Tuesday, December 5, 2023

መንግሥት የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ሕዝባዊ መሠረት እንደሌለው አስታወቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

–  የጎንደር ሠልፍ ተገቢ ጥያቄዎችን እንደያዘ ክልሉ አሳወቀ

በባህር ዳር ከተማ የተካሄደውን ሁለተኛውን አገር አቀፍ የዳያስፖራ ቀን ለማክበር በቦታው የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ የሕዝብ ሳይሆን የጥቂት አመራሮች ችግር እንደሆነ ገለጹ፡፡ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ አንዳንድ ዳያስፖራ ተሳታፊዎች ግን ጉዳዩ ምላሽ ካላገኘ የጎንደርን ህልውና የሚወስን እንደሚሆን ሥጋታቸውን አመልክተዋል፡፡

እሑድ ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ በተካሄደ ሰላማዊ ሠልፍ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች ከጠየቋቸው ጥያቄዎች መካከል ዋነኛው የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄን የሚመለከተው ነው፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር ድንበር በሚጋራባቸው አካባቢ ከሠፈረው የጠገዴ ሕዝብ ጋር በተገናኘ ያሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑን በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ እንደ ወልቃይት ባሉ ቦታዎች የሚኖሩ ሕዝቦች ጥያቄ ካላቸው ሊያቀርቡ የሚገባው፣ ለትግራይ ክልልና ለፌዴራል ተቋማት መሆን እንዳለበትም አስገንዝቧል፡፡

ነገር ግን የወልቃይትና የጠገዴን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል የተለያዩ ግጭቶች መከሰታቸው ይታወቃል፡፡ በባህር ዳር ከተማ ከሐምሌ 25 እስከ ሐምሌ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደው ሁለተኛው የአገር አቀፍ የዳያስፖራ ቀን ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦችም፣ ግጭቶቹና የተከሰተው የንብረት ውድመት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለማንነት ጥያቄዎቹ ምላሽ ቢሰጥ ኖሮ ሊወገዱ ይችሉ ነበር ብለዋል፡፡

አቶ በላይ ታከለ የተባሉ ተሳታፊ የወልቃይትና ጠገዴ ጥያቄ ለዓመታት ሳይፈታ መቆየቱን አስታውሰው፣ አሁን በአስቸኳይ ምላሽ ካላገኘ ጎንደር እንደ ጎንደር መቀጠሏ ያሠጋኛል ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ፀጋ ሥላሴ የተባሉ ሌላ ተሳታፊም ተመሳሳይ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ችግሩ በአመራሮች ልዩነት የመጣ በመሆኑ፣ መፍትሔው እሱን ማስተካከል ነው ብለዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በጎንደር የተካሄደው ሠልፍ ካነሳቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል የተወሰኑት ተገቢና ከመልካም አስተዳደር ጋር የተገናኙ እንደሆኑና በአጭርና በረጅም ጊዜ ምላሽ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ገልጾ፣ ሠልፉ ያለምንም ግጭት መጠናቀቁን ማድነቁ ይታወሳል፡፡ የአማራ ክልል ግምገማም ተመሳሳይ መሆኑን የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ተገቢ የሆኑና ተመርምረው ምላሽ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡ የልማት ፍትሐዊነት፣ የሀብት ክፍፍል ፍትሐዊነት፣ የድንበር ማካለል ጥያቄዎች ከሕዝቡ ጋር በሚደረግ ውይይትና ምርመራ እውነት ሆነው ከተገኙ ምላሽ ይሰጥባቸዋል፡፡ ነገር ግን በዕለቱ ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ጋር የሚፃረሩ መልዕክቶች ተላልፈዋል፣ ድርጊቶችም ታይተዋል፡፡ ለምሳሌ ሰንደቅ ዓላማው ከሕገ መንግሥቱና ከሕግ የተፃረረ ነው፡፡ ለብዝኃነትና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ዕውቅና የማይሰጡ መልዕክቶችም ተላልፈዋል፡፡ ሠልፉ ራሱ የተደረገው ሕጋዊ መሥፈርቶችን ሳያሟላ ነው፡፡ ማሳወቅ ግዴታ ነው፡፡ የሠልፉን ባለቤት፣ መቼና የት እንደሚደረግ ለመንግሥት ማሳወቅ ግዴታ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ንጉሡ በሠልፉ የተላለፉ አንዳንድ መልዕክቶች የጎንደር ሕዝብ ጥያቄ ስለመሆናቸው እንደሚጠራጠሩም አመልክተዋል፡፡ ‹‹በሠልፉ የጎንደር ሕዝብ የትግራይን ሕዝብ እንደሚያከብር፣ ሰላም እንደሚፈልግና ሕግን እንደሚያከብር መግለጹ ተገቢ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው ሕገ መንግሥቱ ሲከበር ነው፡፡ በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ያለው ወሰን በግልጽ አለመከለሉ ለረጅም ጊዜ የነበረ ጥያቄ ነው፡፡ በፍጥነት አለመቋጨቱ የመልካም አስተዳደር ክፍተት ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ጥያቄ በተጨማሪ ከሌሎች አካላት አጀንዳዎች ጋር የተደባለቁ ጥያቄዎችም ነበሩ፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ ከተካሄደው ሠልፍ ጥያቄዎች መካከል ‘ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ዳንሻና ሁመራ ወደ አማራ ክልል ይጠቃለሉ’፣ ‘ከኦሮሞ ወንድምና እህቶቻችን ጎን ነን’፣ ‘ለሱዳን ከመተማ ተቆርሶ የተሰጠው መሬት ይመለስ’፣ ‘ኮሎኔል ደመቀ የነፃነት ታጋይ ስለሆነ ይፈታ’፣ ‘ሕወሓት የሻዕቢያ ተላላኪ ነው’፣ ‘የብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ይፍረስ’፣ ‘ትግሬ እንጂ ትግራይ ተከዜን መሻገር አትችልም’ የሚሉት መፈክሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የአማራ ክልል ኃላፊዎች ተገቢነት ካላቸው የጎንደር ሕዝብ ጥያቄዎች ጀርባ የፀረ ሰላም ኃይሎች እጅ እንዳለበት እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የወልቃይት ጉዳይ ምላሽ ካገኘ በርካታ ዓመታት እንዳለፉት በመግለጽ፣ ዛሬ ጥያቄው ለምን ተነሳ የሚል ጥያቄ አንስተው የሌሎች ኃይሎች እጅ እንዳለ አመልክተዋል፡፡  ወልቃይት አሁን ያለውን ማንነት በምርጫው የወሰነው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ሲመሠረት እንደነበርም አስረድተዋል፡፡

ሰለሞን ጎሹ እና ታምራት ጌታቸው

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -