ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ሆኗል፡፡ ከመስቀል አደባባይ ጀምሮ በከፍታ ላይ የተዘረጋውን የቀላል ባቡር ሃዲድ ከተሸከሙት ኮንከሪቶች አቅራቢያ ታዳጊ ሕፃናትና ወጣቶች ገሚሱ አጀብ ብለው፣ ገሚሱ ተበታትነው ይታያሉ፡፡ እየተሯሯጡ የሚጫወቱ ታዳጊ ሕፃናትም አሉ፡፡ አብዛኞቹ ግማሽ ሊትር ውኃ የሚይዘውን ባዶ የፕላስቲክ ጠርሙስ ይዘዋል፡፡ ከመስቀል አደባባይ ወደ ሜክሲኮ በሚወስደው አቅጣጫ በኩል ወደ ለገሀር ከሚያሳጥፈው መንገድ አጠገብ ካለው ኮንክሪት ጋር ደግሞ ከ10 የሚበልጡ ታዳጊዎች ባዶ የፕላስቲክ ውኃ መያዣ ይዘው ተሰብስበዋል፡፡
ከመሃላቸው በቁመቱ ከእነሱ የሚበልጥ ከያዘው ዕቃ ውስጥ ታዳጊዎቹ ወደያዙት ፕላስቲክ ማስቲሽ ይጨምራል፡፡ አምስት ደቂቃ ያህል እንደቆዩ ታዳጊ ሕፃናቱ ማስቲሽ የያዘ ዕቃቸውን ይዘው መበታተን ጀመሩ፡፡
ገሚሱ ወደ ሜክሲኮ ገሚሱ ወደ ለገሃር ሲሄዱ፣ ሌሎቹ ደግሞ ወደ መስቀል አደባባይ ወረዱ፡፡ ማስቲሽ ሲቀዳ የነበረው ሰውም ከአካባቢው ራቀ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ታዳጊ ሕፃናቱ ማስቲሽ ያለበትን ፕላስቲክ፣ አንዳንዶቹ ከእጅጌያቸው ሥር በመክተት አንዳንዶቹ ደግሞ ከደረታቸው በመለጠፍና በለበሱት ልብስ በመሸፈን፣ የዕቃውን አንገት ብቻ አውጥተው ማስቲሹን መሳብ ጀመሩ፡፡
ወደ ለገሃር በመጓዝ ላይ ከነበሩት ታዳጊ ሕፃናት የ12 እና የ13 ዓመቶቹ የአንድ አካባቢ ልጆች ይገኙበታል፡፡ የመጡት ከአርሲ ነጌሌ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ጐዳና ላይም ሦስት ወራትን ቆይተዋል፡፡ አንዱ ከደረቱ ሥር በሹራቡ የሸፈነውን የፕላስቲክ ዕቃ፣ አፉን ብቻ አውጥቶ የማስቲሹን ሽታ በአፉ እየማገ ከቀየው እንዴት ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ ነገረን፡፡
የ12 ዓመቱ ታዳጊ በአርሲ ነጌሌ ይማርበት ከነበረው የመንግሥት ትምህርት ቤት ሦስተኛ ክፍልን ጨርሶ ወደ አራት ሲዘዋወር ነው አዲስ አበባ የመጣው፡፡ አመጣጡም እሠራለሁ ብሎ ነው፡፡ ሆኖም በሥራ ሳይሆን በልመና ተሰማርቶ አዲስ አበባን ከረገጠ መንፈቅ እንኳን ሳይሆነው የማስቲሽ ሱሰኛ ሆኗል፡፡ በቀን ከሚጐርሳት ቡሌ (ትርፍራፊ ምግብ) የበለጠም ለሚያሸተው ማስቲሽ ዋጋ ይሰጣል፡፡
እኛን እያዋራ፣ በ10 ብር የገዛትና በፕላስቲክ መያዣው ውስጥ የምትታየው ጥቂት ማስቲሽ ሳትደርቅ ከጓደኛው እየተቀባበለ ሳብ ሳብ ማድረግ ጀመረ፡፡ ‹‹እንዳይርበንና እንዳይበርደን ማስቲሹን ይዘን ስንገኝም ፖሊሶች ስለሚመቱን ሕመሙ እንዳይሰማን›› በሚል ማስቲሹን የሚስቡት ታዳጊ ሕፃናት፣ የሱስ ጥማታቸውን ለማርካት ከልመና በተጨማሪ ሸክምና አንዳንድ ሥራዎችን እንደሚሠሩ ይናገራሉ፡፡
በቀን የሚያገኙትንም ለቡሌና ለማስቲሽ ያውላሉ፡፡ ቤንዚንና ሲጃራ ከማስቲሹ ያነሰ ዋጋ ቢኖራቸውም፣ ማስቲሽ ለመግዛት የገንዘብ አቅም ካላነሳቸው በስተቀር አይመርጧቸውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የማስቲሹን ያህል ስለማያረኳቸው ነው፡፡
ታዳጊዎቹ እንደሚሉት፣ በኖሩበት አርሲ እየተማሩ የነበረ ቢሆንም፣ ክረምቱ አልፎ መስከረም ትምህርት ሲከፈት ወደ አርሲ አይመለሱም፡፡ ይልቁንም ራሳቸውን ከትምህርት ነፃ አድርገው በአዲስ አበባ ጐዳናዎች መኖርን ይመኛሉ፡፡
ለሥራ፣ ከቤተሰብ ስለተጣላን፣ ቤተሰብ ስለሞተብን በሚል ሰበብ ወደ አዲስ አበባ የሚነጉዱት ታዳጊ ሕፃናት፣ በየጐዳናው ትክክል አይደላችሁም ወይም ችግራችሁን እንፍታላችሁ ብሎ የሚገራቸው ጠፍቶ፣ ለራሳቸውም ለአገራቸውም እንዳይሆኑ በሚያደርጉ የተለያዩ ሱሶች ተጠምደው ይታያሉ፡፡ ቀላል የባቡር ሃዲድ መስመር ባለበት ስፍራ በተለይ በከፍታ ላይ በሚሄድባቸው አካባቢዎች ቀን ላይ ከሥር ተቀምጠው መኪና ሲመጣ ለመለመን ሲሯሯጡ፣ ቡሌ እየተሻሙ ሲበሉ፣ ሲሰዳደቡ አሊያም ሲጫወቱ፣ ምሽት ላይ ከበው እሳት ሲሞቁ፣ ማስቲሽና ቤንዚን ሲምጉ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ድርጊቱም በተለያዩ የከተማዋ ጐዳናዎች ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ለቤተሰብ አለኝታ፣ ለአገር መከታ ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡት ታዳጊዎችም፣ እንደዋዛ እየጠፉ ነው፡፡
የታዳጊ ሕፃናትና ወጣት ጐዳና ተዳዳሪዎች በአዲስ አበባ ጐዳናዎች መበራከትን ከራሳቸው የልጅ አስተዳደግና አኗኗር ጋር እያነፃፀሩ ከንፈር የሚመጡ፣ ልባቸው ተነክቶ በየጊዜው ምግብ እየሰጡ የሚያልፉና የሚረዱ፣ መንግሥትን የሚወቅሱና ዝምታን የመረጡ ግለሰቦች ሲኖሩ ከዚሁ ጐን ለጐን ታዳጊ ሕፃናቱ ትምህርት ካላገኙና ከሱሳቸው ካልተላቀቁ እያደጉና እየጐረመሱ ሲሄዱ፣ ለደኅንነት ሥጋት ይሆናሉ በማለት አስተያየታቸውንም የሚሰነዝሩ አሉ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ፣ አዲስ አበባ ላይ ሥራ እንሠራለን፣ ገንዘብ እናገኛለን በሚል ግንዛቤ ማነስ፣ ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሱ መብዛታቸውን መታዘባቸውን ገልጸው፣ ለደኅንነት ሥጋት የመሆናቸው አጋጣሚ ግን አነስተኛ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሆዳቸው ባዶ የሆነና የተራቡ ቢሆኑም የሚነጥቁ አይደሉም፡፡ መለመን መልካም ነው ባይባልም፣ አብዛኞቹ የሚለምኑና ለራሳቸውም የተጐዱ፣ የሚያሳዝኑ ናቸው፤›› ይላሉ፡፡
ኮሚሽኑ ወንጀልን ከመከላከል ጐን ለጐን ወንጀል ፈጻሚ የነበሩ ወደ መልካም ሥራ እንዲመለሱና እንዲሠሩ እያስቻለ መሆኑን፣ ሆኖም ከጐዳና ኑሮ ለማላቀቅ ሥልጠና ካገኙ በኋላ ወደጐዳና የተመለሱ፣ አቅም እያላቸው ቁጭ ማለትን የመረጡ፣ ቁጭ ከማለት ብዛትም ጉልበታቸውን ያደከሙ እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ከታዳጊ ሕፃናቱ ጐዳና ተዳዳሪዎች ሊስትሮና ጀብሎ ሠርተው ጐዳና የሚያድሩ እንዳሉም ይናገራሉ፡፡
‹‹ቀንም ሌትም ከተማዋን ስለምንዞር ክረምቱ ላይ ጐዳና ላይ የሚወጡ መብዛታቸውን ከእኛ የበለጠ የሚያይ የለም›› የሚሉት ኮማንደር ፋሲካ፣ ለዚህ ምክንያቱ ትምህርት ሲዘጋ ከየክልሉ አዲስ አበባ መጥተው የሚሠሩና መስከረም ሲጠባ ወደቀያቸው የሚመለሱ በመኖራቸው ነው ይላሉ፡፡ ሆኖም ታዳጊ ሕፃናቱም ሆነ ወጣቶቹ ወደ መልካም ኑሮ እንዲመለሱ፣ ኅብረተሰቡ ለሚለምኑት ከመስጠት ይልቅ ከተቋማት ጋር ተባብሮ በመሥራትና ልጆቹም በትምህርት በሚለወጡበት መንገድ በመተባበር ችግሩን በጋራ መፍታት አስፈላጊ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡
‹‹አንድም ልጅ ሳይማር እንዳይቀር›› የሚለው የአገሪቱ የትምህርት መርህ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጐዳና ላይ ያሉትንና ከቤተሰብ ጋር ሆነው የማይማሩትን በየክፍለ ከተማው በመመዝገብ የትምህርት ተቋደሽ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የቢሮው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይናገራሉ፡፡
ኃላፊው አቶ አበበ ቸርነት እንደሚሉት፣ በ2008 በጀት ዓመት ለ502 ጐዳና ተዳዳሪና ዕድሜያቸው በተለያየ ምክንያት ለትምህርት ደርሶ መማር ላልቻሉ ልጆች የሁለት ወራት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ በ2009 በጀት ዓመት ደግሞ መደበኛ ትምህርት እንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡ ከዚህ ቀደም የተጀመረውና ለተቸገሩ ተማሪዎች የሚሰጠው የምገባ ፕሮግራምም የሚቀጥል ይሆናል፡፡
አቶ አበበ እንደሚሉት፣ ጐዳና ተዳዳሪ ሕፃናትን ወደ ትምህርት ለማምጣት በየክፍለ ከተማ የሚገኙ የትምህርት ቢሮዎች ችግር እየገጠማቸው ነው፡፡ ዛሬ አንድ ቦታ የነበረ ጐዳና ተዳዳሪ ነገ ሌላ ቦታ የሚሄድ መሆኑ አንዱ ችግር ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የምግብ ነው፡፡
ልጆቹ ከተማሩ በኋላ ደብተር የሚያስቀምጡበት ቦታና በትምህርታቸው የሚረዳቸው አለመኖሩ ሌላው ችግር ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ትምህርት ቢሮው እየሠራ ቢሆንም፣ ከችግሩ ውስብስብነትና ስፋት አንፃር ጐዳና ላይ ያሉ ታዳጊ ሕፃናትን መድረስ ተችሏል ማለት አይቻልም፡፡
በጐዳና ላይ ያሉ ሕፃናት የትምህርት ተቋዳሽ ከማድረግ በተጨማሪ ጤናቸው የተጠበቀ እንዲሆን መሥራትም ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ ጐዳና ላይ የሚያድሩ ልጆች ከሌሎቹ በበለጠ ለተለያዩ በተለይም ለተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ ቢሆኑም፣ ለእነሱ ተብሎ ተለይቶ የተቀመጠ የጤና አጠባበቅ ሥርዓትና አካሄድ የለም፡፡ በታመሙ ጊዜ እንደ ማንኛውም ተገልጋይ በመንግሥት ጤና ጣቢያዎች ነፃ ሕክምና ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ በተለይ ጐዳና ላይ ከመሆናቸው አንፃር ድንገተኛ አደጋ ሲገጥማቸው የሕክምና ዕርዳታ የሚያገኙ ቢሆንም፣ ከሱስ ጋር በተያያዘ ለሚገጥማቸው የአዕምሮ መታወክ፣ የመተንፈሻ አካል ችግርና ተላላፊ በሽታዎች ‹‹እንዴት ናችሁ? ብሎ በያሉበት የሚጐበኛቸው አካል የለም፡፡ አንዳንድ በጐ ፈቃደኛ ግለሰቦች ግን በጐዳና ላይ ታመው ሲያገኟቸው ወደ ጤና ጣቢያ ይወስዷቸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የሥራ ሒደት መሪ አቶ ሙሉጌታ አድማሱ፣ በተለይ ከአምስት ዓመት በታች ላሉ ጐዳና ተዳዳሪ ሕፃናት (በብዛት ከእናቶቻቸው ጋር ነው የሚኖሩት) ክትባት ይሰጣል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን፣ በጐዳና የሚኖሩ ታዳጊ ሕፃናትን ዓላማ አድርጐ የሚሰጥ የተለየ ሕክምና የለም፡፡ ማደሪያና መዋያቸውን በየጊዜው የሚቀያይሩ በመሆናቸውም፣ በያሉበት ሄዶ ሕክምና ለማድረግ የተደራጀ መረጃ የለም፡፡
በጐዳና ላይ ያሉ ታዳጊ ሕፃናት የሚራቡ፣ ጐዳና ላይ የሚያድሩ የሚፀዳዱ ከመሆናቸው አንፃር ለበሽታ ተጋላጭነታቸው የሰፋ ነው፡፡ በሱስ ከመጠመዳቸው ባለፈም ለመተንፈሻ አካልና ለአእምሮ መታወክ ሕመም የተጋለጡ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ለሕፃናቱ ቀጥታ ተደራሽ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ሲሠራ አይታይም፡፡
በኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የሕግ ዝግጅትና የሜድኮሌጋል ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ ባህሩ ዘውዴ፣ በጐዳና ላይ የሚኖሩ ታዳጊ ሕፃናት ኬሚካል በማሽተታቸው ለተለያዩ ችግሮችና ሕመሞች የሚጋለጡ ቢሆንም፣ በባለሥልጣኑ በኩል ሥልጠና የሚሰጠው ለባለድርሻ አካላት፣ ለሚኒስቴር ሠራተኞች፣ ሕክምና ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ትምህርት ቤት ላሉ ታዳጊዎች በሱስ አማጭ ኬሚካሎች ላይ ሥልጠና እየተሰጠ ቢሆንም፣ በጐዳና ተዳዳሪዎች ላይ አለመሥራቱን የሚገልጹት አቶ ባህሩ፣ ዕቅድ ሲታቀድ ጐዳና ተዳዳሪዎች ታሳቢ መደረግ እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡
ዕቅድ ሲታቀድ ግን በከተማዋ የሚገኙ ጐዳና ተዳዳሪዎችን ለመድረስ የሚያስችል የተደራጀ መረጃ የለም፡፡ በአዲስ አበባ አጠቃላይ የጐዳና ተዳዳሪዎችን ቁጥር ገምቶ ከማስቀመጥ ባለፈም፣ የመጡበትን አካባቢና ባህል፣ ዕድሜ፣ ፆታ፣ የትምህርት ደረጃ፣ አካል ጉዳተኛ ይሁኑ ባለሙሉ አካል፣ ቤተሰብ ይኑራቸው አይኑራቸው፣ የጤንነታቸው ሁኔታና የትምህርት ደረጃቸውን አስመልክቶ በየፈርጁ የተደራጀ መረጃ የለም፡፡ ይህም ጐዳና ተዳዳሪዎችን በተለይም ታዳጊዎቹን ለመድረስ እንቅፋት ሆኗል፡፡
በሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር የሕፃናት ክፍል ዳይሬክተር አቶ ህሩይ ባህረጥበብ ሚኒስቴሩ መንግሥታዊ ካልሆኑና ከሆኑ አካላት ጋር በመሆን ከሐምሌ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ አዲስ አበባ የሚገኙ ጐዳና ተዳዳሪ ሕፃናትን ከቁጥራቸው ጀምሮ አጠቃላይ መረጃ ለመሰብሰብና ለመለየት፣ በመረጃው መሠረትም ቤተሰብ ያላቸውን ለመቀላቀል፣ የሌላቸውን ደግሞ እንደየችግራቸው መፍትሔ ለመስጠት እየሠራ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እንደየ ችግራቸው በመለየት ሥራውም ከ18 ዓመት በታች ያሉ በሙሉ የሚካተቱ ይሆናል፡፡
አብዛኞቹ በከተማዋ ጐዳና የሚኖሩ ታዳጊ ሕፃናት ከክልል የፈለሱ ናቸው፡፡ ብዙዎቹም በሱስ ተጠምደዋል፣ ከትምህርት ርቀዋል፣ ከወላጅና ቤተሰብ ፍቅር ተነጥለዋል፡፡ ልጅ አድጐ ራሱን፣ ቤተሰቡንና አገሩን ይጠቅማል ከሚባለው አስተሳሰብ ርቀው በልጅነታቸው እየተቀጩ ነው፡፡ ይህንን መጠነ ሰፊ ችግርም አዲስ አበባ ብቻዋን ልትቀርፈው አትችልም፡፡ በመሆኑም የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ከክልሎች ጋር በመወያየት ከክልል የሚፈልሱና ጐዳና ተዳዳሪ የሚሆኑ ታዳጊዎችን ከችግሩ ለማላቀቅ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን አቶ ህሩይ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኙ ጐዳና ተዳዳሪዎችን አስመልክቶ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በተደረገላቸው እገዛና ድጋፍ ከጐዳና ተነስተው ራሳቸውን የቻሉ ቢኖሩም፣ ችግሩ ሲቀረፍ አይታይም፡፡ ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ለዓይን እየበዙና ቀድሞ እምብዛም ያልተለመዱ ኬሚካሎችን የመማግ ድርጊቶች፣ በጐዳና ተዳዳሪ ሕፃናት እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም በሚሸተቱ ኬሚካሎች ላይ ተግባራዊ የሆነ የቁጥጥር ሕግ አለመኖሩ አንዱ ችግር መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በአገሪቱ የሚገኙ ጐዳና ተዳዳሪ ሕፃናትም በቀላሉ የሚገኙትን የጥፍርና የፀጉር ቀለም፣ ቤንዚን፣ የመኪና ፖሊሽ፣ ፍሉድና ማስቲሽ (ሙጫ) ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ታዳጊ ሕፃናቱ ከቅጭታቸው ያገግሙ ይሆን?