Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየቤት ውበት

የቤት ውበት

ቀን:

መኖሪያ ቤት፣ መሥሪያ ቤት ወይም የትኛውም ዓይነት ቦታ ሲገነባ የውጪና የውስጡም ገጽታ ይታቀዳል፡፡ ከቀለም ምርጫ አንስቶ ውበት ያላብሳሉ የሚባሉ ቁሳቁሶች እንደ አንድ ኅብረተሰብ ባህል፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሥርዓት ሊወሰኑ ይችላሉ፡፡ መኖሪያም ይሁን መሥሪያ ቤት እንደየማኅበረሰቡ አንዳች መንገድ ቢከተሉም፣ የውበት መለኪያ ሚዛን ተመሳሳይ የሚሆንበት አጋጣሚም አይታጣም፡፡ ለምሳሌ በክር የተጠለፈ ወይም የሰበዝ ስፌት፣ በእጅ የተሠራ ዳንቴል ወይም የእንስሳት ቆዳ እንደ ጌጥ የሚሆኑባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ አበባ፣ ፎቶግራፍና የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች ለማጌጫ የዋሉባቸውም ይጠቀሳሉ፡፡

ዛሬ ዛሬ ሰዎች ከተወለዱበት፣ ከሚኖሩበትና ከሚያምኑበት ነገር አንፃር መኖሪያቸው ወይም መሥሪያቸውን ለማሳመር ሙያተኛ (ኢንቲሪየር ዲዛይነር) ይቀጥራሉ፡፡ በመኖሪያቸው እንደ አክሱም ሐውልት ያሉ ቅርሶች በቅርፅ የሚያሠሩ ይጠቀሳሉ፡፡ ንግሥተ ሳባ ወደ ንጉሥ ሰለሞን ያደረገችውን ጉዞ የሚያሳዩ የቤት መገልገያዎችን  በቅርፃ ቅርፅ መልክ ለጌጥነት የሚጠቀሙም ጥቂት አይደሉም፡፡ ቤት፣ ቢሮ፣ የሠርግ አዳራሽ፣ ሬስቶራንት አልያም ለማንኛውም አገልግሎት የሚውል ቦታን በግላቸው የሚያስጌጡም እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡

ሰዎች ካላቸው የቦታ ስፋት አንፃር የቱን ዕቃ እንዴት ቢያስቀምጡ፣ ቦታቸውን በአግባቡ መጠቀም ይችላሉ? የትኛው ቀለም ምን ዓይነት ሥነ ልቦናዊ አስተዋጽኦ አለው? የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ ለሚፈልጉ ግለሰቦች ሥልጠና የሚሰጡት ደግሞ የምስራች አበበና ራሔል ታደለ ናቸው፡፡ ሥልጠናቸው ማንኛውንም ዓይነት ሥፍራን በግል ለማስዋብ (ኢንቲሪየር ዲኮሬሽን) ያስችላል፡፡

- Advertisement -

ሁለቱም 24 ዓመታቸው ሲሆን፣ የአርክቴክቸርና ኧርባን ፕላኒንግ ምሩቃን ናቸው፡፡ ማንኛውም ሰው በኢንቲሪየር ዲኮሬሽን የዓመታት ትምህርት ሳይወስድ የራሱን መኖሪያና መሥሪያ ቤት በቀላሉ ዲኮር እንዲያደርግ ያስተምራሉ፡፡ ትምህርቱ የአንድ ማኅበረሰብ ባህልና አኗኗርን በመመርኮዝ በቀላሉ በሚገኙ ቁሳቁሶች ዲኮር ማድረግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅና በምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች የሚዘወተሩ ባህላዊ መገልገያዎች ካለንበት ጊዜ ጋር አብረው እንዲሄዱ ተደርገው ይቀርባሉ፡፡ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን እሴትም ያንፀባርቃሉ፡፡

ብረት ምጣድና ሰፌድ እንደ ግርግዳ ጌጥ ይሆናሉ፡፡ ሰዓትና መብራት ሆነውም ያገለግላሉ፡፡ ሙቀጫን የመሰሉ ባህላዊ ቁሳቁሶችም በዲኮር ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ የጥበብ ነጠላ ለጠረጴዛ ልብስ ወይም መጋረጃ ይውላል፡፡ እቴጌ ዲኮር በተሰኘ ድርጅታቸው ኢንቲሪየር ዲኮር የሚያስተምሩት ወጣቶቹ፣ ማንኛውም ዓይነት ቁሳቁስ ጌጥ መሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ የቦታ ስፋትን ያማከለ የቁሳቁስ አቀማመጥ ወይም የቀለም ምርጫ፣ በዕለት ተዕለት ሕይወት ያለውን ትልቅ ቦታም ያስረዳሉ፡፡ በተለይ ለቤት (ሆም ዲኮር) ትኩረት የሰጠ ሥራ ላይ የተሰማሩትም፣ ሙያው በሰዎች አኗኗር ያለውን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት ነው፡፡

ወጣቶቹ ከተመረቁ በኋላ የአርክቴክቸርና ኢንጂነሪንግ ሶፍትዌሮች ያስተምሩ ነበር፡፡ ትምህርቱን በግልና በቡድንም ይከታተሉ ከነበሩ ሰዎች አብዛኞቹ በአርክቴክቸርና (ሥነ ሕንፃ) ኢንጂነሪንግ የተሰማሩና ዕውቀት ለማዳበር የሚፈልጉ ነበሩ፡፡

ከሙያው ውጪ ቢሆኑም፣ የሆም ዲኮር (የቤት ውስጥ ማስጌጥ) ዝንባሌ ያላቸው ይማሩ ነበር፡፡ ይህን ፍላጎት ያስተዋሉት ወጣቶቹ፣ ሰዎች በአካባቢያቸው በቀላሉ በሚያገኙት ነገር ዲኮር ለማድረግ የግድ ብዙ ዓመት መማር አይጠበቅባቸውም በሚል አጫጭር ሥልጠና ለመስጠት ወሰኑ፡፡ ብዙዎች እንደማስዋቢያ የማይቆጥሯቸው፣ ነገር ግን ታሪክና ባህልን የሚያንፀባርቁ ቁሳቁሶች ላይ አተኩረውም ከዓመት በፊት ሥራ ጀመሩ፡፡

‹‹ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎች ብዙ እንደሆኑ ስናይ የኢንቲሪየር ዲኮር ማስተማሪያ አዘጋጅተን ሥራ ጀመርን፤›› ትላለች ራሔል፡፡ ከ61 ዓመት የቤት እመቤት እስከ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና በተለያየ ሙያ የተሰማሩ ሰዎች ትምህርቱን ከሰጧቸው መካከል ይገኙበታል፡፡ የምስራች፣ ‹‹ኢንቲሪየር ዲኮር ዕድሜና ጾታ አይወስነውም፡፡ የአርክቴክቸር ወይም ተመሳሳይ ትምህርቶች ያልወሰዱ ሰዎች ቢሆኑም፣ የሚኖሩበትን ወይም የሚሠሩበትን ቦታ ማስጌጥ ይችላሉ፤›› ትላለች፡፡

ትምህርቱ በቤዚክና አድቫንስድ ደረጃ ይሰጣል፡፡ አንዳንዶች በቤዚክ (ጀማሪ) ደረጃ የጥቂት ወራት ትምህርት ወስደው ቤታቸውን ለማስዋብ ብቻ ይገለገሉበታል፡፡ ትምህርቱን በስፋት የሚወስዱና እንደ ሙያ የሚይዙም አሉ፡፡ መሠረታዊ ትምህርቱን ብቻ የሚማሩ 3,000 ብር የሚከፍሉ ሲሆን፣ በስፋት በሶፍትዌር የታገዘ ሥልጠና የሚወስዱ 4,500 ብር በ30 ሰዓት ይከፍላሉ፡፡

የምስራች እንደምትለው፣ ብዙዎች የሚኖሩበት ወይም የሚሠሩበትን ቦታ ዘልማዳዊ በሆነ መንገድ ያስውባሉ፡፡ ለምሳሌ በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ዕድሜና የጤና ሁኔታ ያላገናዘበ የዕቃ አቀማመጥና የቀለም ምርጫ ይስተዋላል፡፡ እንደ ኮንዶሚኒየም ያሉ ጠባብ ቤቶች ምን ያህል ዕቃ ይይዙልኛል? ብለው የሚጨነቁም ብዙዎች ናቸው፡፡ አንዳንዴ ሰፋ ያለ ቤት ኖሯቸውም ምን ዓይነት ቁሳቁስ መሸመት እንዳለባቸው ባለማወቅ የሚቸገሩ አሉ፡፡ ወደ ሥራ ቦታ ሲመጣም፣ ተመሳሳይ እክሎች ሊገጥሙ ይችላሉ፡፡ ሰዎች ይህንን ችግር በቀላሉ እንዲቀርፉ ማስቻል እንደሚፈልጉ ትገልጻለች፡፡

‹‹የግድ በባለሙያ መሠራት ያለባቸው ነገሮች ቢኖሩም፣ ግለሰቦች በራሳቸው ሊወጧቸው የሚችሉም አሉ፡፡ ‹‹የቀለም፣ ቁሳቁስና አቀማመጥ ምርጫን በአጭር ጊዜ መማር ይቻላል፤›› ትላለች የምስራች፡፡ ሐሳቧን የምትጋራው ራሔል፣ በማስዋብ ጊዜ ባህላዊ ቁሳቁሶችን መጠቀም እንዲለመድ ማድረግ እንደሚፈልጉ ትገልጻለች፡፡ ብዙዎች ከኢትዮጵያ ውጪ የሚሠሩ ቁሳቁሶች ብቻ ውበት እንዳላቸው በማመን ችላ የሚሏቸው የአገር ውስጥ ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ እንዲውሉም ይመክራሉ፡፡

አንዳንዴ ጌጥ ሊሆኑ የሚችሉ ቁሳቁሶች ይጣላሉ፡፡ እንደ ውኃ ፕላስቲክ ያሉ  የምግብና የመጠጥ ማስቀመጫዎችን በተለያየ መንገድ መጠቀም ይቻላል፡፡ ቀለም በመቀባት፣ ልዩ ቅርፅ እንዲይዙ በማድረግም ለጌጥነት ይውላሉ፡፡

‹‹ባህላዊ ቁሳቁሶችን መጠቀም ማንነትን ይገልጻል፡፡ በቀላሉ በሚገኙ ቁሳቁሶች የሚማርክ ነገር መፍጠርም ይቻላል፤›› ትላለች ራሔል፡፡ ከሰዎች አኗኗር አንፃር በቀላሉ የሚገኙ ቁሳቁሶችን ጥበብ በተሞላት መንገድ ማዘጋጀት የሚያስደስታቸው ሰዎች እንደሙያ ወስደው ካፌ፣ ሬስቶራንትና ሆቴል ለማስጌጥም ይጠቀሙበታል፡፡ ቀርክሀ የብዙዎች ምርጫ ሲሆን፣ የካርቶን ቅዳጅ፣ ባልጩት፣ ብሎኬትና ሌላም መጠቀም ይቻላል፡፡

 ወጪ ከመቆጠብና ቀለል ያለ ሕይወት ከመምራት አንፃር እነዚህ ቁሳቁሶች ያላቸውን ሚና የምስራች ትናገራለች፡፡ አንድ ሰው ካለው የኢኮኖሚ አቅም አንፃር መጠቀም የሚችለውን ቁሳቁሶች በሥልጠናው ያካተታሉ፡፡ የቤቱና የቢሮው አካባቢ ተፈጥሯዊ ይዘትና አቀማመጥም ከግምት ይገባሉ፡፡

ራሔል በበኩሏ ሰዎች በሚሠሩበት ቦታ ያለው የዕቃ አቀማመጥ በሚሠሩት ሥራ ላይ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ትገልጻለች፡፡ አንድ ዕቃ ከሌላው ጋር ሊኖረው የሚችለው ውህደት አንዴ ከታወቀ ዕውቀቱ ከቤትና ከቢሮ በተጨማሪ ማንኛውንም ቦታ ዲኮር ለማድረግ እንደሚውልም ታክላለች፡፡ ‹‹ለምሳሌ ብርቱካናማ ቀለም ለሥራ የሚያነሳሳና ደስተኛ የሚያደርግ ቀለም ነው፡፡ አንድ ቦታ ለሚውልበት አገልግሎት የሚሆን ቀለም ሊቀባ ይገባል፤›› ስትል ታስረዳለች፡፡

ብዙዎች ስለኢንቲሪየር ዲኮር በቂ መረጃ አላቸው ብሎ ለመደምደም ቢያስቸግርም፣ አንዳንዶች ኢንተርኔት ላይ በሚያገኟቸው ጽሑፎችና ምስሎች በመታገዝ ቤታቸውን ለማስዋብ ይሞክራሉ፡፡ ቤትን ማስዋብ በድረ ገጽ በማየት ይሁን ሥልጠና በመውሰድ ቢለመድ መልካም እንደሆነ ወጣቶቹ ይገልጻሉ፡፡

‹‹ማስዋብ ብዙ ወጪ የሚያስወጣና የቅንጦት እንደሆነ የሚያስቡ አሉ፡፡ ይህ የተሳሳተ ነው፡፡ ለኑሮ ወይም ለሥራ ምቹ ሁኔታን በቀላሉ መፍጠር ለሁሉም ሰው ያስፈልጋል፤›› ትላለች የምስራች፡፡

እቴጌ ዲዛይንን የሚያስተዋውቁት በማኅበረሰብ ድረ ገጽና በሌሎችም መንገዶች እንደሆነ የምትናገረው ራሔል፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስለሥልጠናው ያለው መረጃ እየሰፋ መምጣቱን ትናገራለች፡፡ የሚኖሩበትን ወይም የሚሠሩበትን ቦታ በሚፈልጉት መንገድ ለማስዋብ ከመማር ጎን ለጎን ባለሙያ የሚያማክሩም እየበዙ ነው፡፡

የኢንቲሪየር ዲኮር ትምህርት በሌሎች አገሮች የተስፋፋ ሲሆን፣ በሙያው ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚያገኙም በርካቶች ናቸው፡፡ ባለሙያዎቹ ለሠርግ፣ ለበዓላት ወይም ለሌላ ዝግጅቶችም አንድን ቦታ ያስውባሉ፡፡ የኦንላይን ኮርሶች በመውሰድ ቤትና ቢሯቸውን የሚያውቡም አሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...