በሽብርተኝነት ተግባር ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው፣ እነ አቶ በቀለ ገርባ (22 ተጠርጣሪዎች)፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግን ክስ በመቃወም ያቀረቡት የቅድመ ክስ መቃወሚያ ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ውድቅ ተደረገ፡፡
የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች የተቀናጀ ማስተር ፕላንን ሽፋን በማድረግ፣ የኦነግን ዓላማ ለማስፈጸም፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ተቀስቅሶ የነበረን አመጽ እንዲስፋፋና ወደ ሌላ እንዲዛመት በማድረጋቸው የሰው ሕይወት መጥፋቱንና ከ122 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን ዓቃቤ ሕግ በክሱ መግለጹ ይታወሳል፡፡
እነ አቶ በቀለ ገርባ ባቀረቡት የቅድመ ክስ መቃወሚያ፣ በኦሮሚያ ተቀስቅሶ የነበረው የተቃውሞ አመጽ፣ ከጀርባው ምንም ዓይነት ወይም የማንኛውም ድርጅት እንደሌለበት መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡ ይህም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በፓርላማ መነገሩንና ‹‹የኦሮሚያ ተቃውሞ የመልካም አስተዳደር ችግር የቀሰቀሰው እንጂ ከጀርባው የማንም ጣልቃ ገብነት የለበትም፤›› ማለታቸውን በማስረዳት መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል ድርጊቱ ተፈጽሟል ቢባል እንኳን፣ የተፈጸመው በኦሮሚያ ክልል በመሆኑ፣ ክሱ መቅረብ ያለበት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሳይሆን፣ በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሆን እንዳለበት አዋጆችን ጠቅሰው ክሱን ተቃውመው ነበር፡፡ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ በሰጠው የመልስ መልስ፣ ድርጊቱን መፈጸማቸውን፣ ክሱን በአግባቡ መመሥረቱንና የፈጸሙትን ተግባርም ምስክሮቹን በማቅረብ ማስረዳት እንደሚችል በዝርዝር የቅድመ ክሱን መቃወሚያ በመቃወም ለፍርድ ቤቱ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም የክስ መዝገቡን መርምሮ በሰጠው ብይን፣ ተከሳሾቹ ባቀረቡት የቅድመ ክስ መቃወሚያ፣ የዓቃቤ ሕግን ክስ ሊያስተባብሉ አለመቻላቸውን በማስረዳት፣ የቅድመ ክስ መቃወሚያውን ውድቅ ማድረጉን በብይኑ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ነሐሴ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲሰጡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾቹ ብይኑን በመቃወም በችሎቱ ውስጥ ተቃውሞአቸውን በተለያየ መልኩ ገልጸዋል፡፡