በኪንታሮት (Haemorrhoid) ሕመም ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ መሆኑ የሚነገረው፣ የቀድሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) አመራር አቶ ሀብታሙ አያሌውን ሕመም፣ በአገር ውስጥ መታከም መቻል አለመቻሉን፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አጣርቶና አረጋግጦ እንዲልክ ፍርድ ቤት ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
አቶ ሀብታሙ የመጨረሻው የኪንታሮት ሕመም ደረጃ ላይ መድረሱንና በውጭ አገር ካልታከመ ሊድን እንደማይችል፣ ክትትል ሲያደርግበት የነበረው የካዲስኮ አጠቃላይ ሆስፒታል የሕክምና ቦርድ ሦስት ሐኪሞች፣ በፊርማቸው ያረጋገጡበት የሕክምና ማስረጃ ሰነድ፣ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የቀረበ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ለሦስተኛ ጊዜ ሌላ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
አቶ ሀብታሙ ከተከሰሰበት የሽብር ድርጊት ወንጀል፣ በሥር ፍርድ ቤት መከላከል ሳያስፈልገው በነፃ የተሰናበተ ቢሆንም፣ ከአገር እንዳይወጣ የተጣለበት እገዳ ሳይነሳ፣ በሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር የተሰኘው ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ ማቅረቡና ክርክር ተደርጐበት ለብይን መቀጠሩ ይታወሳል፡፡
የተጣለበት ከአገር አለመውጣት እግድ ሳይነሳ፣ ይግባኝ የተባለበት አቶ ሀብታሙ በመታመሙ፣ እግዱን ለማስነሳት ለይግባኝ ሰሚው ችሎት ወደ ውጭ ሄዶ ለመታከም እንዲችል፣ የሕክምና ማስረጃ ያቀረበ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱን ወዲያውኑ ማሳመን አልቻለም፡፡ በመሆኑም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቋል፡፡
ችሎቱ ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደገለጸው፣ አቶ ሀብታሙ ወደ ውጭ አገር ሄዶ እንዲታከም የሕክምና ማስረጃ የሰጠው ካዲስኮ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ ‹‹ሕክምናውን መስጠት የማይቻለው በራሱ በሆስፒታሉ ነው ወይስ በሌሎችም ሐኪም ቤቶች?›› በማለት ጠይቆ፣ በሌሎቹም ሐኪም ቤቶች ከሆነ፣ ይኸንን ለማለት የሚያስችል ሥልጣን ያለው መሆኑን አብራርቶ ለችሎቱ እንዲልክ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አቶ ሀብታሙ አያሌው የታመመውን ሕመም በአገር ውስጥ ማከም መቻል አለመቻሉንም አጣርቶ እንዲልክ ችሎቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ ትዕዛዞቹን ለመጠባበቅና ብይን ለመስጠት ለመስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡