የኦፔራ ሙዚቃ በማቀንቀን የታወቀችው ታዳጊዋ ሃና ግርማ፣ የበርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የሰጣትን የነፃ ትምህርት ዕድል ለመጠቀም ከአሜሪካ ኤምባሲ ቪዛ ጠይቃ በክፍሉ ሠራተኛ ብትከለከልም፣ ከአሳዳጊ ሞግዚቷ አርቲስት ቴዎድሮስ መኮንን (ቴዲማክ) ጋር ኤምባሲው ከተነጋገረ በኋላ ቪዛ ሊሰጣት መቻሉ ታወቀ፡፡
ኤምባሲው ለታዳጊዋ ቪዛ የከለከለበትን መንገድ በመጥቀስ ቴዲማክ ያሰማውን አቤቱታ በረቡዕ፣ የሐምሌ 27 ቀን 2008 ዓ.ም ዕትማችን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ቴዲማክ ለሪፖርተር ገልጾ እንደነበረው ‹‹የኤምባሲው ቪዛ ክፍል ባልደረባ የሆነ አሜሪካዊ ሥነ ምግባር በጎደለው ሁኔታ ታዳጊዋን ድምፃዊ አጉላልቷል፣ ሞራሏን በሚነካ መንገድ አስተናግዷታል፡፡››
ዘገባው ከወጣ በኋላ በማግሥቱ የኤምባሲው ቆንስላ ክፍል ኃላፊዎችና የባህል ማዕከል ተጠሪዎች ቴዲማክን ጠርተው በማነጋገርና ያጋጠመውን ጉዳይ እንዲያስረዳ በማድረግ፣ ከዋሽንግተን በተገኘው ይሁንታ አማካይነት ቪዛው ለታዳጊዋ መሰጠቱን ቴዲማክ አስታውቋል፡፡ በዚህም መደሰቱን፣ ‹‹በኤምባሲው ኃላፊዎች ቅሬታዬንና የደረሰብኝን አዳምጠው፣ ያጋጠመኝኝ አላስፈላጊ መጉላላት በመገንዘብ ላደረጉት ትብብር አመሰግናለሁ፤›› በማለት ገልጿል፡፡ የተሰጣቸው ሕጋዊ ኃላፊነት ያለአግባብ በመጠቀም ያለበቂ ምክንያት በርካቶችን ቪዛ የሚከለክሉ የኤምባሲው ባልደረቦችን የኮነነው ቴዲማክ፣ ቅሬታ የሚሰማና ጠርቶ የሚያናግር አምባሳደር፣ ቆንስላ ወይም የሚመለከተው ኃላፊ መኖሩ ጥሩ እንደሆነም ተናግሯል፡፡
ታዳጊዋ የኦፔራ ሙዚቃ አቀንቃኝ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የኦፔራ ሙዚቃን በማቀንቀን ትልቅ ዕውቅና ያገኘችው ታዳጊዋ ሃና ግርማ፣ በዓለም መድረክም ተቀባይነት እያገኘች የመጣች ሲሆን፣ ከሰሞኑ ታዋቂው የበርክሌ ዩኒቨርሲቲ የሰጣትን የሥልጠና ዕድል ግን እንዳለፈበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ከአንድ ዓመት በላይ የሚቆይ ቪዛ ኤምባሲው ስለሰጣት፣ በአሜሪካ ተዘዋውራና ጎብኝታ እንድትመለስ ለማድረግ ማሰቡን ሞግዚቷ ቴዲማክ ጠቅሷል፡፡
ታዳጊ ሃና በኢትዮጵያን አይዶል አማካይነት ለዕውቅና የበቃች ሲሆን፣ በወቅቱ የውድድሩ ዳኞች ከነበሩት አንዱ ቴዲማክ የታዳጊዋ ተሰጥኦ ጎልቶ እንዲወጣ ሲያግዛት እንደቆየና በኋላም አሳዳጊዋና ጠባቂ ሞግዚቷ በመሆን ሙዚቃ እየሠሩ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡