Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ትርፍ በ231 ሚሊዮን ብር አሽቆለቆለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ 16 የግል ባንኮች ውስጥ በከፍተኛ አትራፊነታቸው ከሚጠቀሱ ሦስት ባንኮች አንዱ መሆን ችሎ የነበረው የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ፣ በ2008 በጀት ዓመት ያስመዘገበው ትርፍ በ231 ሚሊዮን ብር አሽቆልቆለ፡፡ ባንኩ ያጋጠመው የትርፍ ማሽቆልቆል በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ እስከ ዛሬ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የአገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ የ2008 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም የሚያሳየው ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት፣ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ በበጀት ዓመቱ አስመዘገበ የተባለው የትርፍ መጠን ባለፈው ዓመት ከታክስ በፊት አግኝቶት ከነበረው ከ231 ሚሊዮን ብር በላይ ቅናሽ እንደታየበት ያረጋግጣል፡፡

ይህ የትርፍ መጠን ማሽቆልቆል ባንኩ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት በሚያገኘው ትርፍ ይዞት የቆየውን ደረጃ አስለቅቆታል፡፡ ባንኩ በ2008 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ 373 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ከተገኘው ጋር ብቻ ሳይሆን ከሦስት ዓመት በፊት አግኝቶት ከነበረው ትርፍ ያነሰ እንደሆነ ከሪፖርቱ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ባንኩ ከታክስ በፊት አግኝቶት የነበረው የትርፍ መጠን 604 ሚሊዮን ብር እንደነበር በሪፖርቱ ተጠቁሞ፣ በዚህ የትርፍ መጠኑ ከዳሸንና ከአዋሽ ባንክ ቀጥሎ ከፍተኛ ትርፍ በማስመዝገብ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነበር፡፡ ባንኩ በተከታታይ ዓመታት እያስመዘገበ የነበረው ትርፍ ቀጣይ እንደሚሆን ሲገለጽ የነበረ ቢሆንም፣ የዘንድሮ ትርፉ በእጅጉ ቀንሶ መታየቱ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

የባንክ ባለሙያዎች እንደሚሉት በአንድ ዓመት ልዩነት በዚህን ያህል የትርፍ መጠኑ የቀነሰ ባንክ አልተመዘገበም፡፡ በ2008 በጀት ዓመትም ቢሆን ከኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በስተቀር ሁሉም የግል ባንኮች ያስመዘገቡት ትርፍ ጭማሪ የታየበት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በበጀት ዓመቱ በዚህን ያህል መጠን ትርፉ ለምን እንደቀነሰ ለማወቅ የባንኩን የሥራ ኃላፊዎች ለማነጋገር ሪፖርተር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

ከውጭ ምንዛሪ ግኝትና አያያዝ ጋር በተያያዘ የባንኩ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች ከኃላፊነታቸው መታገዳቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ባንኩ ከፍተኛ ትርፍ ያገኝበት ነበር የተባለው ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት መዳከም ለትርፉ ማሽቆልቆል ምክንያት መሆኑን የሚገልጹ አሉ፡፡ ባንኩ በተለይ ከሁለት ዓመታት በፊት ካስመዘገበው ትርፍ ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተገናኘ ነበር፡፡

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከታክስ በፊት በ2003 ዓ.ም. 68 ሚሊዮን ብር፣ በ2004 ደግሞ 140 ሚሊዮን ብር፣ በ2005 268 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ደግሞ ከታክስ በፊት 479.5 ሚሊዮን ብር አትርፎ ነበር፡፡

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ የአገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ ከተቀላቀለ 12 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ያሉ የኅብረት ሥራ ማኅበራትንና አባላቶቻቸውን ያቀፈ ከአሥር ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉት ባንክ ነው፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ በ2008 በጀት ዓመት አዋሽ ባንክ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ፣ ዳሸን ባንክ 990 ሚሊዮን ብር፣ አቢሲኒያ ባንክ 507 ሚሊዮን ብር ከታክስ በፊት በማግኘት በቅደም ተከተል ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ በሌላ በኩል ብርሃን ባንክ ደግሞ 305 ሚሊዮን ብር ሲያተርፍ፣ ካለፈው ዓመት ካገኘው ትርፉ ጋር ሲነፃፀር የ226 ሚሊዮን ብር ብልጫ በማግኘት የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች