Thursday, May 30, 2024

ሁሉን አሸናፊ የሚያደርግ ግድብ የማየት ጉጉት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን እየጎበኙ ለነበሩ የግብፅ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳንና የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የግድቡ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ገለጻ ያቀረቡት የግድቡ የፕሮጀክት ማኔጀር ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሲናገሩ፣ ‹‹ዲዛይን፣ ዕቃዎችና የሥራ ሒደቱን ጨምሮ የግንባታው ሒደት ገጽታዎች በሙሉ ኃላፊነት በተሞላበት፣ ሙያዊና ዓለም አቀፋዊ ደረጃን በጠበቀ መልኩ ተከናውኗል፤›› ብለዋል፡፡ ጋዜጠኞቹ ወደ ግድቡ ያደረጉትን የመስክ ጉብኝት ከምሥራቅ ናይል የቴክኒክ የቀጠና ቢሮ (ኢንትሮ) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የስዊዲን ዓለም አቀፍ የውኃ ኢንስቲትዩት ነው፡፡ ጋዜጠኞቹ ወደ መስክ ከመሄዳቸው በፊት ከሐምሌ 21 ቀን 2008 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ በአዲስ አበባና በአሶሳ የምሥራቅ ናይል ተፋሰስንና ግድቡን በተመለከተ ሥልጠና ተከታትለዋል፡፡

እንደ ኢንጂነር ስመኘው ገለጻ፣ የህዳሴ ግድቡ እየተገነባ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ሲሆን፣ ይህም በአነስተኛ ዋጋ፣ ለአካባቢ ተስማሚ ሆኖና የሚጠቀመውም የውኃ መጠን አነስተኛ ሆኖ የሚከናወን ነው፡፡ ‹‹አሁን ፕሮጀክቱ በሚከናወንበት ቦታ 11,000 ሰዎች በሥራ ላይ ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ከ30 አገሮች የተውጣጡ 350 የውጭ ዜጎች ይገኛሉ፤›› ብለዋል፡፡

የናይል ተፋሰስ አገሮች የጋዜጠኞች ቡድን ይፋዊ ጉብኝት ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡ ጉብኝቱ ከግማሽ ቀን በላይ የወሰደ ሲሆን፣ የጋዜጠኞች ቡድን አብረውት ከተጓዙ ምሁራንና የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ምሽቱን እዚያው አሳልፏል፡፡ ኢንጂነር ስመኘውና ባልደረቦቻቸው ለቡድኑ ያደረጉት አቀባበልም ሙገሳ የተቸረው ነበር፡፡

ከጉብኝቱ አስቀድሞ የተሰጠው ሥልጠና በጋዜጠኞቹ መካከል በነበረው የሐሳብ ልውውጥ፣ በቀረቡት ምሁራን ጥናቶች፣ ከአገሮቹ ኃላፊዎች ጋር በተደረገው ውይይት አዳዲስ ምልከታዎችን የፈጠረ ቢሆንም፣ የመስክ ጉብኝቱ ግን ለጋዜጠኞቹ በተለይ ከኢትዮጵያ ውጭ ላሉት ፈጽሞ የተለየ ምላሽ ነው የሰጣቸው፡፡

ሃይተም ሞሐመድ ባለፉት አምስት ዓመታት ለዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የሠራ ግብፃዊ ጋዜጠኛ ነው፡፡ በእነዚህ አምስት ዓመታት ሃይተም ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ስለ ግብፅ የፖለቲካ ሁኔታ ዘግቧል፡፡ ሃይተም የፖለቲካ ሳይንስ ምሩቅ ሲሆን፣ ሥራ የጀመረውም የፖለቲካ ተመራማሪ ሆኖ ነው፡፡ ‹‹ናይል የግብፅ ሳምባና ልብ ነው፤›› ብሏል፡፡

ለሃይተም ይህ የመስክ ጉብኝት የተለየ ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ ‹‹አሁን ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ የአገሪቱን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሁኔታ በሚገባ ካየሁና ወደ ግድቡ መጥቼ ጉብኝት በማድረግ የግድቡን ማኔጀር ኢንጂነር ስመኘውንና ሌሎች ግድቡ ላይ የሚሠሩ ሰዎችን ካዋራሁ በኋላ ያለኝ የግል ድምዳሜ የተለየ ነው፡፡ ጉብኝቱ በጣም ጠቃሚ ነበር፡፡ ግልጽነት የተሞላበትም ነበር፡፡ አሁን በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል የመተባበር ዕድልን ማየት ችያለሁ፤›› በማለት አብራርቷል፡፡

ይሁንና በግብፅ የህዳሴ ግድብ ለአገሪቱ የናይል ውኃ ድርሻ መቀነስ እንደ ሥጋት እንደሚታይ ሃይተም ይመሰክራል፡፡ ‹‹በግብፅ ያሉ ሕዝቦች የመፍራት መብት አላቸው፡፡ የዚያኑ ያህል በኢትዮጵያ አገራችሁን የማሳደግና የማበልፀግ፣ ለመጪው ጊዜ የማቀድ፣ ማሽኖችና ፋብሪካዎችን የሚያንቀሳቅስ ኃይልና ኤሌክትሪክ የማግኘት መብት አላችሁ፡፡ ሁለቱም አገሮች ጉዳዩን በጋራ ዓይን ማየት ቢችሉ የተሻለ ዕድል መፍጠር ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ በኃላፊነት ከሠራችና ግብፅም ከተባበረች ግድቡ ሥጋት አይሆንም፡፡ ይህ ከሆነ ግድቡ ለኢትዮጵያና ለግብፅ ብቻ ሳይሆን ለናይል ተፋሰስ ወንድሞቻችን ሁሉ የሚተርፍ ነው የሚሆነው፤›› በማለትም አክሏል፡፡

የግብፁ ጋዜጠኛ ሚዲያዎች በምሥራቅ ናይል ተፋሰስ አገሮች የሚንፀባረቀውን የተለያየና አልፎ አልፎም የሚጋጭ ፍላጎት በማመዛዘን ማየት እንዳለባቸው ያምናል፡፡ ‹‹ልማትንና ጥሩ መጪ ጊዜን መጋራት ሰብዓዊ የሆነ ሐሳብ ነው፡፡ ምክንያታዊና ኃላፊነት የሚሰማን ሆነን ከሠራን ግድቡ ሥጋት ሊሆን አይችልም፡፡ በኢትዮጵያ በነበረኝ የስድስት ቀናት ቆይታ ያገኘሁት ትምህርት ይህ ነው፡፡ ይህን መልዕክት ነው ለግብፃዊ ታዳሚዎቹ የማደርሰው፡፡ ውኃ ተፎካክረን የምናገኘው ዕቃ አይደለም፡፡ የሕይወት መሠረት የሆነ፣ ለማደግና ኢኮኖሚያችንን ለማበልፀግ፣ በሕይወትም ለመቆየት የሚያስፈልግ ነገር ነው፡፡ ሚዲያ እውነተኛውን መረጃ ለሕዝቡ በማድረስ ውሳኔ እንዲሰጡ ማድረግ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ሰዎች እንዲመጡ መጋበዝ አለባት፤›› በማለትም ሐሳቡን አካፍሏል፡፡ ሃይተም ሲደመድምም ‹‹እንደ ሰው ኢትዮጵያን የምመክረው ኃላፊነት በሚሰማው ሁኔታ እንደምትሠራ በጽሑፍ ተጨባጭ ቃሏን ለግብፅ እንድትሰጥ ነው፤›› ብሏል፡፡

አያህ አማን ውኃንና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ የምትዘግብ ሌላ ግብፃዊ ጋዜጠኛ ናት፡፡ ‹‹የህዳሴውን ግድብ መሸፈን የጀመርኩት እ.ኤ.አ. በ2010 የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፕሮጀክት ኤክስ ስለመጀመሩ ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው፡፡ በወቅቱ ግብፅ ውስጥ አብዮት እየተካሄደ የነበረ ሲሆን፣ በአገሪቱ ምላሽ የሚሹ በርካታ ጉዳዮችም ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ ዓይኑን ኢትዮጵያ ላይ ጥሎ ፕሮጀክት ኤክስ ምን እንደሆነ ይጠይቅ ነበር፡፡ ግብፅ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን የሚያደርጉትን የድርድር ሒደትም እዘግብ ነበር፡፡ ይሁንና ባለፉት ስድስት ዓመታት ስለ እነዚህ ጉዳዮች የምዘግበው የምጽፍበት ዋነኛ ጉዳይ የሆነውን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ሳላይ ነበር፤›› ብላለች፡፡

ከዚህ አንፃር የግድቡ ጉብኝት እንደ ሃይተም ሁሉ የተለየ ስሜት እንደፈጠረባት አያህ ታስረዳለች፡፡ ‹‹ግድቡን በአካል ማየት፣ ፎቶ ማንሳትና ስለታዘብነው ነገር ለሕዝብ መናገር ለምትጽፈው ነገር ተአማኒነት ይገነባል፡፡ ሕዝባችን ያለውን ቁጣና ፍራቻም ሊቀንስ ይችላል፡፡ ሁሉንም ነገር በአንዴ መቀየር አይቻልም፡፡ ነገር ግን አሁን ቢያንስ የግድቡን እውነታ መቀበል ይቻላል፡፡ ግድቡ ጉዳት እንደማያመጣ በማመን ሁለቱንም አገሮች አሸናፊ የሚያደርግ አሠራር ቢተገብሩ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ፤›› በማለትም አክላለች፡፡

‹‹እውነቱን ለመናገር ግብፅ ውስጥ አሁንም ፍራቻው አለ፤›› የምትለው አያህ በግድቡ ጉዳይ የሚሠሩ ኤክስፐርቶችና የቴክኒክ ሰዎች ይበልጥ በራስ መተማመን አጎልብተው ግድቡ ሊኖረው የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ አብረው ሊሠሩ እንደሚገባ ትመክራለች፡፡ ‹‹ለሦስቱ አገሮች ፖለቲከኞችና ኤክስፐርቶች የድርድር በሩ አሁንም ክፍት ነው፡፡ ይህ በቀጣይ ዘገባዎቼ ላይ የማተኩርበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ማለት ችግር የለም ማለት አይደለም፡፡ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ችግሮች የሰዎችን ሕይወት የሚያጠፉና የምናስብ የነበረውን ያህል የሚጎዱ አይደሉም፡፡ በጋራ የምንሠራ ከሆነ ሁሉም ነገር መቀረፍ ይችላል፤›› በማለትም ተስፋዋን አጋርታለች፡፡

የናይል ተፋሰስ አገሮች ብሩንዲ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ግብፅ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳን የሚያቅፍ ቢሆንም ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የሚገኙበት የምሥራቅ ናይል ተፋሰስ እጅግ ጠቃሚው ክፍል ነው፡፡

የኢንትሮ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ በበርካታ መሥፈርቶች የምሥራቅ ናይል ተፋሰስ እጅግ ጠቃሚው ክፍል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በአገሮቹ መካከል ያለው ውጥረትና አለመተማመን፣ ለትብብር ያለው አቅም፣ በቆዳ ስፋት የተፋሰሱን 60 በመቶ የሚሸፍን መሆኑ፣ በሕዝብ ብዛት 54 በመቶውን የያዘ በመሆኑ፣ ለናይል ውኃ ሀብት 86 በመቶ የሚሆነውን አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑና በመልማትና በዕቅድ ላይ ያሉት አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች የሚገኙት በዚሁ ክፍል መሆኑ ያለውን ልዩ ጠቀሜታ እንደሚያሳይ አስገንዝበዋል፡፡

ቀጠናው ያለበትን ችግር ለመቅረፍ ሚዲያ ቁልፍ አጋር ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የሥልጠናው አዘጋጅ የስዊድን ዓለም አቀፍ የውኃ ኢንስቲትዩትን የወከሉት ማሪያ ቪንክ የውኃ ዲፕሎማሲ አገሮች በድርድር በሚያደርጓቸው ስምምነቶች ውኃን በጋራ ለመጠቀም እንዲችሉ ያስችላል ብለዋል፡፡ የትብብር ድርድሩንም ለበርካታ ባለድርሻ አካላት እንደሚያከፋፍል አመልክተዋል፡፡

ይህ ዲፕሎማሲ የሚይዘውን ቅርጽ ለመወሰን ሚዲያ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ማሪያ ቪንኮ ይናገራሉ፡፡ ‹‹አለመግባባቶችን የማባባስ ሚና ሊጫወት የመቻሉን ያህል ወደ ትብብርም ሊያሸጋግር ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ማሪያ ቪንክ ኢንስቲትዩቱ ያዘጋጀው የሚዲያ ሥልጠና ዓላማዎች በምሥራቅ ናይል ተፋሰስ አገሮች ገንቢ የሚዲያ ዘገባዎችን ለማጠናከር፣ የተሻለ ግንዛቤና ዕውቀት ለመፍጠርና በቀጣናው ትብብርን ለማጠናከር ያለሙ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ከተጀመረበት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በግብፅ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ውጥረት ነግሶ ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ግድቡን ለልማቷና በአጠቃላይ ለተፋሰሱ አገሮች ደኅንነት ጠቃሚ አድርጋ ብትወስደውም፣ የታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ግን ግድቡ ጥቅማችንን ይነካል በሚል ሥጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግድቡ መሠረታዊ ጉዳት እንደማያስከትል ባደረገችው ማጣራት ማረጋገጧን በመተማመን ከግብፅና ከሱዳን ጋር በጋራ ግድቡ ሊኖረው የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመገምገም ፈቃደኝነቷን አሳየች፡፡ በዚህም እ.ኤ.አ. በመስከረም 2011 ይህን የሚያጠና ዓለም አቀፍ የኤክስፐርቶች ፓናል ተቋቋመ፡፡

እ.ኤ.አ. በግንቦት 2013 የፓናሉ ሪፖርት ይፋ ሆነ፡፡ ሪፖርቱ የግድቡን ተፅዕኖ በሚመለከት ተጨማሪ ጥናቶች መደረግ እንዳለባቸው ምክረ ሐሳብ ሰጠ፡፡ ሪፖርቱ ሲወጣ ሱዳን አስቀድማ ከኢትዮጵያ ጋር መሥራት ጀምራ ነበር፡፡ ይሁንና ሦስቱ አገሮች ተጨማሪ ጥናቶቹን ለማድረግ የጀመሩት ሒደት እስካሁን አልተቋጨም፡፡ ቢሆንም ቢአርኤልአይ ግሩፕና አርቴሊያ የተባሉ ሁለት ኩባንያዎች ጥናቱን እንዲሠሩ ተመርጠዋል፡፡ በሥልጠናው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያና የሱዳን ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ኢንጂነር ጌድዮን አስፋውና ፕሮፌሰር ሰይፍ አልዲን ሄምዳን ለተሳታፊዎች እንደገለጹት፣ በ12ኛው ስብሰባቸው ጉዳዩ መቋጫ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ትብብር ምርጫ አይደለም

በሥልጠናው የተሳተፉ ኤክስፐርቶችና የአገሮቹ ኃላፊዎች ለሚዲያ ባለሙያዎች በአፅንኦት እንደገለጹት፣ ትብብር ግዴታ እንጂ ምርጫ አይደለም፡፡ አቶ ፈቅአህመድ ከውኃ አንፃር ትብብር ማለት በጋራና በተቀናጀ መልኩ በአካባቢ፣ በብሔራዊ፣ በክልላዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ውኃውን ማስተዳደርና መጠቀም እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

የምሥራቅ ናይል ተፋሰስ አገሮች ራሳቸውን ለትብብር ክፍት ማድረግ የሚያስገድዱ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ በሥልጠናው ላይ የቀረቡት ጥናቶችም በተመሳሳይ ይህንኑ የሚደግፉ ናቸው፡፡ በሕዝብ ቁጥር ዕድገት፣ በተጨማሪ የውኃ ጥያቄ፣ በውኃ ገብ አካባቢዎች መመናመን፣ በውኃ ጥራት መቀነስ የሚጠቃው አካባቢ ትብብርን በአስቸኳይ የሚሻ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የውኃ አስተዳደር ላይ የጋራ ስምምነት መጥፋቱ ከሰላምና ደኅንነት ጋር የተያያዙ ውጥረቶችን ማንገሱም ይነገራል፡፡

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪው ኢንጂነር ኬቨን ዊለር ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያለው አካባቢያዊ ተፅዕኖ ግልጽ ባይሆንም፣ ግድቡ ግብፅን ተጠቃሚ የሚያደርግባቸው ሳይንሳዊ እውነታዎች እንዳሉ ግን አስረድተዋል፡፡ በተለይ ከአፈር ዝቅጠት፣ ከድርቅና ከጎርፍ የታችኛውን የተፋሰስ አገሮች በተለይ ግብፅን በመጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል፡፡ ይህ ጠቀሜታ ሊገኝ የሚችለው ሦስቱ አገሮች በጋራ ሲሠሩ እንደሆነ ኢንጂነር ኬቨን አስረድተዋል፡፡

አቶ ፈቅአህመድም በተመሳሳይ የናይል ተፋሰስ ትብብርና ቀጠናዋ ትብብሩ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከማኅበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት አመልክተዋል፡፡ የልማት ኤክስፐርትና የዓለም አቀፍ የውኃ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት አለን ኒኮልም የጋራ ትብብር አገሮቹ ምርጫቸው እንዲያደርጉ መክረዋል፡፡

ኤክስፐርቶቹ በሥልጠናው የትብብርን ጠቀሜታና ትብብር ሳያደርጉ መቆየት የሚያስከፍለውን ዋጋ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ከሥልጠናው አዘጋጅ ከስዊድን ዓለም አቀፍ የውኃ ኢንስቲትዩት የተወከሉት አና ኤሊሳ ካስካዮ የተፈጥሮ ሀብት ማኔጅመንት ብክነት፣ አካባቢያዊ መራቆት፣ ያልተቀናጁ ውሳኔዎች፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቶች አለመተባበር የሚያስከፍላቸው ዋጋዎች መካከል እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል፡፡

ለአምስት ቀናት በተናጠል ከመሥራት ይልቅ በትብብር መሥራት ጠቃሚ እንደሆነ በከፍተኛ አፅንኦት የተነገራቸው ጋዜጠኞች የቀረቡትን ሳይንሳዊ ድምዳሜዎች፣ መረጃና ቁጥሮች ላይ ዝርዝር ጥያቄዎች በማቅረብና በመሞገት የተሻለ ግንዛቤ ለመያዝ ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡ አሠልጣኞች በአብዛኛው ጥያቄ ላቀረቡላቸው የግብፅ ጋዜጠኞች የሚችሉትን ያህል አጥጋቢ ምላሽ ለመስጠት ቢሞክሩም፣ ሁሉም በስምምነት የተጠናቀቁ አልነበሩም፡፡ ነገር ግን ከሁሉም አገር እነዚህን መረጃዎች ለመሸጥ የተሞከረው ለግብፆች ስለነበር ከሥልጠናው ዓላማ አኳያ የተሳካ ነበር ተብሏል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -