የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዘመን ባንክ ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶችን ከኃላፊነታቸው እንዲታገዱ ማድረጉን አስታወቀ፡፡ ብሔራዊ ባንክ ሐምሌ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ መሠረት ከኃላፊነታቸው እንደታገዱ የተገለጸላቸው ሁለቱ የዘመን ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንቶች አቶ ሕላዌ ታደሰና አቶ ስብሃት በላይነህ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከብድር ፈቃድና ከውጭ ምንዛሪ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ አድሏዊ አሠራር ተፈጽሟል በማለት ዕርምጃውን እንደወሰደ የሪፖርተር ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች እንደሚገልጹት ደግሞ የብሔራዊ ባንክ ዕርምጃ ያልተጠበቀና ድንገተኛ ሆኗል፡፡
ብሔራዊ ባንክ በምክትል ፕሬዚዳንቶቹ ላይ የወሰደው ዕርምጃ ከሁለት ኩባንያዎች ጋር በተገናኘ ብድር የውጭ ምንዛሪ ፈቃድ አሰጣጥ ሒደት ላይ ግድፈት ታይቶባቸዋል በማለት የወሰደው ዕርምጃ ሲሆን፣ ከመደበኛው አሠራር ውጭ የሆነ አካሄድ ተከስቷል የተባለው ከአምስት ዓመት በፊት ነው፡፡
እንደ ምንጮች ገለጻ አቶ ሕላዌን ለዕገዳ ያበቃቸው ጉዳይ ፓዮኒዬር አግሮ ኢንዱስትሪ ለተባለ ኩባንያ የተሰጠ ብድር ነው፡፡ አቶ ስብሃት ደግሞ በተለይ ሴፍዌይ ለተባለ ኩባንያ እንዲፈቀድ ባደረጉት የውጭ ምንዛሪ ምክንያት ነው፡፡
ከሁለቱ ኃላፊዎች ጋር የተያያዙት ጉዳዮች ለአንድ ዓመት ያህል በብሔራዊ ባንክ ምርመራ ሲካሄድባቸው ቆይተዋል፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቶቹም ገዥው ባንክ ባቀረባቸው ጥያቄዎችና ምርመራ ሒደቶች ላይ ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል፡፡
የብድሩም ሆነ የውጭ ምንዛሪ አሰጣጡ ሕግና ደንብን የተከተለና የሕግ ጥሰት የሌለበት ስለመሆኑ ከአስረጂ መረጃዎች ጋር በማቅረብ የብሔራዊ ባንክ ምርመራ ሒደት ላይ ተከላክለዋል፡፡
የተፈጸመ የሕግ ጥሰት እንደሌለም ተከራክረዋል፤ ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ነገር ባለመኖሩ የዕገዳ ዕርምጃ ባንኩ ይወስዳል ተብሎ እንዳልተጠበቀ ምንጮች አስረድተዋል፡፡
በተለይ ለአንደኛው ኩባንያ ተፈቀደ የተባለው የውጭ ምንዛሪ መጠን ባላቸው የአሠራር ሥርዓትና በራሳቸው መንገድ ደንበኞቻቸውን በሚያስተናግዱበት አግባብ እንደተፈጸመ፣ ምንም ዓይነት የሕግ ጥሰት እንዳልነበረበት ኃላፊዎቹ ለማስረዳት ሞክረዋል፡
የብድር አሰጣጡም ቢሆን በብድር ኮሚቴ የሚወሰንና የታገዱት ኃላፊዎችም ያላቸው ድምፅ አንድ ብቻ በመሆኑ አድሏዊ አሠራር ሊፈጽሙ እንደማይችሉ ጠቅሰው፣ ለብሔራዊ ባንክ መግለጻቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎችም አሉ፡፡
ለአቶ ሕላዌ መታገድ ምክንያት የሆነው ፓዮኔር አግሮ ኢንዱስሪ ለተባለ የአክሰስ ካፒታል አካል ለሆነው ኩባንያ የተሰጠው ብድር፣ ተበዳሪው ድርጅት የተበደረውን ገንዘብ ከአምስት ዓመታት በፊት የወሰደውና ሊመልስ እንደማይችል በመታወቁ በተበላሸ ብድርነት ተመዝግቦ የተዘጋ ሒሳብ መሆኑ ይነገራል፡፡ ሆኖም አቶ ሕላዌ በባንኩ ውስጥ ካላቸው ኃላፊነት ጎን ለጎን በአክሰስ ካፒታል ውስጥም ሲሠሩ ስለነበር ይህም አግባብ ባለመሆኑ ምክንያት ብሔራዊ ባንክ የወሰደው ዕርምጃ አጠያያቂ እንዳልሆነ የሚልጹም አሉ፡፡ ለዕገዳ ያበቃቸው ጉዳይ ግን በባንኩ ባለድርሻዎች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኖ መገኘቱ ተሰምቷል፡፡ ሁለቱም ኃላፊዎች በባንኩ ውስጥ ከአምስት ዓመታት በላይ ማገልገላቸው ታውቋል፡፡