እነሆ መንገድ። ከመሪ ወደ መገናኛ ልንጓዝ ነው። እዚያ ሰማይ አለ። ከሰማዩ በታች ሐምሌ የሸመነው ጥቁር ደመና አለ። ከደመናው በታች የታክሲ ጣራ አለ። ከጣራችን በታች ያልተከፈለበት፣ ያልተቆጠበበት፣ በዕጣ ያልተሰጠን ትንፋሻችን አለ። ትርፍ ከታጎሩት አራት ሰዎች ትንፋሽ ጋር ተዳምሮ የ18 ሰዎች ትንፋሽ መስኮቶቹ ላይ የደመና መጋረጃ ሠርቷል። በዚህ ሁሉ ትፍግፍግ መሀል ነው እንግዲህ ወያላው ቅጠሉን እየቀነጠሰ ጉንጩን በመወጠር የተጠመደው። ‹‹ምናለበት ሥራ ላይ እንኳ ብትተወው? ለአንተስ ቢሆን ምን ምቾት አለው?›› ይሉታል ከሾፌሩ ጀርባ ኮሽኳሻ የዝናብ ጃኬታቸውን እያንኮሻኮሹ የሚቁነጠነጡ አዛውንት። ‹‹በረደኛ! ምን ላድርግ ታዲያ? ቅቅል ድንች እንዳልበላ ድንቹን እየነቀለ ጫት የሚያበቅለው ነጋዴ በሩን ዘጋው። እንኳን ዘንቦብን እንዲሁም በርዶናል አባት፤›› ይላል ወያላው።
‹‹ወይኔ የሰውዬው ልጅ! እኔ ሥልጣን ቢኖረኝ ይኼን ጫት የተባለ ተክል ነበር ከምድረ ገጽ ጠራርጌ የማጠፋው፤›› ብላ መሀል መቀመጫ ጥጓን ይዛ የተሰየመች ወጣት ስታጉተመትም፣ ‹‹ለምንድነው ግን ሰው ሥልጣንና ጥፋትን አጣምሮ የሚመኛቸው? ብሎ መጨረሻ ወንበር ከተሰየሙት አንዱ ጠየቀ። ‹‹እኛ ምኑን አውቀን ወንድሜ! የናፈቀን ሥልጣንና ዴሞክራሲ ሆኖ ሳለ፣ ምርጫና አማራጭ የሚያቀርብ የሚያወያይ የሚያነጋግር ሽማግሌ ሆኖ ሳለ፣ ያም እየተነሳ እኔ ሥልጣን ቢኖረኝ ብሎ ስለመጨፍጨፍ ያም ተነስቶ ስለመደምሰስ ያም ዘሎ ስለመደፍጠጥ ያም እየፎከረ ግንብ ስለመገንባት ያወራል። እንዴት አንድ እንኳ እኔ ሥልጣን ቢኖረኝ ይኼን በገዛ ፍላጎቱና ሐሳቡ መመራት የሚፈልግ ሕዝብ የናፈቀውን የአገር ባለቤትነት ስሜት መልሶ እንዲያገኝ በትንሽ ትልቁ ጉዳይ ምርጫው የራሱ እንዲሆን ጠበቃ እቆምለታለሁ የሚል ሰው ይጠፋል?›› ብሎ አንድ በአንድ በአንክሮ መነጠረን። የነፃነት ታጋይ ነኝ ባዩ ሁላ በተቃራኒው ማዕዘን ቆሞ ሲመዘን የባርነት ጠበቃ እየሆነ አስቸግሮ እኮ ነው እንዲህ የሚወራው!
ጉዟችን ከተጀመረ ጥቂት ጊዜ አልፏል። ጨዋታው ገና መጀመሩ ነው። ‹‹ምንድነው እንደዚህ የጫት ጉዳይ ሁሌ ሲካበድ የምሰማው?›› ብሎ ሦስተኛው ረድፍ ላይ አጠገቤ የተቀመጠ ሲጠይቅ፣ ከብዶን ነዋ የምናካብደው። ይህቺ ማካበድ የምትባል ቃል መቼም ከአምባገነኖቻችን በላይ ተጫውታብናለች እኮ እናንተ? ያቃለልን መስሎን አታካብድ አታካብጂ ስንባባል ኖረን ይኼው ዛሬ ነገር ሁሉ አናታችን ላይ ወጣ፤›› አሉ አዛውንቱ በጥልቅ የሐዘን ስሜት። ወያላው ተራውን ጉዳዩ ይመለከተዋልና፣ ‹‹ወይ አያበሉን ወይ አያስቅሙን። በደሃ መጫወት የሚወደው በዝቶ ነው ብራዘር፤›› አለው። ያኛው ቀጠለ፣ ‹‹እኔ እኮ ምን ለማለት ፈልጌ መሰላችሁ? ከኢትዮጵያ ውጭ ብዙ አገር ኖሬያለሁ። እንደ ጫት ዓይነት አወዛጋቢ እፆችን በተመለከተ ግን በዓለም ላይ እንደ ሆላንዳውያን የዘየደ አላየሁም። እዚያ ያውም ማሪዋና በግላጭ ይጨሳል፣ ይሸጣል። መንግሥት ከሽያጩ ታክስ ይሰበስባል። ድብብቆሽ የሚባል ነገር የለም። ነዋሪው ሁሉ ተፈቅዶሎት የሚኖረው ግን ምንም እንዳልተፈቀደለት ነው። ጭር ባለ ሌሊት አሽከርካሪው ቀርቶ እግረኛው አረንጓዴ መብራት ካልበራለት አስፋልት አይሻገርም። በመከልከል አያምኑም ግን ደግሞ ምንም ነገር አይተላለፉም። ከተጻፈው የነፃነት ሕጋቸው ያልተጻፈው ገደባዊነት ይታይባቸዋል፤›› አለ፡፡
‹‹ኧረ አሳጥረው አቦ ናሽናል ሶሺዎሎጂ አደረግከው?›› እኮ ብሎ አንድ ወጣት ፈገግ አደረገን፡፡ ‹‹እኔ እዚህ አገር ብዙ ነገር አይገባኝም። በአንድ ወገን ከስንት ዓመታት በፊት የሠራ የታይዋንና የኮሪያ የዕድገት ተሞክሮ ዛሬ ካልሠራ ብሎ ችክ ይባላል። በጎን ደግሞ ማኅበራዊ ጉዳዮችና ጥያቄዎች በጥበብ፣ በሰው ልጅ ሥነ ልቦና ፍላጎት ላይ ተመሥርተው እንደ አሸዋ በባህር የሚመሰለውን ሕዝብ የገደቡ ሰዎች ተሞክሮ አይታይም። እስከ መቼ ነው ግን ተከልከል ባዋጅ ፀባይ የሚነግሠው? ሰው ይለወጣል ተብሎ የሚታሰበው?›› ሲል፣ ‹‹ኢሕአዴግ ያልሰማው ጉድ ኒዮሊብራሊዝም ታክሲ መሳፈር ጀምሯል?›› ብሎ ከጀርባችን አንዱ ያላግጣል! የልግጫ ዘመን!
ጉዟችን ቀጥሏል። አሁንም መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ተሳፋሪዎች መሀል ጠና ያለች ወይዘሮ በአይፎኗ ፌስቡክ እየጎረጎች ቆይታ፣ ‹‹በምን ቀን ነው ፌስቡክ የተመዘገብኩት?›› ብላ ጨዋታ ጀመረች። ‹‹አቤት ሰው ግን የምርጫ ካርድ ለማውጣት አይመዘገብም፡፡ ፌስቡክ ላይ ግን ሲንጋጋ አንደኛ ነው፤›› ይላል በሹክሹክታ ዳያስፖራው። ምናልባት የዘመኑ የምርጫ ካርድ ፌስቡክ ሆኖስ እንደሆን?›› ብላ ወይዘሮዋ ስትመልስለት ወዳጃችን ደነገጠ። ‹‹ሰምተሽኝ ኖሯል እንዴ?›› ሲላት እንደማፈር ብሎ፣ ‹‹ምነው ስንት አገር አላየህም እንዴ? አንዳንዴ የሚይዝ እየያዘን እንጂ እኛም የሶሻል ኔትወርኩ አባል ነን፤›› አለችው። ‹‹አባልነት ብቻ ምን ዋጋ አለው? ቁም ነገር ካልሠሩበት?›› አለች ከሾፈሩ ጀርባ ያለው ረድፍ ላይ የተሰየመች ስስ ነጭ ቶፕ የለበሰች ጆሊ ብርድ አይፈራም ባይ።
‹‹እስኪ በነካ ምላስሽ አስታውሽን ቆንጂት ቁም ነገር ምንድነው?›› ሲላት ጋቢና የተሰየመ አፍሮ፣ ‹‹ሐሳብን በሐሳብ ማሸነፍ፣ መመዘን፣ ሳያላምጡ አለመዋጥ፣ ወዘተ. የመሳሰሉት ናቸው፤›› አለችው። ‹‹አቤት ወደፊት ማትሪክ ምርጫ መሆኑ ቀርቶ አብራሩ ይዞ የመጣ ቀን፣ ይኼ ሶሻል ሚዲያ የማይናቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ባንቺ አየሁ፤›› ሲላት፣ ‹‹ለተጠቀመበት፤›› ብላ ድምፅ አልባ ፈገግታ አሳየችው። ‹‹ላይቭ ቻት መሆኑ ነው፤›› ይለኛል ዳያስፖራው። መቼም ታክሲ ውስጥ ስንገናኝ ‹ሎግ አውትና ሎግ ኢን› ያለን አንመስልም። ምናልባት ብሶታችን መውጫና መግቢያ ተምታቶበት ይሆን?!
ወያላችን ምርቅን ብሎ ሃምሳ ሳንቲም ለሚገባው አምስት ብር ይመልሳል። አሥር ብር ለሚሰጠው ሃምሳ ሳንቲም ያቀብላል። ያም ያም ይወርድበት ጀምሯል። አንዱ፣ ‹‹አሥር ብርና ሃምሳ ሳንቲም አትለይም?›› ብሎ ሲጮህበት ከጎኑ ተደርቦ የተቀመጠ ነጭ ጃኬት ለባሽ፣ ‹‹ልዩነት አላቸው እንዴ?›› ብሎ ነገር ጀመረው። ‹‹አሁን ገና ጨዋታ አመጣችሁ . . .›› ትላለች ወይዘሮዋ። ‹‹ይብላኝ ለመሀል ሠፋሪው እንጂ ለደሃ ደሃና ለኪራይ ሰብሳቢስ ዘንድሮ አሥሩም አምስቱም ሃምሳውም ያው ሆኗል፤›› አሉ አዛውንቱ። ‹‹ምነው ጋሼ መቶዋን ረሱዋት?›› ሲላቸው ከጎናቸው፣ ‹‹ተው! የከዳና የተከዳ አታዘበራርቅ። መቶ ብር እኛ ዘንድ በመንፈስ ካልሆነ በአካል ከሙሰኛም ሆነ ከደሃ እጅ ገብታ አታውቅም። አሁን ኪስህ ያለች ይመስልህ ይሆናል። ግን እኮ ሰማዩም ያለ እየመሰለህ እንጂ ኖሮ አያውቅም፤›› ከማለታቸው አዛውንቱ፣ ‹‹እንዴ ሰማዩም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የልማት አቅጣጫ መመራት ጀመረ እንዴ?›› ብሎ መጨረሻ ወንበር የተሰየመ ሸራፋ ጮኸ።
‹‹እኮ ምን የሚያስጮህ ነገር አለ?›› ሲለው አጠገቡ የተሰየመ ተሳፋሪ በሽቆ፣ ‹‹እንዴት አልጮህም አብዮትና ዴሞክራሲ ያላቻ ተጋብተው?›› ብሎ አፈጠጠበት። ሁለቱ ሲፋጠጡ ያየች ከመካከለኛ ረድፍ የአንዱን ኮሳሳነት ያንዱን ፈርጣማነት አስተውላ፣ ‹‹ወይ ዘንድሮ! ያላቻ ከሚጋባው ያላቻ የሚፋጠጠው አላስቀምጠን አለ እኮ እናንተ?›› ብላ አሸሞረች። ‹‹ደግሞ መቼ ተቀምጠን እናውቅና? ተቀምጠውብን እንጂ?›› ሲላት ከጎኗ የተሰየመ ጎልማሳ፣ ‹‹ኧረ እባካችሁ እናንተ ልጆች ክረምቱ በሰላም ይለፍ ተው ተው። ከአሁን አሁን ጎርፍ ወሰደን እያልን እንጨነቅ? ወይስ እኛ ራሳችን ጎርፍ ሆነን እንተራመስ ነው የምትሉት?›› ሲሉ አዛውንቱ፣ ‹‹ምነው አባት ተቆጡ? ጎርፍ እኮ ያለ፣ የነበረ፣ ወደፊትም የሚኖር ነው፤›› አለ ጎልማሳው። ጥያቄው ጎርፉ አረንጓዴ ነው ቀይ የሚለው ላይ ታዲያ ይሰመርበት!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጋቢና ከተሰየሙት ተሳፋሪዎች አንደኛው በስልክ ወሬ ይዟል። ‹‹አይዞህ ወዳጄ። እኔ የቤት ባለቤት ሳልሆን ሦስተኛው የዓለም ጦርነት እንደማይጀመር በህልሜ አይቻለሁ . . . እመነኝ ስልህ . . . ፑቲን? . . . መቼ? ግድ የለም እኔ የቤት ባለቤት ሳልሆን ሦስተኛው የዓለም ጦርነት የሚባል ነገር አይኖርም፤›› ይላል። ‹‹የምን ጦርነት ነው እሱ?›› አዛውንቱ ብርግግ አሉ። ጎልማሳው፣ ‹‹አልሰማችሁም? ጓድ ፑቲን እኔ ከዚህ ወዲያ የምዕራባውያንን ህቡዕ አጀንዳ ማባበልና ማድበስበስ ሰለቸኝ ደከመኝ በማለት ይፋ ያወጡትን ሚስጥር?›› ሲል ሁላችንም ጆሯችን ቆመ። ‹‹ለነገሩ ማን ይነግረናል? ሚዲያዎቻችን እንዲህ ያለ ነገር አነፍንፎ ከማውራት ስለሮናልዶ መጥበሻ መነደል ማወቅ የሚቀላቸው ናቸው። ኢንተርኔቱም ለቻት አልሆነ እንኳን ለሰፊ ሐተታ ንባብ፤›› ካለ በኋላ ፑቲን በቅርብ ዓመታት ውስጥ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት በአሜሪካና በአውሮፓውያን ጥፋት ሲጀመር እንደሚታያቸው ያብራሩትን አብራራልን።
‹‹ዲቪ ወደ ኢትዮጵያ ሞልታችኋል የሚባልበት ጊዜ እየመጣ ነው በለኛ?›› ሲል አንዱ፣ ‹‹ፍሬንድ! ውጊያው እኮ በቤልጂግ ጥይት አይደለም በኑክሌር ነው። እኛስ እዚህ ያለነው ተረፍን ይባል። እዚያ ማን ተርፎ ነው ዲቪ የሚሞላው?›› አለችው ነጭ ቶፕ ለባሽ። ‹‹አይ ሰው? በቃ ሥልጣኔ ሄዶ ሄዶ የሚያውቀው አዋግቶ ማፈራረስ ነው?›› ስትል ወይዘሮዋ፣ ‹‹ምን ይደረግ? የሰው ልጅ ከትናንት ጥፋቱ አልማር አለ! የብሔርተኝነት ስሜት ገነነ! ዘረኝነት ገነነ! ሽብርተኝነት ገነነ! ቀበሌያዊነት ገነነ! እኔነነት ገነነ!›› እያለ ጎልማሳው አዲስ ነገር ሲያመጣ ወያላው ‹መጨረሻ› ብሎ በሩን ከፈተው። አንዳንዱ ግብግብ ብሎ ብሶቱን ሲዘረግፍ ሌላው እያላገጠ ይሰማዋል፡፡ የሐምሌ ዶፍ ያመጣው ይመስል የሚያዳልጠው የበዛ ይመስላል፡፡ መልካም ጉዞ!