Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች የተሞከሩ የተቃውሞ ሰልፎችን መንግሥት በኃይል መቆጣጠሩን ገለጸ

በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች የተሞከሩ የተቃውሞ ሰልፎችን መንግሥት በኃይል መቆጣጠሩን ገለጸ

ቀን:

ጎንደር በተከሰተው ግጭት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

በአዲስ አበባና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ትናንት ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. የተቃውሞ ሰልፍ ሙከራዎች ቢደረጉም፣ በፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ ዕርምጃ በቁጥጥር ሥር መዋሉን መንግሥት አስታወቀ፡፡

ቁጥራቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ትናንት ከማለዳው 3፡00 ሰዓት አካባቢ ለተቃውሞ መስቀል አደባባይ አካባቢ መሰብሰብ ሲጀምሩ፣ የፀጥታ ኃይሎች ወዲያውኑ በወሰዱት ዕርምጃ ተቃውሞውን የበተኑ ሲሆን፣ ቁጥራቸው ከ300 እስከ 500 የሚደርሱትን ሠልፈኞች በቁጥጥር ሥር አውለዋቸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይህንን አስመልክቶ ተጨማሪ ማብራሪያ ለሪፖርተር የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ‹‹እዚህ ግባ የማይባል ቁጥር ያላቸው ሕገወጦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት በተጨማሪ መበተን የነበረባቸውን በፀጥታ ኃይሎች እንዲበተኑ ተደርገዋል፡፡ ለመበጥበጥ እስከወጡ ድረስ መንግሥት አስፈላጊውን ዕርምጃ ወስዷል፣›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይም በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የተቃውሞ ሰለፎች የተደረጉ ሲሆን፣ በነዚህም አካባቢዎች ለሰልፍ የወጡ ሰዎች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው የሰው ሕይወት ማለፉን ምንጮች ገለጸዋል፡፡ ነገር ግን ሕትመት እከገባንበት ሰዓት ድረስ ስለግጭቱ ዝርዝር ማብራሪያ ማግኘት አልተቻለም፡፡

በሌላ ዜና በጎንደር ከተማ ዓርብ ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀትር ላይ በከተማው ነዋሪዎችና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ሕይወት መጥፋቱና በንብረት ላይም ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡ የግጭቱ መንስዔ በዕለቱ ፍርድ ቤት ይቀርቡ የነበሩትን የኮሎኔል ደመቀ ፀጋዬን ጉዳይ ፍርድ ቤት ሳይመለከት በመቅረቱ ምክንያት የከተማው ነዋሪዎች ለተቃውሞ መነሳታቸው እንደሆነ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተከሰተው ግጭት በማስመልከት ሲናገሩም፣ ብጥብጥ አስነስተዋል ያሏቸውንና ተቃውሞ ያሰሙትን ጎንደርን የብጥብጥ ከተማ ለማድረግ ያለሙ ናቸው ሲሉ ወቅሰዋቸዋል፡፡

በተከሰተው ግጭት ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ በብዛት ሲተኩስ መዋሉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት ስለግጭቱ ዓርብ ማምሻውን በሰጡት መግለጫም ‹‹ሕገወጦች በጎዳና ላይ በፈጠሩት ሁከትና ጎንደርን የብጥብጥ ቀጣና ለማድረግ በተነሱ ሕገወጦች የተካሄደ እንጂ የጎንደር ሕዝብ የማይወክል ድርጊት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በግጭቱ ሳቢያ የሰው ሕይወት የጠፋ ሲሆን፣ በንብረት ላይም ጉዳት መድረሱን ፕሬዚዳንቱ ቢያረጋግጡም፣ የሟቾቹን ብዛትና ማንነት አላብራሩም፡፡ ነገር ግን ምንጮች እስከ አራት ሰዎች ድረስ መሞታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ በተጨማሪም በክልሉ በሌሎች ከተሞች የተጠሩ ሠልፎችን ለመቆጣጠር በየደረጃው ያሉ የፀጥታ ኃይሎች ዕርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ መተላለፉንም ይፋ አድርገዋል፡፡

ይህ ውጥረትም ትላንት ቅዳሜ ድረስ የቀጠለ ሲሆን፣ የከተማዋ የፀጥታ ኃይሎች መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ ተጠናክሮ መቀጠሉን የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም የክልሉ ልዩ ኃይል አስለቃሽ ጋዝ ሲተኩስ መዋሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቅዳሜው ክስተት የሰው ሕይወት ማለፉ ባይገለጽም፣ ተደጋጋሚ የተኩስ ድምፅ መሰማቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በሌላ ዜና ባለፈው ሳምንት በጎንደር ከተማ ያለምንም ግጭት በሰላማዊ መንገድ የተካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞና ሠልፍ መነሻ በማድረግ በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች የተቃውሞ ሠልፍ ሊካሄድ መጠራቱ ሕገወጥ መሆኑን፤ ከተካሄደም መንግሥት ዕርምጃ እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በደብረ ታቦር፣ በባህር ዳር፣ እንዲሁም በመላው ኦሮሚያ ክልል የተቃውሞ ሠልፎች እንዲካሄዱ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ቅስቀሳዎች ሲካሄዱ ተስተውሏል፡፡

ቅስቀሳዎቹንና የሠልፍ ጥሪዎቹን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት ሕገወጥ ድርጊቶችን ለመግታትና ሕግን ለማስከበር እንደሚገደድ፣ ለሠልፍ የወጣ ማንኛውም ዜጋ በመንግሥት ለሚወሰደው ዕርምጃ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ጨምረው አስጠንቅቀው ነበር፡፡

በመግለጫቸው በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ሰሞኑን የተካሄዱና አሁንም በመጠራት ላይ ያሉ ሠልፎች አግባብነት የላቸውም ብለዋል፡፡

በሠልፎቹ ‹‹ከሕዝቡ ጥያቄዎች ያፈነገጡ፣ ኅብረተሰቡን የማይወክሉ የፀረ ሰላም ኃይሎች አቋም የተንፀባረቀበት ነበር፤›› ካሉ በኋላ ‹‹የተንፀባረቁት አቋሞች የኦሮሞንም ሆነ የጎንደር ሕዝብን የሚወክሉ አይደሉም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም ይህን ይበሉ እንጂ ባለፈው ሳምንት የተካሄደውን የጎንደሩን ሕዝባዊ ተቃውሞ በተመለከተ የአማራ ክልል በሰጠው መግለጫ ግን፣ የሕዝቡ ጥያቄ የመልካም አስተዳደር ችግር የፈጠረው በመሆኑ፣ የክልሉ መንግሥት ችግሮቹን ለማስተካከል ጠንክሮ እንደሚሠራ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ዓርብ እኩለ ሌሊት ጀምሮ በአብዛኛው የአገሪቱ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን፣ ወደ ሕትመት እከገባንበት ሰዓት ድረስ አገልግሎቱን ማግኘት አልተቻለም፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...