Sunday, January 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለግጭቶች የሚሰጠው ምላሽ ተዓማኒነት የሚያገኘው በዴሞክራሲያዊና በሕጋዊ መንገድ ብቻ ነው!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እያገረሸ ያለው ግጭት መላ አገሪቱን ላለመዳረሱ ምንም ዓይነት ዋስትና የለም፡፡ በተለይ በሁለቱ ክልሎች ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚስተዋሉት የተቃውሞ ሠልፎችና ምላሽ አሰጣጦች ሰላማዊውን ድባብ እየረበሹት ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶት ለትርምስና ለበለጠ ዕልቂት የሚጋብዙ ሥጋቶች አንዣበዋል፡፡ ጥያቄ አለን የሚሉ ወገኖች በሰላማዊ ሠልፍ ምን እንደሚፈልጉ የመግለጽ ነፃነት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ የሠፈረ ቢሆንም፣ እየተከናወኑ ያሉ የተቃውሞ ሠልፎች የግጭት ሰለባ እየሆኑ ዜጎች እየሞቱ ነው፡፡ የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው ነው፡፡ ንብረት እየወደመ ነው፡፡ ችግሮች መፍትሔ በማጣታቸው የግጭት አድማሱ እየሰፋ ከመምጣቱም በላይ፣ ለአገሪቱ ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው፡፡

አገርን የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት እያጋጠሙ ላሉ ችግሮች መፍትሔ ማምጣት ቢጠበቅበትም፣ ምንም ጠብ የሚል ነገር በመጥፋቱ የግጭት ወሬዎችን በተደጋጋሚ መስማት የተለመደ ክስተት እየሆነ ነው፡፡ መንግሥት ውስጡን ከመመልከት ይልቅ ችግሮችን ወደ ውጭ የመግፋት አባዜ ውስጥ በመግባቱ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀምጦ በመነጋገር መፍትሔ ለማስገኘት አልተቻለም፡፡ ይልቁንም በመካሄድ ላይ ያሉትን የተቃውሞ ሠልፎች ሕገወጥና ባለቤት አልባ ከማድረጉም በላይ፣ ከበስተጀርባቸው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ ያሰፈሰፉ በውጭ ኃይሎች የሚገፉ ወገኖች መኖራቸውን በተደጋጋሚ እየገለጸ ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በአማራ ክልልም ሆነ በኦሮሚያ ክልል የገዥው ፓርቲ አባላት ሳይቀሩ ከተቃውሞ ሠልፎች ጀርባ እንዳሉ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ መንግሥት የራሱን ጓዳ ሳይፈትሽና ችግሩን በሚገባ ሳይመረምር ጣቶቹን ወደ ውጭ መቀሰሩ አስተማማኝ መፍትሔ እንዳይገኝ የራሱን ሚና እየተጫወተ ነው፡፡

በተደጋጋሚ እንደምንለው እዚህ አገር ውስጥ በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው፣ እንዲሁም በማኅበራዊው ትስስር ውስጥ ለቁጥር የሚያታክቱ በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡ የእነዚህ ጥያቄዎች መነሻ ደግሞ ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝብ ጥያቄ አለኝ ሲል የሚያዳምጠው ከሌለ የመጨረሻ ውጤቱ ብጥብጥ ነው፡፡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ መጓደልና በሙስና ምክንያት ሕዝቡ እየደረሰበት ያለውን በደል የሚያቀርብበት መጥፋቱ እንግዳ አይደለም፡፡ እነዚህ ችግሮች ሕዝብን በማስመረራቸው የተነሳ ለሥርዓቱ ጭምር አደጋ ናቸው ተብሎ ከወራት በፊት በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀር ተወትውቷል፡፡ በመንግሥትም ሆነ በገዥው ፓርቲ ውስጥ በተሰገሰጉ ኃይሎች ሳቢያ ለአገር ጠንቅ የሆኑ ችግሮች የመፍተሔ ያለህ ሲባልላቸው እንዳልነበር፣ ሕዝብ ጥያቄ ይዞ አደባባይ ሲወጣ አለማዳመጥ ምን የሚሉት በሽታ ነው? መንግሥት ወደ ውጭ የሚገፋውን ድርቅና ትቶ ከሕዝብ ጋር መነጋገር አለበት፡፡ ለተነሱት ጥያቄዎች ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ ምላሽ ያስፈልጋል፡፡

በመንግሥት በኩል እየተሰጠ ያለው ምላሽ ሕዝብን ለማሳመን መቻሉና አለመቻሉ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ ምላሽ አሰጣጡ ሕዝብን ለማሳመን መቻልና አለመቻሉ በረከትና እርግማን አለው፡፡ ምላሽ አሰጣጡ የሕዝብን ተቀባይነት ለማግኘት ከበቃ በረከት ነው፡፡ የሚያስከትለው መዘዝ ይነቀላል፡፡ አለበለዚያ እርግማን ሆኖ መዘዝ ይተክላል፡፡ ምላሽን ተዓማኒ የማድረግ ጉዳይ ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ አፈታትን የማከናወን ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ቁርጠኝነትን የሚጠይቀው ትልቁ ጉዳይ ያለው እዚህ ውስጥ ነው፡፡ ጥያቄ ማንሳትና መቃወምን ለውጭ ጠላትና ለአሸባሪ መሣሪያ እያደረጉ መተርጎም፣ መወንጀልና ማሳደድ ዴሞክራሲያዊ ድባብ ከመፍጠር ጋር አይጣጣምም፡፡ ሕዝብና መንግሥትን ሆድና ጀርባ ከሚያደርጉ ችግሮች መካከል አንደኛው፣ መንግሥት ለተፈጠሩ ችግሮች የሚሰጠው ትርጉምና ሕዝብ ዘንድ ያለው እውነታ አለመጣጣም ነው፡፡

የኃይል ዕርምጃዎችን መውሰድና ጥያቄዎችንና ቅያሜዎችን ሳይሸማቀቁ ጆሮ እንዲያገኙ ማድረግ በፍፁም አይጎዳኙም፡፡ ይልቁንም ይጋጫሉ፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳ ውስጥ ያሉት ጥያቄዎች በጣም የበዙ ናቸው፡፡ ከሰብዓዊና ከዴሞክራሲያዊ መብቶች ጀምሮ ከማንነትና ከመሳሰሉት ጋር የሚነሱ ጥያቄዎች በመጠን እየጨመሩ ናቸው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ አንድን አካባቢ ብቻ ለይቶ ዴሞክራሲያዊ ድባብ መፍጠር አይቻልም፡፡ ለሐሜት በማይመች አኳኋን መዘዝ የሚያስከትሉ ችግሮችን ለመነቃቀል የሚያስችል ሁሉን የሚያስማማ የጋራ መፍትሔ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ የሚመራው መንግሥት ራሱን ብቻ የአገርና የሕዝብ አሳቢ፣ ሌላውን የጥፋት መልዕክተኛ ከማድረግ ያረጀ ኩነና መውጣት ይኖርበታል፡፡ እየቀረቡ ያሉት ጥያቄዎች ሕዝባዊነት ይኑራቸውም አይኑራቸውም በፅሞና ማዳመጥና ምክንያታዊና ተዓማኒነት ያለው ምላሽ መሰማት አለበት፡፡

አሁን እንደሚታየው በየቦታው ለግጭት መባባስ ምክንያት የሆኑ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ እስራት፣ መሰደድና የንብረት ውድመቶች የአገር ሥጋት ሆነዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሥጋት የሆኑ ችግሮች እንዲወገዱ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከሕዝብ ጋር ቀጥተኛ ውይይት መጀመር አለበት፡፡ ኢሕአዴግ በዚህ እሳቤ የውይይት መድረክ ከከፈተ የተለያዩ ጥያቄዎች ያለሥጋት መነጋገሪያ መሆን ይችላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ከሕዝቡና ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተነጋግሮ በመደጋገፍ በጋራ መፍትሔ ወደ መፈለግ ካልተገባ፣ አገሪቱ የገባችበት የግጭት አዙሪት አድማሱን እያሰፋ ለህልውናዋ አደጋ ይሆናል፡፡

ሕዝብ ጥያቄ ሲያቀርብ መንግሥት ምላሽ የማይሰጥ ከሆነና የሚቀርቡ ጥያቄዎችም ምክንያታዊ መሆን ሲያቅታቸው፣ ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ጠንቅ እንደሚሆኑ ማጤን ግድ ይላል፡፡ መንግሥት የሕዝብንና የአገርን ሰላምና ፀጥታ የሚያውኩ ኃይሎች ከተቃዋሚዎች ጀርባ እንዳሉ በመወትወት ብቻ መጠመዱ ለመፍትሔ ፍለጋው አይረዳም፡፡ የራሱን የቤት ሥራ በአግባቡ ሳያከናውንና የሕዝቡን ብሶት በአንክሮ ሳይሰማ፣ ችግሮችን ወደ ውጭ በመግፋት ብቻ መፍትሔ የሚገኝ ከመሰለው ከፍተኛ ስህተት ነው፡፡ ሕዝብ የሕገወጥ ተግባራት ሰለባ እንዳይሆን የማስተማርና የመምከር ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ ከራሱ ከሕዝብ ውስጥ የፈለቁ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ግን የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ ሕዝብ ጥያቄ አለኝ ሲል መንግሥት ተዓማኒነት ያለው ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ ያለበለዚያ ምላሽ ያላገኘ የሕዝብ ጥያቄ በሌሎች ኃይሎች ቢጠለፍ ሊገርም አይገባም፡፡ ይህ እንዳይሆንና ሕዝብ ተደማጭ እንዲሆን የፈለገውን ያህል ቢመር እንኳ መንግሥት መትጋት ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ ከድንገተኛ ነውጥና ብጥብጥ የተላቀቀ የፖለቲካ ሰላም ውስጥ የምትገባው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መንገድ ውስጥ ከተገባ ያለጥርጥር አጠቃላዩ የዴሞክራሲ ጉዞ ዕመርታዊ ለውጥ ያመጣል፡፡ ሥጋቶችን መንቀልም ከባድ አይሆንም፡፡

በዚህ አጋጣሚ ከሰሞኑ ግጭቶች ጋር በተያያዘ የሞቱ ዜጎች ማንነትና ቁጥራቸው፣ የተጎዱ ዜጎችና የንብረት ውድመት መጠን፣ እንዲሁም ለእስር የተዳረጉ ወገኖች ማንነትና ቁጥራቸው በግልጽ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ የታሰሩ ወገኖች ቤተሰቦቻቸው በቅርበት እንዲያገኟቸውና የሚያስፈልገውን ሁሉ እንዲያደርጉላቸው ይቻላቸው ዘንድ በአካባቢያቸው ቢሆኑ መልካም ነው፡፡ የተፋጠነ ፍትሕ እንዲያገኙም መደረግ አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየቦታው የሚነሱና የተነሱ ግጭቶች ዘለቄታዊ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኙ መንግሥት ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና ከመሳሰሉት ባለድርሻ አካላት ጋር ይምከር፡፡ ለግጭቶች መነሳት መንስዔ የሆኑ ጥያቄዎች ሰላማዊ ምላሽ አግኘተው ሥጋቶች ይወገዱ ዘንድ መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣ፡፡ ለተነሱት ግጭቶች የሚሰጠው ምላሽ ተዓማኒነት የሚገመገመው በሕዝብ መሆኑ አይረሳ፡፡ በመሆኑም ለግጭቶች የሚሰጠው ምላሽ ተዓማኒነት የሚያገኘው በዴሞክራሲያዊና በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ ይታወቅ!

 

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት...

አገር የጥፋት ቤተ ሙከራ አትሁን!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የሚለዋወጡ ስትራቴጂዎች እንደሚኖሩት ዕውን ቢሆንም፣ በየጊዜው መዋቅሮችንና ፖሊሲዎችን መለዋወጥ ግን አይችልም፡፡ ‹‹ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ›› የሚለው መጽሐፍ...