Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ ካቢኔ ለዓመታት ቅሬታ ሲቀርብባቸው ለቆዩ ጉዳዮች የመጨረሻ ውሳኔ ሰጠ

የአዲስ አበባ ካቢኔ ለዓመታት ቅሬታ ሲቀርብባቸው ለቆዩ ጉዳዮች የመጨረሻ ውሳኔ ሰጠ

ቀን:

የካሳ ክፍያ መመርያ ተሻሻለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከመመርያዎች ጋር የሚጣረሱ በመሆናቸውና ላለፉት አሥር ዓመታት ሲንከባለሉ በቆዩ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ መስጠቱን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኮንን አምባዬ ባለፈው ዓርብ ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የከተማው አስተዳደር የሰጠው ውሳኔ ታሪካዊ ሊባል ይችላል፡፡

ካቢኔው ውሳኔ ከሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል፣ የካሳ ክፍያ ላይ ማስተካከያ መደረጉ፣ ‹‹ሕገወጥ›› ባለይዞታዎች ‹‹ሕጋዊ›› ለማድረግ የወጣው መመርያ እንዲሻሻል መደረጉ፣ 600 ለሚሆኑ የአያት ሪል ስቴት ቤት ገዢዎች የካርታ ጥያቄ ምላሽ መስጠት፣ ‹‹ሕገወጥ ማኅበራት›› ሕጋዊ መደረጋቸው፣ በጂአይኤስ አለመጣጣም መስተናገድ ያልቻሉ የኮልፌ ነዋሪዎች ጥያቄ መመለሱ ውሳኔ ከተሰጠባቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በልማት ምክንያት ከቀያቸው የሚነሱ የአዲስ አበባ አርሶ አደሮችና ነዋሪዎች ዘወትር ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል የካሳ ክፍያ አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአርሶ አደር ልጆች በካሳ ክፍያ አይስተናገዱም ነበር፡፡

በአዲሱ የመመርያ ማሻሻያ አንድ አርሶ አደር ከቀየው ሲነሳ ምትክ ቦታና የማሳ ክፍያ ይከፈለዋል፡፡ ክፍያው አነስተኛ ነው ተብሎ በመታመኑ የከተማው አስተዳደር ቀደም ብሎ ለሰብል የሚከፈለውን ክፍያ ቀመር በ14 በመቶ፣ ለዛፍ ይከፈል የነበረውን በ42 በመቶና የጓሮ አትክልት በ45 በመቶ አሳድጓል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአስተዳደሩ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ግንባታዎች የሚከፈለው ክፍያ ዝቅተኛው 115 ሺሕ ብር ነበር፡፡ በአዲሱ ማሻሻያ ይህ ክፍያ ወደ 144 ሺሕ ከፍ ተደርጓል፡፡ የአርሶ አደር ልጆችም ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑት የካሳ ክፍያ ተጠቃሚ ሆነዋል ተብሏል፡፡

የከተማው አስተዳደር ከ1988 እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ በሕገወጥ መንገድ መሬት በመያዝ ግንባታ ያካሄዱ ወገኖችን ሕጋዊ ለማድረግ መመርያ አውጥቶ ነበር፡፡ በዚህ መመርያ መሠረት አንድ ባለይዞታ ከያዘው መሬት ውስጥ 75 ካሬ ሜትሩን በአካባቢው የሊዝ መነሻ ዋጋ፣ ቀሪውን ደግሞ በአካባቢው የጨረታ መነሻ ዋጋ እንዲከፍል ተደርጎ ነበር፡፡

ነገር ግን ክፍያው ከፍተኛ ነው በሚል መመርያው ይሻሻል የሚል ቅሬታ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ በዚህ መሠረት የከተማው አስተዳደር ካቢኔ 75 ካሬ ሜትር የነበረውን ወደ 150 ካሬ ሜትር አሳድጓል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ግዙፉ የሪል ስቴት ኩባንያ፣ አያት ሪል ስቴት፣ ለሕጉ በሚፃረር መንገድ ሰርቪስ ኳርተር በመሥራት ለተጠቃሚዎች ማስተላለፉ 600 ቤት ገዢዎች ካርታ እንዳያገኙ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ላለፉት አሥር ዓመታት ለእነዚህ ቤት ገዢዎች የተናጠል ካርታ መስጠት ሳይቻል የቆየ ሲሆን፣ ካቢኔው ባሳለፈው አዲስ ውሳኔ ቤት ገዢዎቹ ካርታ እንዲሰጣቸው ተወስኗል፡፡

በሌላ በኩል ከ1996 እስከ 1998 ዓ.ም. በ66 የቤት ሥራ ማኅበራት የተደራጁ 5,380 ሰዎች ይዞታቸው ሕገወጥ ነው ተብሎ እንዳይስተናገዱ ተደርገው ነበር፡፡ የእነዚህ ማኅበራት ሕጋዊ መሠረት ጥያቄ ውስጥ በመግባቱ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዕግድ ጥሎባቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡

የከተማው ካቢኔ ይህንን ችግር ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት፣ ማኅበራቱን ሕጋዊ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በ146 ማኅበራት የተደራጀ 1757 ሰዎች በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ግንባታ ባለማካሄዳቸው ታግደው ነበር፡፡ ይህ ዕግድ ለረዥም ዓመታት ሲያወዛግብ ቆይቶ፣ በመጨረሻ ካቢኔው የሁለት ዓመት ተጨማሪ የግንባታ ጊዜ በመስጠት ዕግዱን አንስቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በኮልፌ ክፍለ ከተማ የሚገኙ 700 ይዞታዎች ከጂአይኤስ ጋር መጣጣም ባለመቻላቸው ሊስተናገዱ አልቻሉም ነበር፡፡ በአዲስ ውሳኔ ግን በካቢኔው እንዲስተናገዱ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

አቶ መኮንን እንደገለጹት፣ የከተማው መመርያዎች እነዚህ ጉዳዮች እንዲስተናገዱ አይፈቅዱም፡፡ በመሆኑም ላለፉት አሥር ዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ ሲሆን፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሲነሳባቸው ቆይቷል፡፡

‹‹በተለይ በዚህ ዓመት ካቢኔው ብዙ ጊዜውን ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮችን መፍታት ላይ በማተኮር የመጨረሻ እልባት ሊሰጥ ችሏል፤›› በማለት አቶ መኮንን ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...