Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የሚገኝ መሬት ለጨረታ መቅረቡ ጥያቄ አስነሳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ400 በላይ የሚሆኑ ኩባንያዎች የኢንዱስትሪ መሬት በድርድር እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበው እየተጠባበቁ ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በመካኒሳ ለቡ ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የሚገኝ መሬት ለጨረታ ማቅረቡ ጥያቄ አስነሳ፡፡

የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 የኢንዱስትሪ መሬት በምደባ እንደሚሰጥ ቢደነገግም፣ የከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በ22ኛው ዙር ሊዝ ጨረታ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ውስጥ በሚገኘው መካኒሳ ለቡ ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የሚገኝ መሬት ለጨረታ አቅርቧል፡፡

ይህ አሠራር የሊዝ አዋጅንም ሆነ አዋጁን ለማስፈጸም የወጡ ደንብና መመርያዎችን የሚፃረር ነው በማለት የኢንዱስትሪ መሬት በድርድር እንዲሰጣቸው ያመለከቱ ባለሀብቶች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በሊዝ አዋጅ መሠረት የከተማ ቦታ በሁለት መንገድ ለተጠቃሚው ይተላለፋል የመጀመሪያው በጨረታ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በምደባ ነው፡፡ በሊዝ አዋጅ አንቀጽ 12(ሠ) ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች መሬት በምደባ እንደሚተላለፍ በግልጽ ተደንግጓል፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የኢንዱስትሪ መሬት እንዲሰጣቸው ያመላከቱ ባለሀብት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ካሉት ሕግጋቶች በመነሳት ለኢንዱስትሪ የሚሆን መሬት እንዲሰጣቸው ካመለከቱ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ ነገር ግን ምላሽ እየጠባበቁ ባለበት ጊዜ አስተዳደሩ ለኢንዱስትሪ የሚሆን መሬት ጨረታ አውጥቶ መመልከታቸው አስደንግጧቸዋል፡፡

በ22ኛው ሊዝ ጨረታ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለቡ ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የወጣው መሬት 7,803 ካሬ ሜትር ስፋት አለው፡፡ ለዚህ ቦታ 30 ኩባንያዎችና ግለሰቦች የተወዳደሩ ሲሆን፣ ዲሰንት ኢንዱስትሪያል ኩባንያ በአንድ ካሬ ሜትር 11,900 ብር (ከፍተኛ) ማቅረቡ ታውቋል፡፡

ቀደም ሲል ይህ ቦታ በድርድር እንዲሰጣቸው ከጠየቁ መካከል ኤንኤ ሜታልና ስናፕ ትሬዲንግ ይገኙበታል፡፡ በምደባ መሰጠት የነበረበት ይህ መሬት ጨረታ ሊወጣበት የቻለበትን ምክንያት በሚመለከት ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኮንን አምባዬ የኢንዱስትሪ ቦታ ጨረታው የወጣው በኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ መሆኑን አረጋግጠው፣ ይህ የሆነው ቦታው በተለያዩ ምክንያቶች ሳይለማ በመቆየቱ በፍጥነት ወደ ልማት ለማስገባት ሲባል ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የመካኒሳ ለቡ ኢንዱስትሪ ዞን ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ አዲስ አበባን ሲያስተዳድሩ የኢንዱስትሪ ዞኖች ውስጥ አንዱ ነበር፡፡ በዚህ ኢንዱስትሪ ዞን ቦታ አግኝተው ወደ ሥራ የገቡ ኩባንያዎች በሙሉ በድርድር የተስተናገዱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች