በሳሙኤል ረጋሳ
የሰው ልጅ በባህሪው የሚፈልጋቸው ቁሳዊና ህሊናዊ ግብዓቶች አሉት፡፡ ከገንዘብና ከንብረት ጋር የተያያዙ ሊለኩ የሚችሉ አስፈላጊና ከአስፈላጊ በላይ የሆኑ ቁሳዊ ግብዓቶች አንዱ ነው፡፡ ሌላው ፍላጐቱ ደግሞ በስኬት ይኼን ያህል ነው የማይባል ነገር ግን መለኪያቸው ከእርካታና ከመንፈስ ደስታ ወይም ከተስፋ መቁረጥና ከብስጭት ጋር የተያያዘው በዋናነት የመወደድ፣ የመከበርና የመፈራት በውስጡ መኖር ወይም ያለመኖር ናቸው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተጠቀሱት ሦስት ነገሮች በግለሰብ፣ በቡድን፣ ወይም በመንግሥት ደረጃ ያላቸው ቦታ ከማንነት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አላቸው፡፡ ለጊዜው እነዚህን ጉዳዮች ከመንግሥት ጋር አያይዘን እንያቸው፡፡
መወደድ
አንድ መንግሥት የመወደድ ዕድልን የሚያገኘው ለሕዝቡ በሚያበረክተው ቀንና አገልግሎትና የሕዝቡን ችግር ነቅሶ በማውጣት እንደ ሁኔታው ጊዜያዊም ሆነ ዘላቂ መፍትሔ ሲሰጠውና ሲተገብረው ነው፡፡ ሕዝብ እንዳይጉላላ የተቀላጠፈ አሠራርን ማስቀመጥና በተቻለው የመጨረሻ ፍጥነት ችግር ፈቺ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ ሕዝቡ ከመንግሥት ጋር ባለው ግንኙነት በሄደበት መሥሪያ ቤት ሁሉ ፈጣን አገልግሎትና ምላሽ አግኝቶ ከረካ፣ መንግሥት በሕዝብ ልቦና ውስጥ የተደላደለ ሥፍራ ይኖረዋል፡፡ መንግሥት ሕዝብን በእኩል ዓይን ካየ፣ ጤናው እንዲጠበቅ፣ እንዲማርና እንዲሠለጥን ካደረገው የራሱን የፍቅር መንገድ ስላበጀ ይወደዳል፡፡ መንግሥት በሕዝብ ሲወደድ ደግሞ ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡
መከበር
መንግሥት የሚከበረው መዋቅሩን በሚመሩት አካላት ሞራላዊ ቁመና ልክ ነው፡፡ እነዚህ መዋቅሮች በመጀመሪያ ብቃት ባላቸው ሰዎች መሞላት አለባቸው፡፡ ብቃት ሲባል የትምህርት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ያለው የአመራር ብቃት፣ በልምድ ያዳበረው ክህሎት፣ በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነትና ፍቅር፣ የሥራ ተነሳሽነቱ፣ ውሎው፣ ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ያለው ጤናማ ግንኙነቶች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ለእነዚህ አካላት ከማንኛውም ሙስና ጋር ትንሽም ቢሆን ንክኪ የሌላቸው መሆን አለባቸው፡፡ በተጨማሪም የበላይና የበታች ሠራተኛነት በሚፈቅደው ሕግ መሠረት የማዘዝና የመታዘዝ፣ የመፈጸምና የማስፈጸም ግዴታ አለባቸው፡፡ መንግሥት እንዲከበር መዋቅሩን የሚዘውሩት አካላት የሚፈጸሙት ሁሉ ይኼን ማሟላት አለባቸው፡፡
መፈራት
መንግሥት በሚመራው ሕዝብ ዘንድ መፈራት አለበት፡፡ መፈራት ሲባል ኃይልን በመጠቀም ቅስም የመስበር፣ ያለሕግ የማሰርና የመፍታት ጉዳይና እጅ የማስነሳት አይደለም፡፡ ይኼ አሉታዊ ፍራቻ ነው፡፡ አንድ መንግሥት መፈራት ያለበት የሚያወጣው ሕግ ሕዝቡን ምን ያህል ከጥቃት ይከላከላል? ምን ዓይነት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ አላቸው? ብሎ በአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ሊተገበር የሚችል ሕግ ሲያወጣና ሲተገብረው ነው፡፡
ሕጉን ማውጣት የመጀመሪያው ጉዳይ ሆኖ ዋናው ጉዳይ ግን ሕጉ እንዴት ይፈጸማል ነው፡፡ በርካታ አገሮች ጥሩ ሕግ ሊያወጡ ይችላሉ፡፡ ያወጡትን ሕግ የማስፈጸም አቅም ያላቸው ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሕጉ መከበር አለበት ብቻ ሳይሆን መፈራትም አለበት፡፡ ሕግን መጣስ በገንዘብና በእስር ከማስቀጣቱም በላይ እስከ ሞት ቅጣት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ስለሆነም በትክክል የሚተገብር ሕግ ያስፈራል፡፡ በአገራችን ማንም ሰው አንድን ጥፋተኛ ‹‹በሕግ አምላክ›› ብሎ በማስቆም ያለንክኪና ያለሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ለሕግ ማቅረብ የሚችልበት የቅርብ ጊዜ ትዝታ አለን፡፡ ይኼ ሕግ መፈራቱን በትክክል ያሳያል፡፡ ሕግ የሚፈራው በሁሉም ላይ እኩል ተፈጻሚ ሲሆን ነው፡፡
ብዙ መንግሥታት ግን መፈራት የሚፈልጉት በሕግ ሳይሆን ሕገወጥ በሆነ ዲክታተራዊ አገዛዝ ነው፡፡ ዲክታተሮች አሉታዊ በሆነ መንገድ በኃይልና በጉልበት በማስፈራራት ሕዝቡን በጦር መሣሪያ ሰጥ ለጥ አድርገው ለመግዛትና ለመፈራት ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ መንግሥታት ከመወደድ ይልቅ መከበርን፣ ከመከበር ይልቅ መፈራትን ይመርጣሉ፡፡ ሩቅ ሳንሄድ ከአገራችን ደርግን፣ ከጐረቤታችን ሻዕቢያን መጥቀስ እንችላለን፡፡ የዚህ ዓይነት መንግሥታት መጨረሻቸው አገርንም ራስንም ማጥፋት በመሆኑ መፈራትን በጉልበት ሳይሆን በሕግ ማግኘት አለባቸው፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው ሦስት ባህሪያት አዎንታዊ መልሳቸው ሕዝብን ከመንግሥት የሚያዋህዱ ከመሆናቸውም በላይ የአገር ፍቅር ስሜትን በዋናነት የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ሕዝቡ ለአገር ዳር ድንበር መስዋዕት እንዲሆን፣ በተጨማሪም የመንግሥትን ከማንኛውም ጥቃትና አደጋ መጠበቅን እንደ ዋና መርህ ይቀበላቸዋል፡፡
አግባብነት የሌለው ተቃውሞ ማንሳትና ማስነሳት፣ ለጠላት መሣሪያ መሆን፣ በተቻለ ሁሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ መፍጠር፣ አገር ጥሎ መሰደድ ብሎም እስከ አጥፍቶ መጥፋት የሚያደርሰው መነሻው ምንም ይሁን ምን መንግሥትን ከመጥላት፣ ካለማክበርና ከፍርኃት ነው፡፡
አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መንግሥታት የሚወደዱ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመረጣቸው አይደሉም፡፡ ባለሥልጣኖቻቸው የሕዝብን ጥቅም ከማስከበር ይልቅ የራሳቸውንና የባለሟሎቻቸውን ጥቅም ለማሟላት የሚጥሩ ናቸው፡፡ በሥልጣናቸው ይባልጋሉ፡፡ ወገናቸውን ብቻ ለመሾምና ለመጥቀም የተቀመጡ ናቸው፡፡ በሕይወት ዘመናቸው ተጠቅመውበት ሊጨርሱት የማይችሉትና በዘላቂነት የእነሱ መሆኑን እርግጠኛ ያልሆኑበትን ንብረት በሕገወጥ መንገድ ይሰበስባሉ፡፡ በመሆኑም እነዚህ የመንግሥት ሹመኞች በሕዝብ ዘንድ አይወደዱም፣ አይከበሩም፣ አይፈሩም፡፡ ድምር ውጤቱ ግን የመንግሥትን ያለመፈለግ የሚያመላክት ነው፡፡ እጅግ የሚበዛው ቦታ ላይ የሚመደቡት ሰዎች ከሌሎች የተሻለ ብቃት ኖሮአቸው አይደለም፡፡ ይልቁንም ከበላዮቻቸው ጋር ባላቸው የጥቅም ትስስር ወይም ለፖለቲካው ታማኝ ሳይሆኑም ቢሆን በመምሰል የሚሾሙ ናቸው፡፡ እነሱ በሚፈጽሙት ወራዳ ተግባር ሕዝቡ ለመንግሥት ተገቢውን ከበሬታ አይሰጥም፡፡
ሕዝብ መንግሥትን የማይወድ፣ የማያከብርና የማይፈራ ከሆነ መብቶች ሁሉ በጉልበተኞችና በጉበኞች እጅ ገብተዋል ማለት ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መኖር ደግሞ ከክፉ ነገር ሁሉ የከፋ ክፉ ነገር ነው፡፡
እንደ አፍሪካ ባሉ ታዳጊ አገሮች በመንግሥት ደረጃ የመወደድ፣ የመከበርና የመፈራት ዕድል ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በበርካቶች ዘንድ መንግሥት ሕዝብን ማስተዳደር ያለበት ሁሉን በእጁ ሁሉን በደጁ የማድረግ ሥልጣንን የተቀባ ነው የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ መሪዎቹም በአገሪቱ ሀብት የማዘዝ፣ እነሱ ለሚፈልጉት ዓላማ ጦርን ማሰማራት፣ ሕዝቡን በግዴታ ወይም በውዴታ ግዴታ ማዘዝን የመሳሰሉ ሥልጣኖች ሁሉ የእኔ ናቸው ባዮች ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥትንና ሌሎች ሕጐችን መጀመሪያ የሚጥሱት ባለሥልጣናት ስለሆኑ ሌላው ሕዝብ የሚፈራው ሕግም ሆነ መንግሥት የለም፡፡
እነዚህ እውነታዎች በብዙ የአፍሪካ አገሮች የታዩ ሲሆን፣ እኛም በመጠኑም ቢሆን የምንጋራቸው ነገሮች ስለሚኖሩ ከፍተኛ አመራሮቻችን ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ቁጥጥራቸውን ያጠናክሩ፡፡
እስቲ ከአገራችን ሁኔታ ጥቂት ማሳያዎችን ወስደን እንይ፡፡ ከወራት በፊት ኦሮሚያ ውስጥ የተነሳው ብጥብጥ መንስዔው የክልሉ መስተዳድር በሚያደርሰው የመልካም አስተዳደር ዕጦትና በአግባቡ ሕዝብን መምራት ያለመቻሉና ሌሎችም ተጨማሪ ጉድለቶች እንደሆኑ በመንግሥት ደረጃ ተገልጿል፡፡ በዚህ ሁከት ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አልቀዋል፡፡
ታዲያ አጥፊው በመንግሥት ደረጃ በታወቀበት በሕግ አግባብ የተወሰደ ዕርምጃ ሕዝቡ የሚያውቀው የለም፡፡ የሕዝብን ቀልብ ለመሳብ ሁለት ባለሥልጣት የሥራ መደብ ለውጥ አድርገዋል፡፡ ይህንን ያየ ሕዝብ ለወደፊቱ በክልሉ መንግሥት ላይ እንዴት እምነት ሊኖረው ይችላል? እውነት የዚያ ሁሉ ጥፋት ማጠንጠኛ እነዚህ ሰዎች ናቸው? ለወደመው ንብረትና ለሞቱ ሰዎች ምክንያትስ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል? ይኼ ጉዳይ ዘላቂ የሆነ ሰላምን ሊያሰፍን በሚችል ሁኔታ ስላልተጠቃለለ ወደፊት ተመሳሳይ ችግር ላለመፈጠሩ ምን ማረጋገጫ አለ? ችግሩ ሄዶ ሄዶ ተንገራግጮ ስለቆመ መንግሥት ‹‹ሾላ በድፍን›› ብሎ ያለፈው ይመስላል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀው ብሔራዊ ፈተና ከመሥሪያ ቤቱ ሾልኮ በመውጣቱ ከፍተኛ የሆነ ሁለንተናዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡ የሚገርመው ፈተናው ከነመልሱ በፌስቡክ ተለቆ አገር ሁሉ ካወቀው በኋላ የትምህርት ሚኒስትሩ ጉዳዩ ሐሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ በማግሥቱ የፈተናው ሰዓት ደርሶ ሲጀመር የእኛ አይደለም ያሉት ፈተና የራሳቸው ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ስለዚህም ፈተናው እንዲመክን ተደረገ፡፡ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ከየት መጣ? ፈተናውን ያወጣው ትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ በፌስቡክ ተለቆ ፈተናውን ያየው ትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ ፈተናው የእኛ አይደለም ያለው ትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ በማግሥቱ ፈተናው የእኛ ነው ያለውም ያው ትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡
ይኼ ፍቺ ያልተገኘለት እንቆቅልሽ ነው፡፡ ለዚህ ጥፋትና ብክነት እንዲሁም ለተማሪና ለወላጆች ሞራል ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም፡፡ መንግሥትም ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ሾላ በድፍን ብሎ ነገሩን አልፎታል፡፡
ከዚህ ክስተት በኋላ ተመሳሳይ የብሔራዊ ፈተና ሥርቆት ግብፅ ውስጥ ተፈጽሟል፡፡ እንደኛው ሁሉ ጥያቄውና መልሱ በድረ ገጾች ተለቋል፡፡ ታዲያ የግብፅ መንግሥት ጣጣ ሳያበዛ የፈተናውን መሰረቅ አምኖ ዕርምጃ ወስዷል፡፡ አጥፊ ያላቸውን ሁሉ በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡
መጋቢት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ አንድ ጽሑፍ ወጥቷል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢንቨስተሮች በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በወጣ ጨረታ ተካፍለው አዲስ አበባ ላይ ሙሉ ክፍያ ከፍለው በሕጋዊ መንገድ ቤት ገዝተዋል፡፡ ይኼ በፍርድ አፈጻጸም በኩል ዕውቅና አግኝቶ ሳለ የተረከቡትን ይዞታ ክፍለ ከተማው አይገባችሁም ብሎ ቤቱን አፍርሶባቸዋል፡፡ ባለጉዳዮች ለተለያዩ አካላት ቀርበው ጉዳያቸውን ቢያመለክቱ ሰሚ ስላጡ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ፍርድ ቤት ከሰው መብታቸውን ለማስከበር ሞክረዋል፡፡ ፍርድ ቤትም ለባለመብቶቹ ሲወስን ጉዳዩ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትም ቀርቦ ፀንቷል፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን ክፍለ ከተማው ውሳኔውን ሊቀበል አልቻለም፡፡ የሚገርመው ነገር ውሳኔውን ያለመቀበል አንድ ነገር ሆኖ ያልተቀበለበትን ምክንያት የክፍለ ከተማው ሥራ አስፈጻሚ ሲገልጹ፣ ‹‹ባለጉዳዮች ምንም ጥፋት የለባቸውም፡፡ ሁሉን ነገር የፈጸሙት ሕጉን ተከትለው ነው፤›› ብለው፣ ችግሩን የፈጠረውና ያላግባብ የወሰነው ፍርድ ቤት መሆኑን፣ ስለዚህ በእነሱ በኩል መርምረው የመንግሥትን ጥቅም አለመንካቱን ሳያረጋግጡ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተቀብለው መሬቱን እንደማያስተላልፉ ገልጸዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ የከለከሉት መብት
- ባለጉዳዮቹ በሕጋዊ አግባብ ቤቱን የገዙት በመሆናቸው ጥፋት እንደሌለባቸው ገልጸው ነው፡፡
- ችግሩን የፈጠረውና ያላግባብ የወሰነው ፍርድ ቤት መሆኑን ገልጸው ነው፡፡
- ጉዳዩ በሕግ የተያዘ መሆኑን ጠቁመው የመንግሥትን ጥቅም አለመንካቱን ሳያረጋግጡ መሬቱን ማስተላለፍ እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡
እንግዲህ በሕግ አግባብ በመንግሥት አዋጅና ደንብ መሠረት የተሸጠን ቤት ያለማስረከባቸው አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የፍርድ ቤትን ውሳኔ አልቀበልም ማለት ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ እንዲሁም የፍርድ ቤትን ውሳኔ በይግባኝ ሳያሽሩ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ነው ማለት ጠያቂ ቢኖር መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ለመሆኑ ክፍለ ከተማው ማን ሆነና ከፍርድ ቤት በላይ የመንግሥትን ጥቅም የማስከበር ይግባኝ ሰሚ የሆነው? ፍርድ ቤቶች የመንግሥትን ጥቅም አያስከብሩም ማለት ነው?
ግለሰቦች ተነስተው ሕገ መንግሥቱ የደነገገውን የፍርድ ቤት ነፃነት በአደባባይ ሲጥሱ አንድም የመንግሥት አካል የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ አልቻለም፣ ወይም አልታየም፡፡ አስፈጻሚው ቢቀር ፓርላማው ያወጣውን ሕግና በሕዝብ የፀደቀው ሕገ መንግሥት እንደ ተራ ነገር ሲገፋ የርስ በርስ ሚዛናዊ ቁጥጥር (Check and Balance) የለም ማለት ነው? ምንም ጉዳዩ ቀላል የግለሰቦች ጉዳይ ቢመስልም የሕገ መንግሥቱን ምሰሶ የሚያነቃንቅ በመሆኑ ሕግ አውጭውም ሆነ አስፈጻሚው ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡
አንድ ክፍለ ከተማ ደፍሮ የፍርድ ቤትን ውሳኔ የማይቀበል ከሆነ ሕዝቡ በመንግሥትና በሕግ አምኖ መኖር አይቻለውም፡፡ ስለዚህ ሰዎች የሚፈራ ሕግ ስለሌለ እነሱም ሕጉን አይፈሩም፡፡ መንግሥት ደግሞ ሕግን ካላስከበረ አይፈራም፡፡
ከላይ የተነሱት ጭብጦች በከተማ አስተዳደር፣ በክልልና በፌዴራል ደረጃ ለሚታዩ የመንግሥት ህፀፆች ማጣቀሻ ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች አይፈጠሩም አይባልም፡፡ ለምን ተፈጠሩም አይባልም፡፡ መባል ያለበት መንግሥት ጉዳዮቹን እንዴት ያያቸዋል ነው፡፡ መንግሥት የሚፈጠሩትን ስህተቶች በተቻለ ሁሉ ማረም አለበት፡፡ በሁሉም እርከን ያሉ የመንግሥት አካላት እንደነዚህ ያሉ ጉልህ ስህተቶች ሲፈጽሙ መጨረሻው ምን ይሆናል?
አንድ ጋን በአንድ በኩል ሰበራ ሆኖ ውኃውን የሚያፈስ ከሆነና በሌላው በኩል ሁሉ ደህና ቢሆን፣ በተሰበረው በኩል ብቻ ያፍስስ ሌላው አካሉ ደህና ማለት አያዋጣም፡፡ መንግሥትም ችግር ሲፈጠር በጐ ጐን ብቻ አስቦ በሾላ በድፍን መንፈስ ማስተካከያ ያለመውሰድ ትልቅ አደጋ አለበት፡፡
በእርግጥ መንግሥት የመወደድና የመከበር ብሎም የመፈራትን መርህ ሊያሟሉለት የሚችሉ ብቁ መደላድሎች ፈጥሯል፡፡ የሕዝቡን አቤቱታና ቅሬታ ማስተናገድ የሚችሉ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ገንብቷል፡፡ በመርህ ደረጃ የሚከተለው አቋምም ደህና ነው፡፡ ነገር ግን ትግበራዎቹ ወደተፈለገው ግብ እንዳይመሩ በፌዴራል፣ በክልልና በከተማ አስተዳደሮች ደረጃ የሚቀሩት ከበርካታ በላይ ጉዳዮች አሉ፡፡ ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት መንግሥት ለምን ቁርጠኛ እንዳልሆነ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ በእርግጥ መንግሥት መወደድ፣ መከበርና መፈራት ያለበት በአገሪቱ ውስጥ ባሉ በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች አይሆንም፡፡ በአመፀኞች፣ በሕገወጦችና የግል ጥቅምን ከሚያሳድዱ ግለሰቦችና የፖለቲካ ድርጅቶች ይኼንን መጠበቅ አይገባም፡፡ እንደ ሕዝብ ግን ሌላው ቀርቶ በጥቂቱም ቢሆን እነዚህን ጉዳዮች ያለሟሟላት የመንግሥትን አቋም የተወለካከፈና ለወደፊት አብሮ የመቀጠል ጉዳይን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፡፡ ለመሆኑ መንግሥታችን በዚህ በኩል ራሱን ገምግሞ ያለበትን ደረጃ ያውቃል? አንድ ሕዝብ በሚወደው፣ በሚያከብረውና በሚፈራው መንግሥት ከመመራት የበለጠ ምን ያስደስተዋል?
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡