በአዲስ አበባ ከተማ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ከ400 ሺሕ በላይ ሕዝቦች በሴፍቲኔት ፕሮግራም ሊታቀፉ ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም ከሚቀጥለው 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኞችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው ዓርብ ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በዚህ ፕሮግራም ያለረዳት የቀሩ ከ66 ሺሕ በላይ አቅመ ደካሞች ይሳተፋሉ፡፡
በዚህ ፕሮግራም የደሃ ደሃ የተባሉ አካል ጉዳተኞች፣ አቅመ ደካሞችና ሴተኛ አዳሪዎች ሲሆኑ በትክክል ችግር ያለባቸው መሆናቸውን የሚቋቋመው የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ምክር ቤት አጣርቶ፣ በመጀመርያው ዙር በስድስት ከተሞች በሚጀመረው የሴፍቲኔት ፕሮግራም በአጠቃይ ከ600 ሺሕ በላይ ወገኖች ይሳተፋሉ፡፡ ለዚህም 450 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተይዟል፡፡
ከዚህ በጀት ውስጥ 300 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም ባንክ የተገኘ ሲሆን፣ ቀሪው በኢትዮጵያ መንግሥት ይሸፈናል ተብሏል፡፡
የከተማ ቤትና ቤቶች ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ በሁለም የአገሪቱ ከተሞች የሚገኙ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው የደሃ ደሃ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለአብነት ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለምኖ አዳሪዎች፣ ሴተኛ አዳሪዎች ‹‹ሥራ ፈት ዜጎች›› አካል ጉዳተኞች የአደንዛዥ ዕፅ ተጎጂዎች፣ የአዕምሮ ጤና ሕመምተኞችና ወጣት ጥፋተኛ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
መረጃው እንዳለው በዚህ ፕሮግራም 4.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 3.5 ሚሊዮን ሰዎች ወደ ተለያዩ የሥራ መስኮች ሊሰማሩ የሚችሉ ናቸው፡፡ 1.3 ያህሉ ደግሞ ወደ ሥራ ሊሰማሩ የማይችሉና በቀጥታ የማኅበራዊ ሴፍቲኔት የሚያስፈልጋቸው ናቸው ተብሏል፡፡
ይህ ፕሮግራም ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት በቅርብ ለተቋቋመው የከተሞች ምግብ ዋስትናና የሥራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ይሆናል ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ በተለይ በገጠሩ ክፍል ቀደም ብሎ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጀምሮ ብዙ ለውጥ ማምጣቱ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን በከተሞች ይህ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ባለመጀመሩ በ2004 ዓ.ም. በተጠና ጥናት 25.7 በመቶ የሚሆኑ የከተማ ነዋሪዎች ለምግብ ዕጦት ተጋላጭ እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡