Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዩኒሴፍ የሴቶችና የሕፃናት ክብካቤን ለማስፋፋት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር ስምምንት አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአስቸኳይ ሕፃናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) ባሠራጨው መረጃ መሠረት፣ በአሁኑ ወቅት ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ በተቆራረጡባት ኢትዮጵያ፣ ከአምስት ዓመት በታች ዕድሜ ክልል ላይ ለሚገኙ 40 ከመቶ ሕፃናትም አገሪቱ የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ እንደተሳናት ይጠቅሳል፡፡

ከዚህም ባሻገር ሰባት ከመቶ ብቻ ሕፃናት ውልደታቸው በአግባቡ ሲመዘገብ፣ ከነፍሰ ጡር ሴቶች መካከልም አንድ ሦስተኛው ብቻ በጤና ተቋማት ልጆቻቸውን ይገላገላሉ ያለው ዩኒሴፍ፣ የሕፃናትና እናቶች ክትባትም ቢሆን ሽፋኑ ከ70 በመቶ በታች እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ይበልጡን ደግሞም በአሁኑ ወቅት የተከሰተው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) በርካታ ሕፃናትና እናቶችም ለወረርሽኙ ሰለባ በመሆን ላይ እንደሚገኙ ጠቅሶ እንዲህ ያሉ ችግሮች ለመቋቋም ከሃይማኖት ተቋማት ጋር አብሮ ለመሥራት መነሳቱን ይፋ አድርጓል፡፡

በመሆኑም ማክሰኞ፣ ሐምሌ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ በኩል፣ ከኢትዮጵያ ሙስሊም ልማት ኤጀንሲ፣ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ከኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ተወካዮች ጋር ዩኒሴፍ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መልሰ እንዳሉት ቤተ ክርሲያኒቱ ከፓትሪያኩ ጽሕፈት ቤት ጀምሮ እስከታችኛው አስተዳደር እርከንና መዋቅር ባሉት አደረጃጀቶች ውስጥ ስምምነት የፈጸመችባቸው መስኮች ላይ እንደምትሠራ አስታውቀዋል፡፡

የወጣቶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ሕይወት ላይ ለውጥ እንዲመጣና ከሚደርስባቸው ጥቃት ለመከላከልም የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ሃይማኖታዊ ግዴታውን እንዲወጣ ለማደረግ እንደሚሠራ የገለጹት የኢትዮጵያ ሙስሊም ልማት ኤጀንሲ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ሃጂ አዛም የሱፍ ናቸው፡፡ ከእስልምና መርሆዎች ጋር በማይቃረን በማንኛውም መስኮች አብሮ በመሥራት በሴቶችና ሕፃናት ላይ የተጋረጡ ችግሮችን ለማስወገድ ተቋማቸው መዘጋጀቱን ሃጂ አዛም አስታውቀዋል፡፡ ሌሎቹም የሃይማኖት ተቋማት ተመሳሳይ ሐሳቦችን አንፀባርቀዋል፡፡

የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ተወካይ ጊሊያን ሜልሶፕ በበኩላቸው፣ ዩኒሴፍ በአጋርነት ከሚመለከታቸው ጋር ሁሉ በመሥራት ሕፃናት ለመኖር ብቻ ሳይሆን ለብልጽግና ወይም ለመልካም ሕይወት ይበቁ ዘንድ የመሥራት ተልዕኮ እንዳነገበ፣ በዚህም አኳኋን እየሠራ እንደሚገኝ አብራርዋል፡፡

በዩኒሴፍና በሃይማኖት ተቋማቱ መካከል ስምምነት ከተደረገባቸው ዋና ዋና የጋራ የሥራ መስኮች መካከል የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ክብካቤ፣ የሕፃናትና የታዳጊ ወጣቶች ጤና፣ የክትባት፣ የጨቅላና የልጆች አመጋገብ፣ የሃይጅንና ሳኒቴሽን ማስፋፊያ ሥራዎች፣ የወሊድ ምዝገባ፣ የሕፃናት ጋብቻና ሌሎችም በርካታ መስኮች ላይ አብሮ ለመሥራት ስምምነት አካሂደዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች