Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክለወለደ ላገባ ለፈታና ለሞተበት የተሰጠ ሕግ

ለወለደ ላገባ ለፈታና ለሞተበት የተሰጠ ሕግ

ቀን:

ተፈጻሚነቱ ከዛሬ ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡ ሕጉ ሲወጣ ሁለት ዓመታት ቢያስቆጥርም የሕጉ ተፈጻሚነትና ግን ዛሬ ይጀምራል፡፡

ለ3000 ዘመናት የመውለድ፣ የማግባትና የመጋባት፣ የመፍታትና የመፋታት ኩነቶችን ብናሳልፍም ኩነቶቹ ግን አልተመዘገቡም የፍትሐ ብሔር ሕጉ ከ50 ዓመታት በፊት ሲወጣ፣ ወሳኝ ኩነቶቻችን እንዲመዘገቡ ድንጋጌዎችን ቢቀርጽም በአሁኑ ሕግ ልምድ ከመርሕ በልጦ ሳይፈጸም ቆይቷል፡፡

ወሳኝ ኩነቶች አለመመዝገባቸው ለዘመናት ብዙ ትችቶች አስከትለውብናል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ፈላጊዎች፣ ባለመብቶች፣ የመብቱ ተሟጋቾች፣ ወዘተ. ተስፋ ቆረጡብን፡፡ አሁን ግን ልደታችን ሊመዘገብ፣ ዕድሜያችን ሊታወቅ፣ የተጋባውና የተፋታው ሊገለጽ፣ የሞቱብንንም ልንመዘግብ ነው፡፡ መንግሥትም ቁርጠኛ ሆኗል ሕግ አውጥቷል፤ ለመፈጸም የሚያስችል ተቋምም አደራጅቷል፡፡ አሁን ደግሞ ከዛሬ ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአስገዳጅነት ተመዝገቡ፣ አስመዝግቡ ብሏል፡፡

- Advertisement -

በዚህ ጽሑፍ መወለድን መነሻ አድርገን የወሳኝ ኩነቶች ጥቅምንና ፋይዳን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡   

ከአንድ አገር የሥነ ሕዝብ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያላቸውን የሕዝብ ብዛትና ዕድገትን የሚወሰኑ ለኅብረተሰቡ ጥቅም የሚከናወኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕቅዶችና የግለሰቦችን መሠረታዊ መብቶች ለማስከበር ወሳኝ የመረጃ ምንጮች ልደት፣ ጋብቻ፣ ሞትና ፍቺ ናቸው፡፡ በብዙ የሕግና የስታቲስቲክስ መጻሕፍት ወሳኝ ኩነቶች (Vital events) እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ እነዚህ ኩነቶች በአግባቡ ባልተመዘገበባቸው አገሮች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ፣ ቀጣይ፣ ቋሚና አስገዳጅ የሆነ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሕግ የሌላት ቀዳሚ አገር በመሆኗ በተግባር ግለሰቦች መብታቸውን ሲያስከብሩ፣ ተቋማት ደግሞ ሥራቸውን ሲያከናውኑ የተለያዩ ችግሮች እንደሚገጥሟቸው ከዕለት ተዕለት ተሞክሯችን ለመረዳት ብዙም አያስቸግርም፡፡ በእኛ አገር ያለ ዕድሜያቸው የሚያገቡ ሕፃናትን ለመለየት መቸገር፣ ሴቶች በየፍርድ ቤቱ የጋብቻ ሁኔታቸውን ለማስረዳት የሚያጋጥማቸው ረጅምና አስቸጋሪ ውጣ ውረድ፣ ፍች ስለመኖሩ ለማረጋገጥ በማይቻልበት መልኩ ግለሰቦች በጋብቻ ላይ ጋብቻ የሚፈጽሙበት አጋጣሚ፣ የሞተ ሰውን ውክልና በመጠቀም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮችን በሟች ስም መፈጸም በተግባር የሚስተዋሉ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አለመኖር መገለጫ ችግሮች ናቸው፡፡ ለአብነት እነዚህ ተጠቀሱ እንጂ ችግሮቹን መዘርዘር ጊዜም ቦታም የሚበቃው አይሆንም፡፡

በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው ሁሉንም የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሳይሆን የልደት ምዝገባን በተመለከተ ብቻ ይሆናል፡፡ አገራችን ልጆች በብዛት የሚወለዱባት ግን የማይመዘገቡባት አገር መሆኗ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊና አኅጉራዊ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የሕፃናት ልደት እንዲመዘገብ የተለያየ ውትወታ ለዘመናት ቢያደርጉም፣ እስካሁን ሁሉ አቀፍና ምሉዕ የልደት ምዝገባ በአገራችን አልተጀመረም፡፡ አያቶቻችንንና ልጆቻችንን የሚያመሳስለው ሁለቱም በአስገዳጅ የልደት ምዝገባ ሥርዓት ልደታቸው የሚመዘገብበት ሥርዓት አለመኖሩ ነው፡፡ አያቶቻችን ዕድሜያቸውን በኩነት ሲቆጥሩ ቆይተው ሲሞቱ የዕድሜያቸው ልክ በቀብራቸው ቀን ተገምቶላቸዋል፡፡ ‹‹እሷ የተወለደችው በመንግሥቱ ነዋይ ግርግር ጊዜ ነው፡፡ ንጉሡ ወደ አገር በገቡ በዓመቱ ነው፡፡ በሶማሊያ ጦርነት የአምስት ወር እርጉዝ ነበርኩ ወዘተ.›› በሚሉ ከኩነቶች ጋር በተያያዙ የቀናት ምዝገባ ነው፡፡ በዚህ በእኛና በልጆቻችን ዘመን ዕድሜ ለተወለደው የታወቀ ቢሆንም፣ ለሦስተኛ ወገን ግን በትክክል የተረዳ ላይሆን ይችላል፡፡ የልደት ምዝገባ ባለመኖሩ በአሁኑ ዘመን በአገራችን ዕድሜ የማይነገር፣ ሲነገርም የሚቀነስ፣ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ሳይቀር የሚደበቅ አሳፋሪ ቁጥር መስሏል፡፡ አንዳንዴም ዕድሜ እንደ ላስቲክ ይሆናል፤ ለፈለገው ዓላማ የሚሰበሰብ፣ ሲያሻው የሚለጠጥ ሆኗል፡፡ ዕድሜው ስንት እንደሆነ የሚጠየቅ ሰው ‹‹ስንት እንዲሆንልህ ትፈልጋለህ? በማለት በድፍረት የሚመልሰው እኛ አገር ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አሁን ግን ይህ ዘመን ሊለወጥ ይመስላል፡፡ አገራችን አዋጅ አውጥታለች፣ መሥሪያ ቤት አደራጅታለች፡፡ እናም ልደታችን የሚመዘገብበት ዕድሜያችንም የሚታወቅበት ጊዜ በእርግጥ የታወቀ ሆኗል፡፡ በዚህ ሰሞን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲም ይህንኑ ነው እየነገረን ያለው፡፡ በየወረዳችሁ ተገኝታችሁ የእናንተንና የልጆቻችሁን ልደት አስመዝግቡ፣ ዕድሜያችሁ ይታወቅ፣ አሻራም ስጡ ተብለናል፡፡ ለመሆኑ የልደት ምዝገባ በአገራችን ከየት ወዴት ሄደ? የልደት መመዝገብ ጥቅሙ ምንድን ነው? በአዋጁ የተደነገጉ የተመዝጋቢ፣ የአስመዝጋቢና የመዝጋቢ ግዴታዎች ምን ይመስላሉ? የሚሉትን ጭብጦች ተራ በተራ እንመለከታለን፡፡

የልደት ምዝገባ እንደ መብት

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መብት ስምምነት ፈራሚ አገር ናት፡፡ በዚህ ስምምነት የተደነገጉት የሕፃናት መብቶች የሚጀምሩት ከሕፃናት ልደት ምዝገባ ነው፡፡ የልደት ምዝገባ ሕፃኑ እንደ ሰውና የኅብረተሰቡ አባል በመሆን ማንነቱ የሚረጋገጥበት የመጀመሪያው ደረጃ ነው፡፡ የስምምነቱ አንቀጽ 7 ማንኛውም ሕፃን ከተወለደ በኋላ ወዲያውኑ የመመዝገብ፣ በተቻለ መጠን እንደተወለደ ስምና ዜግነት እንዲሁም ወላጆቹን የማወቅና የወላጆቹን ክብካቤ የማግኘት መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሠረት አገሮች የሕፃናት ልደት በመመዝገብ የልደት የምስክር ወረቀት የመስጠት ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፣ ይህ ማስረጃ የሕፃኑን ዜግነት ከመወሰን ጀምሮ ሌሎች ሰብዓዊ መብቶቹ እንዲከበሩ ይረዳል፡፡ የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት በአንቀጽ 24 ሕፃኑ ወዲያው እንደተወለደ መመዝገብ እንዳለበት ይገልጻል፡፡ በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም መድልኦ ለማስወገድ የተፈረመው ስምምነትም በአንቀጽ 6 እና 16 የልደት ምዝገባ መብት የሚሰጠው የዕድሜ መረጃ ሌሎች መብቶች እንዳይጣሱ ወሳኝ መሆኑን አስቀምጧል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የአፍሪካ ሕፃናት መብቶችና ደኅንነት ቻርተር አንቀጽ 6፣ 9 እና 16 የልደት መመዝገብ መብት እንደሆነና ዕድሜን ለማወቅ አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳል፡፡

      ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 36(1)(ሐ) ማንኛውም ሕፃን ስምና ዜግነት የማግኘት መብቱን፣ ሕፃናት ወላጆቻቸውን የማወቅና በወላጆቻቸው የመጠበቅ መብት፣ ዜግነት የማግኘት መብት እንዳላቸው መደንገጉ ሕፃናት የመብቱ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችላቸው የልደት ምዝገባ ሥርዓት መዘርጋት የአገሪቱ ግዴታ መሆኑን በቂ ማሳያ ነው፡፡

      ይህን ሕገ መንግሥታዊ መብት በዝርዝር ጥበቃ ለመስጠት የተሻሻሉት የቤተሰብ ሕግጋትና የወንጀል ሕጉ የተወሰኑ ድንጋጌዎች አስቀምጠዋል፡፡ በሁሉም የቤተሰብ ሕጎች አካለ መጠን ያልደረሰን ልጅ ዕድሜ ለማረጋገጥ የሚቻለው በልደት የምስክር ወረቀት እንደሆነ በግልጽ ተገልጿል፡፡ የዚህን አፈጻጸም ለማገዝ የሚመዘግቡ አካላት የቤተሰብ ሕግጋቱ በፀደቁ በስድስት ወራት እንደሚቋቋሙ ቢገለጽም፣ መዝጋቢ አካል ባለመቋቋሙ የሕፃናቱን መሠረታዊ መብት ለማስጠበቅ እንቅፋት ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል የወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 434 ማንኛውም ሰው ሆን ብሎ ጋብቻንና ሞትን እንዲሁም ሌሎች መመዝገብ ያለባቸውን ግዴታዎች በተሰጠው የጊዜ ሰሌዳ ያላስመዘገበ እንደሆነ እስከ ሦስት ወራት ሊደርስ በሚችል ቀላል እስራት ሊቀጣ እንደሚችል ደንግጓል፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 656 ደግሞ ሕግ በሚያዘው መሠረት የአንድ ሕፃንን መወለድ ለክብር መዝገብ ሹም ያላስታወቀ ማንም ሰው ከአምስት መቶ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከአንድ ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት እንደሚቀጣ ግልጽ ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ የወንጀል ሕጉ ያስቀመጠው ቅጣት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የሚያካሂድ ተቋም ባልተደራጀበት ሁኔታ ተግባራዊ ሳይሆን ዘመናት አሳልፏል፡፡

የልደት ምዝገባ አስፈላጊነት

      የልደት ምዝገባ መሠረታዊ የሕፃናት መብትን ከማስፈጸም ሌላ የተወሰኑ ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡ ቀዳሚው ሕፃናትን ከጥቃት ለመከላከል ይረዳል፡፡ የሕፃናት ዕድሜ በአግባቡ ከታወቀ ያለ ዕድሜያቸው ጋብቻ ውስጥ እንዳይገቡ፣ ለሕይወታቸው አደገኛ በሆኑ የሥራ ሁኔታዎች እንዳይሰማሩ፣ ከወታደርነት ምልመላ፣ ከወታደራዊ ግጭቶች ተሳትፎና ከተለያዩ የጉልበት ብዝበዛ ተግባራት ለመከላከል ይረዳል፡፡ የልደት ምዝገባ ባለመኖሩ ብዙ አካለ መጠን ያልደረሱ ሴት ሕፃናት በባህል ተፅዕኖ ቤተሰቦቻቸው ከፍ ያለ ዕድሜ ያላቸው በማስመሰል ያለ ዕድሜያቸው በጋብቻ ውስጥ ለብዙ ጥቃት እንዲጋለጡ አድርገዋቸዋል፡፡ ሌላው ወጣት ጥፋተኞች አካለ መጠን እንደደረሰ ሰው እንዳይቀጡና የሚያስፈልጋቸው ልዩ ጥበቃ እንዲፈጸምላቸው ያስችላል፡፡ ወጣት ጥፋተኝነትን በተመለከተ በፍርድ ቤቶችና በፖሊስ ምርመራና አያያዝ ወቅት በቅድሚያ እንዲጣራ የሚፈለገው የዕድሜ ደረጃ ነው፡፡ በተለይም ከባድ ቅጣትን የሚያስከትሉ ወንጀሎችን በተመለከተ የወጣት ጥፋተኞች ትክክለኛ የዕድሜ መረጃ መኖር በፍትሕ ሥርዓቱ የሞት ወይም የሕይወት ውሳኔ የመስጠት ጉዳይ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ወጣት ጥፋተኞች ከሌሎች ታራሚዎች ተለይተው የሚኖሩበት የሕግ አግባብ ቢኖርም፣ ትክክለኛ ዕድሜ ካልታወቀ ሕጉን በአግባቡ ለመተግበር ስለማይቻል በእስር ቤቶች ሕፃናት ለከፍተኛ ችግር እንዲጋለጡ ይዳርጋቸዋል፡፡ በሌላ በኩል የልደት ምዝገባ ከልጅነት ዘመን ባለፈ ሌሎች አገልግሎቶችን ለማግኘት ቁልፍ በር ነው፡፡ የልደት ሠርተፊኬት ፓስፖርት ለማግኘት፣ ጋብቻ ለመፈጸም፣ የመንጃ ፈቃድ ለማውጣት፣ የባንክ ሒሳብ ለመክፈት፣ ሥራ ለመቀጠር፣ ለጡረታ አበል ተጠቃሚነት፣ ለኢንሹራንስ፣ ለመምረጥና ለመመረጥ፣ ወዘተ አስፈላጊ ስለመሆኑ ከተለያዩ ሕግጋትና መመርያዎች መረዳት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ የልደት ምዝገባ በብሔራዊ ደረጃ ለሚደረግ ዕቅድ አስፈላጊም ነው፡፡ መንግሥት በአገሪቱ ያለውን ሕዝብ በማወቅ ፍላጎታቸውን ለማሳካት፣ ሞትና ልደት በልማት መርኃ ግብሮች ያላቸውን ተፅዕኖ ለመገምገም፣ በትምህርት፣ በጤና ወዘተ. ሕፃናት ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ የልደት ምዝገባ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይሆንም፡፡

የልደት ምዝገባ በኢትዮጵያ

      ልደትን ጨምሮ ወሳኝ ኩነቶች በኢትዮጵያ የሚመዘገቡበት ሥርዓት የለም ለማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም የምዝገባው ሥርዓት ሁሉን አቀፍ፣ ቀጣይ፣ ቋሚና አስገዳጅ ባለመሆኑ በምዝገባው መጠቀም የነበረባቸው ባለድርሻ አካላት አለመጠቀማቸው በየዓውዱ ይነሳል፡፡ ፍትሕና የሕግ ሥርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት በ2000 ዓ.ም. ያዘጋጀውም ሪፖርት ምንም እንኳን ዓላማው፣ ሒደቱና አፈጻጸሙ ከዘመናዊውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያግባባው የምዝገባ አሠራር አንፃር ደረጃውን የጠበቀ ባይሆንም፣ በተለያዩ መንግሥታዊ ድርጅቶች፣ ማዘጋጃ ቤቶች፣ የከተማ ጽሕፈት ቤቶች፣ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ፣ የጤና ተቋማትና የሃይማኖት ተቋማት ምዝገባዎች ሲካሄዱ እንደነበር ያትታል፡፡ በሪፖርቱ በዝርዝር እንደተገለጸው እነዚህ ተቋማት ከ1930ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ፍትሐ ብሔር ሕጉን ጨምሮ በተለያዩ መመርያዎችና የሃይማኖት ደንቦች ልደትን ጨምሮ የወሳኝ ኩነቶች ማስረጃ ሲሰጡ ቢቆዩም፣ አሠራሩ የዓለም አቀፍ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አሠራር መርሆችን ያልተከተለ፣ አስገዳጅና ቋሚ ያልነበረ፣ በየሃይማኖት ተቋማቱ የሚመዘገቡትም ከሃይማኖት ተቋማቱ አገልግሎት ውጪ ጥቅም ላይ የዋሉበት ሁኔታ ባለመኖሩ ምዝገባው ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ለብሔራዊ ፋይዳ ሳናውለው ቀርተናል፡፡ የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳሚያ ዘካሪያ እ.ኤ.አ. ጁን 5,2009 ፓሪስ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ ኢትዮጵያ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባን ለመፈጸም የተለያዩ ጥረቶች ስታደርግ ብትቆይም፣ ምሉዕና አስገዳጅ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ በቂ የሠለጠነ ባለሙያ አለመኖር እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ተገቢ ትኩረት ባለመስጠታቸው ዓለም አቀፍ መስፈርትን የሚያሟላ የምዝገባ ሥርዓት ሳይኖር እንደቀረ ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሯ እ.ኤ.አ. ጁን ወር 2011 በኒውዮርክ ባደረጉትም ገለጻ፣ ኢትዮጵያ ከእ.ኤ.አ. 2009 ጀምሮ አዲስ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሕግ በማርቀቅ የተጠመደች ቢሆንም፣ ሕጉን በአግባቡ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም ተጨማሪ ጥናት በማድረግ ላይ መሆኗን አስረድተው ነበር፡፡ በ2004 ዓ.ም መጨረሻ ግን ልደትን ጨምሮ የወሳኝ ኩነቶችን ምዝገባ የሚመለከት የሕግ ማዕቀፍ ተቀርጸዋል፡፡

አዋጁ ምን ይላል?

የልደት ምዝገባ በወሳኝ ኩነት ምዝገባና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጁ ቁጥር 760/2004 ዓ.ም. ከተካተቱት ኩነቶች አንዱ ነው፡፡ አዋጁ ልደት የሚመዘግበውን አካል፣ የአመዘጋገቡን ሁኔታና ልደት የሚመዘገብበትን ጊዜ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ልደትን የሚመዘግበው የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ሲሆን፣ እንደ ሁኔታው የክልል መዝጋቢ አካል፣ ኤምባሲዎች፣ የኢትዮጵያ መርከብ ካፒቴን፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ልደትን መዝግበው ለፌዴራሉ ኤጀንሲ ያስተላልፋሉ፡፡ እንደ ሌሎቹ ወሳኝ ኩነቶች ሁሉ ልደት የሚመዘገበው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፣ ተመዝጋቢው በክብር መዝገብ ሹም ፊት በአካል መቅረብ አለበት፡፡ ማንኛውም ልደት ሊያዘገይ የሚያስችል በቂ ምክንያት ከሌለ በስተቀር በ90 ቀናት ውስጥ መመዝገብ አለበት፤ ከዘገየም አስመዝጋቢው የዘገየበትን ምክንያት በማስረጃ ማስደገፍ እንዳለበት አዋጁ ይደነግጋል፡፡

ልደትን የማስመዝገብ ግዴታ የማን እንደሆነ አዋጁ ግልጽ አድርጓል፡፡ የሕፃኑ አባት ወይም እናት፣ ወላጆቹ የሌሉ እንደሆነ የሕፃኑ አሳዳሪ ወይም አሳዳሪ ከሌለ ሕፃኑን በመንከባከብ ላይ ያለው ሰው ልደቱን የማስመዝገብ ግዴታ አለበት፡፡ ሕፃኑ ተጥሎ የተገኘ ወይም ወላጆቹ የማይታወቁ እንደሆነ ይህንን ሁኔታ የሚያውቅ ማንኛውም ሰው በአቅራቢያው ለሚገኝ ፖሊስ ወይም አግባብ ላለው ለሌላ የመንግሥት አካል ሪፖርት ማድረግ አለበት፡፡ ሕፃኑ የተጣለ በሆነ ጊዜ በልደት የምስክር ወረቀቱ ይኼው የሚጻፍ ይሆናል፡፡ በልደት የምስክር ወረቀት ጀርባ ላይ ተጥሎ የተገኘ ተብሎ መጻፍ የልጁ ሥነ ልቦና ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ቢኖረውም፣ አዋጁ ግን ይህንኑ ይላል፡፡ አዋጁ የልደት ምዝገባ ይዘትንም የሚዘረዝር ሲሆን፣ የሕፃኑ ሙሉ ስም፣ ጾታ፣ የተወለደበት ቀን፣ የትውልድ ቦታ፣ የልደቱን ዓይነት (ነጠላ ወይም ከአንድ በላይ) እና በልደት ጊዜ የተደረገ ዕርዳታ፤ የሕፃኑን ወላጆች ሙሉ ስም የትውልድ ቀንና ቦታ፣ መደበኛ መኖሪያ ቦታ፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ ዜግነት፣ ሃይማኖት፣ ብሔርና ወላጆች በሕይወት ካሉ ፊርማቸውን ምዝገባው ከሚይዘው ዝርዝሮች ውስጥ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የልደት የምስክር ወረቀት ላስመዘገበው ሰው ይሰጣል፡፡ በልደት ምስክር ወረቀት የሰፈሩ መረጃዎች ከተሳሳቱ ከአጻጻፍ ስህተት ከሆነ በክብር መዝገብ ሹሙ፣ ሌሎች ዓይነት ስህተቶች ደግሞ በፍርድ ቤት ብቻ የሚታረሙ ይሆናል፡፡ ከወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጋር በተያያዘም አዋጁ የተለያዩ የወንጀል ድንጋጌዎችን አስቀምጧል፡፡ ያላስመዘገበ ስድስት ወር እስራት ወይም ከ500 እስከ 5,000 ብር ቅጣት፣ ሲያስመዘግብ ሐሰተኛ መረጃ የሰጠ ወይም እውነተኛ መረጃ የደበቀ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት፣ በሐሰት በተዘጋጀ ምዝገባ ወረቀት የተጠቀመ ከአምስት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት፣ ምስክር ወረቀት አስመስሎ የሠራ፣ ወደ ሐሰት የለወጠ ከሰባት እስከ አሥራ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት፣ አጥፊው የመንግሥት ሠራተኛ ከሆነ ቅጣቱ እስከ 25 ዓመት ጽኑ እስራት እንደሚደርስ ተደንግጓል፡፡

አዋጁ በዋናነት አዲስ ተወልደው የሚመዘገቡትን ማዕከል ያደረገ ቢሆንም፣ ብዙኃኑን (ሳይመዘገብ ለዘመናት የኖረውን) የረሳ አይመስልም፡፡ በመሸጋገሪያ ድንጋጌው አንቀጽ 68(4) ‹‹በሥራ ላይ በነበሩ ሕጎች ወይም ልማዳዊ አሠራሮች መሠረት ሳይመዘገብ የቆየ ወሳኝ ኩነት የሚመለከተው ሰው ደጋፊ ማስረጃዎችን አያይዞ ሲያመለክት በዚህ አዋጅ መሠረት ተመዝግቦ ለአመልካቹ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የምስክር ወረቀት ይሰጠዋል፤›› ሲል ተደንግጓል፡፡

ቀጣይ ሥራዎች

የልደት ምዝገባን ጨምሮ ለወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የሕግ መሠረት ተጥሏል፡፡ በዚሁ መሠረት ከአሁን በኋላ በአገራችን የማይመዘገብና ዕድሜው የማይታወቅ ዜጋ አይኖርም፡፡ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የሚፈጸመው ለኢትዮጵያዊ ብቻ እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ 3(1) ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ በአገሪቱ የሚኖሩትን የውጭ ዜጎች ስደተኞችንና ስደት ጠያቂዎችን ጨምሮ ቢመዘገቡ፣ ለሰዎቹም ለአገሪቱም ጠቃሚ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ምዝገባ በተጀመረባቸው ወረዳዎች የውጭ ዜጎችም ሊመዘገቡ እንደሚችሉ ጸሐፊው ተገንዝቧል፡፡ ከዚህ አንፃር አሠራሩ ከሕጉ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ሕጉ ተፈጻሚ የሚሆነው በነጋሪት ጋዜጣ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ መሆኑ ቢገለጽም፣ በመሸጋገሪያ ድንጋጌው (አንቀጽ 67) መሠረት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የሚያከናውኑ አካላት ለሁለት ዓመታት ሥራቸውን ላይጀምሩ እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ አንፃር አዋጁ ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. የወጣ ቢሆንም እስካሁን ሕግ አውጭው ካሰበውም ጊዜ ዘግይቶ ከአራት ዓመት በኋላ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ አሁን በተጀመረው አሠራር መሠረት የታሰበው ዜጋው በየወረዳው አንድ ቦታ ይመዘገባል፡፡ በሒደት ግን ማንኛውንም ሕዝባዊ አገልግሎት ለማግኘት በየትኛውም ወረዳ መጠቀም የሚያስችለው የኤሌክትሮኒክ የምዝገባ ሥርዓት ይተገበራል፡፡ ይህ ልክ እንደ ባንኮቹ አሠራር ዓይነት ማለት ነው፡፡ አንድ ቅርንጫፍ የባንክ ሒሳብ ከፍቶ በሌላው እንደማንቀሳቀስ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አሠራር ምዝገባውን ተደራሽ የሚያደርገው ሲሆን፣ ለአሠራርም የተመቸ መሆኑ አይቀርም፡፡ በአገራችን ልደትን መመዝገብ ግን የሚታሰበውን ያህል ቀላል ላይሆን ስለሚችል ሥራውን በአግባቡ ለመፈጸም የተወሰኑ ቀጣይ ሥራዎች እንደሚጠበቁ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡

የመጀመሪያው መዝጋቢው አካል ራሱን በሰው ኃይል፣ በቢሮ፣ ለምዝገባ በሚረዱ ግብዓቶችና በገንዘብ ሊያደራጅ ይገባል፡፡ በእኛ አገር ሕዝባዊ አገልግሎት ለማግኘት ረዥም ሠልፍ መሰለፍ፣ ሥራ ጥሎ መመላለስ፣ ብዙ ቢሮክራሲ ማለፍ ልማድ ከሆነ ቆይቷል፡፡ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ከዚህ ልማድ ሊላቀቅ ይገባል፡፡ የሚመዘገበው አካል በተማረ የሰው ኃይል የተደራጀ፣ በቂ የሰው ኃይልና አመራር ያለው፣ የቢሮ ፋስሊቲውና ለምዝገባ የሚያስፈልገው ግብዓት የተሟላለት ሊሆን ይገባል፡፡

በሁለተኛነት ባለድርሻ አካላት ሕዝቡ መብትና ግዴታውን አውቆ በተገቢው ጊዜ እንዲመዘገብና ልጁን እንዲያስመዘግብ የማሳወቂያ ሥራ ሊሠሩ ይገባል፡፡ የልደት ምዝገባ አስፈላጊነትና ጥቅሙን፣ የሕግ ግዴታ መኖሩንና አለማስመዝገብ የወንጀል ኃላፊነት እንዳለው ኅብረተሰቡን የማሳወቅ ሥራ መሥራት ተገቢ ነው፡፡ አንዳንድ ሰው ምዝገባን በበጎ ላይተረጐም ስለሚችል የተሳሳተ መረጃ ወደ ሕዝቡ ከማስረጹ በፊት በሰፋት በመገናኛ ብዙኃን ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡ አንድ ሞኝ የተከለውን አምሳ ሊቃውንት አይነቅሉትም የሚባለው እንዳይፈጸም፡፡

በመጨረሻም ጥንቃቄ የሚፈልገው የምዝገባ መረጃውን ትክክለኛነት የማረጋገጥ፣ የምዝገባውንም ደኅንነት መጠበቅና ተደራሽ የማድረግ ሥራ ላይ ነው፡፡ በመዝጋቢው በኩል የሰዎችን ማንነት ማረጋገጥ፣ የሰነዶችን ትክክለኛነት ማጣራትና ትክክለኛ መረጃ ወደ ቋት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ተመዝጋቢውና አስመዝጋቢው ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ሊተባበሩ የሚገባ ሲሆን፣ የመረጃው ትክክል አለመሆን የሚያመጣውን የወንጀል ኃላፊነት በመገንዘብ ያልተምታቱ መረጃ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ምዝገባው ወደ መረጃ ቋት ውስጥ ሲገባ የመረጃውን ምስጥራዊነት መጠበቅ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመነጋገር ተደራሽነቱን ማረጋገጥ፣ ደኅንነቱን መጠበቅ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ይጠበቃል፡፡ እንደ ባንኮቹ ኔትዎርክ ሥርዓቱ መተግበር ከጀመረ በኋላ ቢቋረጥ፣ ቢዘገይ፣ ወይም ጥራት ቢጎድለው የልደት ምዝገባ ዓላማውን እንዳያሳካ ያደርገዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...

ያልነቃ ህሊና!

ከሽሮሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት...

የሀብት ምዝገባ አዋጁና የፀረ ሙስና ትግሉ ነገር

በያሲን ባህሩ ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በታተመው ሪፖርተር ‹‹ልናገር››...