Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየማንነትና የብቻ ጎጆ ጥያቄ ችግራችን ምንድነው?

የማንነትና የብቻ ጎጆ ጥያቄ ችግራችን ምንድነው?

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ 25 ዓመታት አልፈውታል፡፡ የብሔርተኝነትና የትምክህት አማሽነት ዛሬም ቀጥሏል፡፡ አሮጌው ትምክህት ሲያደርስ የኖረውን ችግር ሳናክም፣ ማንነትን በብሔረሰብነት ላይ ብቻ አጥብቦ ማየት ዕውቀት ተደርጎ መያዙ በአማራ ክልል ውስጥ ለተከሰተው የቅማንት የይዞታ መተሳሰብ ጥያቄና ብሔረሰብ ግጭት፣ ወዘተ. ድርሻ አበርክቷል፡፡ በየክልሎች ውስጥ የማኅበረሰቦች ትድድር በእኩልነትና በፍትሐዊነት ላይ በአግባቡ እስካልተቋቋመና ማንነትና ክፍልፋይነት አንድ ተደርጎ እስከተቆጠረ ድረስ፣ የቅማንት ዓይነት የብቻ ጎጆ ጥያቄ የሚቀጥል መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

የብሔርተኛና የትምክህት ጥበቶችን አጥፊነትን የሚያቃልሉ መፍትሔዎችም በተግባር እየታዩ አይደለም፡፡ አሮጌው ትምክህተኛነት ዥንጉርጉርነትንና አንድነትን አዛምዶ ማክበር እንደሚተናነቀው ሁሉ፣ የብሔርተኛ ጥበትም ኢሕአዴግ በትክክል እንደገለጸው “በሕዝቦች መካካል ያለውን መሠረታዊ አንድነትና ተመሳሳይነት በመድፈቅ በ(ብሔረሰባዊ) ማንነት ላይ የተመሠረተውን ልዩነት ሕዝቦችን ለማራራቅና ነጣጥሎ ለማናቆር” ይጠቀምበታል፡፡ ኢሕአዴግ እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን አውስቶና ዳስሶ ግን የመፍትሔ መላ የለውም፡፡ “መፍትሔው” የአሥርቱ ትዕዛዛት ዓይነት – በጭፍን አለመቃወም፣ በጭፍን አለመደገፍ፣ በሐሰት መረጃ ላይ ተመሥርቶ ራስንና ወገንን ከሚጎዳ ተግባር መቆጠብ፣ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኛ መሆን . . .፡፡ የዚህ ዓይነት ትዕዛዛት በገፍ ቢደረደሩ ችግሩን አይቆነጥሩም፡፡ ከትዕዛዛትና ከስብከት አልፎ መዘጋት ያለባቸውን ቀዳዳዎችና መከፈት ያለባቸውን በሮች ማስቀመጥና ወደ ተግባር መቀየር ያሻል፡፡

ብሔር/ብሔረሰብነትን የማንነት መለኪያ አድርጎ “ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት” የሚያካሂደው የራስን ማንነት ማወቅ፣ የሌላውን ማንነት ማወቅ፣ በመፈቃቀድ የጋራ ማኅበረሰብ መገንባትና የማንነት አካባቢን ማልማት የሚል ስብከት ለኢትዮጵያ የውስጥ ሰላምና ግስጋሴ የማይበጅና ከዘመን ወደኋላ የቀረ ነው፡፡ ላስረዳ፡፡

  1. ቋንቋ የማንነት አንድ ገጽታ እንደሆነ ሁሉ ሃይማኖትና ባህልም የማንነት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ብዙ አካባቢዎችን ያወናጨፈ፣ የሰው ልጆች የዘር መነሻ ሥፍራ መሆን፣ ከዘር እስከ ባህልና ቋንቋ ድረስ ለዘመነ ዘመናት ሲወራረሱ ከኖሩ ጥንታዊ የኩሴ (የኩሽ-ሴም) ዘመዳም ሕዝቦች መገኘት፣ ብዙ መሰያየፍና መዘናነቅ በታየበት ረዥም ታሪክም ውስጥ ማለፍ የማንነት ገጽ ነው፡፡ የተወራረሱ ብዙ ቋንቋዎችና ባህሎች የተንቆጠቆጡበት ሕይወትና አገር አካል ሆኖ መገኘትም ማንነት ነው፡፡ የጥቁርነትና የአፍሪካዊነት አበሰኛ ታሪክም ማንነት ነው፡፡ የእነዚህ ሁሉ የማንነት ዘርፎች መዋያ የሆነው የሰው ልጅነት ደግሞ ለሁሉም መሠረት የሆነ ማንነት ነው፡፡ እነዚህን መሰሎች የማንነት ገጾች በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ ሁሉ በአንዴ የሚታዩ ሆነው ሳለ፣ ብሔርተኝነት ግን ሌሎቹን ሳጥን ውስጥ አቆዩና በብሔር/ብሔረሰብ ማንነት ብቻ አጊጡ ባይ ነው፡፡ ገጸ ብዙ ማንነታችንን ዘርግተን “የራስን ማንነት ማወቅ፣ የሌላውን ማንነትም ማወቅ” በተሰኘው ቢጋር መሠረት ማዶ ለማዶ የሚነፃፀር የየብቻ ማንነት ለመፈለግ ብንሞክርም፣ የራሳችንን ማንነት በሌላው ውስጥ፣ በራሳችንም ውስጥ የሌላውን ማንነት እናገኘዋለን፡፡ በሌላ አባባል የቋንቋ/የባህል፣ ወዘተ የሚባሉ ልዩነቶች ሁሉ የተወሳሰበ የጋራ ማንነታችን ዥንጉርጉር አካላት ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ዛሬ ውስን ቦታ ላይ የረጋ የሚመስል የወንዝ  ልጅነት በታሪክ ጉዞ ውስጥ ከብዙ ሥፍራዎች ጋር የተያያዘ ጀርባ እንዳለው ሁሉ ወደፊትም በልማት አማካይነት ከብዙ ወንዜነት ጋር መላላሱ የማይቀር ነው፡፡

አሁን ባለንበት ደረጃም ቢሆን፣ ሌሎች የማንነት ገጾችን አደብዝዞ (“የጅማ ልጅ”/ ”የሐረር ልጅ” የሚባሉ ብዙ ቋንቋዎችንና እምነቶችን ያስተቃቀፉ የእኛነት ዝምድናዎችንም ጎማምዶ) የገነነው ብሔር ብሔረሰብነት በተናጠል አካባቢና ቋንቋ ውስጥ በመብቀል ላይ የደረቀ መሥፈሪያውን እንዲያርም የሚያስገድድ እውነታ ተጎልጉሎለታል፡፡ የጉልበት አስገዳጅነትና አዝጋሚ ሽርሸራ በነበረበት የውህደት ታሪክ አማካይነት ዛሬ ከአማራነት ጋር ከሞላ ጎደል በእምነትም፣ በቋንቋም፣ በመዋለድም የማይለዩት ቅማንቶች፣ “ቅማንቴ ነህ/ነኝ” መባባልንና የታሪክ ርዝራዥን ተንተርሰው ራሳቸውን ከአማራነት “መለየታቸው”፣ እንዲሁም የረዥም ዘመን ንክኪ ዝንቅ ባህልንና ከአንድ የበለጠ ቋንቋ ተናጋሪነትን ያቀዳጃቸው ራያዎችና ወልቃይቶች በየተናጠል ቋንቋ የማይፈረጅ ማንነታቸውን ተመርኩዘው ጥያቄ ማንሳታቸው መልዕክቱና ትምህርቱ ኃያል ነው፡፡ አንድ አካባቢንና ቋንቋን መጋራት የአንድ ዓይነት ብሔረሰባዊ ማንነት ማረጋገጫነቱ ላይሠራ እንደሚችል፣ በአንድ ቋንቋ ተናጋሪነት ውስጥ ከአንድ የበለጠ ማኅበረሰባዊ የእኛነት ሥነ ልቦና ሊኖር እንደሚችል፣ በብዙ ቋንቋ ተናጋሪነት ላይም የጋራ ማንነት ሊታነፅ እንደሚችል ዕወቁት የሚል መግለጫ ነው፡፡ ተጎራባች ቋንቋዎችንና ባህሎችን የደበለና ያካለሰ ማኅበረሰባዊ ገጽታ ይዞ መገኘትን እንደ ጥራት ጉድለት ማየትና ወደ “ጥራት” ጎትቶ ለማፅዳት መሞከር (በዚሁ ዓይነት፣ የዛሬን ቡራቡሬ/ቅይጥ ገጽታ እንደ “እንከን”፣ ጥንት የነበረውን እንደ “እውነተኛው የማንነት ገጽታ” አድርጎ በማሰብ የዛሬውን “እንከን” በጥንቱ ለማስለቀቅ መሞከርም) ሊባርቅ የሚችል ጉዞ መሆኑን ልብ በሉ የሚልም ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ከአንድ ቋንቋ ጋር ማንነታችንን ላጣበቅነውም ከብዙ ነገሮችና ቋንቋዎች ጋር የተሳሰረ ገጸ ብዙ ማንነታችንን እንድናስታውስ (ለምሳሌ የስልጤነትንም ሆነ የወለኔነትን ዓይነተኛ ማንነት ለመቆንጠጥ የተጣጣርነውን ያህል ከጉራጌ ማኅበረሰቦች ጋር የምንጋራቸውን የማንነት ክሮች እንድናስተውልና እንድንከባከብ) የሚያነቃ ደወል ነው፡፡

  1. “ብሔር ብሔረሰባዊ” ማንነት የሚያነሳው አካባቢያዊ የይዞታ ቅርጫና ተከታይ ጣጣዎቹ በአራት ዋነኛ ሰበዞች የሚቆሰቆሱ ናቸው፡፡
  • በሥልጣን ላይ ያለው “ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት” ያው ማንነትን በብሔረሰባዊ መገኛ ምድር ላይ የገደገደና ለየብሔረሰባዊ መገኛ ሥፍራ ተቆርቋሪነት መታመንን መርሁና ትምህርቱ ያደረገ እንደመሆኑ፣ በክልሎች ውስጥ በዞንና በወረዳ ከሌሎች ጋር ተጣምረው ወይም በትልልቅ የብሔረሰብ ግቢ ውስጥ ተፈንጥቀው የሚገኙ ማኅበረሰቦች የብቻ ታሪክና የይዞታ ካርታ ይዞ የማቀንቀን ቅናት ውስጥ እንዲገቡ ገዢው  አመለካከት ራሱ ይቀሰቅሳቸዋል፡፡ ይህ የሁሉም ሩጫዎች የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡
  • መነጠልን የሚያክል ጥያቄን በሰላምና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እስከማስተናገድ የተንጠራራ ሕገ መንግሥት ተይዞ ሳለ፣ የዘጠኙን ክልሎች ቁጥር የሚቀይር ጥያቄ እንኳ ባልታየበት፣ ልዩ ወረዳ ወይም ዞን ልሁን ወይም ከዚህ ክልል ወደዚያ ክልል ልግባ የሚሉ ጥያቄዎችን በሕዝባዊ ውይይትና ሕግን በተከተለ ሥርዓት ከማስተናገድ ፈንታ “ማንነትን መካድ”፣ “ፀረ ሕዝብ”/“ፀረ ሰላም”፣ ወዘተ እያሉ ግለሰቦችን በውንጀላ፣ በእስራትና በከፋ የጥቃት በትር ለማሳደድ መፍጠን ሲደጋገም መቆየቱና ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙት፣ በአፈና አልደፈጠጥ ብለው ሲያስቸግሩ መሆኑ የቱን ያህል የዴሞክራሲ አንጀት እንደ ጎደለን ከሕዝብና ከዴሞክራሲያዊ መብቶች ይልቅ የገዥዎች ፍላጎት፣ ንጭንጭና እብሪት ይበልጥ እንደሚከበር የሚያሳይ ነው፡፡
  • የዚህ ዓይነቱ ኢዴሞክራሲያዊነት ከብሔርተኛ ሩጫዎች ጋር ተጋግዞ የይዞታ ድርሻ መተሳሰብንና መፈነጋገጥን ያባብሳል፡፡ ለዚህ ወይም ለዚያ ብሔረሰብ ቆሜያለሁ የሚሉ የክፍልፋይ ብሔርተኛነት እንቅስቃሴዎች ባህሪያቸው ራሱ ሁሉንም ብሔረሰብ በእኩል ዓይን የማየትና የማስተናገድ ብቃትን ይነሳቸዋልና ሥልጣን በያዙበት አካባቢ “መጤ” ከማንጓለል ባለፈ፣ “ነባር” ከሚባሉት ጋርም የሥልጣንና የጥቅም ሽኩቻ ከመፍጠር አያመልጡም፡፡ ከሽኩቻው ውስጥም ጥቅሜ አልተጠበቀም/ፍትሐዊ ተሳትፎ አላገኘሁም የሚሉ ዓይነት ቅሬታዎችና ተከታይ ጥያቄዎች ብቅ ይላሉ፡፡ ክፍልፋይ ብሔርተኝነትን፣ ጠባብ ወገናዊነቱ (አድላዊነቱ) እንደተጠበቀ፣ የዴሞክራሲያዊ እኩልነት ርዕዮተ ዓለም የማድረግ ሙከራ (በ“ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት” ውስጥ እንደምናስተውለው)፣ ወይም ክፍልፋይ ብሔርተኝነት በሚያናፍርበት እውነታ ላይ ዴሞክራሲያዊ እኩልነትንና ፍትሐዊነትን የማቋቋም ትግል ተውሸልሽሎ ከመክሸፍ የማያመልጠው ለዚህ ነው፡፡
  • በአንድ ብሔረሰብ ውስጥ የሚከሰት የአሳታፊነት መዛባት (የማኅበረሰቡ አንድ ክፋይ ተዋናይነቱ ደምቆ የሌላው መሳሳት ወይም መዘንጋት) የራስ ቁራሽ ምድር ወደ መፈለግ ሊወስድ ይችላል፡፡
  • ንድፈ ሐሳቡ ሌሎች ብሔረሰቦችንም የሚጨምር ቢሆንም በሶማሊ ብሔረሰብ ላይ እናተኩር፡፡ በሶማሊ ብሔረሰብ ውስጥ ቅርብና ፊት ለፊት ሆኖ ሕይወትን የሚመራው ጎሳነት ነው፡፡ በየጎሳው ውስጥ ደግሞ ግለሰቦችን እጅግ ያስተሳሰሩ (ለአንድ ግለሰብ የመጣ በረከትንም ሆነ መቀጮን በጋራ የመሸከም ኃላፊነት ያለባቸው) የዝርያ ስብስቦች አሉ፡፡ የገረረ አየር ንብረት፣ ግጭትና የከብት ዘረፋ የሚመላለስበትን ከባድ የአርቢነት ኑሮን አሸንፎ ህልውናን የማዝለቅ የዘመናት ትግል ያጠነከረው የሶማሊ የጎሳዎች መዋቅርም በአጠቃላዩ የአርቢነት ሕይወት ውስጥ ለመጣ ከተሜነትና ነጋዴነት በዋዛ የማይሸነፍ (በየጎሳ ሰንሰለቱ ገጠሬውን ከከተሜው፣ አርቢውን ከነጋዴና ከተማረው ጋር አጣብቆ ለመያዝ ጉልበት ያለው) ነው፡፡ በሶማሊያ ውስጥ ሕግና ሥርዓት ሲፈርስ ኅብረትና ጥሉ በየጎሳ ወገን ለመሆን የቀለለው ለዚህ ነበር፡፡ የጎሳዎች ንቁሪያና ሽብር ያማቀቃትን ሶሚሊያን እንደ መንግሥት የማፅናቱ የአሁኑ ጥረትም የጎሳዎች ፌዴራላዊ መዋቅር መፍጠሩም የማይገርመው ለዚህ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሶማሊ ውስጥም ሆነ በሶማሊያ ውስጥ ጎሳዎች ብሔረሰቦች አከል ህልውና አላቸው፡፡ በሶማሊ ክልል ውስጥ በጎሳዎች ውስጥ ተሰባጥረው እየኖሩ ሃይማኖታዊ ሥራ በመሥራት የተጋጩ ወገኖችን በመገላገልና በማስታረቅ ተከባሪ የሆኑት ሼካሾች፣ ከአሰፋፈር ጋር የተያያዘ የራስ አስተዳደር ሲመጣ ከይዞታ የለሽነትና በዋና ሰፋሪ ጎሳዎች ከመዋጥ ለማምለጥ የራሳቸውን ሠፈራ ወደ መፍጠር ሄዱ፡፡ ይህ ልምድ የራስ በራስ አስተዳደር የግድ ከአንድ ማኅበረሰብ/ክፍለ ማኅበረሰብ የደራ አካባቢያዊ ክምችት ጋር ተጣብቆ መታየት እንደሌለበት፣ በየትኛውም የአስተዳደር አካባቢ ውስጥ ያሉ ማኅበረሰቦች (ትልቅ ሆኑ፣ ንዑስ ወይም የተሰባጠሩ) ሁሉም ቤታችን ነው (ራሳችንን አንድ ጋ እያስተዳደርን ነው) ብለው ለማመን የሚያበቃቸው ውክልናና የዕድሎች ተቋዳሽነት ማግኘታቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡ ይህ ተጢኖ ወደ ተግባር ካልተተረጎመ፣ አብሮም እርስ በርስ መያያዝን ከሚያሳድግ የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር ሒደት ጋር ገጸ ብዙ ማንነት ካልተኮተኮተ፣ ጎሳነት በሶማሊነት የጋራ ማንነት ላይ የማያጠላ እውነታ የሆነበትን ዕድገት ማምጣት ሳይቻል ይቀራል፡፡

ለዴሞክራሲና ለግልጽነት ባይተዋር ሆኖ በኖረ ኅብረተሰብ ውስጥ በጥያቄ ውስጥ ጥያቄን፣ በትርጉም ውስጥ ትርጉምን ማስታከክ ሥር የሰደደ የኑሮ ጥበብ ነውና የጥያቄዎችን ቆዳና እምብርት መለየት ያንገላታል፡፡ ያም ሆኖ “የማንነት”፣ “የራስ በራስ አስተዳደር”፣ የፍትሐዊነት” ወዘተ እየተባሉ የሚደቀኑ ጥያቄዎች በፊት ለፊት ይዘታቸው ብቻ እንደማይወሰኑ መረዳት አይከብድም፡፡ ይህ የጋራ መጠሪያ የኛን ብሔረሰብ ለመግለጽ ይጠባል የሚል ቅሬታ ተስማሚ የጋራ መጠሪያ ተጋግዞ ከመፈለግ ይልቅ፣ ወደ ማፈንገጥ ሲሄድ የሚታየው ሌላ ፍላጎትም ስላዘለ ነው፡፡ ከወረዳ አልፌ “ዞን” ልሁን የሚል ጥያቄ በምንም ዓይነት የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሊሆን አይችልም፡፡ ቀረበ የሚባለውን ጥያቄ ሁሉ ለመፈልፈል የሚያስችል መረጃ ችግር ቢሆንም፣ በጥቅሉ የጥቅም ሩጫዎች (በሌሎች ሹሞች ላይ የታየ ድሎትና የኪስ እብጠት) የሚፈጥረው አስጎምዢነት፣ ከኛ አካባቢ የፈለቀ ሀብት/ገቢ ከኛ አልፎ ሌላውን ጠቀመ የሚል ስስት፣ የአስተዳደር መዋቅር ከፍ ማለቱ ከተሻለ በጀት ጋር ያገናኘናል የሚል ሥሌትና የመሳሰሉት የሕዝብን ጥቅም የማስከበር ልብስ ለብሰው እንደሚመጡ መገመት ይቻላል፡፡

  1. በየትኛውም አወቃቀር ተዋረዳዊ ያስተዳደር ይዞታዎች መኖራቸው አይቀርም፡፡ እስከተቻለ ድረስም አሸናሸኑ የሕዝብ ተመሳሳይነትን መከተሉ ለተግባባ ትድድርና በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ለመስጠት ይቀናል፡፡ ለቀናነቱ ሲባል ብጤ ለብጤ መሆንን መፈለግ አግባብ ነው፡፡ እኛ ዘንድ ያለው የይዞታ ሥሌት ግን ከዚህ ሚዛን የወጣ መሬትንና የተፈጥሮ ሀብትን የማንነነት አካል እስከማድረግ፣ የአስተዳደር ይዞታን የድርሻ ካርታ አድርጎ እስከማየት የተሽቀነጠረ ነው፡፡

በዚሁም ምክንያት ደም ያቃቡ የመሬት መናጠቅ ግጭቶች በተደጋጋሚ ተካሂደዋል፡፡ እስካሁን መቁረጫ ሳያገኙ ያሸለቡ ፍጥጫዎችና ውዝግቦችም አሉ፡፡ ከክልል ውስጥ ተለይቼ ልውጣ (የራሴን ክልል ልመሥርት/ሌላ ክልል ውስጥ ልግባ) የሚል ጥያቄ ቢነሳ፣ ጥያቄው ማንንነትን በመቁረስ ተተርጉሞ ጠብ ሊያማዝዝ የሚችል ነው፡፡ በሌላ አባባል በየአካባቢው የተፈጠረው ምድሬ ባይነት፣ ለገዛ ራሱ መሠረት የሆነውን ሕገ መንግሥታዊ መብት (የራስ ክልል የመፍጠርና ከክልል ተነጥሎ የመውጣት መብት) እስከ መርገጥ ድረስ ሊሄድ የሚችል ሆኗል፡፡

የድርሻ ምድር ባለቤትነትም ነባርነትን መሠረት ያደረገ እንደመሆኑ፣ በየአካባቢው የሚኖር ዜጋ በአንድ ጊዜ በ”ባለቤት” እና በ”ባይተዋር” ግንኙነት ውስጥ ይወድቃል፡፡ አንዱ ጋ “ባለቤት” የሆነ፣ በ“ሌላው” ምድር ውስጥ ሲገባ (ሲኖር) ባይተዋር ይሆናል፡፡ በዚህ እውነታ ላይ የትም ብትኖር የትም ብትሠራ የማንነነት መገኛህን (ባትወለድበትና ባታድግበት እንኳ) አትዘንጋ የሚል ርዕዮተ ዓለም መሰበኩ ደግሞ፣ የ“ባይተዋሩ”ን እንደ አጫራሽ መታየት ተገቢና አይቀሬ ያደርገዋል፡፡ ከባይተዋር የተቆጠረው እዚያው የተዋለደና ሠርቶ ንብረት ያፈራ ይሁን ወይም ከጊዜ በኋላ በኢንቨስትመንት የገባ፣ በብሔርተኛ ስስት እየተሸማቀቀና ነገ የሚሆነው አይታወቅም እያለ፣ ወይም በዘመኑ “የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኛነት” ንቃት እየተመራ አንድ እግሩን “ጊዜያዊ” ቤቱ ውስጥ ሌላ እግሩን “የማንነት ቤቱ” ውስጥ አድርጎ መኖርን ዘይቤው ያደርጋል፡፡

በክፍልፋይ ብሔርተኛነት የተጠመዱ ሰዎች ውጥንቅጥነት በሞላባቸው ከተሞች ውስጥ በንግድ ሥራም ሆነ በሥልጣን ላይ ቢሰማሩ በየብሔረሰብ ወገንተኝነት ማሰባቸውና በየወገን የተዘረዘረ ሩጫ መሞከራቸው የማይቀር ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት አዲስ አበባ ውስጥ በየወገን የመሳሳብና  የወገን ባለሀብት የማበራከት፣ ሀብት እያጋበሱ ወደማንነት አካባቢ የማፍሰስ ሽሚያ ምን ያህል እንዳለ፣ ከዚሁ ጋር ስንት “ወቸው ጉድ!” እና አሉባልታ በየቀኑ እንደሚከካ ጠጋ ብሎ ማስተዋል በቂ ነው፡፡

  1. በዚህ ዓይነቱ ሽሚያ አትራፊ የሚሆኑት በንግድ መረብ፣ በንዋይ፣ በብልጠትና በሠለጠነ የሰው ኃይል አቅም የቀደሙት እጅግ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ ሄዶ ሄዶም መራራቁ ሲያገጥ ንቁሪያ መከተሉ አይቀርም፡፡ ባንዲራ ቀረሽ የሆነ ቁንጥርጣሪ “የማንነት” ይዞታ የመፍጠር ርኩቻ ውስጥ መናወዝም ሕዝብን ጋልበው ኪሳቸውን ሊሞሉ የሚያደቡ ብልጣ ብልጦች መጫወቻ ለመሆን ከማጋለጡ በቀር ከድህነት ማጥ ለመውጣት ጉልበት አይሆንም፡፡

የአስተዳደር ይዞታ መስፋትና መቀነስ በኢኮኖሚ አቅም ላይ ልዩነት ያመጣልና ጭማሪ ሲገኝ በደስታ መቀበል፣ ቅናሽ የሚያስከትል ነገር ሲመጣ ደግሞ ማንገራገር መከሰቱ አይደንቅም፡፡ ኢኮኖሚ ነክ ጥቅምን በብሔረሰባዊ ማንነት ሸፋፍኖ “ማንነትህ ተነካ!”፣ “የፀረ ሰላሞች ሴራ!”፣ ወዘተ እያሉ ሕዝብን ማነሳሳትና በወልቃይት ጥያቄ ላይ እንደታየው “ዕርምጃ እንወሰዳለን!” የሚል ፀረ ዴሞክራሲያዊና ሕገወጥ የሹም ዛቻ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ እስከ ማስተላለፍ መድረስ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ የሚበጀው የነወልቃይት ዓይነቱን ጥያቄ ዓይን ገላጭነት አጢኖ፣ የኢኮኖሚ አቅምን ጉዳይ በማንነት ውስጥ ከማድበስበስ መውጣት ነው፡፡

ያለን አስተዳዳራዊ አከላለል የኢኮኖሚ አቅምን መሥፈርት በሰበዝነት አለማካተቱ ቀላል እንከን አይደለም፡፡ የተመጣጠነ የኢኮኖሚ ልማትን ማዳረስ በአፍ የሚወራውን ያህል በተግባር ቀላል አይሆንም፡፡ ለየክልሉ የዩኒቨርሲቲ ድርሻ በማንጠባጠብ ዓይነት የሚወጡትም አይደለም፡፡ ለምሳሌ ስታዲየም  በየክልሉና በየዞኑ የመገንባት ነገር በፖለቲካዊ ምክንያትና ትዕዛዛት ከሚካሄዱ የስፖርት ውድድሮች ያለፈ ነገር እምብዛም በሌለበት፣ በወኔና በወግ አይቅረኝ ስሜት ቢገፋበት አብዛኛውን ጊዜ ሥራ ፈትቶ ዳዋ የሚለብስ፣ አለዚያም በእንክብካቤ ወጪ የአካባቢ መንግሥታትን በጀት የሚመጥ ዕዳ ከመሆን አያመልጥም፡፡ የዚህ ዓይነቱ ወጥመድ ውስጥ የማይወድቀው ግንባታው ብዙ ቅጥልጥል መተደዳሪያዎችን ከሚያፈልቅ የስፖርት ባህልና የመዝናኛ ልማት ጋር ተግባብቶ ሲመጣ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ልዩ ልዩ የመዝናኛ አገልግሎቶችን የሚሻና መግዛት የሚችል (በዚህም ለውድድሮች መዝለቅ ዋስትና የሚሆን) ከተሜነት በአግባቡ ከመፈጠሩ ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው፡፡ ለኑሮ ደረጃ ዕድገትና መቀራረብ መሠረት የሆነው ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ልማት ደግሞ ከዚህ ምሳሌ ጋር ሲተያይ ውስብስብነቱ የላቀ ነው፡፡

በክልሎች መሀል በቆዳ ስፋት ያለው የሚጢጢነትና የግዙፍነት ልዩነት ብርቱ የኢኮኖሚ አምባ ሆኖ የመውጣት ዕድል ላይ የራሱን የማነቅና የማወላዳት ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው፡፡ አንዳንዶቹ ክልሎች (ጠበቡም ሰፉም) በኢኮኖሚ አውታራትና በሰው ኃይል ልማት ስንቅ ያለባቸው ደካማነት በልዩ ድጎማ የማይገፋ ነው፡፡ ያለው ክልላዊ ሽንሸና ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ እስከ ዛሬ ድረስ የሕዝብ ግምገማ ያላየው እንደመሆኑ፣ ያፈነገጡ ጥያቄዎች ብቅ ብቅ እንደማለታቸው ለክለሳ ክፍት መደረጉ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ከአንድ ክልል ወጥቶ ሌላ ክልል መፍጠርን፣ ክልል ከክልል ጋር ተቀናብሮ ትልቅ ክልል መሆንን (ያለውን የዘጠኝ ክልሎች ቁጥር መቀነስንም ሆነ መጨመርን) ሁሉ የሚፈቅድ ነው፡፡ በተዘዋዋሪም ቢሆን ጠንካራው ደጓሚ፣ ደካማው ተደጓሚ የሆነበትን ግንኙነት በተቀራረበ የኢኮኖሚ ተራክቦ ለመቀየር ከታሰበ፣ ያሉት ብሔረሰባዊ ተዛምዶዎች ሳይናጉ (በራስ የመተዳደሩ፣ ባህልና ታሪክን የመንከባበኩ፣ በራስ ቋንቋ የመማሩ መብት ሁሉ እንደተጠበቀ)፣ ደካሞቹንና ሚጢጢዎችን ክልሎች ከትልቆቹ ጋር ያጎዳኘ፣ በሁሉም ውስጥ ያሉትን የማዕድን፣  የግብርና፣ የፋብሪካ፣ ወዘተ ዕምቅ አቅሞች አውቆና ፈልቅቆ እያስተሳሰረ ሊያሠራ የሚችል ከውስጥና ከውጭ ገበያ ሥምሪት ቅልጥፍና፣ አዋጪነትና መስፋፋት አኳያ በተመረጡ የልማት ቀጣናዎች መዘርጋት የሚገባቸውን ሁነኛ የኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ ተያያዥ አውታሮች ያዋቀረ የልማት ካርታ ማሰናዳት ሩቅ እያዩ ለመራመድ ያስችላል፡፡ ማለትም የፖለቲካ ወኔና ምኞት የሚወልዷቸው ባካናና ደንባራ ፕሮጀክቶች ይቀንሳሉ፡፡ ክልሎች የሚጣመሩባቸው የልማት ዕቅዶች፣ መንግሥታዊና ግለሰባዊ አካላት የሚወጥኗቸውና የሚከፍቷቸው ሥራዎች የአገራዊ አድማስና አቅጣጫ ምሪት ያገኛሉ፡፡ ከተሞች መሄጃ መድረሻቸውን እያዩ በአግባቡ አስፍተውና አሻግረው ማቀድ ይችላሉ፡፡

እውነተኛ የዴሞክራሲ ሒደት ውስጥ እስከተገባ ድረስም የዚህ ዓይነቶቹ የተቀናጁ የልማት ትልሞች፣ የአዲስ አበባና የአካባቢው ከተሞች የጋራ ልማት ዕቅድ የደረሰበት ዓይነት ክሽፈት አያስጋቸውም፡፡ ምክንያቱም፣ የመንግሥት ሥራ አካሄድ በሕዝብ ዓይንና ጠያቂነት ሥር መውደቁ የሕዝብንና የመንግሥትን መተማመን ያስገኛል፡፡ በዚህ ላይ የዘመናችን ግስጋሴና ሰላም ከተፈነጋገጠና ከተነጣጠለ ሩጫ ይልቅ በመተጋገዝና በመሰባሰብ ጎዳና ውስጥ መሆኑ፣ ይኸው የመሰባሰብ እውነታ በኢትዮጵያ ደረጃ ይቅርና በአፍሪካ ቀንድ ደረጃም መጠቃለልን እየጠየቀን መሆኑ፣ ይኸው ጥያቄ ኢትዮጵያን ሕዝቦቿ ለመጪው ትልቅ ቤት የሚሰናዱባት ትንሽዬ ቤታቸው ያደረጋት መሆኑ፣ እነዚህ ሁሉ ስለሚያግዙንና በዴሞክራሲ ነፃነት ውስጥ በሚካሄድ የሐሳቦችና የፖለቲካ ውድድር ውስጥ ትምክህትንና ክፍልፋይነትን ለማዝረጥረጥና ለመብለጥ መቻላችን ፀሐይ በምሥራቅ የመውጣቷን ያህል እርግጥ ነው፡፡ የፈለገውን ያህል ቁርሾኛነት፣ ክልልተኛነትና ተጠራጣሪነት እየተወራጨ ወደኋላ ቢጎትተን ጥል እስካልዘረጠጠን ድረስና በኢንዱስትሪያዊ የልማት ጎዳና ውስጥ አነሰም በዛ እስከቆየን ድረስ፣ ልማቱ ራሱ የገጠር ሕዝብን ክምችት፣ አርብቶ አደርነትንና ትንንሽ ማሳ አራሽነትን እያመናመነ፤ ብሔረሰባዊ አጥሮችን እየቦዳዳሰ፣ ብዙ ዓይነት ብሔረሰቦችን ያገናኘ ጥርቅምቅም ከተሜነትን ማስፋፋቱ አይቀሬ ነው፡፡ -ለዚህም ነው ትንንሽ ማንነትና ይዞታ ላይ ከመናወዝ ወጥቶ ከማይቀረው አቅጣጫ ጋር ዕይታን  አለማስተካከል አላዋቂነት የሚሆነው፡፡

  1. የብዙ ብሔረሰቦች ስብጥርና አንዱ በሌላው ውስጥ መገኘት ባለበት አገር የእኩልነት ግንኙነትን የማቋቋም ተግባር ብሔርተኛና ትምክህተኛ ጥበትን ተሻግሮ ለየትኛውም ዓይነት ብሔረሰብና ዘር የማያዳላ፣ የየትኛውንም ብሔረሰብና ዜጋ መበደልና መንጓለል የሚቃወም አመለካከት ውስጥ መግባትን፣ እናም ሁሉንም አካባቢዎች ለኢንቨስትመንትና ለሥራ መስፋፋት ሳቢ ማድረግንና የሁሉንም አካባቢ ኋላ ቀርነት ጉዳቴ ብሎ ለልማታቸው መረባረብን ይጠይቃል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሚገኙበት የመጠቃለል አቅጣጫ ውስጥ ሰላምን እየተነፈሱ ወደ እኩልነት፣ ወደ ነፃነትና ወደ መልካም ኑሮ ለመገስገስ የሚበጃቸውና ዋስትና የሚሆናቸው ይህንን መሰሉ ህሊና እንጂ የትም ሀብት አፍርቶ ወደ የብሔረሰብ ቤት የመትፋት ውድድር አይደለም፡፡

በብሔር/ብሔረሰብነት በተሸነሸኑ ትንንሽ ዕይታዎች ውስጥ እስከ ተሸጎጥን ድረስ፣ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን ሁላችንንም የሚመለከቱ ሰብዓዊ መብቶች በየትኛውም አካባቢ ኑሮ የመመሥረት መብትን (አንቀጽ 32)፣ እንዲሁም በዘር፣ በብሔረሰብ፣ በቋንቋ፣ በትውልድ፣ በሃይማኖት፣ በፆታና በፖለቲካ አቋምም ሆነ በሀብት ያለመንጓለል መብትን (አንቀጽ 25) በአመዛኙ ያሳካ (ፍንዳታ የማያረግዝ) ሰላም መቀዳጀት ይሳነናል፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ከሞላ ጎደል ሁሉም አካባቢዎች ውስጥ አንደኛና ሁለተኛ ዜጎች ያሉ የሚያስመስል አንጓላይነትና ተንጓላይነት የመኖሩ ምክንያት፣ ሥልጣን የያዘው “ዴሞክራሲያዊ” ብሔርተኛነት የቀድሞውን አድሎአዊ ገዥነት ከመተካት አለማለፉ ነው፡፡

  1. ይህንን እንደ በጎ መቁጠር ወይም እያዩ ማለፍ የራስንም መረገጥ መፍቀድ ነው፡፡  የሙት ልጆች ይዘው የተቸገሩት ዑመር አብሮ የእርሻ ማሳቸውን መያዣ አድርገው ከቀበሌ ሹም 1,700 ብር ይበደራሉ፡፡ ጊዜው ደርሶ የብድሩን ገንዘብ መመለስ ሲሳናቸው ደግሞ ሹሙ መሬታቸውን ለሦስት ዓመታት በመጠቀም ዕዳቸውን እንዲያጣጣ ይስማማሉ፡፡ የሦስት ዓመት ጊዜው ሞልቶ መሬታቸውን ሲጠይቁ ግን ሰውየው ሸጠህልኛል ብሎ ከመካድም አልፎ ወንጀለኛ በማለት ለተወሰኑ ቀናት አሳስሮና ስለመሬት እንዲች ብለው እንዳያነሱ አስፈራርቶ ያባርራቸዋል፡፡ እኚህ ደሃ ፍትሕ ማግኘት የቻሉት የመጀመርያ ልጃቸው ለጥቃት መላሽነት ደርሶ ከሥልጣን የወረደውን ሰው ከከሰሰና በኦሮሚያ ዩኒቨርስቲ በኩል በተገኘ ነፃ የሕግ አገልግሎት ዓመታት የፈጀ ክርክር ከተካሄደ በኋላ ነበር፡፡ (ወሬው የታኅሳስ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ነው) ይህን የመሰለ የቀን ጅብነት ሳይጋለጥ ለረዥም ጊዜ መኖር የቻለው ለማናለብኝነት የማይመች (የግል መብቶችን ረገጣ ፈጥኖ የሚሰማና ምላሽ የሚሰጥ) አስተዳደር ባለመገንባቱ ነው፡፡

በሠለጠኑት አገሮች ከሕግ ውጪ በወንጀለኛ ላይ እንኳ ዕርምጃ መውሰድ እጅግ ተወጋዥና አስደንጋጭ የሚሆነው ለወንጀለኛ መብት መጨነቅ በዝቶ ሳይሆን፣ ወንጀለኛ ተብዬው ንፁህ ሊሆን እንደሚችል፣ በወንጀለኛ የተጀመረ ሕገወጥነትም ወደ ሌላውም ዜጋ እንደሚሻገር ከመረዳትና ለዚህ ቀዳዳ ላለመስጠት ሲባል ነው፡፡ ከእነዚህ ቀላል ምሳሌዎች በደልንና የፍትሕ መረገጥን በየብሔረሰባዊ/ክልላዊ ጎጆ ውስጥ መርጦና ቀንሶ ማሸነፍ እንደማይቻል መረዳት ይቻላል፡፡ በራስ ላይ ሊደርስ የሚችልን በደልና ግፍ ከሩቅ ልናበረውና ድል ልንመታው የምንችለው በማንኛውም ሰው ላይ የሚፈጸም ሕገወጥና ፍትሕ አልባ ተግባርን የሚቃረን ሥርዓትና ባህል ተጋግዘን ከዘረጋን ብቻ ነው፡፡ በመንጃ፣ በወይጦ፣ በቅማንት፣ ወዘተ. ማኅበረሰቦች ላይ ሲሰነዘሩ የኖሩ ቡትቶ ንቀቶች የሚወገዱትም በዚህ ዓይነቱ ለውጥ እንጂ ትንንሽ ይዞታዎች በማበጀት አይደለም፡፡

እናጠቃል፡፡ እስካሁን ያገኙትን እንደያዙ አፈናን በኅብረት በመታገል ዴሞክራሲያዊ የኑሮ ዘይቤዎችን እያስፋፉ የዴሞክራሲ አገዛዝን ለመትከል መብቃት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የማይታለፍ ተግባር መሆኑን በተለያየ ፈርጅ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ትግል ውስጥ አቅም እያበጀን ወደፊት ለመራመድ የሚከተሉትን እሳቤዎችና ተግባሮች መቆናጠጥ ያስፈልገናል፡፡

  • ብሔረሰባዊ ማንነት እንደ ፖለቲካ ጥያቄ ተጠይቆ የሚሰጥ/የሚፈቀድ ነገር ሳይሆን፣ አብሮ የሚኖር በጊዜያት ውስጥ የራሱን ለውጥ የሚያሳይ የማኅበራዊ ገጽታዎች አንድ ቅንብር ነው፡፡ እንኖረዋለን፡፡ ታሪክን መርምሮ ማወቅና ማሳወቅ፣ እሴቶችን መንከባከብ የዚሁ አካል ነው፡፡
  • ማንነትን በፖለቲካ ድንበሮች (ካርታዎች) መለየት ወይም አስሮ ማኖር አይቻልም፡፡ ማንነት የየካርታዎች አካል አይደለም፡፡ ካርታዎችም የማንነት አካል አይደሉም፡፡ ታሪካዊ ማኅበረሰቦች ካርታን አልፈው ይሄዳሉ፣ ይስፋፋሉ፣ ይከላለሳሉ፣ እዚያም እዚያም እንጥብጣቢ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች በ“የመገኛ” ሥፍራዎቻቸው ሳይገደቡ በውስጣዊና በውጫዊ ግፊቶች እንደተንቀሳቀሱና እንደተረጩ ሁሉ ዛሬም በተከለሉ ሥፍራዎቻቸው (ክልል፣ ዞንና ወረዳ) ተገንዘው አይቆዩም፡፡
  • እናም የሠፈራ ምድርን የማንነት ወሰን ማውጫ አድርጎ ከማየት ይልቅ ለተግባባ ትድድርና ለልማት ምቹ ሁኔታ መፍጠሪያ አድርጎ መጠቀም አዋቂነት ይሆናል፡፡ በአስተዳደራዊ ይዞታ ሸንሸና ውስጥ የማኅበረሰቦች ሴመኛነት (ወጥነት) ተንጣሎ እስከተገኘ ድረስ ለአስተዳደር፣ ለትምህርት አሳጣጥና ለልማት ይመቻልና ሚዛን ውስጥ መግባቱ አያወዛግብም፡፡ ከዚህ ጋር በየደረጃው ልማትን ለማላወስ የሚመጥን መልከዓ ምድራዊ ይዞታ፣ የአውታራትና የሰው ኃይል ስንቅ መኖሩን ማየት ይኖራል፡፡ ለሁለቱም መቋጠሪያ የሚሆነው ደግሞ የሕዝብ ውዴታ ነው፡፡ ውዴታ ከታጣ፣ ለማሳመን ጥረት ከማድረግና ሕዝብ ውዴታውን እንዲሞክረው ከመፍቀድ በቀር በጉልበት ማስገደድ ጠንቅ መትከል ነው፡፡ በዚህ ዓይን ከተመራን እንደ ድሬዳዋና ሞያሌ ባሉ ሥፍራዎች ላይ የሚታይ መፋጠጥ ሳያበጣብጥ መቃለል ይችላል፡፡ የወሰንተኛ ክልሎች የአስተዳደር አካላት ከላይ ቢስማሙም፣ የእነሱ ስምምነት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተውን ሕዝብ ፍላጎት ተቃርኖና በልጦ አይጫንም፡፡
  • የራስ አስተዳደር ዕውን የሚሆነው የራስን ታርጋ በለጠፈ የብሔረሰብ ቤት ውስጥ ከብጤ የወጣ ብጤ ገዥ ከአናት በመቀመጡ ብቻ አይደለም፡፡ በከፊል መዛነቅና በከፊል መዳበል ውስጥ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች የጋራ ትድድር ውስጥ መግባታቸውም የራስ አስተዳደር ቅርፅ ነው፡፡ ብዙ ብሔረሰቦችን ባቀፈ የዞን/የክልል ይዞታ ውስጥ በተገቢ ውክልና የተቀናበረ አስተዳደርም የራስ አስተዳደር ገጽታ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ያለው ቅርፁ ላይ ሳይሆን በቅርፁ ውስጥ የዲሞክራሲ ነፃነቶችን፣ ሰብዓዊ መብቶችን፣ እኩልነትን፣ ፍትሕን፣ በሕግ የመጠበቅ ዋስትናን፣ ታሪክን፣ ባህልን፣ ቋንቋንና ሥነ ጽሑፍን የመንከባከብና የማራመድ መብቶችን ዜጎች ማጣጣማቸው፣ የሕዝባዊ ውክልናና የገዢዎች ተጠያቂነት በተግባር እየሠራ መሆኑ ነው፡፡
  • ዓይነተ ብዙ ማኅበረሰቦችን ያሸራረበ ከተሜነት እየተፈጠረ ሲመጣ በውስጡ የራሱን አካባቢያዊ ሥነ ልቦና ይቀምማል፡፡ የጅማ ልጅነት፣ የሐረር፣ የድሬዳዋ ልጅነት የዚህ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ማኅበረሰቦች በወሰንተኛነት ግንባር ለግንባር ተገናኝተው በተለያየ የግፊት ምክንያት አንዱ ወደ ሌላው ሲፋሰሱና ሲቀላቀሉ ዝንቅ ማኅበራዊ ማንነት ይፈጠራል፡፡ ለምሳሌ የወልቃይትና የራያ ገጽታ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የማኅረሰቦች መደራረስ እስካለና እስከቀጠለ ድረስ የዚህ ዓይነቶቹ ገጽታዎች ሊቋረጡ የማይችሉ (ጠቦችና ግጭቶች ቢረብሿቸውና ቢያቆስሏቸው እንኳ እንደገና የሚያገግሙ) ተፈጥሯዊ ሒደቶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ተንጋግቶ የነበረው ብሔርተኛ ሽሚያ እነዚህን ዝንቅ እውነታዎች ባልና ሚስት እስከማፋታት ድረስ በልዩ ልዩ ሥልት (በቅስቀሳ፣ “ባለቤትና “መጤ”ን በመለየት፣ በምድር ትስስብ፣ በብሔርተኛ የማንነት “ተሃድሶ” ተቃርጦ) አበጥሮና አፅድቶ ሊጨርሳቸውና ሊገታቸው ታግሏል፡፡ አፍላ ግርግሩና ወፈፌነቱ ቢያልፍም ዛሬም ክልስ ማኅበረሰባዊ ቅንብሮች በአንድ ወይ በሌላ ብሔረሰብ የስልቀጣ ፍላጎትና በአንጓላይ አመለካከት መቆንጠራቸው፣ እንዲሁም መብትን ማራመድና መብትን መርገጥ የተደባለቁበት ውዥንብር ዛሬም አለና ይህን ለማቃለል የሚረዱ ጥቂት ነጥቦችን እናስቀምጥ፡፡
  • ከዝንቅ ማኅበረሰባዊ ታሪካዊ ቅንብር ውስጥ የግለሰቦች ወደ አንዱ ወይ ወደ ሌላው ብሔረሰባዊ ማንነት (ወደ አንዱ ቋንቋና ባህል) ማጋደል ነፃ መብት ነው፡፡ ታሪካዊ “ማስረጃ” እየደረደሩ፣ “ክልላዊ የማንነት ጉዳይ” እያሉ ወይም ሕዝብ በተወካዮቹ ወሰነ በሚል ጨዋታ ክልስ ማኅበረሰብን ምድብህ በዚህ ብሔረሰብ ውስጥ ነው ማለት፣ ለምሳሌ ወልቃይትን ወደ ትግሬነት ወይም ወደ አማራነት መመደብ ኢዴሞክራሲያዊነት ነው፡፡ “. . . ነህ” ከሚል ፍርድና ምደባ “. . . ነን” የሚል እምነት ይበልጣል፡፡ 
  • ዝንቅነትን የብሔረሰባዊ ጥራት መጓደል አድርጎ በማየት ወይም ለግዛት መቀነስ መነሻ ሊሆን የሚችል ክፍተትን በመዝጋት ሥሌት ብዙ (ሁለት) ቋንቋ ተናጋሪነትንና ደባል ባህልን በተለያየ ሥልት ድምፅ አጥፍቶ መሸርሸር፤ አፍ መፍቻዬ ባሉት የመማር አማራጮችን በደባሎቹ ቋንቋዎች ሁሉ አለመስጠት ደግሞ የባሰ ተፈጥሯዊ የመወራረስ ሒደትንና የተወራረሰ ማንትን ህልውና መፃረር ይሆናል፡፡
  • ከዝንቅ ማኅበረሰብነት ውስጥ በሚነሱ የዚህ የዚያ ብሔረሰብ ወገን ነን በሚሉ ዝንባሌዎች መመናዘርም ወደ መናቆር የሚወስድ እንጂ የሚያስተባብር አይደለም፡፡ ሽፍሻፊ ማሰረጃዎች እየቆጠሩ ወልቃይትነት ትግሬነት ወይም አማራነት መሆኑን ለማሳመን መሞከሩም ብዙም የሚፈይድ አይደለም፡፡ የወልቃይት ሕዝብ ምርጫና ፍላጎት ዞሮ ዞሮ ወሳኝ ቢሆንም፣ በአጠቃላይ የአማራና የትግሬ ተዛምዶ ውስጥ የትግሬነትና የአማራነት መወራረስ ወልቃይትነት ላይ የተወሰነ ሳይሆን ትግራይ፣ ጎንደር፣ ወሎ ድረስ የተረጨ፣ ከወሎም የጎንደሩ መወራረስ የጠለቀ የሆነበት ትልቅ እውነታ መዘንጋት የለበትም፡፡
  • የጠፋ ቋንቋን፣ ባህልንና እምነትን እየቆፈሩና በቅርስነት እየመዘገቡ ማቆየትና ከየት እንደመጡ ማሳወቅ ኃላፊነትን የተረዳ ተግባር ነው፡፡ ነፍስ አዘርቶ በውስጡ ለመኖር መሞከር ደግሞ የግለሰቦች ነፃ ፍላጎት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ዘሎ የጥንቱን፣ እውነተኛው የማንነት መታወቂያ አድርጎ የዛሬውን ገጽታ ደግሞ የማንነት መጉደፍ አድርጎ መፈረጅ፣ በዚህም ላይ የተመሠረተ ምንጣሮ መጀመር መብት ረገጣ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ ውስጥ የመንግሥት አካል እጁን ማስገባትና የተዘነጋ ባህልና ቋንቋን ለመማር ለሚደረግ ጥረት ፖለቲካዊና የጥቅማ ጥቅም ድጋፍ እየሰጡ “ሰዎች በነፃ ፍላጎታቸው የሚያደርጉት ነው” የሚል ድብብቆሽ ውስጥ መሹለክሉክ አደገኛ ተግባር ነው፡፡
  • በተቃራኒው (ያለጫና)፣ ነባርም ህያውም የሆኑ ቋንቋዎችን ባካተተ መልክ ከአንድ የበለጠ አገራዊ ቋንቋ የመማር ዕድልን መክፈት፣ መልካም የባህል እሴቶች ታዋቂነታቸው እንዲሰፋ ማድረግ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች የተባበረና የተሳሰረ ልማት ጋር የሚስማማ ነው፡፡ ልማትና መሰባሰብ የሚወስደን ወደ ጠራ ማንነት ሳይሆን ብዙ ባህል ወደ ተላላሰበት ማንነት ነው፡፡
  • በተጠራቀመ ቅሬታና ጉምጉምታ የአስተዳደር መዋቅር የሚናጥበትን ዕድል ለማቃለልም፡፡
  • በየአስተዳደሩ ውስጥ የሚደርሱ ተዛነፎችንና የፍትሐዊነት ችግሮችን የሚያስተውል መልካም የሕዝብ መተሳሰብ መኖሩን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለየአካባቢው ችግርና ልማት እኩል ተቆርቋሪ፣ እኩል ለፊ፣ የአካባቢውን ባህሎችና ቋንቋዎች እንደ ራስ ወደ ማየትና ወደ ማክበር የሚወስድ አሳታፊነት መፍጠር፡፡ ለዚህም መቃናት ብሔረሰብ የለየ ወይም ንዑስ ማኅበረሰቦችን ውጭ የተወ አደረጃጃትን መቀየር፡፡ እነዚህ አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ በስም “ግንባር” ከመባል በቀር በአቋም አምሳያ ሆኖ እያለ አባላቱን በክልል/በብሔረሰብ እየዘረዘረ የሚያሰባሰብ ኅብረ ብሔራዊ ድርጅት ወደ ውህደት ማምራት ግድ ይለዋል፡፡ የክልል ፓርቲ ሆኖ የዋነኛ ብሔረሰብ/ቦች መሰባሰቢያ በመሆን የተወሰነ ድርጅትም የክልሉን ሕዝብ ከንዑሳኑ ጭምር ሊያንፀባረቅ እንዲችል አድርጎ፣ የአስተሳሰብና የአደረጃጀት በሩን መክፈት ያሻዋል፡፡ ትምክህትንና ጎሰኝነት በመታገል ረገድ የኦሮሞ ፓርቲ መሆንና የኦሮሚያ ፓርቲ መሆን ትልቅ ልዩነት አለው፡፡ ይህ እነ ብአዴንና ሌሎችም ያሉበትን ችግር የሚያሳይ ምሳሌ ነው፡፡ በብሔረሰባዊ ጥንቅር ላይ ብቻ አትኩሮ የተደራጀ ፓርቲ በአግባቡ ዴሞክራሲያዊ ባህርይ መጎናፀፍ ፈተና ይሆንበታልና፡፡  በአካባቢው ውስጥ ያሉ ንዑሳንን መብት ያለአድልኦ የማስከበር ኃላፊነት ከዕይታው ውጪ ይሆንበታልና፡፡ ራሱንም ከጅምላ ወገንተኝነትና ንቁሪያ ማላቀቅ ይቸግረዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ትምክህትንና ጎሰኝነትን በማምከን ከፖለቲካ እስከ ንዋይ የሰፋ ሥምሪት ባለው ሙስና ላይ ሊገኝ የሚችለውን ድል ያጓትታል፡፡
  • በየተወሰነ ጊዜ የአስተዳደር መዋቅሮች በየደረጃቸው ያላቸውን ቀናነት መፈተሽ፣ የሕዝብንም አስተያየት ማጥናት፡፡
  • የአከላለል መዋቅርን የሚመለከቱ ጥያቄዎች በተነሱ ጊዜም በዴሞክራሲያዊ ልዩ ልዩ መንገዶች እንዲብላሉ መተውና ብሎም ሕጋዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው አኳኋን እልባት እንዲያገኙ ማድረግ፣ ከዚህ በተቃራኒ በመንግሥት አካላትም ሆነ በድንገቴ ቱግታ የሚካሄድ አፈና እንዳይሰነዘርባቸው ነቅቶ መጠበቅ፣ በተሰነዘረ ጊዜም ፈጥኖ ማምከንንና ለሕግ ተጠያቂነት ማቅረብን እንደ ሥርዓት ማዝለቅ፡፡
  • አብሮም የመብት ረገጣዎች ከመፈጸም እንዲሸማቀቁ፣ በተፈጸሙ ጊዜም ተጋልጠው እንዲታረሙ፣ እናም የእኩልነት አመለካከትና አያያዝ እየሰፋ ማኅበረሰባዊ ወዳጅነት እንዲጎለብት ነፍስ ያላቸው የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪና የእንባ ጠባቂ ተቋማት በሁሉም ክልሎች ውስጥ ያለሥጋት መንቀሳቀስ እንዲችሉ በተግባር የሚታይ ሕጋዊ ዋስትና መስጠት ይበጃል፡፡
  • የክልሎችን የልማት ርቀት ለማቀራረብ የሚስማማ የተቀናጀ መርሐ ግብር ነድፎ ከማፍጠን ጎን፣ ለክልሎች የሚደረግ የፌዴራል ድጎማ የበጀት ጉድለታቸውን ከማቅለል ባሻገር በአግባብነት እርባና የተመሩ (ከዓመት ወደ ዓመት የሕዝብን መልካም ኑሮ የሚያሳድጉ) የልማት ጉዞዎችን ወደ ማበረታት አቅጣጫ እያዘነበለ እንዲሄድ አድርጎ መምራት፣ ለዝና በሚገነቡ ነገሮች ላይ ጥሪትን የማባከንን ተግባር ለመቀነስ፣ እናም ለሕዝብ እርካታ ቅርብ  ለመሆን ይረዳል፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተቀደዱት ፈሮች ተጋግዘው በብሔረሰብ ስበት ሳይሰነከሉ ሰዎችን በችሎታቸው፣ በትጋታቸውና በጨዋነታቸው መዝኖ የማስቀመጥ ባህል ወደ ሚዳብርበት፣ ተከባብሮ በመነጋገር ንቁሪያ ወደ ሚመክንበትና ጥላቻዎች ወደ ሚታጠቡበት፣ የ”መጤ” ማኅበረሰብ አባል አድልኦ ተደረገብኝ ብሎ ቢቃወም ወይም ቢከስስ አድራጎቱ እንደ መዳፈር ሳይሆን እንደ መብት ወደ ሚታይበት ትልቅ መንገድ ውስጥ ይከቱናል፡፡ በዚህ መንገድ ውስጥ ተጉዘን ኢወገናዊ በሆኑ ተቋማት ላይ የዴሞክራሲን መቋቋም ካሳካን፣ የአንድ ወይም የጥቂት ብሔረሰቦች ሥርዓታዊ የበላይነትን ታሪክ እንዘጋለን፡፡ ይህም ብቻ አደለም፡፡ በዛሬ እውነታችን ይሆናል ተብሎ የማይታሰበው የኦሮሚያ፣ የአማራ ወይም የሌላ ክልል ዋና ብሔረሰብ ተወላጅ ያልሆነ ሰው ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቶ የክልል መሪ የሚሆንበት አስገራሚ ዕለት አንድ ቀን መከሰቱ አይቀርም፡፡ ለአኅጉራችንና ለክፍለ አኅጉራዊ አካባቢያችን ትስስር አርዓያ ለመሆን የምንበቃውም በዚህ የእኩልነትና የነፃነት መስመር ውስጥ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...