Wednesday, February 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ትልቁና ዋናው ምሥል ኢትዮጵያዊነት ይሁን!

ኢትዮጵያችን ለዘመናት ስሟን በክፉም በደጉም ያስጠሩ በርካታ ውጣ ውረዶችን ያለፈች አገር ናት፡፡ በአራቱም ማዕዘናት በተለያዩ መልክዓ ምድራዊ አሠፋፈር ውስጥ ሆነው በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት የራሳቸው ማንነት ያላቸው ልጆቿ፣ ልዩነቶቻቸውን ውበትና ጥንካሬ አድርገው ለዘመናት በአንድነት ኖረዋል፡፡ ምንም እንኳ በተለያዩ ዘመናት የተነሱ ገዥዎች ከበጎ ተግባሮቻቸው በተጨማሪ ያደረሱዋቸው በደሎች ቢኖሩም፣ ኢትዮጵያዊያን ለትልቁና ለዋናው ምሥል ኢትዮጵያዊነት በሰጡት ትልቅ ግምት በመከባበርና በመተባበር አብረው ዘልቀዋል፡፡ ይኼም አብሮነት እስካሁን አለ፡፡ የኢትዮጵያዊነት ትልቁ ምሥል መገለጫ የሆኑት ጥልቅ የአገር ፍቅር፣ አርበኝነት፣ አርቆ አስተዋይነትና ታጋሽነት የሕዝባችን የጋራ እሴት መሆናቸውን ማንም አይክድም፡፡

ኮሎኒያሊስቶች አፍሪካንና የተለያዩ አገሮችን በብረት መዳፋቸው አንቀጥቅጠው በሚገዙበት በዚያ አስከፊ የጭቆና ዘመን፣ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ታላቅ ተምሳሌት የሆነውን የዓድዋ የፀረ ኮሎኒያሊስት ድል በኢትዮጵያ ምድር ዕውን የሆነው በዚህ ታላቅ የኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት ነው፡፡ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መሠረት የጣለውና ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች የአርነት ትግል መነሳሳት ትንሳዔ የሆነው ታላቁ የዓድዋ ድል በኢጣሊያ ወራሪዎች ላይ ብቻ የተገኘ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፉ የቅኝ አገዛዝ ኃይል ላይ የተጎናፀፍነው ወደር የሌለው ድል ነው፡፡ በአገሪቱ የዘመናት ታሪክም እንደ አንድ የታላቅ ዘመን ገድል ይወሳል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከዳር እስከ ዳር ተጠራርተው አገራቸውን ከኮሎኒያሊስቶች ቅርጫ የታደጉበት ብቻ ሳይሆን፣ አገርን በፅናትና በጥልቀት የመውደድ አርበኝነትን ለዓለም ያስተማሩበት ነው፡፡ ይህ ትልቅ የሆነ የኢትዮጵያዊነት ምሥል ማሳያ በፀረ ፋሽስት ትግሉም ሆነ በተለያዩ ጊዜያት በተግባር ተደጋግሞ ታይቷል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በመሆን ለአፍሪካውያን መሰባሰቢያ መሆን የቻለችው በታላቁ የዓድዋ ድል ተምሳሌትነትዋ ነው፡፡ ይህቺ አፍሪካውያንን ያሰባሰበች ታላቅ አገር ሕዝብ ልዩነቱን ለመልካም ተግባር አውሎ ውበትና ጥንካሬ ማድረግ የቻለው፣ ከሚለያዩት ይልቅ የሚያመሳስሉት በርካታ የጋራ እሴቶችና ጥቅሞች ስላሉት ነው፡፡ ሕዝባችን በአርቆ አስተዋይነቱ አገሩን ዘመናትን አሸጋግሮ በአንድነቷ ለትውልድ በቅብብሎሽ ሲያስተላልፍ፣ ደስታውንም ሆነ ችግሩን እንዲሁ በጋራ እየተቋደሰ ነበር፡፡ ምንም በደሉ ቢከፋና ችግሩ ቢጠና እንኳ ቅድሚያ የሚሰጠው ለአገሩ አንድነትና ለታላቁ ምሥል ኢትዮጵያዊነት ነበር፡፡ ይኼም በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ ታይቷል፡፡ በባዕዳን ሳይቀር ተመስክሯል፡፡ ይህ ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ ጉዳይ አሁን ችግር እየገጠመው ነው፡፡

በዚህ ዘመን በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች ለታላቁ የኢትዮጵያዊነት ምሥል የሚሰጡት ዋጋ ምን ይመስላል? በከፍተኛ መስዋዕትነት የተገነባው የዚህች ታላቅ አገር ሉዓላዊነት ምን ያህል ያሳስባቸዋል? ዜጎች እንደመጡበት ማኅበረሰብ ካላቸው ማንነት ጋር ኢትዮጵያዊነትን እንዴት ይመለከቱታል? ከግል ወይም ከቡድን ፍላጎትና ጥቅም በዘለለ ታላቁ የኢትዮጵያዊነት ምሥል ያለው ሥፍራ ምንድነው? ወዘተ የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ስናነሳ አስተዛዛቢ ጉዳዮች ይታያሉ፡፡ አንድ ዜጋ የእኔ ነው የሚላቸው ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት፣ የፖለቲካ አቋምና የመሳሰሉት የራሱ መገለጫዎች ናቸው፡፡ መብቱም ናቸው፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ሁሉ ልጥና ማሰሪያ አገር የምትባል ትልቅ ጎጆ ከአራቱም ማዕዘናት መነሻ ያላቸው ዜጎች የጋራ መሰባሰቢያ ስትሆን፣ ከዚያ አልፋ ተርፋ የፓን አፍሪካኒዝም መሠረትና የአፍሪካውያንም እናት ናት፡፡ በተጨማሪም የዓለም ጥቁር ሕዝቦች በተምሳሌትነት የሚመለከቷትና የሰንደቅ ዓላማዋን ኅብረ ቀለማት የተዋሷት ናት፡፡ ይህንን በአንክሮ የሚመለከት ዜጋ ራሱን እንዴት ይመረምራል?

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፉ ወገኖች በሙሉ ለኢትዮጵያዊነት ትልቅ ምሥል የሚሰጡት ዋጋ ምንድነው? ከጠበበው የፖለቲካ ፕሮግራምና የመተዳደሪያ ደንብ በላይ በርካታ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ባሉባት ኢትዮጵያ፣ ከሥልጣን ባሻገር ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ወቅታዊ የፖለቲካ ወጀብ እንደ ጀልባ ወደፈቀደበት ሥፍራ የሚነዳቸው ሳይሆኑ፣ ይልቁንም ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ይዘው የዘለቁትን በአንድነት ውስጥ ልዩነት፣ በልዩነት ውስጥ አንድነት የሚለውን የጋራ ዓላማ ማስፈጸም ይገባቸዋል፡፡ ከጠባብ የቡድን ፍላጎት በላይ መላ የአገሪቱን ሕዝቦች ለበለጠ አንድነትና ለበለጠ አገራዊ ግንባታ የሚያነሳሱ ተግባራትን በማከናወን፣ ታላቁን የኢትዮጵያዊነት ምሥል ሊያስቀጥሉ ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ዜጎችን በመልክዓ ምድራዊና በቋንቋ ልዩነት እየከፋፈሉ ትልቁን የኢትዮጵያዊነት ምሥል ለማጥፋት የሚደረገው ዘመቻ ተሳታፊ መሆን በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ ከጊዜያዊ የሥልጣን ሩጫ በላይ የአገሪቱና የሕዝቡ ህልውና መቅደም አለበት የሚባለው ለዚህ ነው፡፡

ምሁራን ለዘመናት ከተጫጫናቸው ድብርት ውስጥ ለመውጣት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያሳዩም፣ ተሳክቶላቸው የሚፈለግባቸውን ግዳጅ ሲወጡ ለማየት አልተቻለም፡፡ አልፎ አልፎ ደፈር የሚሉት አደባባይ ብቅ ቢሉም፣ ብዙዎቹ ከታላቁ ምሥል በታች እየተንፈራፈሩ እርስ በርስ ሲወጋገዙ ነው የሚታዩት፡፡ ወይም የራሳቸውን ዝናና ገድል እያጎሉ የማይረባ አጀንዳ ሲጎትቱ ይስተዋላሉ፡፡ በዚህ በዘመነ ግሎባላይዜሽን ከተናጠል ይልቅ ኅብረት፣ ለብቻ ከመቆም ይልቅ ከሌሎች ጋር መዋሀድና ሰፊ አድማስ መፍጠር ሲሰበክ፣ ለአነስተኛ ጎጆ ቅለሳ ከሚባዝኑት ጋር ወዲያና ወዲህ ማለት ያስተዛዝባል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያዊነት ምሥል የጭቆናና የባርነት ማሳያ ሆኖ ሲቀርብ ለማረምና ትክክለኛውን አቅጣጫ ለማሳየት ዳተኛ መሆን አሳዛኝ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ከአገር በላይ ምንም ነገር የለምና ለታላቁ የኢትዮጵያዊነት ምሥል የሚከፈለውን መስዋዕትነት መቀበል የግድ ይላል፡፡ ለነገው ትውልድ በክብር የምትተላለፍ የጋራ አገርን ለመገንባት የምሁራኑ ተሳትፎ ሊታከልበት ተገቢ ነው፡፡ ድብርቱ ይብቃ፡፡

የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች አገርን ለማፍረስ የሚደረጉ ሙከራዎችን የማክሸፍ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ የሚያሰኟት ኦሮሞው፣ አማራው፣ ትግሬው፣ ጉራጌው፣ ጋምቤላው፣ ወላይታው፣ አፋሩ፣ ሶማሌው፣ ሲዳማው፣ ወዘተ. እንጂ የተናጠል ማንነቶች አይደሉም፡፡ እነዚህ ከ80 በላይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ማንነቶች ለዘመናት የገነቧትና መስዋዕትነት የከፈሉላት አገር፣ በጠባብነትና በትምክህት በተወጠሩ ወገኖች መሠረቷ እንዲናጋ አያስፈልግም፡፡ ይልቁንም በታላቁ የኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር እኩልነት እንዲሰፍን፣ ዴሞክራሲ እንዲገነባ፣ ሰብዓዊ መብት እንዲከበር፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር፣ አምባነንነት እንዲጠፋ፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ ወዘተ. መታገል ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ታላቅ ዓላማ በማፈንገጥና የተለያዩ ደካማ ምክንያቶችን በመደርደር የሕዝባችንን የዘመናት አብሮነት ለመሸርሸር የሚደረገው ሙከራ መወገዝ አለበት፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን ብቻ ሲባል የሚሰበኩ አገር የሚበታትኑ ወሬዎች ለሕዝባችን አይበጁትም፡፡ ቅንነት የጎደላቸውን የማቃናት ታላቅ ኃላፊነት የአገር ወዳድ ዜጎች ነውና፡፡ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና የሚረጋገጡት ታላቁ የኢትዮጵያዊነት ምሥል ከምንም ነገር በላይ ትኩረት ሲቸረው ነው፡፡ በመሆኑም ትልቁና ዋናው ምሥል ኢትዮጵያዊነት ይሁን!             

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

‹‹ወልቃይት የአማራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም እስትንፋስ ነው›› አቶ ዓብዩ በለው፣ የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት

ለወልቃይት የአማራ ማንነት መከበር የሚታገለው የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት...

ሕዝብ በሌለበት ሕዝበ ውሳኔ ይካሄድ መባሉን እንደማይቀበለው የቁጫ ምርጫ ክልል አስታወቀ

በኢዮብ ትኩዬ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ይካሄዳል የተባለውን ‹‹የደቡብ...

የድሬዳዋን ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ለመመለስ ሪፈረንደም እንዲካሄድ አማራጭ ሐሳብ ቀረበ

የድሬዳዋ አስተዳደር ራሱን የቻለ ክልላዊ መንግሥት እንዲሆን ወይም ከሶማሌና...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...

የፀረ ሙስና ትግሉ ጅማሮና የመንግሥት ሠራተኛው

በንጉሥ ወዳጅነው   በኢትዮጵያ ሁኔታ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት...