቱ ለዚህ ተብሎ በተቋቋመው ኮሚቴው በማፈላለግ የተገኙቱ ሠራተኞች በእንግድነት ተጠርተው ሽልማት የተሰጣቸው ነበሩ፡፡ የቀድሞ አመራሮች አለመገኘት ምክንያት አይታወቅም፡፡ በዝግጅቱ ግን ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ተገኝቶበታል፡፡

ጸሐፊው የሬዲዮ ዝግጅትና ሥርጭት ሠራተኞቹ ጭምር ወደ ቀድሞው ቦታው ዘነበወርቅ መዛወር እንደ ግዞት በመቁጠር ዋና ርዕስ ማድረጋቸው፣ ኢቢሲ በመልካም አስተዳደር ዕጦት ስቃይ ውስጥ ነው ብለው የመልካም አስተዳደር ልሳን መሆኑ ደግሞ አስገርሟቸው፣ በዚህና በሌሎች ክሶቻቸው መንግሥት ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡ እውነታው በሬዲዮ ዜናና ፕሮግራም ዝግጅት የተሰማሩ ባለሙያ ጋዜጠኞች ወደ ቀድሞ ዘነበወርቅ የመሄዱ አስፈላጊነት ላይ ጥናትና ውይይት አድርገው ባቀረቡት የውሳኔ ሐሳብ መሠረት በበላይ አመራር ተወስኖ ነው፡፡ የዚህ ዓላማ የሬዲዮ ጋዜጠኛውን በማግለል ሳይሆን በቀድሞ አመራር ትኩረት ተነፍጎት ወደኋላ የቀረውን ሬዲዮ ጣቢያ ለሥራው ትኩረት በመስጠት እንዲያንሠራራ በማሰብ ነው፡፡ እስከማውቀው የተመደቡት ሠራተኞች በፈቃዳቸው የመረጡት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ መንግሥት ቦርድ ያቋቋመው የተቋሙን ስትራቴጂካዊ ችግሮች ተረድቶ የበኩሉን ለማድረግ ነው፡፡ ከፍ ሲል ያቀረቧቸውን ጉዳዮች ቦርዱ በተለያየ ጊዜ ያያቸው አሉ፣ ሆኖም ለምክር ቤት ቀርቦ በቅሬታ ወይም በትችት የቀረበበትን አናስታውስም፡፡

በአጠቃላይ የኢቢሲ ጉዞ እንደ አንድ ጋራ ፕሮጀክት ግንባታና ዕድገት ጉዞ ልናየው እንችላለን፡፡ አሁን የሚዲያው አባል የሆነው በአንድ ወቅት ታላቁ መሪ እንዳሉት ወደንና የጋራ ፕሮጀክቱ ተዋናይ መሆን አማሎን ነው፡፡ ሁላችንም የፕሮጀክቱ መሥራች አባላት ቤተኞች ነን፡፡ ሬዲዮ ሆነ ቴሌቪዥን በሙሉ ትኩረታችን ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ከእንግዲህ በተለየ ሁኔታ ቤተኛ ሆኖ ለመቀጠል የሚከጅል ወይም በባይተዋርነት ውጭ ውጭ ማየት የሚከጅል የመኖር አጋጣሚ ውስን ነው፡፡ ሁሉም ለጋራ ፕሮጀክቱ አስተዋጽኦ የማድረግ እኩል ዕድል አለው፡፡ ይህ ሚዲያ ጤናማ ሆኖ የበለጠ ለመጠናከር የመንግሥት ከጎን መሠለፍ የበለጠ ያበረታታናል፡፡

ሕዝቡ እንደ ዋነኛ የመረጃና የፖሊሲ ትንታኔና ክርክር ምንጭ የሚወሰድበት ደረጃ በፍጥነት ይደርሳል፡፡ ፕሮግራሞቹ በጥራታቸው፣ በማራኪነታቸውና በሥነ ምግባር ደንብ አክባሪነታቸው በምሳሌነት የሚጠቀሱ እንዲሆን ተስፋ ይደረጋል፡፡ አለመታደል ሆኖ የአመራሮች ገድል መልካም ሆነው ሳለ አንዳንዶቹ የወደዱትን እንደ መልዓክ፣ የጠሉትን ደግሞ እንደ ጭራቅ ሲያደርጉ የግለሰቦች ሰብዕና በመሀል ቤት ጠፍቶ መልካምም ይሁን እኩይ ሥራው ለቀጣዩ መማሪያ ሳይሆን ማየቱ ያሳዝናል፡፡ መሪና አመራር ግለሰቦች የሚመጡና የሚሄዱ ኃላፊዎች ሲሆኑ በተነፃፃሪ ተቋም ዘላቂ ነው፡፡ ስለዚህ ከመጀመሪያው ሥራና ተግባራችን እንዲያምር ከሆነ የማንንም አስተዋጽኦ የማጣጣልና የማኮሰስ ዓላማ ተገቢ አይደለም፡፡

ከፍ ሲል የዘረዘርኳቸው ጸሐፊ ‹‹አብዮት›› ያቀረቡልን ትዝታዎች እንደተረዳሁት በስማ በለው ያወቁት እንጂ ባላረጋገጡት በርካታ ጉዳዮች እስካሁን እንደ ትውስታ መያዝ ስለማይገባቸው ለጤናቸው ሲሉ ቢረሱት እመክራለሁ፡፡ በአብዛኛው አሉ እያሉ ስለተረኩልን ብዙዎቹ ትረካዎቻቸው ተዓማኒነታቸው አጠራጣሪ በመሆናቸው ከስም ማጥፋት ያልተለየ ውንጀላ መስሎ ይታየኛል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

                                                                                                                                                                       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...