Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‹የዳኛ ያለህ አትሉም ወይ?›

እነሆ መንገድ። ከቦሌ ድልድይ ወደ ገርጂ ልንጓዝ ነው። ሐምሌ የቋጠረውን የዳመነ ብሶት ሳይጨርስ ነሐሴ ዘልቀናል። ወራትን እንደ ፌርማታ ብናስብ መስከረም ተሳፍረን የጀመርነው ጉዞ መዳረሻ ላይ መሆናችን ነው። ምንም እንኳ የባከነች ጳጉሜ ብትጠብቀን፣ ዓመት ሙሉ የባከኑ ህልሞችና ተስፋዎች መፈቻ የምትሆን አይመስልም፡፡ ስለዚህ ያለቀለት የመሰለን ነገር ሁሉ እንደገና ይጀምራል፡፡ የመለስናቸው ጥያቄዎቻችን ዳግም መጠየቅ ጀምረዋል። የሻረልን ቁስል ሲያመረቅዝ እያየን ነው። ጎዳናው እንደ ልማዱ ወስዶ ወስዶ መንታ መንገድ ላይ ገትሮናል። ወደፊት ልቀጥል? ወይስ ወደ ኋላ ልመለስ? ባዩ በዝቷል። የምንራመድ እንምሰል እንጂ የቆምን ብዙ ነን፡፡ የምንሸራተተው እልፍ ነን፡፡ የሚያግደን እርከን ያጣነውን ቁልቁለቱ ይቁጠረን፡፡ ያለስሙ ስም ያለቦታው ሹመት ያለግብሩ ሞገስ የሚቸረው በዝቷል፡፡ ይህን እያዩ አንዳንድ የዕድሜ ባለፀጎች ከንፈር ሲመጡ ተሞክሮውን ገና በሙከራ እያዳበረ የሚቸኩለው ወጣት፣ ትርፍና ኪሳራውን ማሰብም ማስላትም የሰለቸው ይመስላል።

ግርግር ያመቸው ቀማኛ ደግሞ ያው እንደለመደው ኪስ እያወለቀ፣ እዚያ ሲጨፈር እያጫፈረ ወዲያ ሲለቀስ እያቆለቆለ በሁለት ቢለዋ የዋሆችን ያርዳል። መልሶ ደግሞ እሱው ታራጆችን አራጅ፣ ምስኪኖችን ቀማኞች በሚል ውንጀላ ከአገር ከቀዬያቸው ያሰድዳል። ይህን ሁሉ የሚያይ ታዛቢ ወዳጅ የሰማውን ሊያሰማ፣ ያየውን ሊያሳይ መረብ ለመረብ ‹በላይክና ታግ› አብዶ ያሳብዳል። መንግሥት እንደ መንግሥት እንዲሉ መንግሥታውያን፣ የከፋው ቀን መረብ ሲቀድ ደስ ያለው ቀን ደግሞ መረብ ሲሰፋ ይሰነብታል። የሕይወት እሽክርክሪት እንዲህ በነገር አክራሪ ተወጥራ ስትደምቅ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የኳስ ድሪያ ቀለባቸው እስኪሰፈር የተቁነጠነጡ ሪዮ ኦሊምፒክ ላይ አፍጥጠዋል። ብቻ በየመስኩ እንደየስሜቱ እንደየግብሩና ቅዥቱ ሁሉም የሚያፈጥበት ላይ ነው። ይኼው እኛም ተሳፋሪው ላይ አፍጠናል። ዘመኑ በቃ የመፋጠጥ ሆኖ ሊቀር ነው?

“እኔ ምለው? . . . ” ይላል ጋቢና የተሰየመ ወጣት። አምባር መዋያው ላይ ከጥጥ የተሠራ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሹራብ አጥልቋል። “አሁን ‘ኦሊምፒክ’ ስናሸንፍ የትኛው ባንዲራ ነው የሚውለበለበው?” ሲል፣ “ኧረ አንተ ሰውዬ ሠርተን እንኑርበት እባክህ። ተቃውሞ ማሰማት ከፈለግክ ‘ፌስቡክ’ ሳይዘጋ ተቃውሞህን አሰማ፤” አለው ሾፌሩ ኮስተር ብሎ። “ምን ዓይነት ጥያቄ ነው? ስንት ባንዲራ ነው ያለን? ያው አንዱ ባንዲራችን ነዋ፤” ይለዋል በስተቀኙ የተሰየመ ወዳጁ። “ተቃውሞስ የለኝም። እንዲያው ሰሞኑን ቴለቪዥኑ ውስጥ ሁለት ዓይነት ባንዲራ እያስተዋልኩ ስለሆነ ግራ ገብቶኛል፤” አለ ኩምሽሽ ብሎ። “ጉድ ነው! አሁን እስኪ ማሸነፋችንን ምን ያህል እርግጠኛ ብትሆን ነው የሚውለበለበው የባንዲራ ዓይነት ያሳሰበህ?” አሉት ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ አዛውንት።

“እንዴት ጋሼ? ድል ምን ጊዜም የእኛ ሆኖ ነው የኖረው። ወደፊትም የእኛ ነው። ኦሊምፒክ እኮ ነው፤” ሲላቸው ጠምዘዝ ብሎ፣ “አቤት! አቤት! ተናግረህ ሞተሃል ጃል። ዝም ብለህ ሁላችንንም የሚያስማማን ሐሳብ አትናገርም? ከዚያ የተረፈውን ለራስህ መያዝ ነው። ሚስጥሩ ሁሉ ያለው አበበ እግር ላይ ነው። ከፈለግክ ልንገርህ። አየህ ያኔ በሮም ኦሊምፒክ አበበ ብቻው በባዶ እግሩ ሮጦ ሲያሸንፍ እንቅፋት አልመታውም። እሾህ አልወጋውም። ቢወጋውም አልተሰማውም። ለምን በለኝ? ለምንማ የእሱ ባዶ እግር ከብዙ ኢትዮጵያውያን ባዶ እግር ጋር ነበር። ሕዝብ ይዞ ነው የሮጠው። ብቻውን አሮጠም። ታዲያ የአቤ መጨረሻ ለምን አላማረም ብለህ ጠይቅ? መኪና መንዳቱ? አይደለም። ምክንያቱ ብቻውን መንዳቱ ነው። ዓይን በላው አየህ። ምንም ነገር ሥራ ግን አደራ ብቻህን አትሁን። ዘንድሮ ብዙ ሯጮች ተውሳክ የሆነባቸው ይኼው ነው። ከዓይን ያውጣህ። መቼም ሯጭ ስል ማንን እንደሆነ ገብቶሃል?” ሲሉት ተሳፋሪው በሳቅም በጉርምርምታም አጀባቸው። አጀብ ነው ዘንድሮ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላችን ትርፍ ሊጭን ታክሲዋን አስቆመ። እንዳጋጣሚ ሆኖ ታክሲያችንን ያስቆማት መንገደኛ ዓይን የሚገባ የአካል ግዝፈት አለው። ወያላው የት ጋ እንደሚያሸጋሽገው ቸገረው። ድንገት ፈካ ብሎ፣ “እዚያ ጥግ ጋ የተቀመጥከው አዎ አንተ ና እዚህ ጋ ተቀመጥ። እሱ በአንተ ቦታ ይቀመጣል፤” አለ። “ምን?” ቀጭን ትዕዛዝ የተሰጠው ከጎኔ ያለ ተሳፋሪ የሰማውን ማመን አቃታው። “እኮ ለምን?” ጠየቀ ወያላው ላይ አፍጥጦ። “አይበቃውምማ ቦታው። አንተ ቀጠን ስለምትል (ሰውዬው እጅግ የተጎሳቆለ ሰው ነው) እና እዚህ ጋ ትቀመጣለህ (ሞተሩን እየጠቆመ)፤›› አለ ወያላው ታናሽ ወንድሙን ለእንግዳ ቦታ እንደሚያስለቅቅ ታላቅ ወንድም። “ኧረ ምን ዓይነት ጊዜ ላይ ነው የደረስነው? በከሳ በወፈረ ሆነ ደግሞ?” ይላል ቀልድ መስሎት። “አቦ አፍጥነው ልማት ላይ ነን፤” ወያላው አፉን መክፈት ጀመረ። ከእሱ ብሶ ያ የግብፅን ፒራሚድ የሚያህል ሰውዬ፣ “ምናለበት ብትተባበረኝ?” እያለ ለወያላው ይደረባል።

“የምርህን ነው እንዴ ፍሬንድ! እኔ እኮ ቀልዱን መስሎኛል። ትንሽ የሰው መብት፣ ክብር፣ ምናምን ሳታይ ነው ያደግከው?” ብሎ መካከለኛ ረድፍ ላይ የተሰየመ ባለቱታ ጃኬት መንደድ ሲጀምር አጠገቡ የተቀመጡ ወይዘሮ፣ “ማንን አይቶ ልጄ? ማንን አይቶ?” እያሉ ከንፈር መጠጡ። “እንዴ? እንዴት ነው የዚህ አገር ነገር እንዲህ ምስቅልቅሉ የወጣው? ቆይ የሥነ ዜጋና የሥነ ምግባር ትምህርት የተጀመረው ለመቼ ፍሬ እንዲያፈራ ነው?” ብላ መጨረሻ ወንበር የተሰየመች ስትጠይቅ፣ “አሁን እስኪ የአንድ ወያላ የመብት ጥሰትና የመንግሥት የትምህርት ፖሊሲ ውድቀት በምን ይገናኙና ነው?” ብሎ የምሩን ይሁን የቀልዱን እቅፍ አድርጎ የሸጎጣት የከንፈር ወዳጇ ሲናገር ሰማነው። ‘ዕድሜ ፈጣሪ ላበጀው ጆሮዬ የማልሰማው የለም!’ ያለችው ቀጭኔ ሞታ ይሆን?!

ከብዙ ውዝግብና ጭቅጭቅ በኋላ ታክሲያችን ጉዞዋን ቀጥላ ተሳፋሪው ድምፁን አጥፍቶ ለየብቻው ሲብሰለሰል ታየ። ቆያይተን አንዱ አፈነዳው። “እኔ ምለው ምንድነው እንዲህ የሚፈታተነን ጭንቀትና ውጥረት መነሻው?” ከማለቱ፣ “የምን ውጥረት?” አለችው ከጎኑ። መጨረሻው ረድፍ ላይ ይኼ ጥያቄ ተነስቶ ጥያቄው በጥያቄ ሲመለስ የገረማቸው አዛውንት፣ “አይ አንቺ ዓለም?” ብለው ረዥም ሳቅ ሳቁ። “ምነው አባት? ምን የሚያስቅ ተገኘ?” ሲላቸው ወያላው፣ “ምነው ለሳቅም ቀረጥ ክፈሉ ልትለን ነው? ታሪፍ መጠየቅ አማረህ? ‘እስኪ በዓይኔ ልሳቅ ጥርሴስ ልማዱ ነው’ አሉ፤” ብለው ቆዘሙ። “በአንዴ ከሳቅ ወደ ሐዘን?” ስትላቸው ደግሞ ከጎናቸው የተሰየመች ወጣት፣ “ምን ላድርግ ልጄ አንዱን ሲከፋው አንደኛው እስከነ አካቴው የወንድሙን መከፋት አያውቅለትም፡፡ የአንዱ እንባ ለሌላው ፌዝ ነው። መወጣጫ ነው። በሽታ ሳያዳክመኝ የዚህች ከንቱ ዓለም ገጽታ ብቻ እንጃ ሳይገለኝም አይቀር፤” ከማለታቸው፣ “ሰላማዊ ሠልፍ ወጥቶ ከመሞት አይሻልም?” አላቸው መጨረሻ ወንበር።

“ጎዳና ላይ አልሳካ ሲላችሁ ታክሲ ውስጥ ጀመራችሁ? ምናለበት በሰላም ብንኖርበት?” ወይዘሮዋ ተበሳጩ። ‹‹ታክሲና ሠልፍ ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው የተነጣጠሉት?” ይላል አጠገቤ የተቀመጠው። ወያላው ይኼን ጊዜ ጣልቃ ገብቶ፣ “አንዴ ከአፍታ ማስታወቂያ በኋላ ትመለሱበታላችሁ፡፡ ሒሳብ ዱብ ዱብ በሉ፤” እያለ ያላግጥ ጀመር። “አስቀድመህ ሥራህን አትሠራም ነበር? ልናራግፍ ስንል ሒሳብ ትላለህ?”  ሾፌሩ በድንገት ቢጮህበት ወያላው በለዘብታ፣ “በጊዜ ተሰበሰበ ከመሸ፣ ሒሳብ ሒሳብ ነው። እኔ ለማወራርደው አንተን ምን አንገበገበህ?” ብሎ ሽቅብ መለሰለት። አቤት የመገለማመጥ ሒሳብ የተወራረደ ቀን።

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። በቀኝና በግራ ሁለት ተቃራኒ አስተሳሰቦች የተፋጠጡ ይመስላሉ። አንድ ተሳፋሪ ስልኩ ይደወልለታል። አንስቶ፣ “ደግ ደጉን ብቻ እናውራ እሺ። ደግሞ በኋላ ጣጣ እንዳታመጣብኝ፤” ሲል እንሰማዋለን። ይኼን ዓይቶ ሌላው፣ “እነሱማ እንደ ጋርዮሽ ዘመን ይድረስ ለምወድህ ይድረስ ለማከብርሽ እያልን ደብዳቤ እንድጽፍላቸው ነው የሚፈልጉት፤” ይላል። “ስለማን ነው የምናወራው?” ብላ ስትጠይቅ አንዷ፣ “በአደባባይ ዓለም እያያቸው ጠልፈው እንደሚያዳምጡን በኩራት ስለሚያወሩ ሰዎች ነዋ፤” ይላታል። “ኧረ እባካችሁ ነገር አታጋኑ። ትንሿን ነገር እያሾርን ስንቀባበላት የት እንደምትደርስ ተመልከቱ እስኪ?” ሲሉ ወይዘሮዋ፣ “እኛ መድረሻ ያጣነው ሳናስጨንቀዎ የምናነሳ የምንጥለው ያስጨንቅዎታል? እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ፤” ብሎ አንድ ወጣት ተሳፋሪ አማተበ።

“ምናለበት ስለብሔራዊ መግባባት ብናወራ? በፍሬ ፈርስኪ እንዲችው በሄድንበት ጊዜ እየገደልን ለውጥ ይመጣል እንዴ?” ሲል ከጎኔ፣ “እንዴ እስካሁን ለውጥ አልመጣም?” ይላል ሌላው አጋናኝ። “ለውጥማ ነበረ የሚለወጥ ጠፋ እንጂ። ምናለበት ግን እናንተ ልጆች በሰከነ አዕምሯችሁ ብታስቡ። አገር እንዲህ እንደ ቀልድ ፈርሳ እንደ ቀልድ የምትደራጅ መጋዘን መሰለቻችሁ? ደግሞስ መገንባት እንጂ መናድ ቀላል እንደሆነ ጠፍቷችሁ ነው? ሳታዩት ቀርታችሁ ነው?” እያሉ ሲቀጥሉ ከወጣቶቹ አንዱ፣ ‹‹ምን አድርጉ ነው የሚሉን አባት?›› ብሎ አቋረጣቸው። “እኔማ የምላችሁ (አትሰሙም እንጂ ብትሰሙኝ) ስከኑ ነው። እርጉ ነው። የረጋ ወተት ቅቤ አለው ነው የምላችሁ። አለበለዚያ እንዲሁ ተዋክቦ በማዋከብ ብቻ መብት አታስከብሩም። ሰማኸኝ? . . .” ብለው ሲጠይቁት ወያላው “መጨረሻ” ብሎ ገላገለን። ግን የቱ ይቀላል? መገንባት ወይስ መናድ? ይኼን ጊዜ ነው ‹የዳኛ ያለህ አትሉም ወይ?› መባል ያለበት፡፡ መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት