Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለተበላሹበት ባቡሮች በራሱ ወጪ መለዋወጫ አስገባ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለተበላሹበት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡሮች መለዋወጫ አስገባ፡፡

ኮርፖሬሽኑ ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎት ያስገባቸው 41 ባቡሮች አገልግሎት መስጠት በጀመሩ በአሥረኛ ወራቸው 19 ባቡሮች በብልሽት ምክንያት አገልግሎት መስጠት በማቆማቸው ነው መለዋወጫዎቹ የተገዙት፡፡

እንደ ሪፖርተር ምንጮች ገለጻ 19ኙ ባቡሮች በብልሽት ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ የተደረጉ ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክትን ገና አጠቃሎ ያላስረከበው ቻይና ሬልዌይ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ የጥገና አገልግሎት ከመስጠት በስተቀር መለዋወጫ የመግዛት ኃላፊነት እንደሌለበት በመግለጽ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡

ይህንን ውዝግብ ቀደም ሲል በዘገብንበት ወቅት ያነጋገራቸው የኮርፖሬሽኑ የሕብዝ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ ከባቡሮቹ ውስጥ የተወሰነ ብልሽት የገጠማቸው ቢኖሩም፣ አብዛኞቹ ግን በተጠባባቂነት እንደቆሙ ገልጸው ነበር፡፡

አስፈላጊውን የመለዋወጫ ወጪ በመሸፈን ኮርፖሬሽኑ መለዋወጫዎቹን ለማስገባት እየጣረ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡

የቻይናው ኮንትራክተር የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክትን ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ሳያስረክብ፣ ኮርፖሬሽኑ የመለዋወጫ ወጪ እንዴት ሊሸፍን ይገደዳል በሚል ቀርቦላቸው ለነበረ ጥያቄ፣ ‹‹ዋናው ነገር የተበላሹትን ባቡሮች ወደ አገልግሎት ማስገባት  ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ወጪ በቻይናው ኮንትራክተር መሸፈን ያለበት ከሆነም የመያዣ ክፍያ ለኮንትራክተሩ ባለመከፈሉ ወደፊት ከዚያ ክፍያ ላይ ሊወራረድ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ደረጀ ሰሞኑን ለሚዲያ ተቋማት በሰጡት መግለጫ መለዋወጫው ወደ አገር ውስጥ እየገባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እየገቡ ያሉት መለዋወጫዎች ከፍሬን እንዲሁም ከማቀዝቀዣ መሣሪያዎች ጋር የተገናኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የባቡሮቹ ብልሽትም ከዚሁ ጋር የተገናኘ ነው፡፡

ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር 41 ባቡሮችን ያቀረበው CNR ኮርፖሬሽን ባቡሮቹ አልትራቫዮሌት ጨረሮችን 90 በመቶ መከላከል የሚችል መስኮትና ጣርያ የተገጠመላቸውና ከፍተኛ የሙቀት መጠንን እንዲሁም ዝናብን መቋቋም የሚችሉ መሆናቸውን በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡

ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች በበኩላቸው ችግሩ የኢንጅነሪንግ ፕሮኪዩርመንትና ኮንትራት (EPC) የውል ዓይነት በመሆኑ የተፈጠረ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት EPC ኮንትራቶች ኮንትራክተሩ ፕሮጀክቱን አጠናቆ ማስረከብ ብቻ ኃላፊነቱ እንደሆነና ፕሮጀክቱን ከመረከቡ በፊት በተባለው የጥራት ደረጃና ስፔሲፊኬሽን መሠረት መሆኑን የማረጋገጥ ሥራ የኮርፖሬሽኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች