ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ነሐሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ ከወጣቶች ጋር ሊወያዩ ነው፡፡
ውይይቱ ከወጣቶች ፖሊሲ ላይ የተቀዱ ዋና ዋና የልማት ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች፣ እንዲሁም በፕሮግራሞች ውስጥ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ምን ደረጃ ላይ ደርሷል? ስኬቶቹ ምንድን ናቸው? ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ምን ይመስላሉ? ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ምን መሆን አለባቸው? በሚሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል፡፡
የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አዲሱ አረጋ ማክሰኞ ነሐሴ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በብሔራዊ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በውይይቱ ላይ ሦስት ሺሕ ወጣቶች እንደሚሳተፉና ከተሳታፊዎቹም ውስጥ 30 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እንደሚሆኑም ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች፣ በገጠር፣ በአርብቶ አደርና በከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑም አክለዋል፡፡
በተጨማሪም በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚሠሩ፣ ተማሪዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ሥራ አጥና አካል ጉዳተኛ ወጣቶች የውይይቱ ተሳታፊ እንደሚሆኑ አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡
መንግሥት ነሐሴ 13 እና 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ከወጣቶች ጋር በሚያካሂደው ውይይት በጠቅላይ ሚኒስትሩና ወጣቶች መካከል ከሚካሄድ የጥያቄና መልስ መርሐ ግብር በተጨማሪ፣ በጎንዮሽ የሚካሄዱ የተለያዩ መድረኮች እንደሚኖሩ አቶ አዲሱ አስታውቀዋል፡፡
በዚህም መሠረት ነሐሴ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. የኤችአይቪ ሥርጭት ገጽታና የዘርፈ ብዙ ምላሾች አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫን የሚመለከት መድረክ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንደሚካሄድ፣ መድረኩን የሚመሩት ደግሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይ በዕለቱ በሥራ ፈጠራ ስኬታማ የሆኑ ወጣቶች የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ በሚመሩት መድረክ ላይ ተሞክሮአቸውን ለሌሎች ወጣቶች እንደሚያካፍሉ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ኅብረ ብሔራዊ የፌደራላዊ ሥርዓት ግንባታና የወጣቶች ሚና›› የሚል ጽሑፍ ቀርቦ የፓናል ውይይት እንደሚደረግ ይህንን መድረክ የሚመሩት ደግሞ የፌደራልና አርብቶ አደሮች ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃን እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡
ወጣቶች በችግሮቻቸውና በጉዳዮቻቸው ዙሪያ መፍትሔ የሚያገኙባቸው መድረኮች በተለያዩ ደረጃዎች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ያስታወሱት አቶ አዲሱ፣ ተመሳሳይ መድረኮች በአገር አቀፍ ደረጃ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር በ1999፣ በ2000 እና በ2002 ዓ.ም. መካሄዳቸውን አስታውሰዋል፡፡
ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ግን የወጣቶች መዋቅር ወደ ሴቶችና ሕፃናት በመሄዱ ምክንያት፣ ከሌሎች ችግሮች ጋር ተዳምሮ መድረኮቹ አለመካሄዳቸውን አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እንደ አዲስ በመደራጀቱና ወጣቶች በጉዳዮቻቸውና በችግሮቻቸው ዙርያ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን፣ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ፊት ለፊት አግኝተው በጉዳዮቻቸው ላይ ለመወያየት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የሚመካከሩበትን መድረክ መፍጠሩ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መድረኩ መዘጋጀቱን አቶ አዲሱ ጠቁመዋል፡፡