Sunday, January 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅ‹‹ትዝ አለኝ የጥንቱ ….!››

‹‹ትዝ አለኝ የጥንቱ ….!››

ቀን:

ከሠላሳ ስድስት ዓመት በፊት በሞስኮ በተካሄደው 22ኛው ኦሊምፒያድ፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በረዥም ርቀት ሩጫ (5ሺ እና 10ሺ ሜትር) ሁለት ወርቅ በአንድ አትሌት ያገኘችበት አኩሪ ድሏ ነበር፡፡ ያ አትሌት ማርሽ ለዋጩ ምሩፅ ይፍጠር (ይፍጠር ዘሺፍተር) ነበር፡፡ በሐምሌ 1972 ዓ.ም. በሞስኮ ኦሊምፒክ ከተገኙት 81 አገሮች አንዷ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ በኦሊምፒኩ መክፈቻ የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ ልዑኩን መርቶ የገባው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ነበር፡፡ በኦሊምፒክ መክፈቻው ከታዩት ትርዒቶች ባስደናቂነቱ የሚወሳው ትርዒተኞቹ ያሳዩት የሰዎች ፒራሚዶችን ቅርፅ ይህ ፎቶ ይናገራል፡፡

* * *

ወይ ታሪክ!

ታሪክ እነፍሴ ዲብ እየሠራ

ዘመን እልቤ ከምሮ ጋራ

ቀና ቀና ስል ምንም ሳልፈራ

ክብረ ቢስ ችግር ክብሬን ገሶ

ተልኮሰኮስኩኝ ኩራቴ ኮሶ

በልቶ ለማደር አጐነበስኩኝ

ለፍርፋሪ ሞገሴን ሸጥኩኝ፡፡

የአያት ቅድም አያት ያባት እናቴ

የጀግንነቱ ገድሌ ንግርቴ

እልፍ እጥፍ ነበር ዋጋው ግምቱ

ረከሰና ጉርስ ሆነ የዕለቱ

ጊዜ አዘንብሎ ተደፍቶ አንገቴ

ክብሬ ገበያው ሆነ ለዕራቴ

ላብን አፍስሰው በአቅም ሳይጥሩ

ጥሪት ሰብስበው ሠርተው ሳይከብሩ

ወይ ታሪክ እቴ ገድል ቢያወሩ

ኮርቶ ማደር የል ጦም እያደሩ፡፡

  • ተፈሪ ዓለሙ፣ ‹‹የካፊያ ምች›› (2007)

* * *

የግብፅ ወንዶች የወርቅ ጥሎሽን እየተቃወሙ ነው

በዓረብኛ ሻብካ በመባል የሚታወቀው ሥርዓት የግብፅ ወንዶች ለአንዲት ሴት የሚሰጡት የወርቅ ጥሎሽ ሲሆን፣ በቅርቡ የወርቅ ዋጋ በመወደዱ ሳቢያ ሥርዓቱን የግብፅ ወንዶች መቃወም ጀምረዋል፡፡ ባህሉ እንዲቀር የሚፈልጉ ወንዶች የጀመሩት እንቅስቃሴ የብዙዎችን ድጋፍ እያገኘ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ፣ የአንድ ግራም 24 ካራት ወርቅ ዋጋ ግብፅ ውስጥ 50 ዶላር መግባቱን ጠቅሷል፡፡ አቅማቸው ባህሉ የሚጠይቃቸውን የወርቅ ጥሎሽ ለማቅረብ ያልፈቀደላቸው ወንዶችም ወደ ብር ጥሎሽ ይለወጥ የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ አንድ ወንድ ለጋብቻ ከወርቅ ጌጣጌጦች ጥሎሽ በተጨማሪ ቤት መግዛትም ይጠበቅበታል፡፡ አንዳንድ የአገሪቱ ሴቶች ባህሉ እንዲቀር ባይፈልጉም፣ ብዙዎቹ ግን ሐሳቡን ደግፈውታል፡፡ ጥንዶች ያላቸውን ገንዘብ ሕይወታቸውን የተሻለ ለማድረግ ቢያውሉት ይሻላል የሚል አቋም ይዘዋል፡፡

* * *

እርቃኑን የቆመው የንጉሥ ዳዊት ቅርጽ እንዲለብስ ተጠየቀ

በማይክልአንጀሎ የተሠራው ባለ 5 ሜትሩ የንጉሥ ዳዊት ቅርጽ ኮፒ በሩሲያ፣ ሴንት ፒተርስበርግ የቆመው በቅርቡ ነበር፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እርቃኑን የቆመው ቅርጽ በአካባቢው ያሉ ታዳጊዎች ሥነ ልቦና ላይ ተጽእኖ ሊያደርስ ስለሚችል ልብስ ይልበስ ብለዋል፡፡ በቅርጹ አካባቢ ትምህርት ቤቶችና ቤተ ክርስቲያን እያሉ ቅርጹ እርቃኑ መቆም የለበትም የሚል ቅሬታ በመጀመሪያ ያቀረቡት አንዲት እናት ሲሆኑ፣ ሐሳባቸውን ለከተማዋ ኃላፊዎች አቅርበዋል፡፡ ቅርጹ በማይክል አንጀሎ እንደተሠራው እርቃኑን መቆም አለበት የሚሉ ሰዎች ደግሞ የሥነ ጥበብ ኦሪጅናልነት ይጠበቅ ብለዋል፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ የከተማዋ ኃላፊዎች በሁለቱም ወገን ያሉ ሰዎች በጉዳዩ ላይ ድምፅ ሰጥተው የአብላጫው ውሳኔ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል፡፡

* * *

እንግሊዛዊው ሰዎች ከአህያ ጋር የሚግባቡበት መሣሪያ ፈጠረ

እንግሊዛዊው ማርክ ኢንሰን ከ20 ዓመታት በላይ ስለ አህዮች የተመራመረ ሲሆን፣ ሰዎች የአህዮችን ስሜትና ፍላጐት በመረዳት ሊግባቡ የሚችሉበት መሣሪያ ሠርቷል፡፡ መሣሪያው የአህዮቹን ስሜትና ፍላጐት እየመረመረ በጽሑፍ ለሰዎች የሚያሳውቅ ነው፡፡ ‹‹አህዮች በጣም ስሜታዊና ስሜታቸውንም በሰውነት እንቅስቃሴያቸውና በድምፃቸው የሚገልጹ እንስሳት ናቸው፤›› የሚለው እንግሊዛዊው መሣሪያውን አህያ ያላቸው እንግሊዛውያን እንዲገለገሉበት እያስተዋወቀ ነው፡፡ እንደ ሮይተርስ ዘገባ ለዓመታት ብዙ አህዮች ያሳደጉ ሰዎች በፈጠራው እየተጠቀሙበት ነው፡፡

* * *

ፍቅረኛውን ለአሥር ቀን በአየር መንገድ የጠበቀው ጐልማሳ

ጀርመናዊው አሌክሳነደር ፒተር የ41 ዓመት ጐልማሳ ሲሆን፣ በኢንተርኔት ከተዋወቃት ቻይናዊት ጋር የሩቅ ለሩቅ ፍቅር ከጀመሩ ሰነባብቷል፡፡ የ26 ዓመቷን ዥንግ በአካል ለማግኘት ወደ ቻይና ከበረረ በኋላ ግን አየር መንገድ ልትቀበለው እንዳልሄደች አወቀ፡፡ ከአሁን አሁን ትመጣለች ብሎ አየር መንገዱ ውስጥ ሲጠባበቅም አሥር ቀን ተቆጠረ፡፡ በስተመጨረሻ ጀርመናዊው በጣም ተዳክሞ ሆስፒታል መግባቱን ዘ ሰን ዘግቧል፡፡ በጉዳዩ የተደናገጠችው ዥንግ፣ አሌክሳንደር ወደ ቻይና እንደሚመጣ ሲነግራት የእውነቱን እንዳልመሰላት ተናግራለች፡፡ እሱ ቻይና አየር መንገድ እየጠበቃት በነበረበት አሥር ቀናት እሷ ለፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ከከተማ ወጥታ ስለነበር አንላየን ሊያገኛት አልቻለም፡፡ አሌክሳንደር በሁኔታው አዝኖ ከሆስፒታል ከወጣ በኋላ ወደ አገሩ ለመመለስ ቢወስንም፣ ዥንግ ከፕላስቲክ ቀዶ ጥገናዋ ካገገመች በኋላ ፍቅራቸውን እንዲቀጠሉ እንደምትፈልግ ገልጻለች፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...