Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናግብፅ ናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭን ዳግም ለመቀላቀል መፈለጓን ኢትዮጵያ አደነቀች

ግብፅ ናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭን ዳግም ለመቀላቀል መፈለጓን ኢትዮጵያ አደነቀች

ቀን:

–  በናይል ትብብር ማዕቀፍ ላይ ጥያቄ እንዳታነሳ መክረዋል

ግብፅ ከስድስት ዓመታት በኋላ ናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭን (NBI) ደግሞ ለመቀላቀል መፈለጓን የኢትዮጵያ መንግሥት አደነቀ፡፡

የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ምክር ቤት 24 ጉባዔ ሰሞኑን በኡጋንዳ ካምፓላ በተካሄደበት ወቅት ነው ግብፅ ኢኒሼቲቩን ለመቀላቀል ፍላጐቷን ያቀረበችው፡፡ ይህንን ፍላጐቷንም የኢትዮጵያ ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ አድንቀዋል፡፡

ናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ እ.ኤ.አ. በ1999 የተመሠረተ ሲሆን፣ ዋነኛ ዓላማውም አሥሩ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ተፋሰሱን በጋራ ለማልማትና በፍትሐዊነት ለመጠቀም ነው፡፡ በዚህ ተቋም ውስጥ ግብፅ በዓባይ ተፋሰስ ላይ የቅኝ ገዥዎችን ኃይል በመጠቀም የገነባችውን ብቸኛ ተጠቃሚነት ለማፍረስ፣ በኢትዮጵያ አማካኝነት ከ12 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ውይይት መካሄዱ ይታወቃል፡፡

የውይይቱ ዓላማ ሁሉንም የዓባይ ተፋሰስ አገሮች በፍትሐዊነት የተፋሰሱ ተጠቃሚ የሚያደርግ የዓባይ ትብብር ማዕቀፍ (Cooperative Framework Agreement (CFA) በመፍጠር የዓባይ ተፋሰስ ባለሥልጣንን ማቋቋም ዓላማው አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያ አነሳሽነት የተጀመረው ውይይት እ.ኤ.አ. በ2010 የትብብር ማዕቀፉን በመቅረጽ ቢጠናቀቅም፣ ግብፅና ሱዳን የማዕቀፉን አንቀጽ 14 (b) በመቃወም ማዕቀፉን ተቃውመዋል፡፡ ይህ አንቀጽ ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች በፍትሐዊነትና ውኃውን መጠቀም እንደሚችሉ የሚገልጽ ነው፡፡

ይህንን መሠረት በማድረግም ግብፅ ራሷን ከናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ አግላ ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳና ኡጋንዳ የትብብር ማዕቀፉን በፊርማቸው ያፀደቁት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያና ብሩንዲ ደግሞ በሕግ አውጪ ተቋሞቻቸው አፅድቀው ሕግ አድርገውታል፡፡

ግብፅ ከስድስት ዓመት በኋላ ባለፈው ሳምንት በኡጋንዳ በመገኘት ኢንሼቲቩን ደግማ መቀላቀል እንደምትፈልግ ገልጻለች፡፡

‹‹ሁሉንም ተግዳሮቶችና አለመግባባቶች ወደ ጐን በመተው በናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ አባልነታችን መቀጠል እንፈልጋለን፤›› በማለት የግብፅ የውኃና መስኖ ሚኒስትሩ ሞሐመድ አብደል የመንግሥታቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኢኒሼቲቩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የግብፅን ፍላጐት የተቀበለ ቢሆንም፣ ዝርዝር ውይይት እንደሚያስፈልገውና ውይይቱንም ወደፊት ለማድረግ ቀጠሮ ይዘው ጉባዔያቸውን አጠናቀዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው በናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ የምሥራቅ አፍሪካ የተፋሰሱ አገሮች የቴክኒክ ትብብር ጽሕፈት ቤት (ENTRO) ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ፣ በናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ሥር ወዳለው ትብብር ግብፅ እንድትመጣ ኢትዮጵያ ቀደም ብላም ትሻ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ እንደ ግብፅ ሁሉ ሱዳንም የትብብር ማዕቀፉን እንዳልፈረመች ያስታወሱት አቶ ፈቅአህመድ፣ ሱዳን ግን በትብብር ውስጥ እንደቆየችና አሁንም ንቁ ተሳታፊ መሆኗን አስታውሰዋል፡፡

በሱዳን መንግሥት በኩልም በተደጋጋሚ ግብፅ ወደ ትብብር እንድትመጣ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ግብፅ ሰሞኑን ወደ ትብብሩ ለመመለስ ፍላጐት ብታሳይም፣ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጣለች፤ ይህ ደግሞ ትክክል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

ካቀረበቻቸው ጥያቄዎች መካከል የትብብር ማዕቀፉ ላይ ድጋሚ ውይይት እንዲደረግ የሚል ይገኝበታል ብለዋል፡፡ የትብብር ማዕቀፉ በስድስት አገሮች የተፈረመ እንዲሁም ሦስት አገሮች በፓርላማቸው ያፀደቁት በመሆኑ፣ ይህንን ማንሳት እንደማይቻል ነገር ግን በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ በኢኒሼቲቩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...