Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ2.5 ቢሊዮን ዩሮ የሚገነባው የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በመንግሥት ፋይናንስ እንዲካሄድ ሳሊኒ ጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ መንግሥት በሚፈልገው የወለድ ምጣኔ ለኮይሻ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ የሚሆን ብድር ማግኘት ባለመቻሉ፣ መንግሥት 2.5 ቢሊዮን ዩሮ የሚያወጣውን ፕሮጀክት ፋይናንስ እንዲያደርግ ጥያቄ ማቅረቡ ተሰማ፡፡

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ውስጥ ለሚገነባው ኮይሻ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት የሚያስፈልገውን ፋይናንስ የሚያመጣ ከሆነ፣ ፕሮጀክቱ እንዲሰጠው በመንግሥት ተወስኖ ነበር፡፡

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ለዚህ ፕሮጀክት የሚያስፈልገውን 2.5 ቢሊዮን ዩሮ ከአውሮፓ የፋይናንስ ተቋማት ማግኘት ቢችልም፣ የብድሩ የወለድ ምጣኔ መንግሥት ለብድር ካስቀመጣቸው መሥፈርቶች ጋር አይመጣጠንም ተብሏል፡፡

ምንጮች እንደገለጹት ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ፣ ለኃይል ማመንጫ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ መንግሥት እንዲሸፍን ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ግዙፍና ከታላቁ ህዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ ቀጥሎ ትልቅ ፋይናንስ የሚጠይቀው ይህ ፕሮጀክት፣ ከውጭ በሚገኝ ፋይናንስ ይሸፈናል  ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡

የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኮይሻ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ ከውጭ በሚገኝ ብድር እንዲካሄድ የተወሰነ ነው፡፡

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ብድር በመፈለግ ሒደት ላይ እንዳለ እንጂ፣ መንግሥት ፋይናንስ እንዲያቀርብ ስለመጠየቁ አቶ ሞቱማ መረጃው እንደሌላቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኮይሻ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ተጨማሪ 2,200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ታገኛለች፡፡ የኃይል ማመንጫ ግድቡ 170 ሜትር ከፍታና በአጠቃላይ የሚፈጠረው ሰው ሠራሽ ኃይቅ ስድስት ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ የመያዝ አቅም ይኖረዋል ተብሏል፡፡

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን በራሱ ተነሳሽነት ጥናት በማካሄድና ፋይናንስ እንደሚገኝ ተስፋ በማድረግ፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የግንባታ ውል ሳይኖረው በፕሮጀክቱ ላይ ሥራ መጀመሩ ይታወቃል፡፡

ሳሊኒ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በስፋት የሚታወቅ ኩባንያ ነው፡፡ ሳሊኒ ሦስቱን የጊቤ ወንዝ የኃይል ማመንጫዎችንና የጣና በለስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ገንብቷል፡፡ የታላቁ ህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክትን ደግሞ በመገንባት ላይ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በ1977 ዓ.ም. በተከሰተው ድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተካሄዱ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል ከጭዳ ከተማ እስከ ተርጫ ከተማ የተዘረጋውን የመንገድ ግንባታ ማካሄዱ ይታወቃል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ አስተያየት እንዲሰጡ ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች