Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተደረጉ የተቃውሞ ሠልፎች በኃይል ተበተኑ

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተደረጉ የተቃውሞ ሠልፎች በኃይል ተበተኑ

ቀን:

– መንግሥት የሠልፎቹ ዓላማ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መናድ ነው አለ

– በሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል

– የአማራ ክልል ትጥቅ የማስፈታት ዓላማ የለኝም ብሏል

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአማራ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ የተደረጉና የተሞከሩ የተቃውሞ ሠልፎች በኃይል ተበተኑ፡፡ የተቃውሞ ሠልፎቹ በኃይል ከመበተናቸውም በተጨማሪ፣ በሰዎች ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ በርካቶችም ለእስር ተዳርገዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሐምሌ 30 እና ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ሲካሄዱ በነበሩ ሰላማዊ ሠልፎች ላይ መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ፣ በአገሪቱ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ አዳጋች መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡ መንግሥት የሠልፎቹ ዓላማ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መናድ ስለነበር ዕርምጃው ተገቢ ነበር ብሏል፡፡

በአማራና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ በመንግሥት ላይ ተቃውሞ ለማቅረብ ሊካሄዱ በነበሩ ሰላማዊ ሠልፎች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ዕርምጃ በመውሰድ በርካታ ዜጐችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለንብረት ውድመት እንዳጋለጡ በርካታ ዘገባዎችና የሪፖርተር ምንጮች አመልክተዋል፡፡ ሪፖርቶቹ በዕርምጃው ሕይወታቸው ያለፈውን ዜጐች ቁጥር የተለያየ አድርገው አቅርበዋል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከታማኝ ምንጮች አገኘሁት ባለው መሠረት ቁጥሩን 97 አድርሶታል፡፡ በአንፃሩ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በባህር ዳር ሠልፍ የሰባት ሰዎች ሕይወት እንዳለፈና በአምስት የፖሊስ አባላትና በርካታ ዜጐች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ገልጿል፡፡ አምነስቲ በአማራ ክልል ሰላሳ ሰዎች መሞታቸውንና በኦሮሚያ ክልል ደግሞ 67 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ሪፖርት አድርጓል፡፡ ከተገደሉና ጉዳት ከደረሰባቸው ዜጐች በተጨማሪ ለእስር የተዳረጉት በርካቶች መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ከአማራና ከኦሮሚያ ክልሎች ውጪ በአዲስ አበባም ተመሳሳይ ሠልፍ ለማድረግ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጐች ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት መስቀል አደባባይ የተገኙ ቢሆንም፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የማያዳግም ዕርምጃ ሊበታተኑ ችለዋል፡፡ ጫማቸው እየወለቀ ድብደባ ሲፈጸምባቸው እንደነበርና ሮጠው ለማምለጥ የሞከሩትንም በመከታተል ድብደባ እንደተፈጸመባቸው የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በሦስቱም አካባቢዎች ሠልፈኞች የተለያየ አጀንዳዎችና የጋራ አጀንዳዎችን ማንፀባረቃቸውም ተመልክቷል፡፡ የፖለቲካ ነፃነት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ሥራ አጥነትና የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል በጋራ አጀንዳነት ተጠቅሷል፡፡ ይሁንና ለአማራ ክልል የወልቃይት ማንነት፣ ለኦሮሚያ የገበሬዎች መፈናቀልና የመሬት ይዞታ፣ ለአዲስ አበባ ደግሞ የፖለቲካ ነፃነት የተለዩ አጀንዳዎች እንደነበሩ ተገልጿል፡፡ በአማራና በኦሮሚያ ሕገወጥ ተግባር ፈጽመዋል በሚል በቁጥጥር ሥር የዋሉ የፖለቲካ አመራሮች እንዲፈቱም ጥያቄ ቀርቧል፡፡

በኦሮሚያ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ነቀምት፣ አምቦና ደምቢዶሎ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ለተለያዩ ሚዲያዎች እንደገለጹት፣ በሁለቱ ቀናት በፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ 33 ሰዎች ዝርዝር ፓርቲው አጠናቅሯል፡፡

መንግሥት ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ የሚያስፈልገው ቅድመ ሁኔታ በእነዚህ ሠልፎች አለመሟላቱን በመግለጽ ሕገወጥ እንደሆኑ ተከራክሯል፡፡ ከሕጋዊ ቅድመ ሁኔታዎቹ አንዱ ለስብሰባውና ሠልፉ ኃላፊነት የሚወስደውን አካል ማሳወቅ እንደሆነ በመጥቀስ፣ እነዚህ ስብሰባዎችና ሠልፎች ግን ይህን እንዳላሟሉ አመልክቷል፡፡ ከዚህ ይልቅ ጥሪው የተደረገው ውጭ በሚገኙ ሰዎች በኢንተርኔትና በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት በመሆኑ፣ መንግሥት በእነዚህ ቀናት የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ አድርጎ ነበር፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ አሁንም የተቋረጠ ሲሆን ሌሎች የኢንተርኔት አገልግሎቶች ግን ተመልሰዋል፡፡

የሠልፎቹ ዓላማ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ሁከት ለማስፋፋት በመሆኑ በመንግሥት በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት መግለጫ ያመለክታል፡፡ መግለጫው በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች የመንግሥትና የግለሰብ ንብረት ሲያወድሙ፣ መንገድ ሲዘጉና በንፁኃን ዜጎችና በፀጥታ ኃይሎች ላይ የሞት አደጋ ሲያደርሱ በመገኘታቸው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች እንዳሉም ጠቁሟል፡፡ በአዲስ አበባ ሠልፍ ሊያደርጉ የሞከሩት ግለሰቦች ሁከት ለማስፋፋት በሚፈልጉ ኃይሎች ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢ የመጡ እንደነበሩም አመልክቷል፡፡

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ሊቀመንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኰንንና የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ምክትል ሊቀመንበርና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ አስቴር ማሞ ለፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት እንደገለጹት፣ ሠልፎቹ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመናድ በኃይልና በጉልበት ሥልጣን ለመቆጣጠር ያለመ ኃይል መሣሪያ ናቸው፡፡ እነዚህም ኃይሎች ለሠልፎቹ በኢንተርኔት ጥሪ ያደረጉት ሻዕቢያና ኦነግ እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተመሳሳይ ነሐሴ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ ሰሞኑን በባህር ዳር፣ በጐንደርና በደብረ ታቦር ከተሞች የተፈጠረው ሁከትና ግርግር የአብዛኛው ሕዝብ ፍላጐት ሳይሆን ከብጥብጡ እንጠቀማለን የሚሉ ጥቂት ተስፈኞች ሕዝቡን በማደናገር የፈጠሩት ችግር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ምንጮች ለሪፖርተር በአማራ ክልል በላይና ታች አርማጭሆ መንግሥት ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ከፍተኛ ግጭት ውስጥ መግባቱን፣ በሌሎች አካባቢዎችም ያለው ውጥረት አለመርገቡን ገልጸዋል፡፡ በአቶ በረከት ስምዖንና በክልሉ ባለሥልጣናት ማክሰኞ ነሐሴ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ስብሰባ የተደረገ ሲሆን፣ ጠዋት ላይ ከመካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች ጋር በተደረገው ውይይት የወልቃይት ጥያቄና የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጉዳይ ዋነኛ ጥያቄ ሆኖ መውጣቱን ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡  

አቶ በረከት የወልቃይትም ሆነ የኮሎኔል ደመቀ ጉዳይ በአገሪቱ ሕግ የሚስተናገድ እንጂ የተጠናቀቀ ጉዳይ አለመሆኑን መናገራቸውም ተጠቅሷል፡፡ ከሰዓት በኋላ ከወጣቶች ጋር ለመነጋገር የተያዘው ቀጠሮ አለመግባባት በመፈጠሩ አልተካሄደም ተብሏል፡፡ ኮሎኔል ደመቀ ነሐሴ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ግጭት እንዳይፈጠር መሠጋቱም ተመልክቷል፡፡ በባህር ዳርም በተመሳሳይ ውጥረት የነገሠ ሲሆን፣ ነሐሴ 2 እና 3 ቀን 2008 ዓ.ም. መደበኛ እንቅስቃሴ ተገቶ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ተዘግተው ከሰዎች እንቅስቃሴ ይልቅ የፀጥታ ኃይሎች እንቅስቃሴ በጉልህ ይታይ እንደነበረም ተገልጿል፡፡

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በክልል መደበኛ ሕይወትን ለማስፈን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ውጤት እየታየባቸው ነው፡፡ በጐንደር መደበኛ ሕይወት መቀጠሉን አመልክተው በባህር ዳር ትራንስፖርትና መሰል አገልግሎቶች ያልተጀመሩ ቢሆንም አመሻሽ ላይ ሱቆች መከፈት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ በላይና ታች አርማጨሆ የክልሉ መንግሥት ትጥቅ ሊያስፈታ ነው በሚል አደናጋሪ መልዕክቱ የተወሰነ መደናገጥ ተፈጥሮ ነበር ያሉት አቶ ንጉሡ፣ የተለየ ተጨባጭ ቀውስና መንግሥትን ተደራጅቶ በትጥቅ የገጠመ ኃይል አለ መባሉ ምኞት እንጂ እውነት አይደለም ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ በክልሉ መሣሪያ መያዝ ባህልና ለዜጐች ቅርብ የሆነ የተለየ ዋጋ የሚሰጠውና የተለመደ ቢሆንም፣ ማን ምን መሣሪያ እንደያዘ ለማወቅ ከተደረገው ሕገወጥ መሣሪያን ለመቆጣጠር ያለመ ምዝገባ ውጪ እንደ አዲስ ትጥቅ የማስፈታት ዕቅድ እንደሌለም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የክልሉ መንግሥት በግልጽ አቋሙን በማስረዳቱ መግባባት ላይ ደርሰናል፤›› ብለዋል፡፡

የተለያዩ ኃይሎች በክልሉ ብጥብጥ ግጭት እንዲፈጠር ከሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች አንዱ ይኼው ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ ዋነኛው በመሆኑ፣ እሱን ለማስተካከል የክልሉ መንግሥት አበክሮ እንደሚሠራም አስገንዝበዋል፡፡  

በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልሎች መንግሥት ተገቢ የሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎች አሉ ብሎ የሚቀበል ቢሆንም፣ በብዛት ግን መሰል ተቃውሞና ጥያቄ በርትቶ ሲመጣ የውጭ ኃይሎች እንጂ የሕዝቡ ጥያቄ አይደሉም በሚል ወደ ውጭ መግፋቱ እያስተቸው ይገኛል፡፡

በባህር ዳር የተካሄደው ሠልፍ በሰማያዊ ፓርቲ ኃላፊነት የተካሄደ ቢሆንም፣ ፓርቲው ሠልፉን በሰላማዊ መንገድ መርቶ ባለማጠናቀቁ ለደረሰው የሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ተጠያቂ እንደሚሆን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት ሠልፈኞቹ ለመንግሥት ሳያሳውቁ ሠልፍ መውጣታቸው ሕገወጥ ድርጊት መሆኑን ያሰመረበት ቢሆንም፣ አስተያየት ሰጪዎችና አንዳንድ ሪፖርቶች ግን መንግሥት ጥያቄው ሲቀርብለትም ቢሆን የማያሳምን ምክንያት በመስጠት እየከለከለ ሠልፍ የሚባል ነገር በአገሪቱ ብርቅ እንዲሆን በማድረጉ፣ ሠልፈኞቹ ሳያሳውቁ ለማከናወን ሳያስገድዳቸው እንዳልቀረ እየገለጹ ነው፡፡

የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ በእነዚህ ድርጊቶች አሜሪካ ሥጋት እንደገባት የጠቆመ ሲሆን፣ መንግሥት የሕዝቡን ተቃውሞ የማሰማት ነፃነት እንዳይጋፋም ጠይቋል፡፡

በኢትዮጵያ ሕግ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ የሚያስፈልገው ማሳወቅ እንጂ ፈቃድ ባይሆንም፣ የኤምባሲው መግለጫ ግን ሠልፎቹ ያለፈቃድ (without authorization) እንደተካሄዱ አሜሪካ እንደምትገነዘብ ይገልጻል፡፡

እንደ አሜሪካ ኤምባሲ ሁሉ ነሐሴ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. መግለጫ ያወጣው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ግን ሠልፈኞቹ መብታቸውን የጠየቁ በመሆናቸው በአስቸኳይና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...