Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እኛነት መንምኖ እኔነት ገነነ!

ሰላም! ሰላም! ማንጠግቦሽ ሰሞኑን የማይክል ጃክሰንን ዘፈን እየዘፈነች ወደፊት አስመስላ ወደኋላ የመሄድ ዳንስ ስትደንስ ወለም ብሏት ወደቀች። ‹‹አሁን እስኪ በስተርጅና ‘ሙንወክ’ ስትደንስ ወደቀች ብዬ ነው ለእነባሻዬ የማወራው?›› ስላት፣ ‹‹ሙዚቃ የዓለም የነፍስ ቋንቋ ነው። ምነው አንተ በአንድ ምላስህ ዘረኝነትና ጠባብነትን እያወገዝህ በሌላኛው ዳንስን በዕድሜ ትከፋፍላለህ?›› አትለኝ መሰላችሁ? ‘በደንባራ በቅሎ  ቃጭል ተጨምሮ’ ይሏችኋል ይኼ ነው። አሁን እስኪ ከማይክል በፊት እዚህ አጠገብሽ ስንት ዘፋኝ እያለ፣ እነ ጥላሁን እያሉልሽ፣ እነ ብዙነሽ አሳድገውሽ እንደ ጎረምሳ…›› ብዬ ሳልጨርስ፣ ‹‹አንበርብር በማይክል ጃክሰን ጃኬት እንዳደግኩ አትርሳ፤›› ብላ የባሰ ነርቬን ነካችው፡፡ ምን ለማለት ነው? ‹‹እኛም ለብሰነዋል፤›› አልኩ እኩል ለመሆን የትውስታ ጠጠር እያነጣጠርኩ። ‹‹ኡኡቴ ምነው ያኔ ስንተዋወቅ አይደል እንዴ ያቺን የአስመራ ሸራ የቀየርከው፤›› ተባልኩ። ኋላማ፣ ‹‹ምነው አንቺ ምነው አንተ…›› እየተባባልን የአስተዳደግ እንከናችንን ስንማዘዝ የደመነው ሰማይ ሿ ብሎ ምድሩን ያጎርፈው ጀመር። መደማመጥ ስላልቻልን ኃይል ቁጠባ ዝናብ እስኪያበራ ዝም ዝም ሆነ። ይኼኔ ነው ይኼን በየአቅጣጫው አንደማመጥ ማለታችን እየከረረ ከሄደ ዘንድ የኖህ ዘመን ዝናብ ዘንቦ ዝም ያባብለን ይሆን ብዬ ያሰብኩት።

ቀና ብዬ ማንጠግቦሽን ሳያት እኔ የማስበውን ታስብ ይመስል ቁጣዋ በርዶላት ሳቅ ብላ አየችኝ። ዕድሜ ለዝናቡ አልኩኝ። ኋላ ባሻዬ የማንጠግቦሽን ወለምታ ሊያሹ ሲመጡ፣ ‹‹ይኼስ ታሽቶ ይድናል። ግና ዘንድሮ የማይታሸው የአፍ ወለምታ በዝቷል። ከጯሂው ብዛት ከሰሚው ማነስ የተነሳ ወለም ወለም የሚለው እያደር እልፍ ሆኗል፤›› ሲሉ የኖሁን ዘመን ዶፍ እንደ መፍትሔ ባነሳላቸው፣ ‹‹ሰማይ እኮ ቧንቧ ወይም አፍ አይደለም አንበርብር። ሲያሻህ ከፍተህ መልሰህ አትዘጋውም። እሱ የዘጋውን የሚከፍተው፣ የከፈተውን የሚዘጋው እንደሌለ ሁሉ የእኛንም ነገር ለእሱ ለፈጣሪ መተው ነው፤›› ብለው ገሰጹኝ። የአፍታ ማስታወቂያ ባደናቆራት አገር የአፍታ ጥሞና ወስዶ መደማመጥ የሚሰምር አይመስልም። ያውጣን ነው!

እናም በማንጠግቦሽ ወለምታ ምክንያት የደጁን ትቼ የቤቱን ሥራ መሥራት ጀመርኩ። ማንጠግቦሽ አልጋዋ ላይ ተኝታ፣ ‹‹ያንን አንሳው፣ ያንን ጣለው፣ ስጡን አስጣው፣ አስገባው…›› ስትለኝ መዋል። እንዲህ በሪሞት ኮንትሮል የሚታዘዝ ሮቦት ሆኜ ማን ያየኛል? … አገር ምድሩ። መቼም ወሬኛን ወሬ አይቸግረውም አይደል? ግን ለምንድነው ባለመብት መብት የሚቸግረው? ‘ጀስት’ ጥያቄ ነው። ‘አንበርብር ተከርቸም ገባ። ፓ! ሚስቱ ቀለደችበት!’ ሲሉኝ እሰማለሁ። አንዳንዱ ወሬ ብቻውን ኦሊምፒክ ባይኖር እንኳ ሯጭ ያደርጋል እኮ እናንተ። ለነገሩ ኦሊምፒክንስ የፈጠረው ወሬ አይደል? ቀይ ይኼን ይኼን በሪዮ ኦሊምፒክ ከኬንያዎቹ ጋር ሒሳብ እናወራርድና እንጨዋወተዋለን። እና ምን አማረኝ እያልኩ ነበር? አዎ፣ መሮጥ አማረኝ። ብን ብሎ መጥፋት ፈለግኩ። ግን ይኼ ሩጫችንን ሁሉ በሕገወጥ ስደት መዝገብ ውስጥ የሚያስከትብ መጤ ሥልት መቼ ያፈናፍንና? ‘ሰው ከፍቶት ከሄደ…’ ተብሎ በተዘፈነባት አገሬ አካሄዳችን ሁሉ ሕገወጥ እየተባለ ይሆናል እንዴ? ኧረ እንዴት ነው የዘንድሮ አንድምታና ትንታኔ።

እናላችሁ በቀደም ፀሐይ በቀኝ ታይታ በግራ ላጥ ብላ ስትጠፋ ያሰጣሁት ድርቆሽ ዝናብ ሊመታው ሆነ። እንጀራችን እንኳን ደርቆ እንዲሁም ውኃ እየገባው አልታኘክ ብሏል። ደግነቱ ማንጠግቦሽ ዛራና ቻንድራን በንቃት እየተከታተለች ስለነበር ማካፋት መጀመሩን አይታ አልተቆጣችም። ላስገባው ስወጣ የጋራ መፀዳጃ ቤት ተጠቅሞ የሚመለስ ጎረቤቴ ጠጋ ብሎ፣ ‹‹አይዞህ አንበርብር ቻለው። ዛሬ አልጋቸው ላይ በድሎት ተኝተው፣ ኃላፊነታቸውን ዘንግተው ያሻቸውንና ያማራቸውን እየበሉ እየጠጡ የሰቡት ብዙ ናቸው። በአገር የመጣ ነው ቻለው፤›› ብሎኝ አይሄድ መሳላችሁ? በገዛ ሚስቴ? ምነው ሰው ግን ሽቦው በረገፈ አልጋ ያለምርጫው እየተኛ በሰው ሚስት ይፈተፍታል?

ግርም አለኝ። ሌት እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር ያድራል። ለባሻዬ  ባጫውታቸው፣ ‹‹ሚስትን መታዘዝ፣ ሰው ማክበር፣ መተዛዘን፣ አንዱ ሲደክም አንዱ መበርታት ወግ አልነበረም ወይ? ፈጣሪ አይወደውም ወይ?›› ብላቸው፣ ‹‹ኧረ ይወደዋል። ምነው ምን ገጠመህ?›› በማለት ያስመረረኝን እንድነግራቸው ጠየቁኝ፡፡ መንደርተኛው የሚለኝን ነገርኳቸው። ‹‹አይ አንተ። ይኼማ የሐበሻ መዝናኛ ነው፤›› ብለው ሳቁ። ባሻዬ እንዲህ በማይሳቅ ሳቁ ማለት ሁነኛ ፍቺና ትንታኔ አላቸው ማለት ነው። ‹‹እንዴት?›› አልኳቸው ባጭሩ። አንዳንዴ የተንዛዛ ጥያቄም ላልተፈለገ መልስ ምክንያት ይሆናል። ዘንድሮ ደግሞ ‘መጠየቅ መብቴ ነው’ በሚል ዓላማ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ተንቀሳቃሾች ጥያቄ እያንዛዛ በተንዛዛ መልስ ድንኳን ይጥላሉ አሉ። ሲባል የምሰማውን ነው።

እና ባሻዬ ምን አሉኝ፣ ‹‹ሐበሻ እኮ አንድ ልዩ ፀባይ አለው። ዳር ወዳድ ነን አየህ። አንድ ነገር ስንሰማም ሆነ ስናይ ራሳችንን ማዕከል አናደርግም። ለምን? ብዙ ለማለት ስለሚመቸን ነው። በብዙ የማናውቀው ነገር ውስጥ አዋቂ እንድንሆን መንገድ ማመቻቻ ዘዴ ነው። ለምሳሌ ምን ልበልህ? አዎ ቤት ብትሠራ ኡኡኡ ይኼን ቤት እዚህ ጋ እንዲህ ያደረግከው ምን ሆነህ ነው? እንዲህ ብታደርገው?›› የሚልህ መሐንዲስ ተብሎ ይመጣል። መኪና ብትዛ አትነግረኝም ነበር? ምን አስቸኮለህ? እነዚህ መኪኖች እኮ አሁን አይፈለጉም። ልሽጠው ብትል ምን ልትሆን ነው? ብሎ የመኪና ኤክስፐርት ይሆንብሃል። ስትማርም ሥራ አለው ብለህ ነው? ያበላል? አሁን እኮ ዘመኑ የምንትስ ነው ትባላለህ። ምንም ዓይነት ቤት ሥራ፣ ምንም ዓይነት መኪና ግዛ፣ ምንም ዓይነት ትምህርት ተማር እሽክርክሪቱ አንድ ነው፤›› ሲሉኝ ጥፋ ጥፋ ሲለኝ ውስጤ ይሰማኛል። በነገራችን ላይ ባሻዬ መልሱን ነገረውኛል። መቼም ዘንድሮ መልስ ሲባል ሰው ጥይት እየመሰለው ሩጫ አብዝቷል አሉ። መልሱ ደግሞ ደግ አረገ ብሎ በያዙት መግፋት!

ማንጠግቦሽ ቆማ መሄድ ስትችል አስቡት (ወለምታ ሳምንት ካስተኛን ሌላ ሌላውማ ምን ሊያደርገን እንደሚችል) ያሽቆለቆለው ኢኮኖሚዬን ለመካስ ተፍ ተፉን ተያያዝኩት። ዘንድሮ ኢኮኖሚዬ በዚህን ያህል ፐርሰንት ያድጋል ብሎ ለመተንበይ ያልተቸገረ ያለ አይመስለኝም። እንዲህ ብዬ ዘመናዊ ባለሦስት ፎቅ መኖሪያ ቤቱን እንዳሻሽጥለት ለነገረኝ ደንበኛዬ ባጫውተው፣ ‹‹ታዲያስ አሁን መንግሥታችንና አይኤምኤፍ በግምት እንጂ በሪፖርት እንደማይጣሉ ገባህ?›› አለኝ። ምንድነው የሚያወራው? ብዬ ዝም አልኩ። እኔ እኮ አንዳንዱ ሰው ጫፍ ሲሰጠው ደርሶ ቅጠላ ቅጠሉን ሥራ ሥሩን ምንጥር የሚያደርገው ነገር ይገርመኛል። ግን ከሁሉ በላይ የገረመኝ እንዲህ ለወለምታና ለጉንፋን ሳምንት ሁለት ሳምንት ተኝተን የምንነሳ ሰዎች፣ እንደ አሉባልተኛ እሳት ማራገብ መቀጠላችን ነው።

የባሻዬን ልጅ እንዲህ ብለው እሱም እንደ እኔ ተገርሞ፣ ‹‹አይገርምህምም? ልክ እሳት እንደማያውቅ ሁሉ፣ እንዳልተለበለበ ሁሉ።…›› ብሎ ከኪሱ ስልኩን አወጣና ዩቲዩብ ላይ ሰሞኑን ዱባይ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት እየነደደ ከመከስከስ አደጋ የተረፈውን አውሮፕላን ያሳየኝ ጀመር። ‹‹ምንድነው?›› ስለው እየው ሰውን አለኝ። ተሳፋሪዎች ሲተራመሱ አያለሁ። የመኖር ተስፋ ያለው ከመብዛቱ የተነሳ አብዛኛው ተሳፋሪ (መስኮት ሰብሮ መዝለል ሲገባው) ሻንጣውን ለመያዝ ይራኮታል። የባሻዬ ልጅ ቀና ብሎ ዓይን ዓይኔን እያየ፣ ‹‹እሳት በፈጀው ሕዝብና መፈጀቱን በረሳ ሕዝብ መሀል ያለው ልዩነት ይኼ ነው፤›› ሲለኝ፣ ‹‹የመኖር ጉጉት ከሌለህ እንኳን እሳት ወደ አንተ መጥቶ አንተው ዘለህ ትገባለህ፤›› ልለው አስቤ ምን አባባለኝ ብዬ ተውኩት። ወይ እሳትና ሻንጣ!

በሉ እንሰነባበት። ሰሞኑን ስብሰባ የሚጠራኝ ሰው በዝቷል። ሰንበቴ እጠራለሁ፣ ዝክር ድረስ እባላለሁ፣ ጠበል እጠራለሁ፣ አራስ ጠይቅ ይሉኛል እሄዳለሁ። ጨረስኩ ስል ደግሞ ባሻዬ የአካባቢውን ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት በተመለከተ አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ ተብሎ ወደዚያ መጓዝ ጀመርኩ። ድንቅ የሚለኝ ቆሻሻ ለማስወገድ ስንሰበሰብ ቆሻሻ አራግፈን መሆን እንዳለበት የሚናገር ሰው አይቼ አለማወቄ ነው። ምነው? ቆሻሻ እኮ ብዙ ዓይነት ነው። ሐሳብም እኮ ቆሽሾ ይሰነፍጣል፡፡ ካላመናችሁኝ ቆሽሸው የዓለምን ታሪክ ያቆሸሹ ሰዎችን ታሪክ አንብቡ። ዛራና ቻንድራ እንዳለቀ ማለቴ ነው። ደግሞ በነፃነት የራስን የዕይታ ዕድል በራስ በመወሰን መብታችን መጣብን ብላችሁ ሰላማዊ ሠልፍ ውጡ አሉዋችሁ። ሆሆ! ሰላማዊ ሠልፍ ስል ታዲያ መንገዴ ላይ አንዱ፣ ‹‹አንበርብር…›› ብሎ ጠራኝ። ‹‹ወይ?›› አልኩት። ‹‹ቅዳሜ ከዚያ ከዘመመው የስልክ እንጨት ብንጀምር ይሻላል ከኮብልስቶኑ ማለቂያ?›› አይለኝም? ድብድብ አይመስልም እስኪ አሁን ሰው መንገድ ላይ አስቁሞ እንዲህ ቢላችሁ? ‹‹ምንድነው እሱ የምንጀምረው?›› ስለው፣ ‹‹ሰላማዊ ሠልፉን ነዋ!›› ብሎኝ አረፈው።

ስብሰባው ካለቀ በኋላ ተገላገልኩ ስል ባሻዬ፣ ‹‹እኔና አንተ የግል ስብሰባ አለን፤›› ብለው ቤታቸው ይዘውኝ ሄዱ። ‹‹ኧረ እኔም እጠይቅዎታለሁ ስል ነበር? ቅዳሜ ሰላማዊ ሠልፍ ተጠርቷል ሲባል ሰምቼ?›› ብላቸው፣ ‹‹ቆይ ገና ብዙ ትሰማለህ፤›› አሉኝ። ‹‹ጥሪው?›› ብል ሥራ ስፈታ ታይቶኝ ‹‹ወሬውን!›› ብለው ሳቁ። እንጃ ባሻዬ ዘንድሮ ሳቅ ሳቅ ብሏቸዋል። እኔን ግን ጨንቆኛል። ጠሪዬን፣ መካሪዬን ፣ ወዳጄን፣ ጠላቴን፣ መሪዬን… አላይ አላውቅ ብዬ ጨንቆኛል። ሁሉም በየፊናው ያሻውን መዝሙር ይዘምራል። ያሻውን ባንዲራ ይሰቅላል። ሁሉም በተለያየ ልሳን ያለኔ ማን አለ ይለኛል። እኛነት መንምኖ እኔነት ገነነ ማለት ይኼ አይደለም? መልካም ሰንበት!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት