Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉጄኔራል ፃድቃን ከአሥራ አምስት ዓመታት በኋላ የዴሞክራሲ ጥያቄን ለምን እንደገና አነሱት?

ጄኔራል ፃድቃን ከአሥራ አምስት ዓመታት በኋላ የዴሞክራሲ ጥያቄን ለምን እንደገና አነሱት?

ቀን:

በተክለ ብርሃን ገብረ ሚካኤል

እሑድ ሐምሌ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በወጣው የሪፖርተር ጋዜጣ ዕትም ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሣኤ ‹‹የአገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታና የመፍትሔ ሐሳቦች›› በሚል ርዕስ ያቀረቡትን ጽሑፍ በጥሞናና በተመስጥኦ ነው ያነበብኩት፡፡ በመጀመሪያ አንድ ወታደራዊ መኮንን ባለከፍተኛ ማዕረግ ቢሆንም፣ የእዚህን ያህል የጠለቀ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዕውቀት ይኖረዋል ብዬ ባለመገመቴም ሊሆን ይችላል፤ በዚህ ረገድ ያላቸውን በሳል ዕውቀት ሳላደንቅ አላልፍም፡፡ ሁለተኛ ጄኔራሉ ሐሳባቸውን በተሟላ ፍሰትና የቋንቋ ጥራት ማቅረብ እንደሚችሉ በአድናቆት ተገንዝቤያለሁ፡፡

ይህን ካልኩ በኋላ ጄኔራሉ ያነሷቸው አንኳር ነጥቦች ወሳኝ ቢሆኑም፣ አዲስ አይደሉም፡፡ ኢሕአዴግ ፓርቲም፣ መንግሥትም፣ የዳኝነት ሥርዓትም ሆኗል፡፡ በሕግ አውጪው፣ በሕግ ተርጓሚውና በሕገ አስፈጻሚው መካከል ሊኖር የሚገባው ልዩነት መደብዘዝ ብቻ ሳይሆን ጨርሶ ጠፍቷል ነው የሚሉት፡፡ ጄኔራል ፃድቃን ትክክል ናቸው፡፡ ግን ይህ ትችትና ወቀሳ አዲስ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ኢሕአዴግ ችግሮች ሲፈጠሩበት በረሃና ጫካ በነበረበት ጊዜ (በተለይ ሕወሓት) ያደርግ እንደነበረው በዴሞክራሲያዊ ውይይት እንደ መፍታት፣ የኃይል ዕርምጃዎችን ወደ መምረጡ አዘንብሏል ይላሉ፡፡ ይህም ትክክል ነው፣ ግን አዲስ አይደለም፡፡

የኦነግን በኢሕአዴግ መባረር፣ የሕውሓትን መሰንጠቅና የቅንጅት መመታትን አስመልክቶ የሰጧቸውም ምሳሌዎች የኢሕአዴግን አምባገነናዊ አዝማሚያ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ግን ይህም ከዚህ ቀደም ከተባለውና ከተጻፈው የተለየ አይደለም፡፡ ኢኮኖሚውን በተመለከተ ጄኔራል ፃድቃን እንደሚሉት፣ ኢሕአዴግ ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት ስለሚያደርግና በዋና ዋና የምርት ኃይሎች ላይ ያለው ቁጥጥር መጠነ ሰፊ በመሆኑ ሙስና የተንሰራፋበት፣ የሀብት ብክነት የተስፋፋበት ሁኔታ ተፈጥሮአል፡፡ ይህም ነጥባቸው ብዙ የሚያከራክር አይደለም፡፡ በየቀኑ በዓይናችን የምንመሰክረው ክስተት ነው፡፡

ለእኔ አዲሱ ነገር ጄኔራሉ የዛሬ አሥራ አምስት ዓመት ገደማ (ማለትም በ1993 ዓ.ም.) ያነሱትን የዴሞክራሲ ጥያቄ እንደገና ማንሳታቸው ነው፡፡ ያኔ ማለትም በ1993 ዓ.ም. ሕወሓት መርህን በተመለከተ ለሁለት ተከፍሎ፣ ሁለቱ ወገኖች ለበላይነት ሲራኮቱ ኢሕአዴግ የተጠቀመው ዴሞክራሲያዊ አካሄድን ሳይሆን፣ አንደኛው ወገን የሠራዊቱን ከፍተኛ አመራር ተቆጣጥሮ ሌላውን ወገን ከሥልጣን ማባረር ነበር፡፡ ጄኔራል ፃድቃን የዚያ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ድርጊት ሰለባ ሆነው ከሥልጣን መባረራቸው የሚታወስ ነው፡፡

የጄኔራል ፃድቃን ወገን (እነ ስዬን፣ እነ ገብሩን፣ እነ አረጋሽን፣ ወዘተ ያካትታል) ሉዓላዊነትን በማራመድና ተንበርካኪነትን በማውገዝ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የደገፈውን አቋም በመያዝ አጥብቀው ተከራከሩ፡፡ ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ የነበረው የእነ አቶ መለስ ዜናዊ ቡድን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን የጎዳውን የአልጄርሱን ስምምነት (ባድመን ለኤርትራ ያስፈረደላት) መቀበሉ አንሶት፣ ከውስጣዊ ሕገ ደንቡ ውጪ እነ ጄኔራል ፃድቃንን ከሥልጣን ሲያባርር፣ እነ ስዬ አብርሃን በአንድ ጀንበር በተረቀቀና በፀደቀ አዋጅ (የስዬ አዋጅ) እሥር ቤት ወርውሮ አሰቃያቸው፡፡

በአቶ መለስ ዜናዊ በአንጃነት ተፈርጀው ከሥልጣን ከተባረሩት የቀድሞ ባለሥልጣኖች መካከል አቶ ስዬ አብርሃና አቶ ገብሩ አሥራት የደረሰባቸውን በደል ጭምር የሚገልጹ ዳጎስ ያሉ መጻሕፍት የጻፉ ሲሆን፣ ጄኔራል ፃድቃን ደግሞ እንደሚወራው ከሆነ ድምፃቸውን አጥፍተው የቢዝነስ ዓለሙን በመቀላቀል በዶላር ጭምር ሀብት አካብተዋል፡፡ ታዲያ ዛሬ ምን አዲስ ነገር ተፈጥሮ ነው? የዛሬ አሥራ አምስት ዓመት ገደማ አንስተውት የነበረውን የዴሞክራሲ ጥያቄ እንደገና ያነሱት? ማንሳታቸውን ወድጄዋለሁ፡፡ ግን ለምን ዛሬ? በነገራችን ላይ የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖትም ኢሕአዴግን እየወረፉና እየተቹ መጻፍ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ምን አነሳሳቸው?

ከሦስት አቅጣጫዎች የመጣ ጫና

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን በጽሑፋቸው ለመግለጽ እንደሞከሩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢሕአዴግ መንግሥት ላይ የሚያርፈው ጫና ከሦስት አቅጣጫዎች የሚመጣ ይመስለኛል፡፡ አንደኛው የጫና ምንጭ እየጨመረ የሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ ነው፡፡ ለዚህ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በቅርቡ የተከሰቱት ሕዝባዊ አመፆች ጥሩ ምሳሌ ናቸው፡፡ ሁለተኛውና ጄኔራል ፃድቃን በግልጽ ያልጠቀሱት የአሜሪካ መንግሥት ሚስጥራዊ ግፊት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ይከሰታሉ ብሎ የሚፈራቸው ሦስት ዋና ሥጋቶች አሉት፡፡ አንደኛው የእርስ በርስ ጦርነት ሥጋት ሲሆን፣ ሁለተኛው ይህ ሊያስከትለው የሚችለው የሽብርተኝነት መስፋፋት ሥጋት ነው፡፡ ሦስተኛው ሥጋት ከእነዚህ ሁለት ችግሮች ጋር የሚመጣው ስደት ወይም ፍልሰት ነው፡፡ ወደ አንድ መቶ ሚሊዮን የሚጠጋው የኢትዮጵያ ሕዝብ መድረሻ ካጣ አውሮፓን ያጥለቀልቀዋል የሚል ፍራቻ አለ፡፡ በእኔ ግምት ሦስተኛው ጫና በተለይ በኤርትራ መንግሥት ከሚደገፉት የታጠቁ ተቃዋሚ ኃይሎች በኩል የሚሰነዘረው ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ጦርነት መክፈታቸውን አውጀዋል፡፡

እነዚህ ከሦስት አቅጣጫዎች የሚመጡ ጫናዎች የሚያርፉት በኢሕአዴግ መንግሥት ላይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ጫናው እየበረታ ሲሄድ በኢሕአዴግ ውስጥ በተለይም ዋናው የሥልጣን አስኳል በሆነው ሕወሓት ውስጥ መከፋፈል እንደሚፈጠር መገመት አያዳግትም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢሕአዴግ ብሎም በሕወሓት ውስጥ ክፍፍል አለ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ቢያንስ ሁለት ቡድኖች የበላይነቱን ለመያዝ እየተራኮቱ ይመስለኛል፡፡ ዋናው ሽኩቻ ደግሞ የሠራዊቱን ከፍተኛ አመራር ድጋፍ ለማግኘት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ያለውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ በጥገና ለውጥ ለማስቀጠል የሚሞክር ቡድን ያለ ይመስለኛል፡፡ ይህ ቡድን በተለይ በሙስና የተዘፈቀና የሰው ደም ያለበት ነው የሚሆነው፡፡

በአንፃራዊ መልኩ ከዚህ የፀዱት ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቢመሠርቱ ከታሪክ አኳያ ብቻ ሳይሆን፣ በተጨባጭ ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑ ሳይገነዘቡት አይቀሩም፡፡ እናም እነ ጄኔራል ፃድቃንና እነ ጄኔራል አበበ በአሁኑ ጊዜ የዴሞክራሲን ጥያቆ እንደገና እያነሱ ያሉት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ከየትኛው ወገን እንደሆኑም መገመት አያዳግትም፡፡ ይቅናቸው ከማለት ሌላ ምን ይባላል?

ለውጥ ፈላጊው ቡድን ምን ያድርግ?

ለመሆኑ ለውጥ ፈላጊው ቡድን ማን ነው? በመጀመሪያ ለውጥ ፈላጊው ቡድን ሲባል፣ በኢሕአዴግ በተለይ በሕውሓት አመራር ውስጥ ያለው ወይም እንዳለ የሚታመነው ለውጥ ፈላጊ ቡድን ማለት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የዚህ ዓይነት ቡድን የለም የሚሉ አሉ፡፡ አይፈረድባቸውም፡፡ ሃያ አምስት ዓመታት ሥልጣን ላይ ከቆየና ተቀናቃኞቹን ሁሉ ከአጠፋ ሥርዓት ውስጥ ለውጥ ፈላጊዎች ይወጣሉ ብሎ መገመት ሊያስቸግር ይችላል፡፡ ግን ለውጥ ተፈጥሮአዊ ሒደት ስለሆነ፣ ይዘገይ እንደሆን እንጂ የማይቀር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ እናም ወደተነሳንበት ጉዳይ ስመለስ ለውጥ ፈላጊው ቡድን ምን ያድርግ?

በመጀመሪያ በኢሕአዴግ ውስጠ ዴሞክራሲ መርህ መሠረት በኢሕአዴግ በተለይ በሕውሓት አመራር ውስጥ ዴሞክራሲያዊውንና ግልጽ ውይይቱን አጠናክሮ በመቀጠል፣ የለውጥ ፈላጊው አቋም ተጠናክሮ እንዲወጣ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛ በተለያዩ ምክንያቶች ለውጡን ለሚቃወመው ቡድን ‹‹የጀግና መንገድ›› መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ጉዳይ በሚገባ የሚታወቅ በመሆኑ፣ እዚህ ላይ ዝርዝር ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ ሦስተኛ በተለይ የቀድሞ የሕወሓት ባለሥልጣናት የነበሩ ሰዎች (ማለትም እንደ ጄነራል ፃድቃን እና ጄነራል አበበ ያሉት) ያለአንዳች ተፅዕኖ ሐሳባቸውን በአደባባይ እንዲገልጹ የተጀመረውን በጎ ተግባር እንዲቀጥል ማድረግ የለውጥ ሒደቱን ለማፋጠን ያግዛል፡፡ አራተኛ ሕዝቡ በተለይ በሕጋዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አስተባባሪነት ብሶቱንና ምኞቱን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲገልጽ መፍቀድና ለውጡ በየት አቅጣጫ መሄድ እንዳለበት ለማወቅ መሞከር ተገቢ ይሆናል፡፡

የዚህ ለውጥ ሒደት ውጤት ምን ይሆናል? እንደ እኔ ምኞት የለውጡ ውጤት መሆን ያለበት አንድም ሰው ሳይሞት ወይም ምንም ደም ሳይፈስ፣ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ማምጣት ነው፡፡ ይህን ሲናገሩትና ሲጽፉት ደስ የሚል ምኞት ተግባራዊ ለማድረግ በመሬት ላይ ያለውን የፖለቲካ እውነታ መጋፈጥ ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ዘመን የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚሽከረከረው በአራት ዓበይት ኃይሎች ነው፡፡ እነዚህም ሕውሓት/ኢሕአዴግ፣ የታጠቁ ተቃዋሚዎች፣ እነዚህን የሚደግፈው የኤርትራ መንግሥትና የአሜሪካ መንግሥት ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ የንቃተ ኅሊና ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ሰላማዊ ሕዝባዊ ትግል ለማካሄድ የሚሞክሩት የኢትዮጵያ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን ምንም ውጤት ለማስገኘት አልቻሉም፡፡

በዚህ የኃይል አሠላለፍ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ከታጠቁ ተቃዋሚዎች ጋር ብቻ ውይይት ለማድረግ ቢፈልግ፣ ደጋፊያቸው የኤርትራ መንግሥት አይፈቅድላቸውም፡፡ ምክንያቱም ለእነሱ ድጋፍ የሚያደርግላቸው የራሱን ብሔራዊ አጀንዳ ለማራመድ ነውና፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይ የባድመ፣ የአሰብና የድንበር መካለሉ ጉዳዮች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ የታጠቁት ተቃዋሚዎች አቋም፣ ‹‹እኛ ነፃ አውጪዎች እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ውክልና ስለሌለን በአገር ጉዳይ ላይ መወሰን አንችልም›› የሚል መሆኑን ሰምቼአለሁ፡፡ እንዲያውም ይህን አቋም በመውሰዳቸው የኤርትራ መንግሥት የሚሰጣቸው ድጋፍ የተጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ ከዚህ አኳያ ሕወሓት/ኢሕአዴግ የኤርትራ መንግሥት የሚፈልገውን በመስጠት የታጠቁ ተቃዋሚዎቹን ሊያኮላሽ ይችላል፡፡ ግን ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሰባ ሺሕ ሠራዊት ያስጨረሰበትን ባድመን ለሻዕቢያ ሊሰጥ (አስፈርዶለታል)፣ ሠራዊቱ ራሱ ዝም ብሎ የሚያይ አይመስለኝም፡፡ ግን በሌላ በኩል የአሰብ ወደብን ያስረከበ ሠራዊት ድንገት ተነስቶ አንበሳ ይሆናል ለማለትም ያስቸግራል፡፡

ያም ሆነ ይህ ለሕወሓት/ኢሕአዴግ የሚቀለው ከታጠቁ ተቃዋሚዎች ጋር መደራደር ነው፡፡ ምክንያቱም እነሱ የሚጠይቁት (እኔ እንደተረዳሁት) በኢትዮጵያ እውነተኛ የሕዝብ ውክልና ያለው መንግሥት ሥልጣን እንዲይዝ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እነ ጄኔራል ፃድቃን እና ጄኔራል አበበ ጭምር የሚደግፉት መሠረታዊ ሐሳብ ነው፡፡ በእኔ ግምት በሕወሓት/ኢሕአዴግ አመራር ውስጥ ያለው ለውጥ ፈላጊ ቡድንም ከዚህ የተለየ አቋም ያለው አይመስለኝም፡፡ ይሁንና የታጠቁ ተቃዋሚዎች ከጀርባቸው ደጋፊያቸው የኤርትራ መንግሥት ከሌለ የመደራደር አቅማቸው ደካማ ስለሆነ፣ ዋስትና የሚሰጣቸው ሌላ ኃይል ይፈልጋሉ፡፡ ያ ኃይል ደግሞ የአሜሪካ መንግሥት ነው፡፡ የታጠቁ ተቃዋሚዎች የአሜሪካ መንግሥትን ዋስትና ካገኙ ከለውጥ ፈላጊው የሕወሓት/ኢሕአዴግ አመራር ቡድን ጋር ተደራድረው በኢትዮጵያ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ሽግግሩን ዕውን ለማድረግ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ከሻዕቢያ ጋር የምታደርገው ድርድር በጠንካራ ብሔራዊ አንድነት መሠረት ላይ የቆመ እንደሚሆን ይገመታል፡፡

የእኔ ምኞት    

መቼም ምኞት አይከለከልምና ጥሩውን እመኛለሁ፡፡ በመጀመሪያ የጠብመንጃ ጩኸት መስማት አልፈልግም፡፡ ደም ሳይ ያጥወለውለኛል፡፡ ቀላሉ ነገር በሕወሓት/ኢሕአዴግ አመራር ውስጥ እንዳለ የሚታመነው ለውጥ ፈላጊ ቡድን የፖለቲካና የወታደራዊ የበላይነቱን ይያዝ፡፡ ከዚያም ለታጠቁና ላልታጠቁ ተቃዋሚዎች የሰላማዊ ውይይት ጥሪ ያስተላልፍና ታሪካዊ ጉባዔ ያካሂድ፡፡ ከጉባዔው በኋላ የሽግግር መንግሥት ይቋቋምና በተወሰነ የጊዜ ገደብ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ተካሂዶ፣ የአብላጫውን ሕዝብ ድምፅ ያገኘ ቋሚ መንግሥት ይመሥረት! በቃ! ይኼው ነው! ሕዝቡ እኮ የሚፈልገው እንደ አቅሙ ሠርቶ በሰላም መኖር ነው! ሰላም!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...