Saturday, June 22, 2024

አንቀጽ 94(2) ስምምነት ያልተገኘለት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በግንቦት ወር 1998 ዓ.ም. የኦዲት ሪፖርታቸውን ይዘው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኙት የቀድሞው ዋና ኦዲተር አቶ ለማ አርጋው፣ ቀደም ብሎ በነበረው የበጀት ዓመት የፋይናንስ አፈጻጸም ላይ 7.2 ቢሊዮን ብር ምን ላይ እንደዋለ በኦዲት ማረጋገጥ አለመቻላቸውን ለምክር ቤቱ ይፋ አደረጉ፡፡ ከጠቀሱት ኦዲት መደረግ ያልቻለ ገንዘብ ውስጥ ትልቁን ድርሻ ማለትም ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው፣ ፌዴራል መንግሥት በድጎማ በልዩ ድጋፍ ለክልሎች የሰጠው ገንዘብ መሆኑን ግልጽ አድርገዋል፡፡

በዚያው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የቀጣዩን ዓመት በጀት ለማስረዳት በፓርላማው ተገኝተው የነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በምን ላይ እንደዋለ አልታወቀም የተባለውን 7.2 ቢሊዮን ብር የኦዲት ግኝት እንዲያስረዱ፣ በወቅቱ በፓርላማው የተወሰነ መቀመጫ ከነበራቸው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ትችት ያዘለ ጥያቄ ተጠይቀው ነበር፡፡

ተራ የሒሳብ አዋቂ የማይሳሳተውን ስህተት ዋና ኦዲተር መሳሳቱን በቁጣ በመግለጽ ምላሽ መስጠት የጀመሩት አቶ መለስ፣ ኦዲት መደረግ አልቻለም ተብሎ በኦዲተር መሥሪያ ቤት የቀረበው የገንዘብ መጠን ውስጥ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ለክልል መንግሥታት የተሰጠ ድጎማና ልዩ ድጋፍ እንደሆነ ማስረዳታቸው ይታወሳል፡፡

የክልል መንግሥታት ሥልጣናቸውን ቆርሰው የፌዴራል መንግሥትን ያቋቋሙ የመሆናቸውን የፌዴራሊዝም ትርጉም በማጣቀስ፣ ክልሎች ነፃ መንግሥታት መሆናቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

ክልሎች የሚያገኙትን ድጎማ ‹‹ከፈለጉ ሊያቃጥሉት ይችላሉ›› የሚለው ንግግራቸውም እንዲሁ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

አቶ መለስ ይህንን ቢሉምና የሰላ ትችት በዋና ኦዲተሩ ላይ ቢሰነዝሩም፣ ከዚያም ዋና ኦዲተሩን ከወራት በኋላ በጡረታ እንዲገለሉ ቢያደርጉም፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 94 ንዑስ አንቀፅ (2) እስካሁን አወዛጋቢነቱን ይዞ ቀጥሏል፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 94 ንዑስ አንቀጽ ሁለት፣ ‹‹የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች የተመጣጠነ ዕድገት እንቅፋት ካልሆነ በስተቀር ለአስቸኳይ ዕርዳታ፣ ለመልሶ መቋቋምና ለልማት ማስፋፊያ ለክልሎች ብድርም ሆነ ዕርዳታ ሊሰጥ ይችላል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት ክልሎች ለሚያስፈልጋቸው ወጪ የሚያደርገውን ድጎማ በሚመለከት ኦዲትና ቁጥጥር የማድረግ ሥልጣን ይኖረዋል፤›› ይላል፡፡

በማከልም በአንቀጽ 101 (2) ስለዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤት መቋቋም በመግለጽ በንዑስ አንቀጽ ሁለት ድንጋጌው፣ ‹‹ዋናው ኦዲተር የፌዴራሉን የሚኒስቴርና ሌሎች መሥሪያ ቤቶች ሒሳቦች በመቆጣጠር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመደበው ዓመታዊ በጀት በበጀት ዓመቱ ለተሠሩት ሥራዎች በሚገባ መዋሉን መርምሮ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀርባል፤›› የሚል ኃላፊነት ሰጥቶታል፡፡ አቶ ለማ አርጋውም በዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌና በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ነበር ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሞከሩት፡፡

ከዚህ አስደንጋጭ ክስተት በኋላ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን ድጎማ በተመለከተ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኦዲት እያደረገ እንዳልሆነ ማስረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በተቃራኒው ግን የፌዴራል መንግሥታት ከዓለም አቀፍ አጋሮች ለመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ ከሚያገኘው ድጋፍ ለክልሎች በየዓመቱ የሚያስተላልፈውን ቢሊዮን ብሮች ግን፣ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኦዲት እያደረገ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡

ይህንን የድጎማ በጀት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌውን በጠበቀ መንገድ ኦዲት ለማድረግ የሚያስችል የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ነበር፡፡

ይህ ማሻሻያ ዋና ኦዲተር በተጨማሪ የኦዲት ዘርፎች መሰማራት የሚችልበትን ሕጋዊ ማዕቀፍ የሚሰጥ ከመሆኑም ባሻገር፣ አወዛጋቢ ለሆነው የክልሎች ድጎማ በጀት መፍትሔ ለመስጠት በረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ላይ የቆረጠ ቢመስልም የረቂቁ ድንጋጌ ግን ተመሳሳይ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌውን ያስቀምጣል፡፡

‹‹በቀድሞው አዋጅ ንዑስ አንቀጽ 14 ሥር የተቀመጠው ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ቁጥጥሩ ግን በክልሎች ጣልቃ በመግባት ትዕዛዝ የመስጠትን ትርጉም እንዳይዝ ትብብርን መሠረት ያደረገ እንዲሆን አስፈላጊውን ቁጥጥር በመተባበር ያደርጋል፤›› የሚል ማብራሪያ ሠፍሯል፡፡ ይሁን እንጂ የዚሁ ማሻሻያ አንቀጽ 5(2)፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥት ለክልል መንግሥታት የሚሰጠውን የበጀት ድጋፍና ልዩ ድጎማዎች ኦዲት ያደርጋል፣ ያስደርጋል፤›› የሚል ረቂቅ ድንጋጌ ነው የያዘው፡፡

ፓርላማው ለእረፍት ከመበተኑ አስቀድሞ ይህንን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር ዕይታ ለመንግሥት ወጪ አስተዳደር መርቶት የነበረ ሲሆን፣ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ለእረፍት የተበተነው ፓርላማ በአስቸኳይ እንዲሰበሰብ በጠሩት መሠረት ይህ ረቂቅ አዋጅ ሐምሌ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በአጀንዳነት ተይዞ ነበር፡፡

በዚሁ መድረክ የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በረቂቅ አዋጁ ላይ ያደረጉትን ዝርዝር ምልከታና የውሳኔ ሐሳብ ለምክር ቤቱ ሪፖርት አድርገዋል፡፡ በዚህ የውሳኔ ሐሳብ መሠረትም የፌዴራል ዋና ኦዲተር ለክልል መንግሥታት የሚሰጠውን ድጎማ ኦዲት የማድረግ ሥልጣኑ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ፣ የረቂቅ አዋጁም ድንጋጌ ከዚሁ መጣጣም እንዳለበት የሚገልጽ ነበር፡፡

ይህንን ያልተቀበሉ የምክር ቤት አባላት ግን ዋና ኦዲተር እንዴት ነፃ የሆኑ ክልሎችን የበጀት አጠቃቀም ኦዲት ሊያደርግ ይችላል? የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ለጥያቄው ምላሽ መስጠት የጀመሩት፣ ተመሳሳይ ጥያቄ በሦስተኛው የፓርላማ ዘመን ተነስቶ እንደነበር በማስታወስ ነው፡፡ ጥያቄውን በመያዝ ከአስረጂ ባለሙያዎች ጋር መወያየታቸውን፣ በውይይቱ ወቅትም ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌውንና ተያያዥ ሕጎችም አብረው መታየታቸውን ገልጸዋል፡፡

 በሕገ መንግሥቱ በግልጽ እንደተደነገገው የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን ድጎማና ልዩ ድጋፍ ኦዲት የማድረግ ሥልጣን እንዳለው የገለጹት ሰብሳቢው፣ ከአሠራር አንፃር ግን አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዳሉት በተግባርም እየታየ እንደሆነና በክልሎችም ዘንድ ሐሳቡ እንደሚነሳ ተናግረዋል፡፡

‹‹በቋሚ ኮሚቴ ደረጃ የደረስንበት ድምዳሜ ማሻሻያ አንቀፁ ከሕገ መንግሥቱ ጋር በተጣጣመ መንገድ እንዲቀመጥ፣ ነገር ግን በሌሎች መንገዶች ክልሎች በራሳቸው የተጠናከረ ኦዲት ሊያደርጉ የሚችሉበትን አሠራር መከተል እንደሚገባ ከዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ጋር ስምምነት ተደርሷል፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ይህንን አሠራር ለመዘርጋትም ምክር ቤቱ በራሱ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የተጣጣመ አሠራር ሊያስቀመጥ እንደሚገባ መስማማታቸውን የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ሁለት ጊዜ ኦዲት (Double Audit) በነጠላ ኦዲት (Single Audit) ደረጃ መሠራት እንዳለበት በዝርዝር ዕይታው ወቅት ስምምነት የተደረሰበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይህንን አሠራር ለማበጀት በሦስተኛው ምክር ቤት ተጀምሮ የነበረ ውይይት ወደ ውጤት ሳይሸጋገር መቋረጡን ከዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች መረዳታቸውን የገለጹት አምባሳደር መስፍን፣ ይህንን ሥራ ማስቀጠል እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

‹‹ነገር ግን ለክልሎች የሚሰጠውን ድጎማና ልዩ ድጋፍ ኦዲት የማድረግ ሥልጣን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሆኑ በግልጽ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠ በመሆኑ የምክር ቤት አባላት ከሕገ መንግሥቱ ልትገነዘቡት ትችላላችሁ፤›› ብለዋል፡፡

በተሰጠው ማብራሪያ መሠረት ወደ ድምፅ መስጠትና ረቂቁን ወደ ማፅደቅ ከመገባቱ በፊት ግን የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ የመንግሥትን አቋም ለመግለጽ ዕድል እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየትም የፓርላማ አባላት ያነሱት ጥያቄ ተገቢ መሆኑን፣ በሦስተኛው የፓርላማ ዘመንም በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ማብራሪያ ትክክል እንደነበር፣ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በሕገ መንግሥቱ ላይ ድጎማን ኦዲት የማድረግ ሥልጣን የዋና ኦዲተር መሆኑ በግልጽ ተቀምጧል ያሉትም ልክ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

‹‹ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ እንደ ሙሉ ማዕቀፍ (Package) ነው መታየት ያለበት፡፡ ሕገ መንግሥቱ የተመሠረተው በፌዴራሊዝም መርህ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ ሁሉ ነገር መነሻ ፌዴራሊዝም ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት የተመሠረተው ክልሎች ቆርሰው በሰጡት ሥልጣን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ ከመግቢያው ጀምሮ የክልሎችን ነፃነት፣ እንዲሁም ለፌዴራል መንግሥትም ሥልጣን የሰጡት እነሱ መሆናቸው ግልጽ ሆኖ ሳለ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሰጠውን ድጎማ እየሄደ ኦዲት ያደርጋል የሚለው ትክክል አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሦስተኛው የፓርላማ ዘመን የተሰጠው አቅጣጫም ይህንኑ የሚያንፀባርቅ በመሆኑ ያልተቋጨ ነገር የለም ብለዋል፡፡

‹‹የቀረበው ማሻሻያ አዋጅ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የሚለው ዋና ኦዲተር ለክልሎች የሚሰጠውን ድጎማና ድጋፍ በክልል ኦዲተሮች ኦዲት እየተደረገ መሆኑን በመተባበር ክትትል ያደርጋል ነው፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተስማማነውም በዚህ መልኩ ነው፤›› በማለት የመንግሥታቸውን አቋም አብራርተዋል፡፡

‹‹ክልሎች ራሳቸውን የቻሉ መንግሥታት ናቸው፡፡ ነፃ ሆነው ሥራቸውን ማከናወን የሚችሉት ራሳቸው ባወጡት ሕግና አሠራር ብቻ ነው፤›› ሲሉ አቶ አስመላሽ ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ይህንኑ የአቶ አስመላሽ ማብራሪያ፣ ‹‹በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ማስተካከል ይቻላል፤›› በማለት የተቀበሉት ሲሆን፣ ምክር ቤቱም አቶ አስመላሽ የሰጡትን ማስተካከያ ሐሳብ ተቀብሎ ረቂቅ አዋጁን አፅድቆታል፡፡

የአቶ አስመላሽ ማስተካከያ

አወዛጋቢ በሆነው በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች የአቶ አስመላሽን ማስተካከያ ሐሳብ ይተቻሉ፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ክልሎች ነፃነት ቢኖራቸውም ነፃነታቸው የሚገለጸው ከፌዴራል መንግሥታት ጣልቃ ገብነት ነፃ እንዲሆኑ፣ አልያም እንደሌላ አገር ተደርገው መሆን እንደሌለበት ይከራከራሉ፡፡

በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የተናጥል አስተዳደርና የጋራ አስተዳደር (Self Rule and Shared Rule) መኖሩን የሚጠቅሱት ባለሙያዎቹ፣ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሰጠውን ድጎማና ልዩ ድጋፍ ኦዲት የማድረግ ሥልጣን የፌዴራል መንግሥት ነው ማለት በጋራ አስተዳደር ውስጥ መውደቁን የሚያመለክት እንጂ፣ የክልሎችን ነፃነት የሚጋፋ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የፌዴራል መንግሥት እንደ ውጭ አካል ተለይቶ የሚቆጠር ሳይሆን፣ በዚሁ አስተዳደር ውስጥ ለክልሎችም ኃላፊነት እንዳለው ይገልጻሉ፡፡

ሌላ የሕግ ባለሙያ በበኩላቸው የተገለጸው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ የክልሎችን ነፃነት የሚጋፋ ከሆነ፣ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል አንቀጹን ማውጣት እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡

በማከልም የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ የሰጡት አስተያየት ይህንን ተከትሎም ፓርላማው አዋጁን ማፅደቁ በራሱ ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ የሚሰጡት ምክንያትም ፓርላማውም ሆነ አቶ አስመላሽ ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን እንደሌላቸው፣ ይልቁንም ይህ ሥልጣን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠ መሆኑ ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡ ፓርላማው የቀረበለትን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በአቶ አስመላሽ ማስተካከያ ማፅደቁ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሰጠ ያስቆጥረዋል በማለት ይከራከራሉ፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የሕግ ባለሙያ በበኩላቸው፣ አቶ አስመላሽ ሕገ መንግሥቱን እንደ ማዕቀፍ ማየት ተገቢ ነው ባሉት መሠረት ጉዳዩን መተንተን እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ መሠረት ከተተነተነ የፌዴራል መንግሥት የሚሰጠውን ድጎማና ድጋፍ ዋና ኦዲተር ኦዲት ማድረግ እንዳለበት የሚያስገነዝብ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ የፊሲካል ፌዴራሊዝም የድጎማና ልዩ ድጋፍ መርህ ምሰሶ የሚያጠነጥነው የዜጎችን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጥቅሞች በእኩል ማረጋገጥ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡

ለዚህ የበጀት ድጎማ በመርህነት ከሚጠቀሱት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች መካከል የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41(3) አንዱ ሲሆን፣ ይኼም ‹‹የኢትዮጵያ ዜጎች ሁሉ በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ ማኅበራዊ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው፤›› እንደሚል፣ በማከልም በአንቀጽ 89(2) ‹‹መንግሥት የኢትዮጵያውያን የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ለማሻሻል፣ እኩል ዕድል እንዲኖራቸው ለማድረግና ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚከፋፈልበትን ሁኔታ የማመቻቸት ግዴታ አለበት፤›› በማለት ግዴታ ጭምር እንደሚያስቀምጥ ያስረዳሉ፡፡

በመሆኑም ከእነዚህ መሠረታዊ ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎች አንፃር ሲታይ የፌዴራል መንግሥቱ የሚሰጠውን ድጋፍና ድጎማ ኦዲት በማድረግ መቆጣጠር ካልቻለ፣ ከላይ የተገለጹትን የዜጎችን በእኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ኃላፊነቶች መወጣት እንደማይችል ይገልጻሉ፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41(3) እንዲሁም 89(2) ድንጋጌዎችም የክልሎችን ሥልጣን የሚጋፉ ናቸው ካልተባሉ በስተቀር ድጎማና ድጋፉን የፌዴራል መንግሥቱ ኦዲት ቢያደርገው የሚጋፋው ነፃነት የለም፡፡ የሕገ መንግሥቱ የመጨረሻ ግብም አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው በማለት መንግሥት በትኩረት እልባት እንዲሰጥበት ያሳስባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -