በያሲን ባህሩ
‹‹የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግን እንደ ሞት ሽረት የሚቆጥሩ መንግሥታት በተፈጠሩበት ቆዳ ተጠቅልለው የሚሞቱ ናቸው፡፡ አንድ አገር ወይም ሕዝብ የሚመራበት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂዎችና ርዕዮተ ዓለማዊ ፍልስፍናዎች እንደ ተጨባጩ ዓለማዊ ሁኔታ ወይም ሕዝቡ ከደረሰበት የግንዛቤና የውጤት ደረጃ አንፃር መቃኘት አለባቸው፡፡ ይህን ማድረግ አለመቻል ነው ጉዞን የሚያደናቅፈው፤›› ይላሉ ቤንጃሚን ፍራንክሊን የተባሉ የሥነ ጽሑፍና የሥነ መንግሥት ሊቅ፡፡
ለዛሬ የጽሑፌ መግቢያ የአውሮፓዊው ሊቅ አባባልን የገለጽኩት ወድጄ አይደለም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን እየታየ ከመጣው የመንግሥትና የሕዝብ አለመግባባት፣ ቀላል በማይባል ሁከትና ግጭት የተነሳ የሕዝብ ጥያቄ ብሎም ‹‹ጽንፈኛ›› የሚባለው የውጭ ተቃዋሚ ኃይል ይበልጥ እየተደመጠ መምጣት አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ነው፡፡
‹‹ይህ ታዲያ በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ ምን ችግር አለው? መንግሥት የጊዜ ጉዳይ እንጂ ውጤት ካላመጣ ተቀባይነት ሊያጣ ይችላል…›› የምትሉ ወገኖች ትኖራላችሁ፡፡ እኔ እንደ አንድ ዜጋ ሐሳቡን የማነሳው ግን ለ25 ዓመታት አገሪቱን በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ አሳልፎ እዚህ ያደረሳት መንግሥት ሊቀየር ይችላል በሚል ሥጋት አይደለም፡፡ ይልቁንም ከረጅም ጊዜ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ኋላቀርነትና ድህነት በኋላ ቀና ማለት የጀመረ ሕዝብና አገር ጅምር ጉዞ እንዳይደናቀፍ ነው፡፡
ከሁሉ በላይ በጭቆና ውስጥ እንኳን ለዘመናት ተቻችሎ፣ ተከባብሮና ተዋልዶ የኖረን የአንድ አገር ሕዝብ የሚነጣጥል አደጋ እንዳይሰነቀር ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ እንዳለው ‹‹ቋንቋና ማንነት ተኮር የሆነውን ፌዴራላዊ ሥርዓት›› ተጠቅሞ ሕዝብን ከሕዝብ ለመነጠል የተጀመረውን ጽንፈኛና ዘረኛ አካሄድ ያለጥርጥር ቆም ብሎ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ ሕዝቡ ለተዛባና አጥፊ አስተሳሰብ ተገዥ እንዳይሆን መንግሥትና ኃላፊነት የሚሰማቸው ወገኖች ሁሉ ጥረት እንዲያደርጉም ለማሳሰብ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በሥራ ላይ ያዋለችው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ‹‹ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ›› መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ አገሪቱን 11 ክልሎች እንዲኖራት አድርጓል፡፡ ከ700 በላይ ወረዳዎችና 17 ሺሕ የሚደርሱ ቀበሌዎች ከመኖራቸውም በላይ ከ80 የማያንሱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ዕውቅና የሰጠ ሥርዓት ነው፡፡
በዚህ ያልተማከለ መንግሥታዊ ሥርዓት በአገሪቱ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የኖረው ‹‹አንድ አገር፣ ባንዲራ፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ…›› ወደሚል ጭፍለቃ ይደረግ የነበረው ጉዞ ተገትቷል፡፡ በዚህም ማንነታቸውና ታሪካቸው ተደፍቆ የኖሩ ሕዝቦች በነፃነትና በእኩልነት መንፈስ የመንቀሳቀስ ዕድል አግኝተዋል፡፡
ከሁሉ በላይ በራሳቸው ቋንቋ የመዳኘትና የመማር፣ እንዲሁም በየብሔሩ ተወላጆች የመተዳደርና የመመራት ጅምር ተፈጥሯል፡፡ ክልሎች በጋራ የገነቡት የፌዴራል መንግሥት (ከነስብጥር ችግሮቹ) አቋቁመው እየተዳደሩም ይገኛሉ፡፡
‹‹ይህ መንገድ ለ25 ዓመታት በማራመዱ የሕዝቦችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ ተሳትፎና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት አምጥቷል፤›› የሚሉ ወገኖች በአንድ በኩል አሉ፡፡ በሌላ ወገን ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የአገሪቱን ሕዝቦች ነጣጥሏል፡፡ ጠባብነትና የጎሳ ፖለቲካ ተንሰራፍቷል፡፡ የአገሪቱ ድንበር፣ የወደብ ሀብትና የዜጐች ተዟዙሮ የመንቀሳቀስ መብት ለአደጋ ተጋልጧል የሚል ተከታታይ ጩኸትም አልቆመም፡፡
በእነዚህ ሁለት ጠርዞች መሀል ላይ ያለው መከራከሪያ ደግሞ የፌዴራል ሥርዓቱን ሳይኮንን ብሔርና ቋንቋ ተኮር መሆኑ ያለውን አደጋ የሚያቀነቅን ነው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ በኋላ ወደ አሀዳዊነት ሊመለስ ባይችልም ጂኦግራፊ፣ ሥነ ልቦናና ማኅበራዊ ትስስርን የዘነጋ ቋንቋና ማንነት ተኮር አከላለል የጠባብነትና የጎሳ ፖለቲካ መባባስ ዕድል እያሰፋ ነው፤›› የሚል ነው፡፡
ይህን ሐሳብ እነ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ካሉበት መድረክ አንስቶ ኢዴፓ፣ መኢአድና መሰል የተሻለ ተቀባይነት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያቀነቅኑት ነው፡፡ እንዲያውም በቅርቡ ‹‹ዘመን›› ለተሰኘው መንግሥታዊ መጽሔት ሐሳባቸውን ያካፈሉት ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹እናንተ መድረክ ለምን አይዋሀድም ትላላችሁ፡፡ ለ25 ዓመታት አገር የመራው ኢሕአዴግ፣ ሰፊ ካፒታልና ከስድስት ሚሊዮን በላይ አባል ያለው ኢሕአዴግ እንኳን እስካሁን ከግንባርነት አልፎ አንድ ውህድ ፓርቲ መሆን አልቻለም፡፡ ይኼ ደግሞ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ውጤት ነው፤›› ነበር ያሉት፡፡
አደጋው ግን ይኼ ብቻ አይደለም፡፡ ብሔር ተኮር ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በየዓመቱ ከፍተኛ ወጪ እየተመደበለት በፌስቲቫል መልክ በብሔራዊ ደረጃ እየተከበረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ተሞክሮ ከአገር አልፎ ለአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ‹‹ልምድ›› ይሆናል ተብሎም ዓለም አቀፍ መድረኮች ሳይቀሩ በአዲስ አበባ ተከፍተዋል፡፡ ኅትመቶች፣ ዶክመንተሪዎችና የተለያዩ ክርክሮችም ተካሂደውበታል፡፡
ያም ሆኖ ግን አሁንም ‹‹የማንነት ጥያቄ›› መንግሥት እንደሚለው ‹‹ተመልሶ ያለቀ ጉዳይ›› አልሆነም፡፡ ለአብነት በደቡብ ክልል (ኮንሶ፣ ጋሞጎፋ፣ ካፋ…)፣ በአማራ ክልል (የቅማንት)፣ በትግራይ (የወልቃይት) ተደጋግሞ የሚጮኽ ድምፅ አለ፡፡ አስከፊው ነገር በውህደትና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ‹‹ኅብረ ብሔራዊ›› ትስስር ይፈጠራል እየተባለ ዜጎች በብሔርና በሃይማኖት ሰበብ እየተገለሉና እየተሰደዱ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የአማራ ክልል ተወላጆች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች፣ የትግራይ ተወላጆችም በሰሜን ጎንደር በቅርቡ የደረሰባቸውን ጥቃት ያጤኑዋል፡፡
ብሔር ተኮር ፌዴራል ሥርዓቱ በተለያየ መንገድ በማንነታቸው የሚሰባሰቡ ዜጐችን አበራክቷል፡፡ ቀስ በቀስ እንኳን የፖለቲካ ድርጅትና የአክሲዮን ማኅበር ይቅርና ‹‹የፀበል ፀዲቅ ማኅበር›› እንኳን በብሔር የሚደራጅ ሆኗል፡፡ ዕቁብ፣ ቅሬና ደቦ ሳይቀሩ በመንደርተኝነት ተቃኝተዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ሃይማኖትን ከብሔር፣ ጋብቻን ከዘር ሐረግ ጋር ለማስተሳሰር የሚያዳክሩንን ‹‹ተው!›› ያላቸው አልነበረም፡፡
በመንግሥት አሠራርና ሥርዓት ውስጥም ከፌዴራላዊ ሰንደቁ ይልቅ የክልል ባንዲራዎችና ኮፍያዎች በርክተው ይታያሉ፡፡ ከፌዴራሉ መንግሥት ቋንቋ ይልቅ የየብሔሩ ቋንቋዎች ይበልጥ ተፅዕኖ ፈጥረዋል፡፡ ከፌዴራል ፖሊስ ጀምሮ ‹‹የፌዴራል›› የሆኑ ሚዲያዎች፣ ስትራቴጂዎችና ዕቅዶች የተቀባይነት ደረጃቸው እየወረደ የመጣ መስሏል፡፡ ለዚህ አብነቱ አሁን በተጨባጭ በክልሎች እየታየ ያለው እውነታ ነው፡፡
አንዳንድ የፌዴራል መንግሥታት ጥናት ላይ ያተኮሩ ምሁራን ‹‹የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ሀብትና አቅም ወደ ክልሎች መከፋፈል አለበት፡፡ የተሰበሰበው ሥልጣንም ሊበተን ይገባል፤›› ሲሉ ይደመጣል፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነት ግን ‹‹እንኳን ዘንቦብሽ›› የሚሉት ነው፡፡ ክልሎች በዚህም ደረጃ ‹‹ድንበሬ፣ ወሰኔ፣ የግል መሬቴ…›› የሚሉት ከአገር የወጣ አስተሳሰብ አየሩን ሞልቶታል፡፡
አዲስ አበባ ከመላው ኢትዮጵያ ሕዝቦች ሀብትነትም አልፋ የአፍሪካ መዲና ሆናለች፡፡ ይሁንና ከኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ጋር እንኳን የሚያስተሳስራትን የጋራ ማስተር ፕላን መተግበር የማትችልበት ደረጃ ተፈጥሯል፡፡ ሌላው ቀርቶ መዲናዋ ለምትጠጣው ውኃና ለምትደፋው ቆሻሻ ‹‹ከሌላ አገር ጋር የመደራደር ያህል›› ሁኔታዎች እየከበዷት መጥተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ የከተማዋ የረጅም ጊዜ ጉዞም ቅርቃር ውስጥ እየገባ ይመስላል፡፡ ግን ለምን መባልም አለበት፡፡
የፌዴራል ሥርዓቱ ዜጐች በእኩልነትና በነፃነት አንድ ጠንካራ አገር የመገንባት ህልም ነው ሊኖረው የሚችለው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን በየመንደሩ ተመሳሳይ ቋንቋ መናገር የሚችሉ ጥቂት ወገኖች ተሰባስበው ‹‹ማንነታችን ይታወቅ›› ነው እያሉ ያሉት፡፡ ከዚያም አልፎ ወደ ታሪክ መነጣጠቅ፣ ደምና አጥንት መቁጠር ለመግባት የተጀመረው ጥድፊያ አገር የሚያፈርስ ጅምር ነው፡፡ አንዱ ወደ ቀኝ ሌላው ወደ ግራ መዘረጣጠጥና መፈላቀቅ አገር ያፈርስ እንደሆነ እንጂ ሊገነባ አይችልም፡፡
በዚህ ላይ ‹‹ካልበላሁት ልድፋው›› ባዩ ፖለቲከኛ የብሔር ጥላቻን በጠባብነት መርዝ እየለወሰ በመዝራት ላይ ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ግብ ብዙ ‹‹አገሮችን›› መፍጠር የሆነ ይመስል እገሌ ይገንጠል፣ ከእነገሌ ጋር አንድ ነን እያለ ይለፍፋል፡፡ ይህ ሁሉ ቀዳዳ የተከፈተው ደግሞ ያለጥርጥር ጠንካራ ውህደት፣ ብሔራዊ መግባባትና ትስስር ባለመፈጠሩ ነው ባይ ነኝ፡፡
ሌላው በፌዴራል ሥርዓቱ አፈጻጸም ውስጥ አንድ ዓብይ ተግዳሮት ታይቶ መፈተሽ ያለበት ‹‹አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ›› የሚካሄደው መጋጋጥ ነው፡፡ በአገሪቱ ለብሔር፣ ለእምነት፣ ለፆታና ለዕድሜ ብዝኃነት የተሰጠውን ትኩረት ያህል ‹‹የአመለካከት ብዝኃነት›› እንደሌለ የመቁጠር ዝንባሌ እየገነገነ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከዴሞክራሲ ምሰሶዎች (የሐሳብ ነፃነት፣ መደራጀት፣ መቃወምና ድጋፍ ማድረግ…) ጋር ክፉኛ ሊጋጭ ይችላል፡፡
በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አመለካከትና ፖሊሲ ውጪ የሚያራምዱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ አራማጆች እየተዳከሙ መጥተዋል፡፡ እርግጥ ለእነዚህ ኃይሎች መዳከምና መውደቅ ቀዳሚዎቹ ተወቃሾቹ ራሳቸው ቢሆኑም ፍርኃትን አስወግዶ፣ የመደራጀትና ሐሳብን የመግለጽ ልዕልና የማረጋገጥ ኃላፊነት የመንግሥትም ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ‹‹ከልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ፖሊሲ›› ውጪ ማቀንቀን ‹‹ኃጢያት›› ከመሰለ የሰላም በሮች ይዘጋሉ፡፡ የፀብ፣ የነውጥና የግጭት በሮች ይበረገዳሉ፡፡
የፌዴራል ሥርዓቱ የአመለካከትና የፖለቲካ ልዩነት ያለውን ዜጋ አቻችሎ ስለመያዝ ብቻ አይደለም መጨነቅ ያለበት፡፡ በብሔርና በማንነት ደረጃም ቢሆን ለዘመናት ተገፍቶ የኖረውን ሁሉ ዕውቅና እየሰጠ ሲያጎለብት፣ ብዙኃኑን አለመግፋቱና አለመድፈቁን እየፈተሸ ሊሄድ ይገባል፡፡
ከዚህ አንፃር በቀዳሚነት የኦሮሞና የአማራ ብሔሮች ቀድመው ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ሕዝቦች እስከ 68 በመቶ የአገሪቱን ሕዝብ ያህል ቁጥር ይይዛሉ፡፡ በቆዳ ሽፋን ረገድም ሰፊውን ድርሻ ከመያዛቸው ባሻገር በተማረ የሰው ኃይል፣ በሀብትና ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ረገድ የአገሪቱ እምብርት ናቸው ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡ ስለዚህ የእነዚህን ሕዝቦች ተጠቃሚነትና እኩልነት ብቻ ሳይሆን ‹‹እየተበደልኩ ነው›› የሚለውን ስሜት ተገንዝቦ መልክ ማስያዝ የሥርዓቱ ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ‹‹ተበደልኩ›› የሚለው ስሜት የሚመነጨው በፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ከሌሎች ብሔሮችና ሕዝቦች ያነሰ ተጠቃሚ ስለሆኑ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከብዝኃነት ወይም ከታሪክ አጋጣሚ ከነበራቸው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሥፍራ አንፃር አገራዊ ስሜታቸውን የማያጡበት ብልኃት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ በየትኛውም ብሔር ውስጥ ተሰንቅሮ የግል ፍላጎቱን ለማቀንቀን የሚሻው ጥገኛ ይልቅ፣ ይህን ክፍተት መሠረት አድርጎ ሕዝብን ለማነሳሳትና ሥርዓቱን ለማደፍረስ እንደማይመለስ መገመት ተገቢ ነው፡፡
የኢፌዴሪ (የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት) በሕገ መንግሥቱ አጽንኦት ሰጥቶ የደነገጋቸውን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ትኩረት ሰጥቶ መተግበርም ዋነኛው የሥርዓቱ ዋስትና ነው፡፡ በዚህች አገር ከ20 ዓመታት በፊት የወጣ ሕገ መንግሥትን ዛሬም ድረስ ‹‹በማስፈጸም አቅም ማነስ›› ሰበብ ተግባራዊ አለማድረግ ውጤቱ አደገኛ ነው፡፡
በመረጃ ነፃነት፣ በመደራጀት፣ ነፃ ማኅበራትን በማቋቋም፣ በዜጐች የትም ተዘዋውሮ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብት፣ በሰላምና ደኅንነት የመኖር መብት፣ ሃይማኖትን በነፃነት የማራመድ መብት፣ የሕግ የበላይነት፣ በየመስኩ የግልጽነትና ተጠያቂነት፣ የዜጐች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት … (እንደመጣልኝ የዘረዘርኳቸው) ይበልጥ ተከብረው ሕዝቡ የፌዴራል ሥርዓቱን እንዲያምነው መሆን አለበት፡፡ እዚህ ላይ በፌዴራል ሥርዓቱ ስም በየክልሉና በየመንደሩ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት፣ ሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነት ካቆጠቆጠ መንገዱ ሁሉ ውድቀት ነው፡፡ የሕዝብ ቅያሜና ቁጣም ሊቀር አይችልም፡፡
በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ‹‹ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል›› የሚለው ብሂል አይሠራም ባይባልም፣ ዋነኛው ሕዝብ ማሳመኛ ግን ተግባር ነው፡፡ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ በሚገኙ አንዳንድ ክልሎች ሕዝቡን ፊት ለፊት ወርዶ በልበ ሙሉነት ማናገር የተሳናቸው ፖለቲከኞች ለምን በዙ? ፍትሐዊ የሀብት፣ የሥራ ዕድልና የሥልጣን ክፍፍልን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ምክክር እንዴት እየነጠፈ ሄደ? በአገራዊና በብሔራዊ ጉዳይ በአንድ መንፈስ ‹‹ቀጭን ትዕዛዝ›› የሚያወርድ ለምን ጠፋ (ኢዴሞክራሲያዊ ባህሪ እንኳን ቢኖረው) ብሎ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡
ዛሬ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በአመለካከት… የቆዘሙና የተለያየ አቋም የሚያራምዱ ዜጐች መብዛታቸውን ማየት እየተቻለ ነው፡፡ እነዚህን ኃይሎች በበሰለ የፖለቲካ ድርድርና ዴሞክራሲያዊ ውይይት ወደ አገራዊ የጋራ አጀንዳ የሚያስጠጋ የስበት ማዕከል መፍጠር ይጠይቃል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ የታጨቁ የመርህና የአፈጻጸም ተግዳሮቶችን ደፍሮ በመቅረፍና የማሻሻያ ዕርምጃዎችን ፈጥኖ በመውሰድ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ እናንተስ?!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡